የከተማ ግብርና በበርካታ ሀገራት የሚተገበር ሲሆን የአደጉ ሀገሮች አብዛኛውን የከተማ የምግብ ፍጆታቸውን የሚሸፈኑት በከተማ ግብርና ነው።በዓለማችን 125 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና ተሳታፊ እንደሆኑ ሰነዶች ያሳያሉ።ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በዲግሪ እና በሰርተፍኬት መርሃ ግብራቸው የከተማ ግብርናን አካተው ያስተምራሉ። ይህም ዘላቂነት ያለው የከተማ ምግብ ስርዓትን በተሳካ ሁኔታ ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል፡፡
በጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ግብርና ፕሮግራም ዳይሬክተር ቦቢ ዊልሰን ‹‹የአትላንታ የከተማ አትክልት እንክብካቤ ፕሮግራም ዘርን ከመትከል እና ሲያድግ ከመመልከት ያለፈ ነው። ማኅበረሰቦችን ስለማሳደግ፣ አዳዲስ አመራሮችን ማሰልጠን፣ የተራቡትንና ቤት የሌላቸውን መመገብ፣ የገበሬዎች ገበያ ስለማቋቋም እና በአትክልት ከወጣቶችና ጎልማሶች ጋር መሥራት ነው።››ይላሉ።የከተማ ግብርና ስንል አዝዕርቶች አትክልቶችና እንስሳት እርባታን የሚያካትት ሲሆን አትክልትና ፍራፍሬዎች ሳይበስብሱ ፣ሳይደርቁ በቅርበት ለነዋሪዎች በቶሎና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ ያስችላል። ወደ ሀገራችን ስንመጣ ግብርናን ከገጠርና ከሠፊ መሬት ጋር ብቻ የማያያዝ ልምድ በስፋት ይስተዋላል።በበኩሌ የከተማ ግብርና የሚለውን ስም ያወቅኩት በቅርቡ ነው።እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞች የከተማ ግብርናውን ሥራዬ ብሎ የሚያካሂደው አለ ወይ? የሚለውም ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው።ቀደም ሲል (ከሃያ ዓመት በፊት) ለፒያሳ አትክልት ተራ ከመሀል ከተማ አንዳንድ ቦታዎች አትክልት ተመርቶ ለሽያጭ ይቀርብ ነበር።በወቅቱ የእርሻ ትምህርት በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይሰጥም ነበር ። ነገር ግን ቀስ በቀስ ከከተማዋ መስፋፋትና ከነዋሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ምርቱ ከከተማው ውጪ ካሉ አካባቢዎች ብቻ መምጣት ጀመረ።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማ ግብርና ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ እያየን መሆኑ ግን በራሱ አንድ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው። ይህም ሆኖ ወንዛ ወንዙ ሁሉ መጸዳጃ ቤትና ቆሻሻ መጣያ (ማለትም የማይበሰብሱ ላስቲኮች ፌስታልና ሃይላንድ የሚጣልባት) ለሆነባት ሸገር የከተማ ግብርና መጀመሩ የግብርና ባለሙያ ክትትልና ጥንቃቄ የሚያሻው ነው።አስከ ቅርብ ግዜ በአንዳንድ የከተማዋ ቦታዎች አትክልት በሚመረትበት አምራቾቹን የሚደግፍ ባለሙያ አልነበረም ።
ዛሬ ቢያንስ መንግስት ለመደገፍ አለሁ እያለ በመሆኑና ዘርፉ ከተሠራበት ሰዎች ራሳቸውን ከመመገብ አልፈው በመሸጥ ገቢ ሊያገኙበት የሚያስችል በመሆኑ ለከተማ ግብርና የሚሆን ቦታ ያለው ሁሉ በሙሉ በአቅሙ በማምረት የዋጋ ንረትን ሊዋጋ ይገባል። ሰሞኑን በከተማ ግብርና ቲማቲም ፣ጎመን፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ድንች፣ ሀባብና ሽንኩርት ወዘተ በማምረት ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለሽያጭም እያቀረቡ መሆናቸውን ከኅብረት ሥራ ኮሚሽን የወጣ መረጃ አሰምቶናል።ይህም በትኩረት ከሠራንበት የከተማ ግብርና ለምግብ እህል እጥረትና ለዋጋ ንረት መፍትሔ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ያመላክታል፡፡ በአዲስ አበባ አብዛኛው ነዋሪ የራሱ መኖሪያ ቤትና ግቢ የሌለው ከመሆኑ አኳያ ያለው የመሬት ጥበት ለከተማ ግብርና አዳጋች እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ገን የከተማ ገብርና በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን በህንፃዎች ጣራ፣ በበረንዳዎችና በጓሮዎች በሠፊው ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል።
በሌላ በኩል በየሰፈሩ ለከተማ ግብርና ሊውሉ የሚችሉ በግለሰብ ባለቤትነት ያልተያዙ ቦታዎች ቢኖሩም ከቆሻሻ ማጠራቀሚያነት የዘለለ ፋይዳ ሲሰጡ አይታይም። ዛሬ ዛሬ በአንዳንድ አካባቢዎች ክፍት ቦታዎች በአበቦች በዛፎችና በአረንጓዴ ተክሎች ተውበው፤ የሚያረኩና የሚማርኩ ሆነው ማየት እየጀመርን ነው። በተጨማሪ በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ በከተማው ዳርቻ ያሉ ነዋሪዎች የጓሮ አትክልት እያለሙ ለከተማው ነዋሪ ቢያቀርቡ ራሳቸውንም ወገናቸውንም መጥቀም የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው።
ሠፊ ግቢ ያላቸው በተለይ በቦሌ፤ ኮተቤና ኮልፌ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ጓሯቸውን ቆፍረው የጓሮ አትክልት ሲያለሙ አይታይም። ምክንያቱን ለእነሱ ብንተወውም ሸምቼ መብላት እየቻልኩ ምን አደከመኝ? ከሚልና ትኩረት ካለመስጠት የሚነሳ ይመስላል። ጥቂቶች ሠፊ ግቢ ቢኖራቸውም መዝናኛ መሥራትን እንጂ የጓሮ አትክል ት ማምረትን አያስበውም።
በመዲናዋ በዘንድሮው የመኸር ወቅት እንኳ ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደሮችና ከተማ ግብርና ኮሚሽን አስታውቆ ነበር። ይህም ‹‹ምግባችን ከደጃችን›› በሚል መሪ ቃል ክረምት ከመግባቱ በፊት በስድስት ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የእርሻ ማረሻ ትራክተር ፣ የአፈር ማዳበሪያና ልዩ ልዩ ምርጥ ዘር ድጋፍ ተደርጎ ነው። ያለንበት ወቅት ክረምት መባቻ እንደመሆኑ ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ።
በዚህም ሠፋፊ መሬት ባላቸው የትምህርት ቤት ግቢዎች የጓሮ አትክልት በማምረት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ እንዲጠቀም ብሎም በአቅራቢያቸው ለሚገኝ ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጡበት ሁኔታ ቢያመቻቹ ፋየዳው ከፍተኛ ነው።ባለፈው ዓመት በአስር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድንች፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም በማልማት በትምህርት ቤቶቹ ለሚካሄደው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በሽያጭ እያቀረቡ ገቢ ማግኘታቸው፤ ዘርፉ በትኩረት ከተሠራበት ለነዋሪው መትረፍ እንደሚችል አንዱ ማሳያ ነው።
በታላቁ ቤተመንግሥት የጓሮ አትክልት በማምረት ለነዋሪዎች ሲታደል ከመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል፡ ፡ይህም ሌሎች ሠፋፊ ግቢ ያላቸው መንግሥታዊ ተቋማት ተመሳሳይ ምርቶችን አምርተው ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪ በርካሽ ዋጋ እንዲጠቀም ቢያመቻቹ የከተማ ግብርናው ከጋዜጣዊ መግለጫ በዘለለ ስኬታማ ይሆናል።ቀደም ብሎም አንዳንድ የመዲናዋ ጤና ጣቢያዎች ባላቸው ቦታ በከተማ ግብርና እያለሙ ሲጠቀሙ አስተውለናል።ሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ባላቸው ቦታ በከተማ ግብርና እየተሳተፉ ግዴታቸውን እየተወጡ ለህዝቡ ምሳሌ ቢሆኑ መልካም ነው።
በተጨማሪ በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ በከተማው ዳርቻ ያሉ ነዋሪዎች የጓሮ አትክልት እያለሙ ለከተማው ነዋሪ ቢያቀርቡ ራሳቸውንም ወገናቸውንም መጥቀም የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው። በፊኒፊኔ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በከተማ ግብርናው አዝዕርትና አትክልት በማምረት ለሸገር ነዋሪ እየሸጡ ከኑሮ ውድነት ችግር ራሳቸውን ሊያወጡ የሚችሉበት ዕድሉ ሠፊ ነው።
ባጠቃለይ የከተማ ግብርና በአግባቡ መተግበር ከተቻለ ጥቅሙ ድርብ ድርብርብ ነው በአንድ ወገን በከተማ ግብርና አምራቹ ሲጠቀም ሸማቹም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት ያገኛል።እንደ ሀገር ደግሞ የአየር ሁኔታ እንዲስተካከል በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ ይቻላል። በመሆኑም የዋጋ ንረትን ለመቀነስ፤ የአየር ብክለትን ለመከላከል፤ ከተማችንን ጽዳትና ውበት ለማላበስና ጤናችንን ለመጠበቅ በቻልነው ሁሉ በከተማ ግብርና እንሳተፍ መልእክቴ ነው፡፡
ይቤ ከደጃች ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29 /2014