በ 2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች በሁለት ዙር የተፈተኑ ሲሆን፤ በሁለቱም ጊዜ የተለያየ ችግር አጋጥሞ እንደነበር ይታወሳል። በተለይም የሁለተኛው ዙር ፈተና በጦርነቱ አካባቢ ለሚኖሩ ተማሪዎች ትልቅ ተግዳሮት ነበር። ምክንያቱም ተረጋግተው ባለመፈተናቸውና የደረሰባቸው የስነ ልቦና ጉዳት ውጤታቸው ላይ ጥላ በማጥላቱ። በዚህም ውጤት ይፋ በተደረገ ጊዜ በስፋት የችግሩ ሰለባ የነበሩ አካባቢ ብዙ ጥያቄ ሲያነሱ ነበር።
በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ተጎጂ ከነበረው ክልል መካከል የአማራ ክልል ውጤት ብዙዎችን ያሳዘነና ጥያቄ ያስነሳ እንደነበረም ታይቷል። በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ተማሪዎች ዳግም ፈተናውን እንዲወስዱ አቅጣጫ አስቀምጧል። ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ግጭት ለነበረባቸው ክልሎች ተስፋ ሰጪ እንደሆነም ይነገርለታል። ሆኖም በሚገባ ከተዘጋጁበት ብቻ ነው እድሉ ለስኬት የሚያበቃው።
ይህ እድል ከተሰጣቸው መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ሲናገሩ፤ አካባቢው በወረራና በጦርነት ውስጥ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ዋና ትኩረቱን አድርጎ የነበረው ራሱን ማዳንና መታገል ላይ ነበር። ተማሪዎችም የዚሁ አካል ነበሩ። ይህ ደግሞ ብዙ ጫና አሳድሯል። ስለሆነም በስነልቦና ተዘጋጅተው መፈተን አልቻሉም። ውጤቱ ያሰቡትን ያህል እንዳይሆንም ያደረገው ይህ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው እድል ለመጠቀም የችግሩን አሳሳቢነትና ውስብስብነት ለባለድርሻ አካላት የማሳወቅ ሥራ እንደተሠራ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ሁሉም ትምህርት ቤት አውቆ እንዲሠራበትም አቅጣጫ ወርዷል። ውሳኔዎች ከተላለፈባቸው መካከልም ቅድሚያ የተሰጠው ውጤት ማሻሻልን የተመለከተው ጉዳይ ሲሆን፤ ጎን ለጎን የስነልቦና የምክር አገልግሎትም እንደሚደረግ አንስተዋል።
የውጤት ማሻሻያ ተብለው የተወሰዱ ውሳኔዎች ምንም እንኳን ተማሪዎቹ በብዙ መንገድ ትምህርቱን የሸፈኑና የፈተናውን ሁኔታ የተለማመዱት ቢሆንም፤ ተረጋግተው አላደረጉትምና ያውቁታል ለማለት ያስቸግራል። ስለሆነም ዳግም ሁሉንም መደበኛ ትምህርት የሚከታተሉበትን ዕድልመፍጠር አስፈልጓል። ከመደበኛ ተፈታኞች ጋር አብረው እንዲማሩና ሞዴል ጭምር እንዲወስዱም ውሳኔ ተላልፏል። በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ ሳይቀር እንዲማሩ የሚደረግበት ሁኔታ ተመቻችቷል። የማጠናከሪያ ትምህርት (ቲቶሪያል) ክላስም እንዲሁ ከመደበኛው ተማሪ እኩል እንዲሳተፉም መደረጉን አስረድተዋል።
የመጽሐፍ እጥረት የሚያጋጥም ሲሆን፤ ተማሪዎች ዋይ ፋይ ባለባቸው ቦታዎች ላይ እየገቡ መጽሐፍትንና የተለያዩ ነገሮችን በማውረድ የሚያጠኑበትን አጋጣሚ ክፍት መደረጉን ያነሱት ኃላፊው፤ ቤተ መጽሐፍትም እንደፍላጎታቸው የሚጠቀሙበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል። በትምህርት ሥርዓቱ ከሰኔ 30 በኋላ ትምህርት ያበቃል። ሆኖም ዳግም ተፈታኞችም ሆኑ መደበኛ ተፈታኞች ሐምሌና ነሐሴ መዘናጋት እንዳይገጥማቸው ባለበት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉም እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ምን ምን ነገሮች መሟላት እንዳለባቸው ከአሁኑ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህንን የፈተና ጊዜ ለማለፍ መምህራን ከምንም በላይ እየተጉ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ የዘንድሮ ውጤት ተማሪውን ብቻ ሳይሆን የክልሉን ነዋሪ ጭምር ልብ የሰበረ ነው። በተለይ መምህሩ በእጅጉ አዝኗል። በዚህም ቁጭታቸውን ለመወጣት ከምንም በላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በማስተማር ላይ ናቸው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የተለያዩ ወርክ ሽቶችን ያሠሯቸዋል። ተማሪዎች በሚመቻቸው ልክ ቀርበዋቸው ይደግፏቸዋል። ይህ ደግሞ ተማሪዎች በሚፈለገው መጠን እንዲዘጋጁ እያደረጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ሥራውን ሲያከናውኑ መጀመሪያ የተማሪዎች ውጤት በአግባቡ ተፈትሾ ወዳቂው እንዲታይ ማድረግ፣ ከዚያም ባሻገር ጎበዝ ተማሪዎች ውጤታቸው ታይቶ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድል እንዲያገኙ ማስቻልና በመጨረሻም ቀሪዎቹ ዳግም እንዲፈተኑ ማገዝ የሚሉ ሲሆኑ፤ ሁሉም በተደረጉት ውይይቶችና ትግሎች ውሳኔዎች ተላልፎባቸዋል። ምክንያቱም ክልሉ በግጭት ረጅም ጊዜን በማሳለፉ ችግር ገጥሟል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ በውሳኔው ልክ ትግበራው ሙሉ ለሙሉ እየሄደ ነው ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም ሁኔታዎች ወደውሳኔው ለመግባት ላያስችሉ ይችላሉ። ለአብነት የክፍል ጥበት ካለ ቅድሚያ የሚሰጠው ለመደበኞቹ ተማሪዎች ይሆናል። እናም ዳግም ተፈታኞች እድሉን ላያገኙ ይችላሉ። በተመሳሳይ የመጽሐፍት እጥረትና መሰል ነገሮች ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ግን የተለዩ አማራጮችን ከመጠቀም ወደኋላ አልተባለም። ለምሳሌ፡- ፈረቃ እያስተካከሉና ጊዜያዊ መማሪያ ክፍል እየገነቡ ማገዙ አንዱ ነው። የመጽሐፍት እጥረትን ደግሞ ቤተመጽሐፍት ገብተው በጋራ እንዲጠቀሙ ማስቻል መፍትሔ ተደርጓል።
ከፍተኛ ግጭት በነበረበት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ፍላቂት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማረው ዳግም ተፈታኝ ሳሙኤል ጸጋዬ እንደሚለው አቅጣጫው በተለይም እነሱ ባሉበት ወረዳ ላይ ሙሉ በሙሉ እየተተገበረ አይደለም፣
ተማሪዎች በራሳቸው ጥረት የቻሉትን ያህል እያደረጉ እንደሚገኙ የሚያነሳው ሳሙኤል፤ በአቅራቢያቸው ያሉ ትምህርት ቤቶች ላይም ተግባሩ እየተከናወነ ነው ለማለት እንደሚቸገር ይገልጻል።
የዘንድሮ ፈተና ባልጠበቅነውና ባልተረጋጋንበት ሁኔታ እንድንፈተን መሆኑ በውጤታችንም ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖን አሳድሯል የሚለው ተማሪ ሳሙኤል አሁንም ለተማሪዎች የተሰጡ የዳግም ፈተና እድሎች በትክክል መሬት ወርደው ተግባራዊ ቢሆኑ ውጤቱ እንደሚሻሻል የመንግስት ጥረትም ውጤት እንደሚያመጣ ነው የሚናገረው፡፡
እርሱ ያመጣው ውጤት 407 ነው ጎበዝና ፈተናውን በአግባቡ እንደሠራው ስለሚረዳ ዳግም እንዲታረምለት ጠይቆ እንደነበር ገልጾ ይህም ምላሽ አለማግኘቱ ቅሬታ እንደፈጠረበት ያብራራል ፡፡
እርሱ እንደሚለው፤ ለተማሪዎቹ ውጤት መላሸቅ አንዳንድ ብልሹ አሠራሮች አሁንም ስለሚታዩ ይህንን ማረም ያስፈልጋል፤ ካልሆነ ግን ሰዎች በተለያየ መንገድ ያለእውቀታቸው ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገባሉ፤ መግባት የነበረባቸው ጎበዝ ተማሪዎች ይቀራሉ፤ ይህ ደግሞ ለሀገርም ኪሳራ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ባሉት ሂደቶችም ሊታሰብበት እንደሚገባ አብራርቷል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው፤ እንደ ክልል የተሰጠው እድል ብዙ ነገር ይዞ ይመጣል። ኦሮሚያ ክልልም ብዙ የተጠቀመበት ነው። ወደ 21 ሺህ ከሚጠጉት ተማሪዎች ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው እድል ሦስት ሺህ ያህሉ ተጠቃሚ ሆነዋል። አሁንም የቀሩት ተማሪዎችን ብዙ ቢሆኑም ለማገዝ ይሞከራል ብለዋል።
በክልሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብዙ ናቸው። በሀገሪቱ ከሚፈተነው ተማሪ ውስጥ 42 በመቶውን ይይዛሉ። ስለሆነም ዳግም ተፈታኞችን በመደበኛው ልክ ለማገዝ አዳጋች ነው የሚሉት ዶክተር ቶላ፤ በተቻለ መጠን አንዳንድ እድሎችን ለመስጠት እንደሚሠራ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ቤተመጽሐፍትን እንዲጠቀሙ፣የማጠናከሪያ (ቲቶሪያል) ትምህርት ላይ እንዲሳተፉ ፣እንዲሁም ተማሪዎቹ በራሳቸው እንዲዘጋጁ የማድረግ ሥራዎች ይሠራሉ፣ ይህ በመንግሥት የተመቻቸው እድል ለሁሉም ይሠራ ዘንድ እስከታች ተወርዶ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ግጭት ያለባቸው ቦታዎች ተብለው የተለዩና በሁለተኛ ዙር የተፈተኑት ተማሪዎች ወደ 54 ሺህ የሚደርሱ ሲሆኑ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት በ43 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ 152ሺ 144 ተማሪዎች እንዲማሩ ተደርጓል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን ሚኒስቴሩ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የፈተና ውጤትን ለመለየት ዳግም ፈተና ለወደቁት እንዲሰጥ ተገዷል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ ተማሪዎች ይህ እድል ሲሰጣቸው አንድም አዎንታዊ ሌላም አሉታዊ ነገር ይገጥማቸዋል። እንደቢሮ ግን የሚፈለገው አዎንታዊው እንዲሰፋ ነውና ለዚህ የሚያግዝ ሥራ እየተሠራ ነው። ይሁን እንጂ ተማሪዎች ካልተጠቀሙት እድሉ በራሱ ይዞ የሚመጣው ነገር የለም። ስለሆነም በሆነው ነገር ሳይቆዝሙ እድሉን መጠቀሙ ላይ ትኩረታቸውን ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል። መምህራን፣ቤተሰብ ፣ የክልሉ ማኅበረሰብም ለዚህ ሥራ ውጤታማነት ተሳትፎን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ዶክተር ቶላ በበኩላቸው፤ ይህ እድል መቼም ያልሆነና ወደፊትም ሊፈጠር የማይችል በመሆኑ ተማሪዎች ከመዘናጋት ወጥተው ቤተ መጽሐፍትንና የማጠናከሪያ ትምህርት (ቲቶሪያል) ላይ ባለመቅረት የራሳቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ይህ ደግሞ የማስታወስና የማንበብ ክህሎታቸው በአለበት እንዲቀጥል ያደርጋቸዋል። ለውጤታማነታቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አምነው ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
እድሉ በቀላሉ የመጣ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ይህ ሥራ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው። በተለይም ተማሪዎች የተሰጣቸውን እድልና የሚደረግላቸውን ድጋፍ በቸልታ ሊያዩት አይገባም።
‹‹በግጭት አካባቢ የነበሩ ተፈታኞች በተለይም ጎበዝ የሚባሉት ውጤታቸው ዳግም እንዲታይ እንኳን አልተደረገም። ስለሆነም በሁሉም መንገድ የተጎዳ ተማሪ አድርጎናል›› የሚለው ተማሪ ሳሙኤል፤ የተሰጠው እድል መልካም ቢሆንም አሁንም ጥንቃቄ ያሻዋል። መንግሥት ይህንን አይቶ ከመቼውም በላይ ትኩረት ሊያረድግ ይገባል። የሚሰጣቸውን እድሎች ታች ወርዶ መተግበራቸውን ማየት፤ የእድሉን አሰጣጥ ግልጽ ማድረግ፤ ሁሉንም ለመጥቀም መሞከር ያስፈልጋል ብሏል ።
ይህ እድል የተሰጣቸው ተማሪዎችም ቢሆኑ በስነልቦናም ሆነ በትምህርት መታገዝ አለባቸው የሚለው ተማሪው፤ ተማሪዎቹም ይህ እድል የማይደገም ነውና በአግባቡ ተስፋ ሳይቆርጡ መጠቀም እንዳለባቸው ይመክራል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014