የወጣትነት እድሜ ብዙ ስራ የሚሰራበት ነው:: ትኩስ ጉልበት ያለውም ከወጣቱ ዘንድ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ በየግዜው ጠንካራና አስደማሚ ስራዎች ይሰራሉ:: በርካታ ሀገራትም በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው በመስራታቸው የብልፅግና ማማ ላይ ወጥተዋል:: የዛሬዎቹ የዓለም ሀያል ሀገራት አሜሪካና ቻይናም የወጣት ተኮር ስራ ውጤት ናቸው::
ወጣቶች ሀገርን ሊለውጥ የሚችል ጉልበት ፣ እውቀት፣ ሃሳብና የስራ ፈጠራ ክህሎት አላቸው:: ነገሮችን በፍጥነትና በጥራት የማከናወን ብቃትም ተክነዋል:: በተለይ ደግሞ ለቴክኖሎጂ ቅርብ በመሆናቸው ዓለምን የሚቀይሩ በርካታ የስራ ፈጣራ ውጤቶችን ጀባ ብለዋል::
በኢትዮጵያም በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት ቢኖርም እንደ አንድ አንጡራ ሃብት በሚገባ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም:: እንደሀገር ለወጣቶች የሚሰጠው ትኩረትም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: በወጣቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ ግን ሀገሪቱን በልዩ ልዩ መንገድ መቀየር እንደሚቻል እሙን ነው:: ለዚህም መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል::
የመንግስት ድርሻ እንዳለ ሆኖ ታዲያ አንዳንድ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ከራሳቸው አልፈው ወገናቸውንና ሀገራቸውን ሲጠቅሙ ይታያል:: በተለይ ደግሞ በእነርሱ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች የእውቀት አድማሳቸው ሰፍቶ ቀጣይ ሕይወታቸው የተቃናና ለሀገራቸውም በጎ አሳቢ እንዲሆኑ የሚታትሩ አልጠፉም:: ለዚህም ድጋፍ አጥተው አቋረጡት እንጂ እነ ወጣት ኑሪያ የጀመሩት ሃሳብ ትልቅ ማሳያ ነው::
ተማሪ ኑሪያ አሚር የዚህ ሃሳብ ጠንሰሽና መስራች ከሆኑት ተማሪዎች ውስጥ አንዷ ናት:: በአዲስ አበባ ረጲ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሰትሆን የንባብ ባህልን ያዳበረችው ገና በልጅነቷ ነው:: ይህ የማንበብ ልምድ ታዲያ በሂደት ዳብሮ የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተከሰተበት ወቅት ከሌሎች ሁለት ጓደኞቿ ጋር በመሆን ቤተ መፅሃፍት ለመከፍት አግዟታል::
በዚህም በወረርሽኙ ምክንያት እቤት ተቀምጠው የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ቤተ መፅሃፍቱን ለመጠቀም እድል ከፍቶላቸዋል:: መፅሃፍ የማንበብ ልምዳቸውን ለማዳበርም በእጅጉ ረድቷቸዋል:: በተለይ ደግሞ በጀሞ ሁለት አካባቢ አንድ ብቻ ቤተ መፅሃፍት የነበረ በመሆኑ ይታይ የነበረውን የቤተ መፅሃፍ እጥረትም መቅረፍ ችሏል:: በዋናነት ደግሞ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚኖሩ ተማሪዎች ቤተ መፅሃፍትን በአቅራቢያቸው አግኝተው እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል::
እርሷና ጓደኞቿ ጀሞ አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ ተከራይተው የከፈቱት ቤተ መፅሃፍት ለተከታታይ ስድስት ወራት ዘልቆ የነበረ ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከዚህ በላይ ሊቀጥል አልቻለም:: ወትሮም ቢሆን ቤተሰብ እያስቸገሩ የቤተ መፅሃፍቱን ኪራይ ሲሸፍኑ የቆዩ ቢሆንም በመጨረሻ አቅማቸው ተሟጦ ቤተመፅሃፍቱን ለመዝጋት ተገደዋል::
ተማሪ ኑራና ሁለቱ ጓደኞቿ ቤተ መፅሃፍታቸው ተዘግቶ አገልግሎት ቢያቆምም ያለስራ ከመቀመጥ በጥቂቱም ቢሆን አንባቢውን ማህበረሰብ ይጠቅማል በሚል በተለያዩ አጋጣሚዎች በራሳቸው ጥረትና በስፖንሰር ድርጅቶች አሰባሰበዋቸው የነበሩትን አንድ ሺ መፅሃፍቶች ለአብርሆት ቤተ መፅሃፍት በቅርቡ አበርክተዋል::
ምንም እንኳን በገንዘብ እጥረት ምክንያት የቤተመጽሀፍቱ አገልግሎት ቢቋረጥም ኑራና ጓደኞቿ የጀመሩትን ትልቅ አላማ ከግብ ለማድረስ ይፈልጋሉ:: ለዚህም በተደጋጋሚ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላትንና የግል ተቋማትን በር ቢያንኳኩም እስካሁን ድረስ በቂ ምላሽ አላገኙም:: አላማቸው ቤተመፅሃፍትን ማቋቋም ብቻ ሳይሆን በወጣቶች ዙሪያም ትላልቅ ስራዎችን የመስራት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተቻው አካላት ለወጣቶቹ በቂ ምላሽ እንደሚሰጧቸው ይጠበቃል::
ተማሪ መሰረት አሰፋም የዚህ ቤተመፅሃፍት መስራች ስትሆን ልክ እንደ ኑራ ሁሉ በረጲ ሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናት:: ቤተመፅሃፍቱን የማቋቋሙን ሃሳብ እርሷና ጓደኞቿ የጀመሩት ገና የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነው:: ግዜው የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተበት በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የሚሄዱት በሳምንት ሶሰት ቀን በመሆኑና የቀረውን ግዜ በእረፍት ስለሚያሳልፉ በዚህ ግዜ ተማሪዎች በትርፍ ግዚያቸው መፅሃፍት በማንበብ እንዲያሳልፉ ቤተ መፃህፍት የመክፈት ሃሳብ መጣላቸው::
የቤተ መፅሃፍቱ መከፈት በአካባቢው ያሉ ተማሪዎችን ከመጥቀም በዘለለ ተማሪ መሰረትና ጓደኞቿ በወቅቱ አስረኛ ክፍል የነበሩ በመሆናቸው ለብሄራዊ ፈተና ጥሩ ዝግጅት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል:: በቤተሰቦቻቸው ዘንድም ሃሳቡ ትልቅ ተቀባይነት በማግኘቱ አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ ተደርጎላቸዋል::
ገና ቤተ መፅሃፍቱን የመክፍት ሀሳቡን እንደጠነሰሱ በቅድሚያ የሄዱት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ሲሆን ሃሳባቸውም ወዲያውኑ ተቀባይነት አግኝቷል:: ቤተ መፅሃፍት ለማቋቋም የሚያስችል ህጋዊ ሰውነት ከፅህፈት ቤቱ ካገኙ በኋላ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በመሄድ መፅሃፍቶችን ማሰባሰብ ችለዋል:: በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከወመዘክር መፅሃፍቶችን በማሰባስብ ቤተመፅሃፍቱን አቋቁመው ወደ ስራ ገብተዋል::
በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ በርካታ ተማሪዎች ይኖራሉና፤ ቤተመፅሃፍቱንም ይጠቀማሉ በሚል የጀመሩት የቤተመፅሃፍት አገልግሎት መጀመሪያ ተማሪዎች ቤተመፅሃፍቱን እስኪለምዱትና የማንበቡንም ልምድ እስከሚያዳብሩ በነፃ ይገለገሉ ነበር:: በሂደት ግን ሃሳባቸው ተማሪዎቹ እየከፈሉ ቤተመፅሃፍቱን እንዲገለገሉ የነበረ ቢሆንም ይህ ባለመሳካቱ ቤተመፅሃፍቱ በቤተሰባቸው ድጋፍ ኪራዩን እየሸፈነ ለስድስት ወራት ከቆየ በኋላ የገንዘብ እጥረት አጋጥሞት ስራውን አቁሟል::
‹‹በአሁኑ ግዜ ለአብርሆት ቤተ መፀሃፍት ከ አንድ ሺ በላይ መፃህፍትን አስረክበናል›› የምትለው ተማሪ መሰረት ይህንንም ያደረግነው የእኛ ቤተ መፀሀፍት ስራ በማቆሙ መፅሃፍቶቹ ያለስራ ከሚቀመጡ አብርሆት ገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መሆኑን ትገልፃለች::
በቀጣይም የሚመለከታቸው አካላት በማናገርና በመሰባሰብ ቤተመፃህፍቱን ዳግም ከማቋቋም በዘለለ ሁሉን አቀፍ የወጣቶች ማእከል ለማቋቋምና በተለያየ መልኩ ወጣቶችን የመታደግ ሃሳብ እንዳላቸውም ታስረዳለች:: በዚህ አጋጣሚ ወቅቱ ክረምት ነውና ወጣቶች አልባሌ ቦታ ከሚያሳልፉ ግዚያቸውን በንባብ እንዲያሳልፉ ትመክራለች::
ተማሪ ታሪኳ አብሼም እንዲሁ በረጲ ሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ኑራና መሰረት ቤተመፀሃፍት ሲቋቁሙ እርሷም የበኩሏን ጥረት አድርጋለች:: እርሷና ጓደኞቿ የመሰረቱት ቤተ መፅሃፍት በሁለት እግሩ ከቆመ በኋላ በገንዘብ እጥረት መቆሙ ይቆጫታል:: ግን ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት በቂ ድጋፍ ቢገኝ ከዚህም የተሻለ ቤተ መፅሃፍትና የወጣቶች ማእከል መገንባት እንደሚቻል ታስባለች::
የተለያዩ ሀሳብና እቅድ ያለቸው በርካታ ወጣቶች አሉ የምትለው ተማሪ ታሪኳ፤ ወጣቶቹ ያሰቡት አላማና እቅድ እንዲሳካ ከበርካታ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ትናገራለች:: በተለይ ደግሞ መንግስት እንዲህ አይነት ወጣቶችን ሀሳብ መደገፍ እንዳለበት ትጠቁማለች::
‹‹የእኛም ሀሳብ ከዚህ የተለየ አይደለምና የሚመለከታቸው አካላት አላማችንን ሊደግፉን›› ይገባሉ ትላለች:: በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነቱ ሀሳብ በወጣቶች ሁለንተናዊ ስብእና ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ከመሆኑ አንፃር ድጋፉ የግድ እንደሚያስፈልግ ትጠቁማለች:: እኛም እንዲህ አይነቱን ድጋፍ ብናገኝ ኖሮ የተሻለ ደረጃ መድረስ እንችል ነበር ስትል ትገልፃለች::
የእርሷና የጓደኞቿ ህልምም ቤተመፅሃፍቱን መልሶ ማቋቋም ብቻ ሳይሆን የወጣቶች ማእከልም ጭምር መገንባት በመሆኑ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለሚያስችል በዚህ አጋጣሚ መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚገባው ታመለክታለች::
ወጣቶችም ቢሆኑ አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ የክረምቱን ወቅት በንባብ ቢያሳልፉ ያተርፋሉ እንጂ አይከስሩም ትላለች:: ንባብ አንድም እውቀት ለመቅሰም ሁለትም የእረፍት ግዜን እየተዝናኑ ለማሳለፍ ስለሚጠቅም ወጣቶች የማንበብ ባህላቸውን ከወዲሁ ማዳበር እንዳለባቸውም ትጠቁማለች:: በዚህም የተሻለ ማንነታቸውን መገንባትና የህይወት አቅጣጫ ማየት እንደሚችሉ ትጠቅሳለች::
የወጣቶች ስብእና የሚገነባው በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤትና በአካባቢ ማህበረሰብ ነው:: ከዚ ባሻገር ወጣቶች ስብእናቸውን የሚገነቡትና የእውቀት አድማሳቸውን የሚያሰፉት በንባብ ነውና ኑራ፣ መሰረትና ታሪኳ የጀመሩት ስራ እንደቀላል የሚታይ አይደለም:: እናም እንዲህ አይነት ተግባራት ለሀገርም ለወገንም ይጠቅማሉና መንግስት፤መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ባለሃብቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል የእለቱ መልእክታችን ነው:: ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2022