እንደምን አላችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ፣ ጥሩ ነበር አይደል? የፈተና ውጤታቸችሁስ ምን ይመስል ነበር? መቼም የፈተና ውጤታችን በጣም ጥሩ ነው እንደምትሉኝ አምናለሁ:: ምክንያቱም ጎበዝ የሆነ ተማሪ በምንም መልኩ በፈተና አይወድቅም:: በዚያ ላይ እናንተ ዛሬ የተማራችሁትን ዛሬውኑ የምታነቡ ልጆች ስለሆናችሁ በጥሩ ውጤት ከክፍል ወደ ክፍል እንደተዛወራችሁ ይሰማኛል::
ንባብ የሚወድ ልጅ የዛሬውን ፈተና ብቻ ሳይሆን የነገውን ተስፋውን ጭምር የሚያቃና ነው:: እናም እናንተ ይህንን እንደምታደርጉ እርግጠኛ ነኝ። ደግሞ አሁን ወቅቱ ክረምት ስለሆነ የበለጠ የምታነቡበት ጊዜ ይኖራችኋልና በደንብ ተጠቀሙበት:: ብዙ እረፍት ስታገኙ መዘናጋት የለባችሁም:: ጎበዞች ከሆናችሁ ለአገራችሁም ለቤተሰባችሁም ኩራት ትሆናላችሁ። ልጆች ለዛሬው ይዘንላችሁ የመጣነው በጣም የምትወዱትን የእረፍት ጊዜ ይመለከታል:: ልጆች እንዴት ይህንን የእረፍት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉ ይገባል በሚል ተሞክሯቸውን ያካፈሉንን ልጆች ነውም የምናቀርብላችሁ::
እነርሱ የሚያደርጉትን ነገር በደንብ ነግረውናል:: እናንተም ማድረግ ያለባችሁንም እንዲሁ በምክር መልኩ አስረድተውናል:: ልጆቹን ከማስተዋወቃችን በፊት ግን ስለ ክረምት ምንነት ጥቂት እንበላችሁ:: ልጆች ለመሆኑ ክረምት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? የምታውቁ ጎበዞች የማታውቁ ደግሞ እኔ ጥቂት ነገር ከተለያዩ መረጃዎች ያገኘሁትን አብነት በማድረግ ልንገራችሁ::
ክረምት ማለት ስርወ ቃሉ ከርም፤ ከረመ የሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም ወርኃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ ማለት ነው። በተጨማሪም የዝናብ፣ የአዝርዕትና የዕጽዋት መለምለምና ምድር በአረንጓዴ የምታሸበርቅበት ወቅት እንደማለት ነው:: በመሆኑም በአገራችን ብዙው የግብርና ሥራ የሚካሄደው በዚህ ጊዜ ነው::
የክረምት ወቅት የሚባለው ከሰኔ 26 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም 25 ቀን ድረስ ነው። ይህንን ወቅት ደግሞ ብዙ ሰዎች በተለያየ አስተምሮ ይገልጹታል፤ ይዘምሩለታልም:: አንዱ ኢትዮጵያዊው የቅኔና የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ ሲሆን፤ በድጓው ‹‹ ‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናብ ሶቦ ይዘንብ ዝናብ ይትፌስሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናብ ሶበ ይዘንብ ዝናብ ይፀግቡ ርሁባን› የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ ረሀብተኞችም ይጠግባሉ::›› በማለት ይዘምረዋል::
ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹ ሰማዮችን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃልና፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም›› በማለት በዝማሬው ይሰብካል:: እናም ልጆች ክረምት ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰላም የሚሰጥ ወቅት ነው:: ስለዚህም በብዙ መልኩ መጠቀም ይኖርባችኋል:: ያነጋገርኳቸው ልጆችም በብዙ ነገር እንደሚጠቀሙበትና ገና ትምህርት ሳይዘጋ እቅድ ይዘው እየተጠባበቁት እንደነበር ነግረውናል::
መጀመሪያ ያነጋገርኳት ልጅ ሕንደኬ ሙሉቀን ትባላለች:: የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን አስኮ አካባቢ በሚገኝ ሚረር አካዳሚ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ትማራለች:: በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ስትሆን በበጋው ወቅት ትምህርቷን በአግባቡ ተከታትላና አንብባ ውጤታማ ሆናለች:: በዚህም የደረጃ ተማሪ በመሆን ተሸልማለች:: ክረምትም ቢሆን የቀጣዩን ክፍል በከፍተኛ ውጤት ለማለፍ ቀድማ እንደምትዘጋጅበትና መፀሐፍቶችን በእጇ እንዳስገባች ነግራኛለች::
ልጆች ማንኛውም ተማሪ ዝም ብሎ ጎበዝ አይሆንም:: ባለው ጊዜ እውቀት ሊያስጨብጠው የሚያስችለውን ተግባር መከወን አለበት የምትለው ህንደኬ፤ በተለይ ክረምትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል:: ትምህርቱ ያልደረስንበት ቢሆንም የከበደንን ከሚያውቁት ወላጆቻችን ጠይቀን እየተረዳን ማንበብ አለብንም ባይ ናት:: የልጆች አንዱ የክረምት እቅዳቸው ይህ መሆን እንዳለበትም ትመክራለች::
ልጆች እንደኬ ሌላው ያነሳችው ነገር ክረምት ከባድ ዝናብ የሚጥልበት ወቅት በመሆኑ ልጆች ከቤታቸው ሲወጡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው:: እንደውም ከወላጆቻቸው ፈቃድ ውጪ የትም መሄድ የለባቸውም:: ብቻቸውንም ባይወጡ መልካም ነውም ትላለች::
እንደኬ መሆን የምትፈልገው ሞዴሊስትና ዶክተር መሆን ነው:: ዶክተርነትን የመረጠችበት ምክንያት የታመሙ ሰዎችን ማከም ስለምትፈልግ ነው:: ስለዚህም ለዚያ የሚያበቃትን ዝግጅት ከአሁን ጀምራ እየከወነችም ትገኛለች:: ሳይንስ ትምህርቶችን አጥብቃ የመውደዷም ምስጢር ይህ እንደሆነ ታስረዳለች:: ሌላው የነገረችን ነገር በክረምት ማድረግ ከሚያስደስታት ውስጥ አንዱ ጨዋታ ነው:: ከጥናት በኋላ እረፍት እንደሚያስፈልጋት በደንብ ታውቃለችም የምትወዳቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ለመጫወት ትሞክራለች:: ልጆችም ጥናታቸውን ሲጨርሱ ራሳቸውን ዘና ማድረግ እንዳለባቸው ትመክራለች:: ነገር ግን ይህንን ሲያደርጉ ለእነርሱ የሚመጥን ጨዋታ መምረጥ እንዳለባቸው ታሳስባለች::
ወንድሟ ኀርየነ-መስቀል ሙሉቀንም እንዲሁ የእርሷ አይነት ባህሪ አለው:: ይሁን እንጂ ከእርሷ በአንድ ነገር ይለያል:: ይህም በጣም ጎበዝ ተማሪ በመሆኑ በማጠቃለያው ፈተና አንድ ክፍል ከፍ ብሎ ያልተማረውን ተፈትኖ ሁሉንም የትምህርት አይነቶች በመድፈን እና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ያለፈ ልጅ ነው:: መምህሮቹ በጣም ይገረሙበታልም:: ምክንያቱም ሁሌም ትምህርቱን በሙሉ ይደፍነዋል:: ኤክስ የሚባል ነገር አያውቅም:: እንደውም አንዳንዴ መምህራንን ጭምር በእርሱ እድሜ ደረጃ የማይጠየቁ ጥያቄዎችን እያነሳ ያስገርማቸዋል::
ኀርየነ-መስቀል በቤት ውስጥ ጭምር የተጠየቀውን ቀድሞ የሚመልስና የሚያደርግ ልጅ ነው:: እናም ክረምትን ማሳለፍ የሚፈልገው በማንበብና የክረምት ትምህርት በመማር እንደሆነ ነግሮናል:: አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እረፍት ሲኖረው ቤተሰቡን በማገዝ ማሳለፍ ይፈልጋል:: መሆን የሚፈልገው እንደ እህቱ ዶክተር ቢሆንም የመጀመሪያ ምርጫው ግን ፖሊስነት ነው:: ይህንን የሚፈልገው ደግሞ ሌቦች በአገራችን እንዳይኖሩ ለማድረግና ሕግን ለማስከበር ስለሚፈልግ ነው:: እንዴት ነው ልጆች፤ ጎበዝ አይደለም? እርግጠኛ ነኝ የሁለቱንም ልጆች ታሪክ ወዳችሁታል:: ምክራቸውንም እንደምትሰሙ አስባለሁ:: ምክራቸውን ስሙ እያልን ለዛሬ አበቃን:: መልካም የክረምት ወራት ይሁንላችሁ !!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2014