በ2011 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሪነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር (Green Legacy Initiative) ባለፉት ሦስት ዓመታት 18 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። ይህ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከማሻሻል ባሻገር ለምግብ ዋስትናና ለአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች አማራጭ መፍትሄ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ዓመታት ስለተከናወኑት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች እና ስለዘንድሮው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም አረንጓዴ ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ዓላማ እንዳለው አስታውሰው፤ መርሃ ግብሩ እስካሁን በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል። በመርሃ ግብሩ የሦስት ዓመታት ትግበራ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ 18 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞች ተተክለዋል፤ ዓመታዊ የመጽደቅ ምጣኔውም ከ80 በመቶ በላይ ነው። ከ183ሺ በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል ዕቅድ ተይዞ በዕለቱ፣ በ12 ሰዓታት ብቻ፣ 354 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ከእቅዱ በላይ ማሳካት ተችሏል። ሀገራዊ ምርጫ በተካሄደበት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ኢትዮጵያውያን ድምፃቸውን ከመስጠታቸው በተጨማሪ በዕለቱ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈው የማይረሳ የዴሞክራሲና የአረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለችግር መጋለጧን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለዚህ ችግር ከተሰጡ ፈጣን የተግባር ምላሾች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትግበራ የተከናወኑና በቀጣይም የሚከናወኑ ተግባራት የካርበን ልቀትን እንዲሁም የአየርና የውሃ ብክለትን ለመቀነስ፣ እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች ዝናብ እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው አንጠራጠርም›› ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራው አራተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ‹‹አሻራችን ለትውልዳችን›› በሚል መሪ ቃል ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል። ከሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ የተዘጋጁበት የዘንድሮው መርሃ ግብር፣ በአራት ዓመታት ለማሳካት የታቀደው 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ከእቅዱ በላይ የሆነ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ ያስችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ‹‹ላለፉት ሦስት ዓመታት በስኬት ሲከናወን የቆየውና ዘንድሮም የቀጠለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ትልልቅ ነገሮችን መጀመር ብቻ ሳይሆን የምትጨርስ ሀገር እንደሆነች ለዓለም ያሳየችበት ነው›› ብለዋል። ‹‹በቀኝ እጃችን ልማታችንን በማስቀጠል በግራ እጃችን ደግሞ ጠላቶቻችንን በመዋጋት ሀገራችንን ለመለወጥ እንሠራለን›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት አንድ ሰው መቶ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር እንደሚጀመርና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አንዱ ትኩረት የተሰጠው አትክልትና ፍራፍሬ መትከል መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹በአሮጌ አስተሳሰብና አተያይ ኢትዮጵያን የመሰለ ታላቅ አገር ማስቀጠል ያስቸግራል። የኢትዮጵያውያንን አመለካከት በማደስ ኢትዮጵያን ማደስ አለብን። ስለሆነም ሕጎችን፣ አሠራሮችን እያሻሻልን ነው፤ ቤቶች እያደስን ነው፤ የቆሙ ፕሮጀክቶችን በማፋጠን እየተጠናቀቁ ነው፤ ይህ በቂ ስላልሆነ ችግኞችን በመትከል ምድራችን እያደስን ነው›› በማለት ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዓለምን ያስደመመ ሥራ መሰራቱን አስታውሰው፣ ለዚህ ዘመን ትውልድ የሚመጥን በበጎ መልኩ ሊወረሱ የሚችሉ ተግባራትን ማውረስ እንደሚገባ ገልጸዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ለስነ ምህዳር መጠበቅ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደምትገኝ ማሳያ ስለመሆኑም ተናረግዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ከተዘጋጁት ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሲሆኑ 47 በመቶው የደን ችግኞች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሑሴን ናቸው። ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ችግኞቹ የመሬት መራቆትን በመግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። በችግኝ ተከላው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተለዩ እየተተከሉ እንደሆነም አቶ ዑመር ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ውጤቶች የተገኙበትና መልካም ተሞክሮዎች የተቀሰሙበት ተግባር ስለመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመስክሮለታል። በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ ባለፉት ሦስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የትግበራ ዓመታት በየዓመቱ ያስገኛቸው ብዙ መልካም ተሞክሮዎች እንዳሉ ይገልፃሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ የፍራፍሬ ችግኞች ተከላ በየዓመቱ እያደገ መጥቷል። ዘንድሮ ደግሞ ካለፉት ሦስት ዓመታት በላቀ መልኩ ለፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት ተሰጥቶ ለተከላ ዝግጅት ተደርጓል።
ኅብረተሰቡ ስለአረንጓዴ አሻራ ያለው ግንዛቤ እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ያለው የማኅበረሰብ ግንዛቤ ከአራት ዓመታት በፊት ከነበረው በእጅጉ የተሻለ ነው። የግንዛቤው ማደግ የኅብረተሰቡ ችግኝ የመትከልና የመጠበቅ ባህሉና ጥረቱ እንዲጨምር ያደርጋል። ችግኝ መትከል እንደባህል እየተለመደ መጥቷል። የእነዚህ ቅንጅት ደግሞ ከችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የሚፈለገው ውጤት እንዲገኝ እድል ይፈጥራል።
ለሀገር በቀል ዛፎች የተሰጠው ትኩረትም በየዓመቱ እያደገ መምጣቱ ሌላው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ውጤት ነው። ከመርሃ ግብሩ መጀመር በፊት በነበሩት ዓመታት ይተከሉ የነበሩት ችግረኞች የውጭ ዝርያ ያላቸውና በፍጥነት የሚደርሱ ችግኞች ነበሩ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከበጋ ወራት የሥነ አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ጋር አቀናጅቶ ማዝለቅ መቻሉም በመርሃ ግብሩ ትግበራ የተገኘ ውጤት ነው። የበጋ ወራት የሥነ አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ሲሰሩ በክረምት የሚከናወነው የችግኝ ተከላ ስራ ታሳቢ ተደርጎ መሰራቱ እና እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች ውሃን ለመሰነቅ የሚደረጉት ጥረቶች እየተሻሻሉ መምጣታቸው በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በእርግጥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የተከናወነው ፍፁም ከችግሮች በፀዳ መልኩ እንዳልሆነ ይታወቃል። አቶ ተፈራ እንደሚናገሩት በመርሃ ግብሩ በመልካም ተሞክሮነት የተገኙት ውጤቶች እንከን አልባ ናቸው የሚባሉ ስላልሆኑ የእነርሱ ጉድለቶች በመርሃ ግብሩ ትግበራ ላይ እንዳጋጠሙ ችግሮችና የአፈፃፀም ክፍተቶች ተደርገው ይቆጠራሉ። ሀገር በቀል ዛፎችን የማዘጋጀትና የመትከል ስራው አሁንም ገና ብዙ የሚቀረው ተግባር ነው። የድህረ ተከላ ስራዎችም ከአፈፃፀም ክፍተቶች መካል የሚጠቀሱ ናቸው። ችግኞች ከተተከሉ በኋላ የሚከናወኑ አንዳንድ የድህረ ተከላ ተግባራት በአጥጋቢ ሁኔታ አለመከናወናቸው በችግኞች የመጽደቅ ምጣኔና በሚጠበቀው ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል።
‹‹በእርግጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የችግኝ የመጽደቅ ምጣኔ አመልካቾች እንደሚያሳዩት የችግኞች የመፅደቅ ደረጃ ከ70 ከመቶ በላይ ከሆነ የተሻለ አፈፃፀም እንደተመዘገበ ይቆጠራል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች የተመዘገበው የመጽደቅ ምጣኔ ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ ነው። እኛ ግን ከዚህም በላይ እንዲጸድቅ ፍላጎት ስላለን እንጂ ባለፉት ሦስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሮች የተመዘገበው የመፅደቅ መጠን ከዓለም አቀፍ መመዘኛ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ተደርጎ የሚወሰድ ነው›› ይላሉ።
የጥበቃ ስራ ከድህረ ተከላ ስራዎች የሚመደብ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተፈራ፣ በዚህ የድህረ ተከላ ተግባር ረገድ በአንዳንድ ቦታዎች ለችግኞች የሚደረገው ጥበቃ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ከመርሃ ግብሩ ትግበራ ችግሮች መካከል አንዱ እንደሆነም ይናገራሉ።
ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም፣ በይፋ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ አራተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአራት ዓመታት የችግኝ ተከላ ወቅቶች ለማሳካት የታቀደው 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ከእቅዱ በላይ እንዲሳካ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህኛው ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል፤ የመትከያ ቦታ ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል።
ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን በላይ የደን ችግኞች፣ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ የጥምር ደን ችግኞች፣ ከ500 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞች፣ 35 ሚሊዮን የቀርከሃና 800 ሚሊዮን ደግሞ ለእንስሳት መኖ ጥቅም የሚሰጡ ቁጥቋጦዎች እና ለከተማ ውበት የሚያጎናጽፉ ችግኞች መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህ መርሃ ግብር ከሚተከሉት ችግኞች መካከል ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑት እንደ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና አፕል ያሉ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበስ የደን ሽፋኗን ከመጨመር የተሻገረ ዓላማና ፋይዳ እንዳለው ዓይነተኛ ማሳያ ነው። መርሃ ግብሩ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ማካተቱ ለምግብ ዋስትናም ሆነ ለግብይት አገልግሎት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
አቶ ተፈራ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተዘጋጁት ችግኞች በብዛትም ሆነ በስብጥር ካለፉት ዓመታት የተሻሉ እንዲሆኑ ስለመደረጉ ይገልፃሉ። ‹‹ለአብነት ያህል ዘንድሮ ለተከላ የተዘጋጀው የፍራፍሬ ችግኝ ቁጥር ባለፉት መርሃ ግብሮች ከተተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች የበለጠ ነው። የዛፍ ዝርያ ያላቸው ብዙ ዓይነት ችግኞችም ለተከላ ተዘጋጅተዋል። የደን፣ የቀርከሃ፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ፣ የከተማ ውበት ማስጠበቂያ፣ የመኖና ሌሎች ችግኞች ተዘጋጅተዋል። የተተከሉ ችግኞች እንዳይፀድቁ አንዱ መሰናክል ልቅ ግጦሽ ነው።
ልቅ ግጦሽን ማስቀረት የሚቻለው ለእንስሳት ቀለብ የሚሆን ምግብ ማቅረብ ሲቻል በመሆኑ ለመኖ ችግኞች ትኩረት ተሰጥቶ ለተከላ እንዲዘጋጁ ተደርገዋል›› በማለት ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት መዋቅርን በመጠቀም ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ስለመከናወናቸው፣ ከመንግሥት የተመደበው በጀት በአግባቡ ለችግኝና ለተከላ ቦታዎች ዝግጅት እንዲውል ስለመደረጉ እንዲሁም የችግኝ ተከላውን ውጤታማ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በቅንጅት ስለመሰራቱም ያብራራሉ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በቂ ዝግጅት መደረጉን ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር። ቋሚ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም የተከናወኑትን የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ውጤታማነት መገምገሙንና ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የተከናወኑት የዝግጅት ተግባራት ጥሩ አፈፃፀም እንደነበራቸው ገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴርም ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመንግሥት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች፣ በማህበር በተደራጁ ወጣቶች እና በግለሰቦች የተዘጋጁ በቂ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ እንደተደረጉ መግለፁ ይታወሳል። እንደሚኒስቴሩ መረጃዎች የዘንድሮው መርሃ ግብር የተጋለጡ መሬቶችንና ከዚህ ቀደም ችግኝ ተተክሎባቸው ውጤት ያላመጡ መሬቶች ላይ በድጋሚ በመትከል እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ አዳዲስ መሬቶችን እየፈለጉ በመትከል የሚተገበር ይሆናል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሲጀመር 27 የነበሩት የችግኝ ጣቢያዎች በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው 121 ሺህ ደርሷል።
ችግኝ መትከል ብቻ ውጤት እንደማያስገኝ በኅብረተሰቡም የታወቀ፣ በመንግሥት አካላትም ተደጋግሞ የሚነገር ሃሳብ ነው። እንክብካቤ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ተግባር እንደሆነ ማብራሪያ የሚፈልግ ጉዳይ አይደለም። ‹‹ችግኝ መትከል በራሱ ግብ አይደለም›› የሚሉት አቶ ተፈራ፣ ‹‹ግብ ሊሆን የሚችለው የተተከሉት ችግኞች ፀድቀውና አድገው ማገዶ፣ የቤት መስሪያ መሆን ሲችሉ፣ የሚፈለገውን ምርት ሲሰጡና ከምርቱ ተጠቃሚ መሆን ሲቻል በአጠቃላይ ችግኞቹ አድገው በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የተተከሉበትን ዓላማ ማሳካት ሲችሉ ነው። ስለሆነም የድህረ ተከላ ተግባራትን በትልቅ ትኩረት ማከናወን ይገባል›› ይላሉ። የድህረ ተከላ ስራዎች በየዓመቱ መሻሻሎችን እያሳዩ ቢሆንም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተፈተነች የመሆኗ እውነታ በአረንጓዴ አሻራ በንቃት የመሳተፍ ተግባር ለኢትዮጵያውያን አማራጭ ሳይሆን ግዴታ እንዲሆን ያደርገዋል። ኢትዮጵያውያን ‹‹ችግኝን ተክሎ አለመንከባከብ ማለት ወልዶ መጣል ማለት ነው›› ሲሉ ይደመጣሉ። እውነት ነው፤ችግኝ እንክብካቤና ክትትል ስለሚፈልግ ችግኝን በልጅ፣ የተከለውን ችግኝ አለመንከባከብን ደግሞ ልጅን ወልዶ ከመጣል ጋር ማነፃፃር ስህተት አይሆንም። ስለሆነም በችግኝ ተከላው በንቃት መሳተፍና የተተከሉ ችግኞችንም በመንከባከብ በአሁኑ ወቅት ዓለምን ለረሀብ፣ ለስደትና ለመከራ የዳረጋትን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት በብርቱ ማገዝ ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2014