ፀጉራቸው ሽብት፣ ቆዳቸው ደግሞ ሽብሽብ ብሏል፤ ከዓመታት በፊት ነጣ ያለ ነጠብጣብ እንዳለበት የሚያስታውቅ ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ከመለበሱ የተነሳ በመንገዱ ላይ የተደፋውን አቧራ የሚመስል ባለ አበባ ቀሚስ ለብሰዋል። ክስት ባለው ቀኝ እጃቸው አጠገባቸው ያለውን ትልቅ የጥድ ዛፍ ደገፍ እንደማለት ብለው በስርጉድ አይኖቻቸው ዙሪያውን ይቃኛሉ።
በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በአቤ ደንጎሮ ወረዳ የቱሉ ዋዩ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እኚህ እናት ኩሜ ዋቆ ይባላሉ። ወይዘሮ ኩሜ በሚኖሩበት አካባቢ ህክምና ማግኘት ፈፅሞ አይታሰብም። እናም ድንገተኛ ህመም ሲከሰተም ሆነ በተለይ ነፍሰ ጡር እናቶች የወሊድ ክትትል ለማድረግ ካሻቸው ከቀያቸው በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር መጓዝ ግድ ይላቸዋል። በዚህ አሰልቺ ጉዞ ታዲያ ህመማቸው የጠና ከመንገድ ይወድቃሉ። አንዳንዶቹ እናቶች ደግሞ ከጤና ተቋማቱ ሳይደርሱ ከመንገድ ላይ ልጅ ይገላገላሉ። አሊያም የናፈቁትን ልጅ ለመመልከት ሳይታደሉ ህይወታቸውን ይነጠቃሉ።
በዚህ የህይወት ኡደት ብዙ ስቃይና መከራ የተጋፈጡት ወይዘሮ ኩሜም በህክምና እጦት ልጆቻቸውንና ዘመዳቸውን ተነጥቀዋል። እናም ሁልጊዜም ቢሆን ህክምና በአቅራቢያቸው አግኝተው ነገን ከትናንት ስቃይ መገላገል የምንጊዜም ምኞታቸው ነው።
ከቀናት በፊት ታዲያ ወይዘሮ ኩሜ ለዓመታት ሲናፍቁት የነበረው የህክምና ተቋማት ህልማቸውን እውን አድርጎላቸዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከሃምሳ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአካባቢያቸው ህክምና ያገኙ ዘንድ የአቤ ደንጎሮ ሆስፒታልን አስገንብቶላቸዋል።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት እኚሁ አዛውንት ታዲያ እድሜ የደስታቸውን መጠን በአደባባይ እንዲገልፁ ፈቃድ ባይሰጣቸውና ፊታቸው ላይ የትናንት ሃዘን ቢኖርም፤ ዛሬ ላይ ስለመደሰታቸው በቀላሉ መለየት ይቻላል። አዛውንቷም ስለ ስሜታቸው እንደሚገልፁት ታዲያ፤ በአካባቢያቸው ያልጠበቁት ሆስፒታል እውን መሆን ከምንም በላይ የትናንት ጥያቄአቸው መልስ እንዲሁም የደስታቸው ምክንያትና የነገ ዋስትና ሆኖላቸዋል።
በሌላ አቅጣጫ ፊታቸው በሳቅ የፈካ፣ በሙሉልብስ ድምቅ ያሉት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የጉዱሩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ልኬ ዴሳ የዓመታት ጥያቄም ይህው የህክምና አገልግሎትን በቅርበት የማግኘት ነው። በአካባቢያቸው ለበርካታ ዓመታት የጤና ተቋማት ባለመኖሩ በተለይ በነዋሪዎቹ ላይ ከባድ ጉዳት ይደርስ እንደነበርና በተለይ እናቶች እቤት ውስጥ ልጆችን ይገላገሉ እንደነበር ወይዘሮ ልኬ ያስታውሳሉ፤ ወረዳው ከነቀምቴና ሻምቡ ሆስፒታሎች በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በመሆኑ በህመም ወቅት ህዝቡ ለከፍተኛ እንግልትና ሞት በተለይ በወሊድ ጊዜ የበርካታ እናቶችና ህፃናት ህይወት ሲያልፍ መቆየቱን ወይዘሮዋ ይናገራሉ፡፡
‹‹ከብዙ እንግልትና ስቃይ በኋላ፤ የክልሉ መንግስት ከሃምሳ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጉዱሩ ሆስፒታልን መገንባት የዓመታት ጥያቄና ወቅታዊ መልስ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ልኬ፤ የሆስፒታሉ በአቅራቢያቸው መገንባት ካላስፈላጊ ወጪና እንግልት ብቻም ሳይሆን ከሁሉ በላይ የእናቶችና የህጻናትን ሞት ለመቀነስና በተለይ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ተገቢውን ክትልል በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ ስለመሆኑ ነው አፅንኦት የሰጡት።
ወደኋላ ያጣመራቸው እጆቹን በማፋታት አቧራ የተሞጀረበት ፀጉሩን ለማራገፍ እንኳ በቂ ጊዜ ማጣቱን የሚያሳብቅበት አቶ ቡሎ ዋቁማ በጉዱሩ ሆስፒታል በምርቃ ስነ ስርዓት ላይ ከተገኙት ታዳሚዎች አንደኛው ነው።
አቶ ቡሎ፤ ቀደም ሲል በአቅራቢያው የህክምና ተቋም ባለመኖሩ እርሱም ሆነ ቤተሰቦቹ እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ጌዶ፣ ሻምቡ አሊያም አዲስ አበባ ሲመላለሱ መቆየታቸውን ያስታውሳል፡፡ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት በሚያደርጉትም ረጅም ጉዞ ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንደሚዳረጉም ይገልፃሉ፡፡ በርካቶችም ወደ ጤና ተቋማቱ ደርሰው የህመማቸውን ምንነት እንኳን በቅጡ ሳያውቁ መንገድ ላይ ይህቺን ዓለም ይሰናበቱ እንደነበርም ይመሰክራል፡፡
«ከሰሞኑ በአካባቢው የተመረቀው ሆስፒታልም የዓመታት የህዝብ ጥያቄ ነው» የሚለው አቶ ቡሎ፤ የትናንት ስቃዩን አስረስቶ፤ ለነገ ለድህንነቱ ዋስትና እንደሰጠው ይተማመናል። ደስታውም እንዲቀጥል እምነቱም እንዲፀና ግን የሆስፒታሎቹ መገንባት ብቻ ሳይሆን በግብዓትም ሆነ በሰው ሃይል ለማጠናከር ተገቢውን ክትትል ማድረግ የግድ እንደሚል ይናገራል፡፡
በአቤ ደንጎሮ ወረዳ የቱሉ ዋዩ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ዱጉማም፤ ያለፉትን ዓመታት ለህዝቡ ልማት ጥያቄዎች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደነበር ይመስከራሉ። ‹‹ትኩረት ከተነፈጋቸው የህብረተሰብ ጥያቄዎች መካከልም የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ እንዲሁም የህክምና ተቋማት ተደራሽነት ዋነኞቹ ናቸው» የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ ዘግይቶም ቢሆን በአሁኑ ወቅት የእርሳቸውም ሆነ የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጥያቄ መልስ ወደ ማግኘት መሸጋገሩን ነው ያሰመሩበት። የአካባቢው ነዋሪዎችም በሆስፒታሉ መገንባት ደስተኛ ከመሆን በተጓዳኝ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ ስለመሆናቸው ነው ያስታወቁት።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማም፤ ‹‹ክልሉ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በተለይም በጤናው ረገድ የተቋማት ተደራሽነትና ጥራትን ለማጎልበት በርካታ ስራዎች በመስራት ላይ ናቸው›› ይላሉ። በዚህ በክልሉ 1ሺ 400 ጤና ጣቢያዎች፣ 79 ሆስፒታሎች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ ሰላሳ ሆስፒታሎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም ይገልፃሉ።
እያንዳንዳቸው 56 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውና እያንዳንዳቸው አራት መቶ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጡት ሁለቱ ሆስፒታሎችም የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ያስረዱት ዶክተር ደረጀ፤ ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ የሆኑት የአቶ ቡሎ ዋቁማ የሆስፒታሎቹ በግብዓትና በባለሙያ የመማሏት ጥያቄ ክልሉ ትኩረት መስጠቱን ያሰምሩበታል።
‹‹የክልሉ ጤና ቢሮ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ሆስፒታሎቹን ከመገንባት ባለፈ አስፈላጊ የሆነ ግብዓትና ባለሙያዎችን ለማሟላት ትኩረት ሰጥቷል፤ ትላልቅ የሆኑ ህክምና መስጫ ግብዓቶች በጉዞ ላይ ናቸው» ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ደረጀ ገለፃ፤ ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁት ሆስፒታሎች የተመላላሽ፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ሕክምና፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የራጅ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አላቸው። ሆስፒታሎቹም እያንዳንዳቸው በአካባቢው በሚገኙ ተጎራባች ወረዳዎች ለሚገኙ ከ400 ሺ ለሚበልጡ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።
ጤናማና አምራች ዜጋ የማፍራት ጥረትም በቀጣይ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን በማመላከትም፤ ህብረተሰቡም የግሉ ሃብት ለሆኑት ሆስፒታሎች ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰንም፤ «ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ክልሉ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ቆይቷል፤ በእነዚህ ዓመታት የህዝቡ ጥያቄም ሆነ የመንግስት ትኩረት የነበረው የፖለቲካ ጥያቄዎችን መመለስ በመሆኑ ለልማት ጥያቄዎች የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል» ይላሉ።
እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ገለፃ፤ አሁን ላይ የተገኘውን የፖለቲካ ድል ተከትሎ ክልሉ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ወደ መመለስ ተሸጋግሯል። ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት በማዞርም ህዝቡን የዓመታት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ከህዝቡ የዓመታት ጥያቄዎች አንዱ የጤና ተቋማት ተደራሽነት መሆኑንና ህዝቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው፤ ይህን ማድረግም የመንግስት ኃላፊነት ብቻም ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆኑን የሚያስገነዝቡት ወይዘሮ ጠይባ፤ ይህን የተረዳው የክልሉ መንግስት በየአካባቢው የጤና ተቋማት ተደራሽነት ለማስፋት በመትጋት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከቀናት በፊትም የተመረቁ ሁለቱ ሆስፒታሎችም፤ የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ መልስ መስጠት ማሳያ ስለመሆናቸው ነው ያመላከቱት።
በቀጣይም የልማት ጥያቄዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከሁሉ በላይ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ህዝቡ አሁን ላይ የያዘውን ሰላም አጠናክሮ በመያዝና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ምርጫው እንዲያደርግም ነው ጥሪ ያቀረቡት። ህብረተሰቡ ሆስፒታሉ የራሱ ሀብትና ንብረት መሆኑን ተረድቶም እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቃቸው እንደሚገባም ሳያሳስቡ አላለፉም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2011
ታምራት ተስፋዬ