
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ከሚገኙ 36 የነዳጅ ኩባንያዎች መካከል 26ቱ ከጂቡቲ ተነስቶ ማደያዎቻቸው ስለደረሰው ነዳጅ አስፈላጊውን ሪፖርት አለማድረጋቸውን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ዴሬሳ ኮቱ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ 10 ኩባንያዎች ብቻ የነዳጅ ጭነትና አቅርቦታቸውን በተመለከተ ተገቢውን ሪፖርት አዘጋጅተው ልከዋል። 26ቱ የነዳጅ ኩባንያዎች ደግሞ ሪፖርት ባለማቅረባቸው በሕጉ መሰረት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
እያንዳንዱ ኩባንያ በጂቡቲ በስሙ የጫነውን ነዳጅ በየማደያዎቹ መድረሱንና አለመድረሱን የሚገልጽና የነዳጅ አቅርቦቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያስረዳ ሪፖርት እንዲያደርግ ታዞ እንደነበር አቶ ዴሬሳ አስታውሰዋል።
በዚህ መሰረት ቶታል፣ ኦይል ሊቢያ ፣ የተባበሩት፣ ዛጎልና ሌሎች 10 የነዳጅ ኩባንያዎች የሚጠበቅባቸውን ሪፖርት አቅርበው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁንና በቂ ሪፖርት ያላቀረበው ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) ን ጨምሮ 26 ኩባንያዎች የሚፈለገውን ሪፖርት ባለማቅረባቸው ከእስከ ዛሬ ግማሽ ቀን ድረስ ተገቢውን ሪፖርት እንዲልኩ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
ኩባንያዎቹ በቀጣይ ጊዜ የነዳጅ ሪፖርቱን የማያቀርቡ ከሆነ ሌላ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት አቶ ዴሬሳ፤ ኩባንያዎቹን ከነዳጅ አቅርቦት ድልድል ከማስወጣት አንስቶ የንግድ ፍቃዳቸውን እስከመሰረዝ እንዲሁም ለሕግ እስከማቅረብ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ዴሬሳ ገለጻ፤ ማንኛውም የነዳጅ ኩባንያ ባለቤቶች ከጂቡቲ አንስቶ የሚያጓጓዙትና በየማደያዎቹ የሚያከፋፍሉት ነዳጅ ከግማሽ በላዩ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የወጣበት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ይህን ከግምት ካስገቡ ሥራቸውን በግልጽነት ብቻ ማከናወን እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው።
ከዚህ ውጪ የሚታይ ሂደትና ነዳጅን ለመደበቅ የሚደረግ ሙከራ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን አውቆ መንቀሳቀስ ይገባል ያሉት አቶ ዴሬሳ፤ ማደያዎችም የገዙትንና የሚያከፋፍሉትን ነዳጅ በሕጋዊ መንገድ በማቅረብ ሕዝብን ከእንግልት መታደግ አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልልና የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎችም በነዳጅ ስርጭትና አቅርቦት ላይ ያለውን ሕገወጥ ተግባር ላይ ጠንካራ ቁጥጥጥር ማድረግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
እንደ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን መረጃ ፤ ከጂቡቲ በየቀኑ 300 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ጉዟቸውን ወደኢትዮጵያ ያደርጋሉ። ከዚህ ውስጥ 60 በመቶው የሚሆነው ነዳጅ ናፍጣ የጫኑ ናቸው።
በመላ አገሪቷ የሚገኙት ነዳጅ ማደያዎች ከአንድ ሺህ 300 በላይ ሲሆኑ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 137 ማደያዎች አሉ፤ ከዚህ ውስጥ 20ዎቹ በተለያየ ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም