ኢትዮጵያውያን ከሞላ ጎደል እምነት ወይም ሃይማኖት አለን። አማኝ ነን ብለንም በየእምነት ቦታችን እንገኛለን፣ እንመላለሳለንም። በየትኛውም እምነት ውስጥ እንገኝ እምነቶች ሁሉ የሚጋሩት ትዕዛዝ በጎ መሆንን፣ ለሰው ልጆች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ብሎም ለሌሎች መኖር ነው። ሃይማኖታዊ እምነታችን ምድር ላይ እስካለን ለሰው ልጆች መልካም እንድንሆን ፍቅርና ኅብረት እንድናስተምር ያዘናል።
የተለያዩ ጥናቶች ላይ በመመርኮዝ መረጃዎች ስናገላብጥ እኛ ኢትዮጵያውያን የእምነትና ሃይማኖት ባለቤቶች መሆናችንን የሚያሳዩ ማስረጃዎች በርከት ብለው ይገኛሉ።ኢትዮጵያ አማኞች በብዛት ከአምላካቸው ጋር ባላቸው ትስስር የሚታወቁባት አገር መሆኗን እኛ ሳንሆን ሌሎችም ሊመሰክሩ ይችላሉ።
ዛሬ እዚህ እውነት ላይ ተመርኩዤ አንድ ጥያቄ ማንሳት ፈለኩ። የእውነት እኛ ኢትዮጵያውያን የእምነትና ሃይማኖት ሰዎች ነን? ሃይማኖትና እምነታችን ባዘዘን፣ እንድንሆን በሚፈቅድልንና እንድናደርግ በሚያዘን መልካም መንገድ ላይ ነኝ? አዎ ይሄን ጥያቄ እያንዳንዳችን እራሳችንን ጠይቀን ምላሽ መስጠት ያለብን ወቅት ላይ እንገኛለን። እኔ እውነት እምነቴን የማውቅ ጠንካራና ለሰው ልጆች የማሰብ በሰዎች ዘንድ በመልካምነት የምታወቅ ነኝ ወይ? ማለት ተገቢ ነው።
አገራችን የሃይማኖትና እምነት ሀገር ናት፤ ሕዝቦቿም አማኞች ናቸው የሚለው ጉዳይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተግባርና ከሁኔታችን ጋር እየተፋለሰ መጥቷል። አማኞች ስነምግባር የተላበስን መሆናችንን የሚያጠያይቅ አጠራጣሪ ምልክቶች እዚህም እዚያም መበርከት ጀምረዋል። እምነታችንን አውቀነው የሚያዘንን መተግበር፣ ከሚከለክለን ደግሞ መታቀብ የእኛ መሠረታዊ ጉዳይ ቢሆንም ከዚያ መሠረት ግን ርቀናል። እምነታችን በትክክል በስነምግባር ማሳየት፣ መተግበሩና መኖሩ ላይ እጅጉን ደክመናል። እምነታችን በመልካም ነገሮች መርሕ የቆመ ሆኖ ሳለ እኛና ተግባራችን፣ የዘወትር ልምዳችን ከዚህ ፍፁም ያፈነገጠ ነው።
እዚህ ላይ ቆም ብለን በማሰብ እራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል። አሁን ላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎችና መፈናቀሎች አማኞች ካስባሉን እውነታ የሚቃረን ነው።
የብዙዎቻችን እምነትና የምናምነው አምላክ ከመነሻው የሰው አፈጣጠር ላይ ልዩነት የለውም። መነሻው ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ ለምን በብሔርና በጎሳ እየለየን ሌላውን እናጠቃለን? ነገር ግን ዛሬ የሰው ልጆች መነሻው አዳም/አደም መሆኑ እኛም የእሱ ልጅ ልጆች መሆናችን ክደን በየጎሳና በየጎጥ ተለያይተን እንጋደላለን። አምላክ በምክንያት የፈጠረው ለራሱ ጥበብ ያሰኘውን የሰው ልጅ ስለምን እዚህ ተገኘህ ብለን ለመጉዳት ተነሳን? እኛ አቅም እና ብዛት አለን ብለን ባሰብንበት ቦታ ላይ አነስ ብሎ የሚገኘውን ለመጉዳት በምንስ ድፍረት ተሞላን?
በዚህች የምዕመናት አገር በተባለችው ኢትዮጵያ፤ እንግዳ ተቀባይ ኩሩ ሕዝቦች አገር የራስዋ ልጆች መስማማት እንደምን ተሳናቸው? አዎ የሰላምና የፍቅር አገር በተባለችዋ ምድር መስማት ሳንፈልግ የምንሰማቸው፣ ማየት ሳንፈልግ የምንመለከታቸው መዓቶች ተከታትለው ያለ እረፍት እየቀረቡን ነው። በዚህ ዘመን ሰው ሊፈጽማቸው የሚከብዱ ዘግኛኝ ግድያዎች እየተፈፀሙ ነው። ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት ተንሰራፍቶ በየቦታው ሰቆቃ በርክቷል።
እኛ አማኝ ከሆንና በስነምግባር ከታነፅን፤ እንዴት አምላካዊ ፍጡርን ያለአግባብ ለመቅሰፍ በረታን። እንዴትስ የሰዎች ሞት ስንሰማ በተመሳሳይ አግባብ ያን ግድያና ሰቆቃ መቃወምና ማውገዝ ያቅተናል። ወገን እምነቶች ለሰው ልጆች መልካም አሳቢዎች ለምድርም ሰላም ምንጭ ከሆኑ ከእኛ ተግባርና ሥራ ጋር እንዴት ተለያዩ።
አዎን ታመናል፤ ወይ እምነታችንን አናውቀውም አልያም ደግሞ እምነት አለን እንጂ አማኝ አይደለንም። እምነትና መርሆችን ጥሰን እምነት አልባዎች የሚደርጉትን ከአንድ አማኝ የማይጠበቅ ተግባር ላይ ተጥደናል። በክፉው ተግባር ባንሳተፍ፣ ክፉውን ተግባር ባንደግፍ እንኳን ይህ ተገቢ ያልሆነ ክፉ ተግባር እንዲቆም ያደረግነው አስተዋፅዖ እንደ አማኝ ኢምንት ነው። ሰዎች መልካም እንዲያስቡ ግጭትና የእርስ በርስ መጠፋፋት እንዲገታ መጣር ተስኖን በጥቂት ክፉዎች ተውጠናል።
ወገን፤ የክፉ ሥራ ክፋትነት ላይ እንኳን አልተግባባንም እኮ፤ ክፉው ተግባር እኛ ጋር ሲሆን መቅለል ሌላው ጋር ሲሆን መግዘፍ እንዴት ይችላል? ክፉ ተግባርን ሁሌም ክፉ መሆኑ እንዴት ዘነጋን? አማኝ እኮ ከፍትሕ ጎን ነው የሚቆመው፤የእምነት ሰው እኮ በእውነት ላይ ነው የሚፀናው። በደሉ የተፈፀመው ከወገኑ በኩል እንኳን ቢሆን ከማያውቀውና የእውነትና የፍትህ ባለቤት ከሆነው ጋር ነው የሚቆመው። ደሞ በምንስ ስሌት ነው ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ እያየን በአካባቢና በቦታ በክልልና በእምነት እየለየን ማልቀስና እየለየን ማውገዝ የተላመድነው።
የምንገድለውም የምንገደለውም እኛው ነን። የምንወቅሰውም የምንወቀሰውም እራሳችን። ይህ አያያዛችን ተያይዘን ማለቅ እንጂ አንዳችን በሌላችን ማለቅ ወይም መጎዳት የምናተርፍ ሊሆን አይችልም። ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ሕዝባችን ሰላማዊ ኑሮውን እንዲቀጥል ሁላችንም የእውነት አማኝ እምነታችንም የሚይዘን በጎ ተግባር ላይ የምንገኝ በስሜት ሳይሆን በትክክለኛ እውቀት ላይ የቆምን የመርህ ሰዎች እንሁን።
የእምነት አባቶች የሌላውን መጥፎነት ከመግለፅ ምዕመናንን በበጎነት ስበኩ፤ የእምነት ተከታዩ ማኅበረሰብ የእምነታችሁ ስነምግባር ይላበስ ዘንድ መልካምን ነገር ስበኩ። አምላክ ምድር ላይ ያስገኘው ሁሉ በራሱ ፍቃድና መሻት ነውና እናንተ ሌሎችን በማጥፋት የእናንተ እምነትና ጎሳ ምቾት በፍፁም ሊያገኝ አይችልም። የሁላችንም እምነት በጎ መሥራት የሚደግፍ፣ ግፍ መሥራትና የሰው ልጆች መበደል የሚፀየፍ ነውና አማኞች በጎነት ላይ እንዲያዘወትሩ በርትታችሁ ሥሩ።
እምነት የሌለው ማኅበረሰብ እዚህ አገር ላይ የለምና የፖለቲካ ተሳትፎውም ላይ ያለው ከእያንዳንዱ እምነት የሚፈልቅ የሕዝብ አገልጋዩም መነሻው ማኅበረሰቡ ነውና፤ ተግባርና ሥራው የተበላሸ አሁን ላይ እንደምንሰማው ጭካኔ የተሞላበት ፈፅሞ ሊሆን አይችልም። የእምነት ስነ ምግባሩ የተሟላ ሰው የሌሎችን ሙሉ መብት ያከብራል።
ብዙዎች እምነት እንጂ አማኝነት ከእኛ የራቀ መሆኑን በብዙ ማስረጃዎች ያመላክታሉ። አሁን ላይ ያለንበት ዘርፈ ብዙ ችግር ደግሞ ዋንኛ የዚህ ማስረጃና ማሳያቸው ነው። አንድነትና ኅብረታችን መላላት፣ መደጋገፍና መረዳዳታችን መለዘብ፣ የእርስ በርስ ግጭትና ፍጅት መበራከቱ፣ መተሳሰብና መተጋገዛችን መላላቱ ለዚህ አስረጂ ምክንያት መሆኑን ይነግሩናል።
ትልቅ የቤት ሥራ አለብን ትውልዱን በስነምግባር መቅረፅ፣ እምነት ሳይሆን አማኝ በስነምግባር የታነፀ የሰዎችን መብት እንደራሱ የሚያከብርና የሚያስከብር ዜጋ መቅረፅ፣ የሰላማችን መደፍረስ ዋንኛ ምክንያት የሆኑና የሚያጣርሱን ከእርስ በርስ መግባባት የሚያርቁን ጉዳዮችን መመርመርና እዚያ ላይ መግባባት ላይ መድረስ።
ሀገራችንን ከወደድን ይህቺ ልዩና ካወቅንበት ገነት ማድረግና ለእያንዳንዳችን በበቂ ሁኔታ ሁሉም ማሟላት የምንችልባት ውዷ ሀገራችን እንድትበለፅግና ሰላምዋ እንዲረጋገጥ ከፈለግን ቀድመን ለሰላሟ ዘብ መቆም፣ አጥፊን በአንድነት ተው ማለት፣ የተሳሳተ ተግባር በጋራ መኮነንና ፍትሕ እንዲረጋገጥ መሥራት ይገባናል። ይህን ማድረግ ደግሞ ለሌላው የምንተወው ሳይሆን እኛው ተሳታፊ የምንሆንበትና የእያንዳንዳችን ተግባርና ኃላፊነት ሊሆን ግድ ይላል። እናም ወገን እምነት ያለን ብቻ ሳይሆን አማኞችም እንሁን፤ ትክክለኛ አማኝ ደግሞ ለሰዎች ሰላም ዘብ የሚሆን በእሱ መኖር ሌሎቹ የሚጠቀሙ እንጂ የሚጎዱ ፈፅሞ ሊሆን አይችልምና። ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ