የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት /ኢጋድ/ ከአንድ አመት በፊት የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ስልጠና አንዱና ወሳኙ የጅቡቲ ድንጋጌ አካል ሲሆን ስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾች እና ስደት አስተናጋጅ ማህበረሰቦች ትምህርት እቅድ ጋር አብሮ የሚሄድ መርሃግብር ነው።
መርሃግብሩም ስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾችና ስደት አስተናጋጅ ማህበረሰቦች በከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች ተደራሽነታቸውን ማጠናከር ላይ ያተኩራል። መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት እ.ኤ.አ ከየካቲት
2021 እስከ ግንቦት 2022 ድረስ በሙከራ ደረጃ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ተሳትፈውበታል።
የመምህራን ስልጠና መርሃግብሩ የሙከራ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በሶስቱ ሀገራት የሚገኙ ሁለት ክልሎችን በመምረጥ ሲሆን እነዚህም በኢትዮጵያ ጋምቤላና ሶማሊያ፣ በሱዳን ነጭ አባይና ገዳሪፍ /ከከሰላ ጋር በማቀናጀት/ እንዲሁም በኡጋንዳ ደቡብ ኡጋንዳና ደቡብ ናይል ናቸው። የአስር ቀን የመምህራን ፍላጎት ዳሰሳ ከተሰራና አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ መምህራን ተመርጠው ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ መርሃ ግብሩ እ.ኤ.አ እስከ ግንቦት 2022 ድረስ በሶስቱ ሀገራት ሲከናወን ቆይቷል።
መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ እ.ኤ.አ እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ ከሶስቱ ሀገራት 600 መምህራን ሥልጠና ወስደው ስደተኞችን፣ ከስደት ተመላሾችንና ስደት አስተናጋጅ ማህበረሰቦችን እያስተማሩ ይገኛሉ። ይህም በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር የሰለጠኑ 200 መምህራንን ያጠቃልላል።
ከነዚህ ውስጥ 106 ያህሉ በመጀመሪው ዙር እንዲሁም 100ዎቹ በሁለተኛው ዙር በጥቅሉ 206ቱ ከኢትዮጵያ ናቸው። በመጀመሪያው ዙር ከሰለጠኑ 106 ኢትዮጵውያን መምህራን መካከል ደግሞ 89 ወንዶች፤ 17 ደግሞ ሴቶች እንዲሁም በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያውያን ሰልጣኞች 90 ወንዶች 10 ሴቶች ናቸው።
ኢትዮጵያዊቷ መምህርት ትግስት ወልደሃና የዚህ ስልጠና ተጣቃሚ ከሆኑት ውስጥ አንዷ ስትሆን በሶማሌ ክልል ዶሎ አዶ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ባዮሎጂ ትምህርት ታስተምራለች። በመምህርነት ሙያም መስራት ከጀመረች ስድስት አመት ሆኗታል። በዚህ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ማስተማር ከጀመረች ደግሞ ሶስት አመታትን አስቆጥራለች።
መምህርት ትግስት ወደዚህ የስደተኞች ካምፕ ለማስተማር ከመምጣቷ በፊት በሶማሌ ክልል ዶሎ አዶ ከተማ ለአራት ተከታታይ ዙር የኢጋድ መምህራን ስልጠና መርሃ ግብር ተከታትላለች። በስልጠናውም የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያግዙ የትምህርት ማበልፀጊያ፣ ስነልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ፣ የህይወት ክህሎትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይ ሲ ቲ) ኮርሶችን ወስዳለች።
ስልጠናውን ካጠናቀቀች በኋላ እንደ ኢጋድ አባል ሀገር በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሚገኘው የዶሎ አዶ የስድተኞች መጠለያ የባዮሎጂ ትምህርት እያስተማረች ትገኛለች። በኢጋድና በጂ ቲ ዜድ ትብብር ያገኘችው ስልጠና የመምህርነት ሙያዋን ለማበልፀግ እንደረዳትና ራሷንም ለማብቃት እንዳስቻላት ትናገራለች። እንዲህ አይነቱ ስልጠና ተጓዳኝ ድጋፍ መሆኑንና ሞራል የሚሰጥና የሚያበረታታ እንደሆነም መምህርት ትግስት ትገልፃለች።
ስልጠናው ትምህረቱን በተረጋጋ መንፈስ ለማስኬድ እንደረዳት ገልፃ፤ በስደት ጣቢያው ያሉ ተማሪዎችን ሊደግፍ የሚችሉ በርከታ ጠቃሚ ነገሮችን ከስልጠናው አግኝታ ስታስተምር እንደቆየችም ትጠቁማለች።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ትምህርት የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ከፍያለው አያኖ እንደሚናገሩት የኢጋድ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ስልጠና መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት ትምህርቱን ለማስኬድ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ተዘጋጅተዋል። ስልጠናው ደግሞ በመምህራን የስልጠና ፍላጎት ላይ ያተኮረ ነበር። ስልጠናውን ለመስጠት የተፈለገበት ዋነኛ አላማም በስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾችና ስደት አስተናጋጅ ማህበረሰብ ተማሪዎች ላይ የትምህርት ጥራት ለውጥ ለማምጣት ነው።
ስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾችና ስደት አስተናጋጅ ማህበረሰብ ተማሪዎች በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲ እንደማይገቡ በመረዳትም ነው በኢጋድ አነሳሽነት ስልጠናው የተጀመረው።
በዚህ ዓላማ መነሻ መምህራን በትምህርት ማበልፀጊያ፣ ስነልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ፣ የህይወት ክህሎትና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (በአይ ሲ ቲ) ላይ በሁለት ዙር ስልጠናዎችን ወስደው አጠናቀዋል። ከኢትዮጵያም 206 የሚሆኑ በጋምቤላና በዶሎ አዶ የስደተኞች ጣቢያ ለሚያስተምሩ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ይኸው ስልጠና በሁለት ዙር ተሰጥቷቸው ካጠናቀቁ በኋላ እያስተማሩ ይገኛሉ።
በዚህ የሁለት ዙር ስልጠና የሰለጠኑት 206 የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ በጋምቤላና በዶሎ ኦዶ የስደተኞች ጣቢያ ለሚገኙ ስደተኞች፣ከስደት ተመላሾችና ስደት ተቀባዮች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተደራሽ ይሆናሉ። በዚህም ተማሪዎቹ በተዘዋዋሪ የዚህ ስልጠና ተጠቃሚ ይሆናሉ።
አስተባባሪው እንደሚሉት የትምህርት ጥራት እንዲህ በቀላሉ በአንድ ግዜ የሚመጣ ባለመሆኑ ለትምህርት ጥራት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች በመኖራቸውና ከነዚህ ውስጥም ካሪኩለም፣ የመምህራን ስልጠና፣ የተማሪዎች ዝግጅት፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ሌሎችም ግብዓቶች ላይ መስራት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ዋነኛው መምህራን በመሆናቸው መምህራን ላይ አተኩሮ መስራት ውጤታማ ያደርጋል ።
መምህራን ተማሪዎችን በአግባቡ ካላስተማሩ ውጤታቸው ሊሻሻል አይችልም። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዋናውና የመጀመሪያው እቅድም በመምህራን ላይ ለመስራት ነው። በዚህም እስካሁን ድረስ በስልጠናው አማካኝነት ጥሩ ውጤት ማምጣት ተችሏል። የተማሪዎች ውጤትም ከአምናው ጋር ሲወዳደር መሻሻል አሳይቷል።
መምህራን ተማሪዎችን እንዴት ተቀብለው ማስተማር እንዳለባቸውም በስልጠናው ለማወቅ ችለዋል። ከተማሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነትም አጠንክሯል። መምህራን የተሻሉ የማስተማር ስነ ዘዴዎችንም እንዲከተሉ አድርጓቸዋል። ይህም በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
የትምህርት ጥራት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሀገራት ችግር ቢሆንም በመጠንና በስፋት ግን ይለያያል ። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የትምህርት ጥራት ችግር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም ቢሆን ግን በአንድ ጀምበር ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብም ከባድ ነው ። በኢጋድ አነሳሽነት ለመምህራን የተሰጠው ስልጠና እንደመነሻ ሆኖ ቀስ በቀስ ግን ሌሎች ስራዎችን በማከል የትምህርት ጥራቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ ማድረግ ይቻላል።
ስምንቱ የኢጋድ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ጅቡቲ ሲሆኑ የመምህራን ስልጣና ፕሮግራሙ በሙከራ ደረጃ በኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ሱዳን ነው የተጀመረው። በቀጣይም ወደሌሎቹም የኢጋድ አባል ሀገራት እየሰፋ እንደሚሄድ የተገለጸ ሲሆን በተለይ ስልጠናውን በጅቡቲና ኬንያ ለመጀመር ውጥን ተይዟል።
የኢጋድ የትምህርት፣ሳይንስ ቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ከፍተኛ አስተባባሪ ዶክተር ከበደ ካሳ በበኩላቸው እንደሚሉት ስልጠናው የተጀመረው በሶስት የኢጋድ አባል ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ነው። በመምህራን ስልጠና ላይ ማተኮር የተፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራን የሙያ ጥራትና ተነሳሽነት ወሳኝ በመሆኑ ነው። የመምህራንን አቅም መገንባት ካልተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣትም አስቸጋሪ ይሆናል ።
አባል ሀገራት በትምህርት ላይ ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ በተጨማሪ ኢጋድም ትምህርትን እንደ አህጉራዊ መተሳሰሪያ አድርጎ ስለሚሰራ በመምህራን ላይ የሚሰራው ስራ ታች ተማሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ህብረተሰቡ ላይ ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ይችላል በሚል የስልጠና ፕሮግራሙን ጀምሯል።
ይህን በሙከራ ደረጃ የተጀመረውን ሥልጠና በመያዝ በሌሎች አባል ሀገራት ያሉ በርካታ መምህራንን ሊያሳትፍ በሚችል መልኩ ለመስራት ታስቧል። ለዚህም የልምድ መለዋወጫ ስብሰባዎችን (ወርክሾፖችን) በአዲስ አበባ ተዘጋጅቶ የተሰሩ ስራዎች ተገምግመዋል። በጎ ተሞክሮዎችም ተጋርተዋል። ያጋጠሙ ችግሮችም ተለይተዋል። ለሚቀጥለው ርምጃ መነሻ ግብአቶችም ተሰብስበዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም የተሰሩ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ ተጠናቀዋል። በተለይ ስልጠናው የተካሄደባቸው ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች የሚገኙባቸው ሀገሮችም ከፍተኛ ትብብር አድርገዋል። ይህንኑ ትብብር በሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት ለማሳደግና ወደፊት ከዚህ የተሻለ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ግንዛቤ ለመጨበጥ ተችሏል።
ለመምህራን በተሰጠው ስልጠና መነሻነት የመጡ ለውጦች ወደፊት የሚለኩ ሆነው እስካሁን በሁለት ዙር በሶስቱም ሀገራት 600 መምህራን ሰልጥነዋል። ከዚህ ውስጥ 30 ከመቶ የሚሆኑት ሴት መምህራን ናቸው። ይህም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ስራ መሰራቱን ያሳያል ። በስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጣቢያዎች የሚታየውን የትምህርት ጥራት ጉድለት በማስተካከል ረገድም ስልጠናው ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።
በተለይ በመምህራን ተነሳሽነትና በተማሪዎች ትምህርት አቀባበል በኩል ለውጦች እየታዩ ነው። የትምህርት ቤቶቹ ተነቃቂነትና የማስልጠኛ ተቋማቱ ፍላጎትም እየጨመረ መጥቷል። ወደፊት ለሚታቀደውም ይህ እንደ ጥሩ ግብአት ሆኖ ያገለግላል። እስካሁንም መልካም ተሞክሮዎች ከስልጠናው ተገኝተዋል። በተለይ ግብአቱ የተሻለ እቅድ እንዲኖርና በቀጣይ ሰፋ ባለ መልኩ ለመተግበር ይረዳል።
ከዚህ አኳያ ይህ አበረታች ጅምር ውጤቱም ጥሩ በመሆኑ ወደፊት ቀጣይነት ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል። በዚህም ሁሉንም በትምህርት ላይ የተሰማሩ በየሀገሩ ያሉ የጋራ አጋሮች ላይ ከፍተኛ ስራ ይሰራል።
እስካሁን በሙከራ ደረጃ የተከናወነው የስልጠና መርሃ ግብሩ በሶስት ሀገራት ሲከናወን የቆየ ቢሆንም ከዚህ የተገኘውን ጠቃሚ ግብአት በመውሰድ በቀጣይም በሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት የማስፋት እቅድ አለ። በተለይ በቀሪዎች የኢጋድ አባል ሀገራት በኩል ፍላጎቱ ያለ በመሆኑ መርሃ ግብሩን ወደተቀሩት ሀገራት የማስፋትና በስልጠናው እንዲታቀፉ የማድረግ እድል ይኖራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014