ወቅቱ ክረምት ነው። ይህ የክረምት ወቅት በርካታ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ኮሌጆች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደየቤታቸው የሚመለሱበትና ገሚሶቹ ደግሞ የሚመረቁበትም ነው። ትምህርታቸውን አጠናቀው አልያም ደግሞ ተመርቀው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ወጣቶች ታዲያ ይህን የክረምት ወቅት በተለያዩ መንገዶች ያሳልፉታል።
አንዳንዶች በሥራ ሲያሳልፉ ሌሎች ደግሞ አጫጭር ኮርሶችን በመማር ያሳልፋሉ። በመዝናናትና በበጎ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የሚያሳልፉ ወጣቶች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም። ያም ሆነ ይህ ግን ወጣቶች ይህን የክረምት ወቅት ባልባሌ ነገር ከሚያሳልፉት በሥራ፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎትና በቀጣይ እነርሱን ሊጠቅሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ቢያሳልፉ ይመረጣል።
የዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ተጀምሯል። ወጣቶችም በአረንጓዴ አሻራ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሰላም፣ በመንገድ ደህንነት፣ በኮቪድ-19 መከላከልና በሌሎችም የጤና አጠባበቅ ሥራዎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልና ግንዛቤ መፍጠርና ሌሎች አስራ አንድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች ላይ የመሳተፍ አማራጭም ከፊታቸው ቀርቦላቸዋል።
ከዚህ ባለፈ በተለይ ተመራቂ ወጣቶች በቀጣይ ራሳቸውን ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሊያመቻቹ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ከበርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ በአንድ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት አማካኝነት ለወጣቶች እየተመቻቸ ይገኛል።
ወጣት አቤኔዘር መላኩ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቂሊንጦ ቅርንጫፍ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው። ኢኒሺዬቲቭ ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተሰኘ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ባዘጋጀው ወጣቶችን ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የማገናኘት ፕሮግራም ላይ የሮትራክት ክለብ ለውጥን ወክሎ እንደቀረበ ይናገራል።
ይህን ክለብ ከተቀላቀለ ስድስት ወር እንደሞላውም ገልፆ፤ በቆይታውም የተለያዩ እውቀቶችን መቅሰሙን ያስረዳል።አሁንም በዚህ ፕሮግራም ላይ በመሳተፍ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከማኅበራዊ ክለባትና የሥራ ዕድል ሊያመጡ ከሚችሉ ሌሎች ተቋማት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ዕድል እንዳገኘም ይናገራል።
እርሱ የተቀላቀለበት ክለብ ከአስራ ስምንት እስከ ሰላሳ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን የማኅበረሰብ ክፍሎችን አካቶ ወጣቶች ራሳቸውን ጠቅመው ማኅበረሰቡንም እንዲያገለግሉ የሚያስችል እንደሆነ ያመለክታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አስራ አራት የሮትራክት ክለቦች ውስጥ እርሱ ያለበት አንደኛው የሮትራክት ለውጥ ክለብ ሲሆን በእአምሮ ጤና ረገድ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን የመደገፍ፣ መጽሐፍትን የማሰባስብና ለትምህርት ቤቶች የመለገስ ሥራዎችን እንደሚሠራ ያብራራል።
ከዚህ ባለፈ ክለቡ በየአስራ አምስት ቀኑ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት የተለያዩ የሞያ ማበልፀጊያ ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቶች ራሳቸውን ለውጠው ማኅበረሰቡንም እንዲያገለግሉ እየሠራ እንደሚገኝም ይጠቁማል።በዚህ ፕሮግራም የሚሳተፉ ሌሎች ወጣቶችም እርሱ ወዳለበት ክለብ እንዲገቡና ራሳቸውን ለውጠው ማኅበረሰቡንም እንዲጠቅሙ ጥሪ ያቀርባል።
ይህን ክለብ ከመቀላቀሉ በፊትና ከተቀላቀለ በኋላ ሰፊ ልዩነት እንዳለም የሚናገረው ወጣት አቤኔዘር በተለይ ክለቡን ከተቀላቀለ በኋላ ከሰዎች ጋር ያለው የመግባባት ክህሎቱ እንደጨመረና ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደማይመስል ይገልፃል። በክለቡ በየአስራ አምስት ቀኑ በሚደረጉ ስብሰባዎች ከተለያዩና ከማያውቃቸው ወጣቶች ጋር እንደሚገናኝና ከእነርሱ ጋር በቀላሉ ትስስር በመፍጠር እውቀት ለመለዋወጥ እንደቻለም ያስረዳል።
ሌሎች ወጣቶችም በተመሳሳይ የመግባባት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና ትስስር በመፍጠር የልምድና እውቀት ልውውጥ እንዲያደርጉ በእንደነዚህ ዓይነት ክለቦች ውስጥ ገብተው መሳተፍ እንዳለባቸው ይመክራል።
ወጣት መላኩ ኃይሉ ደግሞ የሞዴል አፍሪካ ዩኒየን ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ዳይሬክተር ነው።እ.ኤ.አ በ2017 ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በሶሺዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ በዲግሪ ተመርቋል። አጀንዳ 2063 ቀልቡን ስለሳበውና ስለዚህ ጉዳይ በጥልቀት ለማወቅ በውስጡ ፍላጎት በማደሩ ድርጅቱን እንደተቀላቀለ ይናገራል።
ድርጅቱን ከተቀላቀለም በኋላ ለዚህ አጀንዳ መሳካት በተለይ የኢትዮጵያ ወጣቶች አስተዋፅኦ ምን መሆን አለበት በሚለው ዙሪያ እየሠራ ይገኛል። አብዛኛውን ሕይወቱን በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ በዚሁ ድርጅት ውስጥ ያገለግላል።
ወጣት መላኩ ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረ አራት አመታትን እንዳስቆጠረና በዋናነት በአፍሪካ ኅብረት የሚነገሩ ነገሮችንና የሚሠሩ ሥራዎችን፣ ፖሊሲዎችንና መዋቅሮችን ወጣቶች እንዲያውቁና ለዚህም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የማብቃት ሥራ እንደሚሠራ ያብራራል። 700 የሚሆኑ ወጣቶች የዚህ ድርጅት አባል መሆናቸውንም ይጠቁማል።
በአራት አመታት ውስጥ ድርጅቱ ታላላቅ ሥራዎችንም እንደሠራ ተናግሮ፤ በተለይ የአፍሪካ ኅብረት ካሉት በርካታ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ የሆነው አጀንዳ 2063ን ለማኅበረሰቡ፤ ዕድሜያቸው ከአስራ ስድስት እስከ ሰላሳ አምስት ያሉ ኢትዮጵያውያንና የአፍሪካን ዳያስፖራ ወጣቶች እንዲረዱት መሥራቱን ይጠቁማል።
ወጣቶች በአፍሪካ ኅብረት ፕሮግራሞች ውስጥ ያሉ ስለሰላም፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና፣ ስለ አካታች ወጣቶች ተሳትፎና ፖሊሲ አድቮኬሲ እንዲያውቁም ሥራዎችን እንደሠራም ይጠቅሳል።አፍሪካ የተሻለ ደረጃ እንድትደርስና ኢትዮጵያን በመወከል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን ላለፉት አራት አመታት ድርጅቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱንም ያስረዳል።
የድርጅቱ ዋነኛ አላማም ወጣቶች የአፍሪካ ኅብረትን አጀንዳ 2063 እና ዘላቂ የልማት ግቦችን እንዲያውቁ የማድረግ እንደሆነና የሚመለከታቸው አካላትም ከድርጅቱ ጎን በመሆን ባላቸው ሀብት እንዲደግፉት ጥሪውን ያስተላልፋል።
የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተለይ ደግሞ በወጣቶች፣ ባህል፣ አጀንዳ 2063ን ከማሳካት አንፃር ዙሪያ የሚሠሩ እንደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጅቱን እንዲደግፉትም ወጣት መላኩ ይጠይቃል።
አቶ ፍፁም ኃይሉ ኢኒሺዬቲቭ ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የተሰኘ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው በ2011 ዓ.ም ሲሆን በዋናነት በዴሞክራሲ ግንባታ፣ በሰብአዊ መብቶች፣ በሰላም ግንባታና በወጣቶች አቅም ግንባታ ዙሪያ አተኩሮ ይሠራል። ከዚህ በፊትም በተለያዩ የአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በተለይ ደግሞ በአገር አቀፍ ምርጫ በመሳተፍ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልል 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ተደራሽ ያደረገ የመራጮች ትምህርት ሰጥቷል።
ከዚህ ጋር የተያያዙ የልማት ሥራዎችንም ሠርቷል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ወጣቶችን ለሥራ ዕድል በማመቻቸትና እንዲሠሩ በማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰላም እንዲሰፍን የማድረግ ሥራዎችንም አከናውኗል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ወጣቶች ከሲቪክ ማህበራት፣ ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ከማኅበራዊ ክለብ፣ የሥራ ዕድል ሊያመጡላቸው ከሚችሉ ተቋማት ጋር ግንኙነት አንዲፈጥሩ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል።በዚህም ድርጅቶቹ የሚሠሩትን ሥራ ያስተዋውቃሉ። ወጣቶች ደግሞ ከእነርሱ ጋር የሚኖራቸውን ትስስር ያስፋሉ።
ተማሪዎቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች በፍቃደኝነት ተውጣጥተው የመጡ ሲሆን ከአንድ ሺ ፍቃደኛ ወጣቶች መካከል በሎተሪ ዕጣ ሦስት መቶዎቹ ተመርጠዋል። እነዚህም በዩኒቨርሲቲው ባሉ የማኅበራዊ ክለቦች ውስጥ በንቃት የሚሳተፉ ናቸው።
ድርጅቱ በፈጠረው የትስስር ፕሮግራም አማካኝነት ወጣቶቹ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ይረዳቸዋል። በዚህ መድረክ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎትና የተለያዩ ሲቪክ ማህራት የሚሳተፉ በመሆናቸው ተማሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ የማህበራዊ ግንኙነት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ያስችላቸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ፕሮግራሙ ወጣቶቹ የእርስበርስ ግንኙነትን እንዲያጎለብቱና የሥራ ዕድላቸውን እንዲያሰፉ ይረዳቸዋል። ወጣቶቹ ከተመረቁ በኋላ ሥራ እስኪያገኙ ድረስ በበጎ ፍቃደኝነት ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸው በኋላ ላይ ወደ ሥራ ዕድል ፈጠራ የመቀየር አቅማቸውን እንዲያሰፉም ያግዛቸዋል። በተለይ ደግሞ የአመራርነትና የሥራ ክህሎት ስልጠናዎችን እንዲገኙም ያስችላቸዋል። የሲቪክ ማህበራት ባለስልጣን ባዘጋጀው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይም ተመዝግበው አገልግሎቱን እንዲሰጡም ይረዳቸዋል።
በዚህ ፕሮግራም የተለያዩ የመንግሥት፣ የግልና የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የሚሳተፉ በመሆኑ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ተማሪዎች በራሳቸው ጥረት ከነዚህ ተቋማት ጋር ይነጋገራሉ። ተቋማቱ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መሳተፍ የሚፈልጉ ከሆነም ወጣቶቹ በተቋማቱ ውስጥ ገብተው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመስጠት ዕድል ይፈጠርላቸዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር ወጣቶችን የማስተሳሰር ሥራ ሲሠራ ድርጅቱ የመጀመሪያው ቢሆንም ቀደም ሲል በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ በስፋት ተደራሽ የሆነባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጣቶች ናቸው። በቀጣይም ከወጣቶች ጋር በተያያዘ ለመሥራት በርካታ እቅዶች አሉት።
አስናቀ ፀጋዬ