እንደ ሪፖርተር መረጃ ሰርሳሪ፤ ማራኪ ፕሮግራመኞችን ቀማሪ፤ እንደ አርታኢ (ኤዲተር ) መንገድ መሪ፤ እንደ ጉዞ ዘጋቢ አገር ዟሪ፤ እንደ ሴት የጽናት አስተማሪ ፤ በቤቷ ደግሞ ጥሩ ሚስትና እናት ናት ይሏታል የሙያ አጋሮቿ አንጋፋዋን ጋዜጠኛ ጸሃይ ተፈረደኝ::
ጋዜጠኛ ጸሀይ ተፈረደኝ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ኢትዮጵያን እንቃኛት በሚል ፕሮግራም ላይ ረጅም ዓመትን ሰርታለች፤ በሴቶች ዙሪያ በሚሰራው የሴቶች መድረክ ፕሮግራሟም በብዙዎች ትታወሳለች:: ላንቺና ላንተ በሚል ፕሮግራሟም ብዙዎች እናውቃታለን :: ለአብነት እነዚህን አነሳን እንጂ ጸሃይ የሰራቻቸው ፕሮግራሞች በርካታ ናቸው::
እኛም ይህ የሙያ ትጋቷ የህይወት መንገዷ ለብዙዎቻችን አርአያ ይሆናል በማለት የዛሬ የህይወት ገጽታ አምዳችን እንግዳ አድርገናታል::
ጋዜጠኛ ጸሀይ ተፈረደኝ የተወለደችው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ነው:: ነገር ግን ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ላይ ነው:: እንደ አለመታደል ሆኖ ጸሃይ እናትና አባቷን ገና በጠዋቱ ነው ያጣቻቸው፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ከእናትና አባት የሚወለድ እህትም ሆነ ወንድም የላትም:: ነገር ግን ደጓ አክስቷ ወስደው አሳደጓት፤ እሳቸውም ያለቻቸው አንዲት ሴት ልጅ ናትና ጸሀይም አንድ እህት አለችኝ ትላለች::
የሶስት ወይንም የአራት ወር ህጻን ሆና ከመጣችባት አዲስ አበባ ከተማም እየኖረች እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በቀጥታ ያመራችው ተክለሃይማኖት አካባቢ ወደ ሚገኘው ንጉስ ወልደጊዮርጊስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው:: ትምህርቷን እዚህ ትጀምር እንጂ ከሶስተኛ ክፍል አልዘለለችም:: ቤተሰቦቿ ሌላ ትምህርት ቤት መቀየር አለባት በማለት ልደታ አካባቢ በሚገኘው ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ትምህርቷን እንድትቀጥል አደረጓት::
“…. ንጉስ ወልደጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ለቤቴ በጣም ቅርብ ነበር፤ ነገር ግን ቤተሰቦቼ ትምህርት ቤት እንድቀይር አድርገውኝ ልደታ አካባቢ ወዳለው ተስፋ ኮከብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄድኩ፤ ከቤቴ ከተክለሀይማኖት ተነስቼ ልደታ እስከምደርስ ድረስ አካባቢው ጫካ ነው ሰውም ብዙም የለም፡፡ መንገዱም ቀጫጭን ነው፤ ይህ ደግሞ ለእኔና ለጓደኞቼ ምቹ ነበር፤ ሁላችንም ከቤታችን ገመድ ይዘን በመውጣት በዛ ሜዳ ላይ እየዘለልን እየቦረቅን መንገድ ላይ ቆም እያልን እየተጫወትን በጣም በደስታ ነበር ትምህርት ቤት ደርሰን የምንመለሰው፤ ውይ ሳስበው ራሱ በጣም ነው ደስ የሚለኝ” ትላለች ልጅነቷን ስታስታውስ::
ነገር ግን ጸሃይ እዛ የመማር እድልን ያገኘችው ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር:: አሁንም በቤተሰቦቿ ፍላጎት ደጃዝማች አባ ነፍሶ ወደሚባል ትምህርት ቤት እንድትዘዋወር ሆነ::
ምንም እንኳን ጨዋታ ብትወድም ቤተሰቦቿ ለትምህርት ልዩ ትኩረትን የሚሰጡ በመሆናቸው ትምህርትን ማጥናትና ውጤታማ መሆን ግዴታ እንደነበር ነው ጸሃይ የምትናገረው::
“……ያደኩበት ቤት የድሮ ስርዓት ያለበት ቤት ነው:: የአክስቴ ባል አባቴ ተፈረደኝ ነጋዴ ነበር፤ ጥሩ ኑሮ ስለነበረውም ሁሉንም ነገር በስነስርዓት ነበር የሚመራው፡፡ በልጅ አስተዳደግም በኩል ጥብቅ ስነስርዓት ነበር፤ ማስቸገር የሚባለውን ነገር ባናስበው ነው የሚሻለው፤ ሁሉ ነገር ስነስርዓት አለው:: እኔም በተለይም በትምህርቴ ጥሩ የምባል ነበርኩ:: አባቴ ተፈረደኝ የእድሮች ዳኛ አስተባባሪ ስለሆነ የእድሮቹን ሂሳብ መደመር መቀነስ፤ ድግስ ሲኖር የጥሪ ካርዶች ላይ የሰዎችን ስም የመመዝገብ ኃላፊነቱ የእኔ ነበር፤ እኔም ኃላፊነት ይሰማኝ ነበር” ትላለች::
በተለይም አባቷ የሚያሰሯት የሂሳብ ስራ በትምህርት ቤት የሂሳብ ትምህርቷ ላይም ላቅ ያለ ውጤት እንድታመጣ ከሌሎቹ ተማሪዎች ተለይታ እንድትታይ ያደረጋት ከመሆኑም በላይ አምስተኛ ክፍል እያለች የሂሳብ መምህሯን ሂሳብ ልጆቹን በማስተማር ትረዳቸው እንደነበርም ትናገራለች:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በስድስተኛም ሆነ በስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ ከፍ ያለ ውጤትን እንድታመጣም አግዟታል::
ጸሃይ አንደኛ ደረጃን አጠናቃ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪ ስትሆን ግን ነገሮች ተቀየሩ፤ እንደውም ተማሪ ሆና መቀጠልም የማትችልበት የህይወት አጋጣሚ ተፈጠረ:: ዘጠነኛ ክፍል ላይ ወደ ትዳርም ገባች::
“……አምስተኛ ክፍል ተማሪ እንዳለሁ የመሬት ላራሹ ጉዳይ ጭቅጭቅ እያስነሳ አንዳንድ ነገሮችም መፈጠር ጀምረው ነበር፤ በዚህ ደግሞ ምኑም ባይገባንም እኛም የችግሩ አንድ አካል ሆነን ፖሊስ እየመጣ ይደበድበን ነበር፡፡ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ተፈተንን፤ ጥሩ ውጤት አመጥቼም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለመቀጠል ልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባሁ::
ነገር ግን ትምህርቱን መቀጠል አልቻልኩም፤ በየቀኑ ፖሊስ ዱላ ይዞ መጥቶ ይደበድበናል:: እቤት ስንሄድ ደግሞ ቤተሰቦቻችን ለምን አርፋችሁ አትማሩም በማለት ይቀበሉናል:: በዚህ ሁኔታ እንዳለን መከላከያ ሚኒስቴር ሴት ወታደሮችን እቀጥራለሁ ብሎ ማስታወቂያ አወጣ:: እኛም ተያይዘን ሄደን ተመዘገብን ” ትላለች::
ጸሃይ በጣም ስለምትወደው የወታደርነት መያዋ አውርታ አትጠግብም “…ወታደርነት ሙያዬ በጣም የምወደው ስራዬ ነው፤ ዘጠነኛ ክፍልን እየተማርን በመካከል አቋርጠን ነው ወደ ውትድርና ስልጠና የገባነው ” ትላለች::
ምንም እንኳን ወታደር ሲመለመል የሚሄደው ወደፊቼ ማሰልጠኛ ጣቢያ ቢሆንም ጸሀይና ጓደኞቿ ሴቶች ስለሆኑ ልዩ ጥንቃቄና ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ምንም ዓይነት ወንድ ሳይቀላቀላቸው በሆለታ የሚኒሊክ ቤተመንግስት ውስጥ ለአንድ አመት ያህል ስልጠና ወሰዱ::
“……የወታደር ቤት ቆይታዬ ራሱን የቻለ ትልቅ ህይወት ነው:: የሚገርመው ነገር ወታደር ቤት የሄድኩት በትምህርት ቤት የሚደርስብንን ድብደባ ለመዳን እቤትም ለምን አርፋችሁ አትማሩም የሚለውን የቤተሰብ ጭቅጭቅ በመሸሽ ነበር፡፡ ነገር ግን ትልቅ የህይወት ትምህርት ያገኘሁበት እጅግ በጣም አስደሳች ጊዜን የኖርኩበት በጠቅላላው በጣም የምወደው ጊዜ ነበር” ትላለች::
“….እኔና ጓደኞቼ የሰለጠነው ሙሉውን የውትድርና ስልጠናን ነው:: ከግራ ቀኝ እርምጃው ጀምሮ መሳሪያ አነጣጥሮ እስከመተኮስ ድረስ ” ትላለች::
የሚገርመው ነገር ደግሞ ጸሀይ በወታደር ቤት የነበራት ቅልጥፍና፣ ተግባቦት፣ ለስልጠናው ያላት ተሳትፎና ጎበዝነቷ ታክሎበት በአንድ አመት የስልጠና ቆይታዋ 13 እና 14 ጊዜ በኃላፊነት ተሹማለች:: በዚህ ሹመትም ጠዋት ተነስታ ጦሩን መቀስቀስ፤ ወደ ቁርስ እንዲሄዱ ማድረግ ከዛም ሰልፍ ሜዳ ሄደው ተቆጥረው ወደስልጠና እንዲሄዱ ታደርግ ነበር:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በህይወቴ የማልረሳው እጅግ በጣምም የምወደው የህይወት ጊዜዬ ነው በማለት ትገልጸዋለች::
በዚህ ተሳትፎዋ ደግሞ አለቆቻቸው የሴት ሰራዊት ይቋቋማልና ጎበዞች ይመረጡ በሚባልበት ጊዜም ጸሃይ ከ62 ሰልጣኞች መካከል ከተመረጡት 13 ሴቶች ግንባር ቀደም በመሆን ተመርጣም ነበር::
“…..አዎ ሴት ሰራዊት እናቋቁማለን በማለት ጎበዞች ይመረጡ ተባለ፡፡ በዚህን ጊዜ 13 ሴቶች ሲመረጡ አንዷ ሆንኩኝ:: እኛን ደግሞ ለሚቋቋመው ሰራዊት በማስተባበር ሌሎችን ነገሮች ያግዛሉ በማለት ከእስራኤል አገር በመጣች ሴት ሻምበል ልዩ የሆነ ስልጠናን እንድንወስድ ተደረገ፤ ይህች አሰልጣኝ ከሰጠችን ስልጠና ወይንም ደግሞ ስትነግረን ከነበረው ነገር የማልረሳው ” እናንተ እድለኞች ናችሁ፡፡ ውትድርና የተቀጠራችሁት ወይንም ደግሞ እየሰለጠናችሁ ያላችሁት አገራችሁን ልታገለግሉ ከጠላት ልትጠብቁ ነው፤ እኛ ግን አገር የለንም፤ አገር ለማግኘት ነው የምንሰለጥነው፤ የምንዋጋው ” ትለን ነበር በማለት ታስታውሳለች::
ወታደር ቤት ሆና የነበራት ተሳትፎ ላቅ ያለ ነበር፤ በተለይ ምርቃታቸው ሊደርስ ሲል ኮሚቴ ተዋቀረ አንዱ ስራ የነበረው ለጦሩ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆን ቲያትር መስራት ነበር:: ጸሃይ ከትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር ወደጦር ካምፑ እንደመግባቷ ጓደኞቿ ትምህርት ቤት ሆነው ለበዓላት ጊዜ የተለያዩ የስነ ጽሁፍ ስራዎችን እየሰራች ስታቀርብ ያውቋታልና የቲያትሩን ክፍል ጸሀይ ትያዝ አሉ፡፡ ሁሉም በሃሳቡ በመስመማታቸው ጸሀይ ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆነውን ቲያትር የማዘጋጀት ኃላፊነትን ወሰደች::
“……አዎ ቲያትር አዘጋጇ ሲሉኝ ትንሽ ግር አለኝ፤ ምን ላቀርብ እችላለሁ ብዬም አሰብኩ፤ ነገር ግን የ7ተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ አንድ ድርሰት ጽፌ ነበር፤ እሱም ቤተሰቦቼ ቤት አስቀምጬ ነው የመጣሁት፡፡ እናም ሳስብ እሱን ድርሰት ለምን ቲያትር አላደርገውም አልኩና ሄጄ ጽሁፉን አመጣሁ፡፡ የምፈልጋቸውን ልጆችም ከሰልጣኞች መካከል መረጥኩና ያዝኩ:: ጽሁፉንም ለአለቃዬ አሳየሁ እሳቸውም ወደዱትና መቀጠል ትችያለሽ አሉኝ:: የሚገርመው ነገር ቲያትሩን ለመተወን ሁለት ወንዶች ያስፈልጉ ነበር፤ እኛ መካከል ደግሞ ወንድ እንዳይገባ ሆኖ ብቻችንን ነው እንድንሰለጥን የተደረገው፤ እናም ምን እናድርግ በቃ አንዱን የወንድ ክፍል እኔ ልተውን ሌላውን ደግሞ ጓደኛዬ ልትይዘው ተስማምተን ወደ ልምምድ ገባን” ትላለች::
በጣም የሚገርመው ነገር ግን ጸሃይ በልጅነት አእምሮዋ የደረሰችውና በኋላም ቲያትር ሆኖ እንዲታይ የተመረጠው ድርሰት በጦር ቤቱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም:: የሆለታ ከተማ ሙሉውን ማለት ይቻላል ደራሲ ጸሃይ ተፈረደኝ የሰራችው እየተባለ በየምሰሶው በሰዎች አጥር ላይ በባህር ዛፎች ላይ ሳይቀር ተለጥፎ ማስታወቂያ ተሰራለት:: ከዛም መጀመሪያ ጦሩ፣ በመቀጠል ተማሪዎች፣ ኋላም ህዝቡ እንዲያይ ሆነ:: በዚህም ጥሩ ገንዘብ ተሰበሰበ፤ ምርቃታቸውም በጥሩ ሁኔታ ተደግሶ መበላቱን ታስታውሳለች::
ጸሃይና ጓደኞቿ እድለኛም ናቸው ማለት ይቻላል ምክንያቱ ደግሞ ምርቃታቸው የተከናወነው በግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ በመሆኑ::
“…… ጃንሆይ ወታደር መርቀው አያውቁም፤ በወቅቱ ግን የጦር ኦፊሰሮች ስልጠናቸውን አጠናቀው ለምርቃት ተዘጋጅተው ነበር፤ እንደአጋጣሚ ሆኖ እኛም ስልጠናችንን ከእነሱ እኩል ጨረስን፤ በዘህ ምክንያት ጃንሆይ ኦፊሰሮቹን እንጂ ወታደሮቹን አይመርቁም ተባለ፤ የትምህርት ቤቱ አዛዥ ግን እነዚህ ልጆች እድላቸው ነው ለምንድነው አብረው የማይመርቁት ብለው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጃንሆይን አናገሯቸው፤ እሳቸውም እመርቃቸዋለሁ አሉ”::
“….ጃንሆይ እነዚህን ወታደሮች እመርቃቸዋለሁ ብለው ለመፍቀዳቸው ዋናው ምክንያት በወቅቱ እሳቸው ሆለታ አካባቢ ያሉ ቤተክርስቲያኖች ሲነግሱ በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው ይመጡ ነበር እኛ ደግሞ መኪናቸውን አጅበን “ጠቅል ምናለ፤ አገሬን ለሰው አልሰጥም አለ፤ እያልን እየዘመርን እያወደስን እያሞገስን እንሸኛተዋለን:: እሳቸውም እኮ ግን ባዶ እጃቸውን አልነበረም የሚመጡት በትልቅ የእንጨት አገልግል ፍትፍት፣ ጠጅ ቁርጥ ይዘው ነው የሚመጡት፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ መምጫቸው በጣም ይናፈቅ ነበር” በማለት ወደኋላ በመሄድ ትዝታዋን ትናገራለች::
“…..እንግዲህ በዚህ ሁኔታ እኔም ከእሳቸው እጅ ነው ሰርተፍኬቴን ተቀብዬ የተመረኩት:: ይህ ለእኔ እጅግ በጣም ውድና ትልቅ እንዲሁም እድሜዬን ሙሉ የምደሰትበት ታሪኬ ነው” ትላለች::
ከምርቃት በኋላ ምድር ጦርን በ 29 ብር የወር ደመወዝ እንድትቀላቀል ሆነ:: ” ….29 ብር በጣም ብዙ ነበር:: ከላዩ ላይ 6 ብር እቁብ ይጣላል፤ 3 ብር የምግብ ማጣፈጫ ተብሎ ይገዛል፤ ሌላው ደግሞ ይለበስበታል ” ትላለች::
ኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደስራው ሲገቡ ደመወዛቸውም ወደ 120 ብር ከፍ አለ፤ ነገር ግን እነሱ ስራ ላይ ሆነው ስድስት ወር እንኳን ሳያስቆጥሩ ጃንሆይ ከስልጣናቸው በሃይል ተገለበጡ:: በዚህ ጊዜ ሁሉም ፊቱን ወደእነሱ በማዞር ” ወታደር አትመርቁ ስንላቸው እነዚህን ሟርተኛ ሴት ወታደሮች መርቀው ከስልጣናቸው ተገለበጡ መባል ተጀመረ”፤ በማለት ታስታውሳለች::
ጃንሆይ ከስልጣናቸው ከመነሳታቸው በፊት ግን “….አንድ ቀን ስብሰባ ተደርጎ የማዕረግ አሰጣጥ ይነገራል፤ እናም ጀነራል፣ ሌተናል ጄኔራል የሚኮነው ሰልጥኖ ሰርቶ ብዙ ዋጋ ከፍሎ ተወዳድሮ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን የጃንሆይ ማዕረግ የተለየ ነው ማንም አይደርስበትም ይላሉ:: ከዛም እኔ እጄን አወጣሁና እሳቸው ግን የት ተምረው? ከማን ጋር ተወዳድረው ነው? የመጨረሻው ማዕረግ ላይ የደረሱት ብዬ ጠየኩ:: ሁሉም ደነገጡ በድፍረቴም የሚያረጉኝ ነገር አጡ:: በወቅቱ ግን እኔ እውነቴን የተሰማኝን ነበር የተናገርኩት:: ከዛም በቃ ለእኔም መልስ ሳይሰጠኝ ስብሰባው ተበተነ ” በማለት ወደትልቁ የህይወት መንገዷ ያስገባትን አጋጣሚ ትናገራለች::
ይህ አጋጣሚ ደግሞ በአለቆቿ እንዲሁም በሌሎቹ ዘንድም ደፋር ያስባላት፣ የብዙዎችን ቀልብ እንድትስብ ሁሉም ለእኔ ለእኔ እንዲል ያደረገ ሆነ:: ነገር ግን አየር ወለድ የነበረውና በሶማሌ ጦርነት ወቅት ከአየር ሲወርድ ጉዳት ደርሶበት በሌላ ስራ ላይ የነበረው አቶ ብርሃነ ገብረመስቀል ግን ይህችን ጀግና ሴት የእኔ ካላደረኩ እሞታለሁ አለ::
እህል ውሃ ወይም የእሱ ጥንካሬ ታክሎበት ጸሀይም ጥያቄውን በአዎንታ በመቀበሏ ጀግናዋና ተግባቢዋን ጸሀይን የራሱ የግሉ ማድረግ ቻለ:: ብዙም ሳይቆዩ ተጋቡ::
“……ያደኩት በጣም ሴትነት ከሞላበት፤ ሴቶቹ ብዙ ነገር ከሚሰሩበት፣ የሚፈጩበት የሚወቅጡበት በጠቅላላው እረፍት የሌለበት ቤት ውስጥ ነው፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ትዳር ብዙም አስቸጋሪ አልሆነብኝም፤ ካገባሁ በኋላ የማልረሳው የእኔንም የባሌንም ደመወዝ ይዤ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ወጣሁ፤ እናም ገበያው ያፈራውን ነገር በሙሉ በያዝኳት ብር ገዛሁ፤ መጨረሻ ላይ ግን 25 ሳንቲም ለታክሲ አጣሁ፤ በጣም ደነገጥኩና ቆም ብዬ ሳስብ ለመጨረሻ ጊዜ የገዛሁት እርድ ነው በቃ ይህንን እርድ መልሱልኝ ልበልና ለታክሲ ላግኝ ብዬ ወደሸጡልኝ አሮጊት ሄድኩና እማማ እባክዎ እርድ ገዝቼ ነበር ግን አሁን ለታክሲ ጨረስኩ እናም እርዱን መልሱልኝና ሳንቲሟን ስጡኝ? ስላቸው በጣም አዝነው እርዱን ተቀብለውኝ ሳንቲሙንና ትንሽ እርድ ሰጥተውኝ በይ ለሌላ ጊዜ ብቻሽን ገበያ እንዳትመጪ ብለው ሸኙኝ” በማለት የትዳር ገጠመኟን ትናገራለች::
ከዛ በኋላ ግን ባለቤቷም እየረዳት ብዙ ነገሮችን አብረው እያደረጉ እየወሰኑ ቀጠሉ” ድሮ እኮ ጎረቤት ዘመድ፣ ቤተሰብ መንገድ ያሳያል፣ ያግዛል:: እኔ ትዳር ይዤ ስወጣ የገባሁበት ግቢ ብዙ ሰው ነበር፡፡ ሁሉም እኔን ለማገዝ እርስ በእርሳችን ለመረዳዳት ምንም ምክንያት አንጠብቅም ነበር በጣም የሚገርም ፍቅርና ቤተሰባዊ ሁኔታም ነበረን ” በማለት ስለጎረቤቶቿ ትገልጻለች::
ጸሃይ ትዳር ይዛ ከአመት በኋላ የመጀመሪያ ልጇን ወለደች፤ ከዛም አከታትላ አምስት ልጆችን በመውለድ እንዲሁም ስድስተኛ ልጅ በማሳደግ ቤተሰቧን አበዛች:: አሁን ላይ ሁሉም በትልልቅ የስራ ኃላፊነቶች ውስጥ ያሉ ከመሆኑም በላይ የልጅ ልጅም ለማየት በቅታለች::
ጸሃይ ልጆቿን እየወለደች ትማር ነበር፡፡ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከወሰደች በኋላ ግን ወደ ትምህርት ሳትመለስ ረጅም አመትን ለመቆየት ተገደደች:: ነገር ግን መማር ህልሟ ነበርና ሁሌም ታስባለች:: በመካከልም ንግድ ስራ ኮሌጅ ገብታ በሴክሬቴሪያል ሳይንስ በሰርተፍኬት ተመርቃለች:: የጸሃይ ግቧ ግን እሱ አልነበረም:: ብዙ መማር ትፈልጋለች::
በ12 ተኛ ክፍል ትምህርት ውጤቷን እንደያዘች የጀመረችው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጠኝነት እንደቀጠለ ነው:: ግን በ12ኛ ክፍል እንዴት ወደጋዜጠኝነት ገባሽ አልኳት” አዎ እኔ 12ተኛ ክፍል ነኝ:: ከጦር ሃይሎች ሬዲዮ ከወታደር ቤት ነው ፕሮግራም አርታኢ ሆኜ ኢትዮጵያ ሬድዮ የገባሁት:: በሙያዋ ጎበዝ ነች ተብዬም ዲግሪ ካላቸው በላይ ሆኜ የተመደብኩት:: ደመወዛችንም ትልቅ ልዩነት ነበረው፤ በዚህም መስሪያ ቤቴ በስራዬ አምኖ እኔን እዚህ ቦታ ላይ ካደረሰኝ እኔ ደግሞ ራሴን አብቅቼ መገኘት አለብኝ በማለትም ነው ወደ ትምህርቱ የገባሁት” ትላለች ::
“…..በጋዜጠኝነት ላይ የተማረና ያልተማረ የሚለው ነገር በጣም ያስቸግራል:: የመጀመሪያ ዲግሪም ይሁን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው ተሰጥዖ ስለሌላቸው ውጤታማ መሆን የሚሳናቸው ብዙ ናቸው:: ኢትዮጵያ ሬዲዮም የገጠመው ይኸው ነበር፤ እናም ትምህርት ባይኖራቸውም መጻፍ የሚችሉ ድምጻቸው የሚያምር ሰዎችን እንድንቀጥር ይፈቀድልን? ብለው ጠይቀው ለአንድ ጊዜ ብቻ ተፈቅዶላቸው ነው የቀጠሩን:: እኔም ጥሩ ቦታ አግኝቼ ነው ስራውን የጀመርኩት” ትላለች::
ነገር ግን ተሰጥዖው ቢኖራትም በስራዋ ላይ የምታጎለው ነገር ባይገኝባትም ከባለዲግሪዎቹ ጋር ግን መስራት በጣም ፈታኝ ሆኖባት ነበር:: እንደውም አንዴ የማስታውሰው ትላለች “አንዱ ዲግሪ ያለው ወጣት ስራ ይዞ መጣ፤ እኔም አየሁትና በዚህ በዚህ መልኩ አስተካክለው ስለው በጣም ተናዶ” እንኳን መሀይም ልጆችም ቢያዙኝ እሰራለሁ” ብሎ ሄደ “::
ይህ ሁኔታ ደግሞ መማር እንዳለባት አመላከታት እንጂ አልችልም ብላ እንድትቆም አላደረጋትም:: ይህንን የተናገራትን ሰው አሁንም ታመሰግነዋለች:: ምክንያቱም ንግግሩ በትምህርቷ ለመግፋቷ መንገዱን ስላሳያት::
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ግን” ማስ ሚዲያ ትሬኒንግ ኢንስቲትዩት” የሚባል የጋዜጠኝነትን ትምህርት አስተምሮ በዲፕሎማ የሚያስመርቅ ተቋም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተከፈተ:: የመጀመሪያው ዙር ስለሁኔታው ሳትረዳ ምዝገባው አለፋት :: ጸሀይ በዚህ ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ገብታ እንዳለች ግን የስራ ባልደረቦቿ “ለምን አትማሪም የሚል ጥያቄ አቀረቡላት ” የእሷም መልስ “ለምን አልማርም መማር እችላለሁ” የሚል ሆነ::
ይህንን የተረዳችው የስራ ባልደረባዋና ጓደኛዋ ሰሎሜ ደስታም ስብሰባ ላይ ሀሳቡን አቀረበች:: ኮሚቴ ሆነው የተቀመጡት ግን “እሷ የልጆች እናት አይደለች እንዴት ብላ ነው የምትማረው” አሉ:: በዚህን ጊዜ ጓደኛዋ የልጆች እናት ብትሆንም እማራለሁ ብላለች እድል ይሰጣት አለች በቃ ትወዳደርና ትማር ብለው ወሰኑ::
“…..ጓደኛዬ ስብሰባ ላይ ባቀረበችው መሰረት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ ሂጂና ተወዳደሪ አሉኝ:: እኔም እሺ ብዬ ወደ ውድድሩ ቦታ ስሄድ የ12ኛ ክፍል ውጤቴን ሲያዩት ከሚፈልጉት መግቢያ ነጥብ በላይ ነው በቃ አንቺማ አትወዳደሪም ዝም ብለሽ ግቢ አሉኝ፤ በቃ አልፌ ገባሁ” ትላለች::
ቁጭ ብላ ትምህርት ቤት መግባቷን ስታስብ በሁለት ነገሮች መወጠሯን ታስታውሳለች አንዱ እንዴት ብዬ ነው ውጤታማ የምሆነው ሲሆን ሌላው ደግሞ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ትምህርት ቤት መግባት መቻሌ እድለኛ ነኝ የሚል ነበር::
“…..ትምህርት ተጀመረ፡፡ እኔም ተማሪ ሆንኩ ከዛ የመጀመሪያ የእንግሊዘኛ የሙከራ ፈተና ተፈተንኩ:: እኔም በሞራል በደስታ ፈተናውን ሰራሁት፤ በሁለተኛው ቀን ውጤቱ ሲመጣ ግን በጣም አስደንጋጭ ሆነ፡፡ ከሃያው ያገኘሁት ” ዜሮ” ነበር:: መቼም ድንጋጤዬ ድንጋጤ አይደለም ወረቀቱን እጥፍጥፍ አድርጌ ለማንም ሳላሳይ እንደውም 15 ከሃያ አገኘው እያልኩ ጓደኞቼን እየዋሸሁ እያለቀስኩ ወደ ቤቴ ሄድኩ ” በማለት ታስታውሰዋለች::
በለቅሶ ብዛት እራሷን አሟትና ደክሟት የተኛችውን ጸሃይ የመጀመሪያ ልጇ ከትምህርት ቤት ስትመጣ እናቷ ተኝታለች:: ምን እንደሆነች ብትጠይቅም የሚነግራት አላገኘችም:: ከዛም የተኛችውን እናቷን ቀስቅሳ ምን እንደሆነች ስትጠይቃት ለማንም እንዳትናገሪ በማለት የተፈጠረውን አሳየቻት:: ልጇም ቁጭ ብላ ፈተናውን ስታየው እናቷ የተሳሳተችው ምን እንደሆነ ገባት:: ስህተቷን አሳይታ ምን ማድረግ እንደነበረባት ነግራ ከዚያ በኋላም በሁሉም ነገር እንደምትረዳት ቃል ገብታ አጽናናቻት::
“……ልጄ ፈተናውን ስታየው አልደነገጠችም፡፡ እንደውም ስህተቴን ቁጭ ብላ በማየት ነገረችኝ ማድረግ ስለነበረብኝ ነገር አብራራችልኝ፤ ስህተቴም ትዕዛዝ አለማንበቤ መሆኑ አወቅሁ፤ ከዛ በኋላ እኔ አለሁ አለችኝ:: ለወንድሟም ነግራው እሱም እናቴ እኔም እረዳሻለሁ ቀጥይ አለኝ፤ ከዛ በኋላ የቤት ስራ ሲኖርብኝ እነሱ እያሳዩኝ ከእነሱ ጋር መስራት ጀመርኩ፡፡ በኋላም እኔም እየገባኝ በደንብ ወደትምህርቱ እየገባሁ መጣሁ:: ያ በዜሮ የተጀመረው ትምህርት በማዕረግ በመመረቅ ተጠናቀቀ ” ትላለች::
ጸሃይ ማንም ሰው በትክክል ችግሩን ተናግሮ እርዳታ ከፈለገና በዛ ልክ የሚረዳው እንዲሁም የሚረዳው ካገኘ ያሰበበት ይደርሳል:: ይህ ደግሞ በእኔ ህይወት አይቼዋለሁ ትላለች::
በዚህ ሞራል የተጀመረው ትምህርትም አሁን መስመር ይዟል:: ጸሀይ ዲፕሎማዋን እንደያዘች ትምህርት ቤቱ ወዲያውኑ የዲግሪ ፕሮግራም በመጀመሩ እዛው ቀጠለች:: ለዚህ ሁሉ ነገር ግን ልጇ ያበረከተችውን አስተዋጽዖ ደጋግማ ትናገራለች:: ታመሰግናታለችም:: ጸሃይ በዚህ አላበቃችም፡፡ ከጡረታ በኋላ ሁለተኛ ዲግሪዋን በመማር የትምህርት ጥማቷን ተወጥታዋለች::
ኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ እረፍት የለሽ ስራ ነበር የምንሰራው የምትለው ጸሃይ በሳምንት ሁለትና ሶስት ፕሮግራሞችን አየር ላይ ማዋል:: በሳምንት ሁለት ጊዜ ፕሮግራም መሪ መሆን፤ የመስክ ስራ መሄድ፤ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን አዳምጦና አርትኦት ሰርቶ ይለፍ ብሎ መፈረም፤ የተለያዩ ድራማዎችንም ይዘታቸውን ማየትና ማረም ብቻ ጥሩ ነበር በማለት ታስታውሰዋለች::
“…..በህይወት ዙሪያ የሚል ፕሮግራም ነበረኝ፤ በዚህም ሴቶችን ህጻናትን ገጠር ከተማውን የሚመለከት ነበር:: እዛ ላይ የሰራሁትን ስራ ምንጊዜም ቢሆን አልረሳውም፤ እወደዋለሁ፤ ኢትዮጵያን እንቃኛት የሚል ፕሮግራምም ነበር፤” ትላለች
ሁሉም ስራዎቿ የመስክ ጉዞን የሚፈልጉት ጸሀይ የምታደርገው ነገር አንዴ መስክ ከወጣች ብዙ ጊዜ ትቆያለች በዚህ ቆይታዋ ደግሞ ለሴቶች ፕሮግራም፣ ለኢትዮጵያን እንቃኛት እንዲሁም ሌሎች በመንገዷ ያገኘቻቸውን ለፕሮግራም ይመጥናሉ የምትላቸውን በሙሉ ነው ሰብስባ የምትመጣው::
ጸሃይ በስራዋ እጅግ በጣም ታታሪ ናት፤ ይህንን ደግሞ ብዙ ጓደኞቿም እንዲሁም ስራዋም ይመሰክራሉ”….የሚገርመው ነገር ልጆቼን ባሌን ትቼ ረዘም ያለ የመስክ ስራ እሄዳለሁ፤ ለስራው በጣም ራሴን ከመስጠቴ የተነሳ ክልል ላይ ለመሄድ ሳስብ የተቋሙ መኪና እስኪዘጋጅ እንኳን አልታገስም፤ ራሴ ትኬቴን ቆርጬ ከህዝብ ጋር ጉዞ አደርጋለሁ፤ ይህንን አሁን ላይ ሳስበው በጣም ይገርመኛል” በማለት ወደኋላ ሄዳ የስራ ጊዜዋን ታስታውሳለች::
በጋዜጠኝነት ህይወቷ ከማትረሳቸው በርካታ ገጠመኞቿ አንዱን ስትናገር ” አንድ ጊዜ ከእንግሊዝ አገር ልዕልት አን መጣች፤ እዚህ ከደረሰች በኋላ የሚያጅባት ሰው ስለጠፋ አንድ ሴት ጋዜጠኛ ላኩ ይባላል፤ ስራ አስኪያጁ ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ይጠራኝና 10፡30 ላይ ኡጋዴን ስለምትሄጂ አሁን አድርሶ የሚመልስሽ መኪና ተዘጋጅቷል ቤትሽ ሄደሽ ልብስሽን ይዘሽ ነይ፤ አሉኝ፤ በጣም ደንግጬ እሺ ብዬ ወደቤቴ ሄድኩ ልጆቼ ትምህርት ቤት ናቸው፤ ባለቤቴ ስራ ነው፤ ማንም ማግኘት አልችልም፤ እንደ አሁኑ የእጅ ስልክ (ሞባይል) የለም በቃ እቤት ላለችው አጋዤ የት እንደምሄድ ነግሬያት ቻው ብዬ ወጣሁ፤ 15 ቀን ያህል አልተመለስኩም:: ይህ የማልረሳው የመስክ ስራዬ ነው” በማለት ያለፈችበትን ከባድ ጊዜ ታስታውሳለች::
እንደዚህ አይነቱን ወታደራዊ ትዕዛዝ እኮ ያኔም አሁንም ማንም እሺ አይልም፤ ነገር ግን በእኔ ውስጥ የተለየ የሙያ ፍቅርና ክብር ስለነበረኝ ህጻናት ልጆቼን እንኳን ትቼ ስዘምት ነው የኖርኩት በማለት ትናገራለች::
ነገር ግን ብዙ ከለፋችበት ብዙም ልትሰራ እቅድ ካደረገችበት መስሪያ ቤት የ 1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በተፈጠሩ ምቹ ያልሆኑ የስራ ሁኔታዎች ምክንያት ለመቀጠል ባለመቻሏ ጡረታዬ ሲደርስ አስከብራለሁ ብላ በፍቃዷ ስራዋን ስለመልቀቋ ትናገራለች::
ብዙ የሚያስገርሙ ነገሮችን እያወራን መጥተናል ግን ለአንቺ በህይወትሽ ትልቅ የምትይው አስገራሚ ክስተት ምንድነው ? ብዬ ለጠየኳት ስትመልስ ፤ “….. በህይወቴ ብዙ የሚያስገርሙ ነገሮችን አልፌያለሁ:: ነገር ግን ልፋቴን ድካሜን ፈጣሪ ቆጥሮት ነው መሰለኝ ኢቢሲን በለቀቅሁ በ15 ዓመቴ ለሽልማት መጠራቴ በጣም ይገርመኛል:: በወቅቱ እንደምሸለምም አላውቅም የጠሩኝም ጓደኞቼ ናቸው:: እናም በዚህ በጣም እደሰታለሁ” ትላለች::
ጸሃይ በስራዋ ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ቃኝታ አስቃኝታናለች፤ “አገሬ ውብ ናት ከእኛ የመስራት አቅም በላይ የሆነች ናት፤ ምንም አልሰራንም እዚሁ አዲስ አበባን ከበን ነው ያለነው፤ ወጣ ሲባል በጣም የሚገርም መልከዓ ምድር ያላት ናት፤ ህዝባችንን ለስራ ማሰማራት ብንችል ከእኛ በላይ ሀብታም አይኖርም:: ግን ይኸው እስከ አሁንም እየተራብንና እየተቸገርን ነው፤ ብዙ ማሰብም ብዙ መስራትም ይጠበቅብናል” ትላለች:: ጸሀይ ከኢትዮጵያ ውጪም ኬኒያ፣ ጋና፣ ግብጽና ስዊዲን ሄዳለች::
በጋዜጠኝነት ህይወትሽ አልሰራሁትም ብለሽ የምትቆጪው ነገር አለሽ? ስላት”…..አይ አልሰራሁትም ሳይሆን መቀጠል ሲገባኝ አለቦታው ስራዬን አቆምኩት:: እንደውም ልጆቼ እያደጉ የሚጎትተኝ ነገር እየቀነሰ ስጋቶቼ ሁሉ ተቃለው ስራዬን ሰፋ አድርጌ ልሰራ በምችልበት ጊዜ ማቆሜ በጣም ይቆጨኛል፤ ኢትዮጵያን ለትውልዱ ማስጎብኘት አለመቻሌ እስከ አሁን ይቆጨኛል፤ ” በማለት ትናገራለች::
ዛሬ ላይ የምንወቅሰው የምንከሰው ትላንት ያልፈጠርነውን ወጣት ነው፤ ወጣቱ ለረጅም ዓመታት በሚባል መልኩ ተመልካች አጥቷል፤ ወላጅ እንዳይዝ የሚጎትተው ነገር ብዙ ነው፤ በመሆኑም ትውልዱን እናስተምር ልምዳችንን እናካፍል በጎውን መንገድ እንምራ በማለት ከጎደኞቼ ጋር ዩቱዩብ ከፍተን ለማስተማር እየተዘጋጀን ነው ትላለች::
ጸሀይ ኢቢሲ ከ 15 ዓመት በኋላ ለሚዲያው ባበረከትሽው አስተዋጽዖ በሚል ሽልማት አበርክቶላታል:: ከዛ ተከትሎም “ተወዳጅ ሚዲያ” የሚባል ተቋም ደግሞ እሷ ሳታውቅ ከልጆቿ ጋር በመነጋገር “ጸሃይን እናመስግን” በማለት ፕሮግራም አዘጋጅተው እውቅና ሰጥተዋታል፤ በዚህም ትልቅ ደስታና ክብር ይሰማኛል ትላለች::
መልዕክት
አሁን ላይ በሙያ ላይ የሚታዩ አንዳንድ አጓጉል ሁኔታዎች አሉ፤ ለምሳሌ ስራውን ራስን ለማውጫ ከሌሎች ጋር በጥቅም ለመወዳጃ የማድረግ ነገር ይታያል:: ይህ ደግሞ ሙያውን የማያሳድግ እንደውም የሚገል ሆኖ አገኘዋለሁ:: ለምሳሌ አንድ ጋዜጠኛ አንድ ቦታ ላይ ይሄድና በቃ ከዚህ በኋላ እኔ ብቻ ነኝ የምመጣው ሌላ ሰው ቢመጣ መረጃ እንዳትሰጡ ብሎ ዘግቶ ይመጣል፤ ገንዘብ አለ ተብሎ በሚታሰብበት ቦታ ላይ ራስንና ሙያውን አዋርዶ መሻማት ይታያል፤ የጋዜጠኝነት ህይወት ደግሞ ፍጹም ይህንን የማይፈልግ ይልቁንም ራስን መስጠት የሚፈልግ ነው:: በመሆኑም በሙያው ውስጥ ያሉ ወጣቶች ከጥቅም ይልቅ ለሙያዊ ስነምግባር ታማኝ በመሆን ለህብረተሰቡ አርዓያ መሆን አለባቸው::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2014