አብዛኛው ሕዝቧ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኑሮው በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመሰረተባት ኢትዮጵያ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች።
በሀገሪቱ በመንግሥትና በዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች የተደገፉ ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በቀደሙት የመንግሥት ስርዓቶች የተተገበሩት የባለ ብዙ ዘርፍ የግብርና ልማት ማዕቀፍ ፕሮግራም (Comprehensive Agricultural Package Program) እና የግብርና ልማት ኤክስቴንሽን ትግበራ (Extension Program Implementation Department (EPID) እንዲሁም የቅርብ ጊዜዎቹ የኢትዮጵያ የልማት ፕላን መመሪያ ማዕቀፍ፣ የግብርና መር ኢንዱስትሪ ፖሊሲ (Agricultural Development Led Industrialization (ADLI)፣ የዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ ፕሮግራም፣ የመጀመሪያው እና ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች (GTP I እና GTP 2) ተጠቃሽ ናቸው።
በእነዚህ የግብርና ዘርፍ ማሻሻያ መርሃ ግብሮችም በእርግጥ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሪ ማሳየት ችሏል፤ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተችሏል፤ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ከድህነት መላቀቁን መረጃዎች ያመለክታሉ። የግብርናና ገጠር ልማትን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮችን መፍጠር ችለዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የስራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም። አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ይታያል። ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው። በአጠቃላይ መንግስት አቅዶት የነበውን የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እውን ማድረግ አልተቻለም።
የግብርናውን ዘርፍ ችግሮች ለመለየት በመንግሥት ከተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አንዱ ችግሮቹን የሚለይና ምክረ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ተቋም ማቋቋም ነበር። በቅርቡ አደረጃጀቱ ወደ ኢንስቲትዩት የተቀየረው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (Ethiopian Agricultural Transformation Agency – ATA) የዚሁ የመፍትሄ እርምጃ አካል ነበር። የኢትዮጵያ ግብርና በበርካታ ችግሮች የተተበተበና ከግብርና የሚገኘው ውጤትም ከሀገሪቱ አቅምና ፍላጎት ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ የዘርፉን ችግሮች ለመለየት ጥናት ተደርጎ፤ የተቋማት የመፈፀም አቅምና የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮች የዘርፉ ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸው በጥናቱ ማወቅ ተችሏል። እነዚህ ችግሮች እልባት ያገኙ ዘንድ ምክረ ሃሳብ የሚሰጥ ተቋም ያስፈልግ ስለነበር የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተቋቋመ።
ኢንስቲትዩቱ በ2003 ዓ.ም ሲቋቋም በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን፣ በተለይም የአፈፃፀም ማነቆዎችን፣ በመለየትና ምክረ ሃሳብ በማቅረብ፤ በግብርናው ዘርፍ ተቋማት መካከል ቅንጅት እንዲፈጠር በማድረግ፤በፈጠራና ቴክኖሎጂ ለግብርናው ዘርፍ የእውቀት ማዕከል በመሆን፤ ሰርቶ ማሳያ ፕሮጀክቶችን በመተግበርና በመደገፍ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ተግባራትን በማከናወን የግብርና ዘርፍ ሽግግርን የማሳካት ኃላፊነትን ይዞ ነው። እነዚህን ተግባራት በማከናወን ረገድም ብዙ ውጤቶችን አስመዝግቧል። በፖሊሲዎች እና በምርምሮች መካከል ያሉ የአሰራር ክፍተቶችን በመለየትና ምክረ ሃሳብ በማቅረብ የግብርና ባለድርሻ አካላትን ቅንጅት የሚስተባብረው ተቋሙ፣ በቅርቡ ደግሞ አደረጃጀቱን ወደ ኢንስቲትዩት በመቀየር የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት (Ethiopian Agricultural Transformation Institute – ATI) ሆኖ ተደራጅቷል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን ኤጀንሲው/ አሁን ኢንስቲትዩት ተብሏል/ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን በመለየትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ስለማበርከቱ ይናገራሉ። ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት እስከ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የመሸፈን አቅም መፍጠር በተቻለበትና በርካታ አርሶ አደሮችን ባሳተፈው የኩታ ገጠም እርሻ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ መፍጠር መቻሉንና የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ ያደረጉ አርሶ አደሮችን የምርታማነት ችግሮች ሊፈታ የሚችል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ይጠቅሳሉ። ተቋሙ በፖሊሲና በአሰራሮች ውስጥ ያሉ ችግሮችን የመለየትና መፍትሄ የመጠቆም ተግባራትን እንዳከናወነም ይገልፃሉ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ እንደሚሉት፣ ኢንስቲትዩቱ የግብርና ስርዓቱን ችግሮች በጥናት የመለየት፣ የአፈፃፀም ድጋፍ የመስጠት፣ ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በትግበራ እገዛ የማሳየት እና በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያንን የማቀናጀት ተልዕኮዎችን ይዞ ሲሰራ ቆይቷል። ተቋሙ የዘርፉን ችግሮች በጥናት ከለየ በኋላ ምክረ ሃሳቦችንም ያቀርባል። ምክረ ሃሳቦቹ በባለድርሻ አካላት የማይተገበሩ ከሆነ የትግበራ ድጋፍ ይሰጣል።
በዚህ ሂደት ባለድርሻ አካላቱ ምክረ ሃሳቦቹን ለመተግበር ተጨማሪ አቅም ይፈጠርላቸዋል ማለት ነው። በመንግሥት ሊቀጠሩ የማይችሉ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በመቅጠር የምርምር፣ የግብይትና የኢንቨስትመንት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋል። ለአብነት ያህል በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በኅብረት ስራ ኮሚሽንና በሌሎች ተቋማት ውስጥ ሆነው የምርምር፣ የግብይትና የኢንቨስትመንት አዋጭነት ጥናት የሚሰሩና የአቅም ግንባታ ስራዎችን የሚያከናውኑ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች የዚሁ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ ተግባራት ኢንስቲትዩቱ የፈፃሚ አካላትን አቅም እንደሚገነባ አመላካቾች ስለመሆናቸው ዋና ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ።
እንደዶክተር ማንደፍሮ ገለፃ፣ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያንን ማቀናጀት ሌላው የኢንስቲትዩቱ ተልዕኮ ነው። በዚህ የኢንስቲትዩቱ ዓላማ ረገድ ከሚጠቀሱ ተግባራት መካከል አንዱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከአርሶ አደሩ ጋር ማስተሳሰር ነው። ለምሳሌ ያህል በኩታ ገጠም እርሻ የብቅል ገብስ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ከብቅል አምራች ፋብሪካዎች ጋር እንዲሁም የዘይት ግብዓቶችን የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ከዘይት አምራች ፋብሪካዎች ጋር ማገናኘት የዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ኢንስቲትዩቱ ካከናወናቸው ውጤታማ የግብርና ሽግግር ተግባራት መካከል አንዱ የኩታ ገጠም እርሻ ዘዴ (Agricultural Commercialization Clusters/Cluster Farming) ነው። ዶክተር ማንደፍሮ ኢንስቲትዩቱ ይህን የአስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ ያደረገበትን አሰራር አስመልክተው ሲያስረዱ ‹‹ትራንስፎርሜሽን ማለት ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ አስተራረስ ተላቆ ምርትን ለገበያ ወደማቅረብ መሸጋገር ነው። አንድ አካባቢ ለኩታ ገጠም እርሻ ከተለየ በኋላ ስልጠና ይሰጣል፤ከዚያም ድንበር አልባ ሆኖ ይታረስና አርሶ አደሮቹ ባለድርሻ ይሆናሉ። እርሻው በትራክተር፣ የአረም ርጭት፣ በአውሮፕላንና በሌሎች መሳሪያዎች እንዲሁም አጨዳም በኮምባይነር ይከናወናል። ይህ ሲሆን አርሶ አደሮቹ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ እርሻ ወደ ኢንተርፕራይዝነት አድገው ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፈው ለውጭ ገበያ ወደማቅረብ ይሸጋገራሉ። በ10 የሰብል ዓይነቶች (ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ሰሊጥ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ቲማቲምና ሽንኩርት) የተጀመረው ይህ አሰራር እስካሁን በ300 ወረዳዎች ተግባራዊ ተደርጓል›› ይላሉ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ በበኩላቸው፣ ኤጀንሲው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በአፈር ለምነትና በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ የተሰሩ ስራዎችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ‹‹የአፈር ለምነት መጎዳት ከግብርናው ዘርፍ ችግሮች መካከል አንዱ ነው። ከ800 ወረዳዎች በተሰበሰበ 80ሺ የአፈር ናሙና ላይ ጥናት በማድረግ አካባቢዎቹ ምን ዓይነት ማዳበሪያዎች እንደሚያስፈልጋቸው በመለየት ምርታማነት እንዲጨምር ያስቻሉ ስራዎች ተከናውነዋል። ግብርናውን በሜካናይዜሽን አሰራር ለመደገፍ ሲሰራበት የነበረው አሰራር ብዙ ችግሮች ነበሩበት። የግብርና ሜካናይዜሽን ስራዎችን የሚያሳልጡ ግብዓቶች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት በቀረጥ ነበር። ቀረጥ ተከፍሎባቸው ሲገቡ ለአርሶ አደሩ የሚቀርቡበት ዋጋ ውድ እንደሚሆን በጥናት የተደገፈ ምክረ ሃሳብ ለመንግሥት አቅርበን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል። ይህም ግብዓቶቹ በቀረጥ ሲገቡ ከሚከፈልባቸው ዋጋ ባነሰ ገንዘብ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል። ይህን ለመደገፍም የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከላት (Mechanization Service Centers) ተቋቁመዋል›› ይላሉ።
‹‹ኤጀንሲው የተቋቋመው በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተቋማትን አቅም በመገንባትና የተሻሻለ አሰራር እንዲተገብሩ በማገዝ የግብርና ሽግግርን እቅድን ለማሳካት ነው›› የሚሉት ዶክተር ይፍሩ፣ ኢንስቲትዩቱ ከምርምር ጀምሮ እስከ ገበያ ድረስ የሚዘልቅ የአሰራር ሰንሰለት እንዳለውም ያስረዳሉ። ‹‹በዚህ ሰንሰለት ውስጥ አንዱ ደረጃ ችግር ካጋጠመው ከእቅዱ የሚጠበቀውን አጠቃላይ ውጤት ስለሚያበላሸው ስራዎቻችንን የምንሰራው በቅንጅት ነው። ኢንስቲትዩቱ በግብርና መዋቅሮችና አደረጃጀቶች በኩል ከአርሶ አደሩ ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው። እነዚህን መዋቅሮች በመጠቀም ለአርሶ አደሮች ስልጠና የመስጠትና የመከታተል ስራዎችን እንሰራለን። እኛ የጀመርነው ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ተስፋፍቶ ዛሬ ያለበት የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል›› ይላሉ።
በግብርና ሚኒስቴር ስር ካሉ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አደረጃጀቱ ኢንስቲትዩት ሆኖ ከተዋቀረ በኋላ ከአስፈፃሚውም ሆነ ከአጋር አካላት ጋር በሚኖረው የሥራ ግንኙነት ለውጥ ላይ ለውጥ ይጠበቃል። አቶ ኡመር በግብርና ሚኒስቴርና በኢንስቲትዩቱ መካከል ስለነበረውና በቀጣይ ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት ሲያስረዱ ‹‹ከዚህ ቀደም ከኢንስቲትዩቱ ጋር የምንሰራው፣ ጥናት አጥንቶ ሌላ ፈፃሚ አካል በመጠበቅ ነበር። አሁን ግን ኢንስቲትዩቱ ያደረገው ጥናት ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር ይፈፅማል። እንደተጠሪ ተቋም እቅድ ወይም ሪፖርት መቀበል ሳይሆን ስራዎቹን በጋራ እንፈፅማለን። በእርግጥ ከሌሎች ተጠሪ ተቋማት ጋር ያለን ግንኙነት የአለቃና የምንዝር ሳይሆን ውጤትን መሰረት ያደረገና ያቀድነውን ከግብ የሚያደርስ ነው›› ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ በእውቀት የተደገፈ ቁርጠኛነት ያላቸው ባለሙያዎች እንዳሉት ጠቁመው፣ የግብርናውን ዘርፍ ችግሮች የመለየት ኃላፊነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ወደፊት የሚያከናውናቸው ተጨማሪ ተግባራት እንደሚኖሩ በመገንዘብ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል።
‹‹ከአጠቃላይ ሀገራዊ ፍላጎቱ አንፃር ገና ብዙ መስራት ይገባል። በሰብልና ሆርቲካልቸር ዘርፎች ላይ የነበረውን ትኩረት ወደ እንስሳት ሀብት ዘርፍም ማስፋት ያስፈልጋል። በግብርናው ዘርፍ ያለው ሀገራዊ ፍላጎት እያደገ ስለሆነ ኢንስቲትዩቱ ለዚህ ፍላጎት የሚመጥን ምላሽ መስጠትን ታሳቢ ያደረገ ቁመና ሊኖረው ይገባል›› ብለዋል።
ዶክተር ይፍሩም ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ዘርፍ አካላት ጋር ያለው ትብብር ጠንካራ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ያለን ትብብር ከምንጊዜውም በላይ የተቀናጀ ነው። ለአብነት ያህል የመንግሥት የአስር ዓመት የልማት እቅድ ሲዘጋጅ አብረን አዘጋጅተናል። የግብርናው ዘርፍ ሊለወጥ የሚችለው ምን ብናደርግ ነው ለሚለው ወሳኝ ጉዳይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለይተናል። ግብርናውን ማዘመን፣ መስኖን ማስፋፋት፣ ግብርናውን ከአምራቹ ዘርፍ ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም የግብርና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ትኩረት የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው›› በማለት ይገልፃሉ።
ተቋሙ ወደ ኢንስቲትዩትነት ከተሸጋገረ በኋላ የምርምር ስራዎችን እንዲያከናውን ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ዶክተር ማንደፍሮ እንደሚሉት፣ ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ የሚያከናውናቸው የምርምር ተግባራት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚያከናውናቸው የሰብል እንስሳት ምርምሮችን ሳይሆን ስርዓት ተኮር የሆኑ የምርምር ስራዎችን ነው። የግብርናው ዘርፍ ምርምር ስለሚሻሻልበት መንገድም ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። የኤክስቴንሽን፣ የግብይትና የኢንዱስትሪ ትስስር ስርዓቶች የበለጠ ውጤታማ የሚሆኑባቸውን መንገዶችን የሚጠቁሙ ምርምሮች ይደረጋሉ። ከሰብል በተጨማሪ በእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶች፣ በተለይም በዶሮ እና ወተት፣ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ዶክተር ማንደፍሮ ለኢንስቲትዩቱ ዓላማ መሳካት ድጋፍ የሚያደርጉ በርካታ ሀገራትና ተቋማት እንዳሉ ጠቁመው፣ በቀጣይ ስራዎቻችን አርሶ አደሮቹ ምርታማነታቸውን አሳድገው ወደ ትልልቅ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ጥረታችንን እንቀጥላለን። የግብርናው ሽግግር እንዳይሳካ መሰናክል የሚሆኑትን ነገሮችና መፍትሄዎቻቸውን እንለያለን። በጥናት የተገኙት ሃሳቦች እንዲተገበሩ እናደርጋለን›› ብለዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014