ገቢያቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ፤ ጭራሹኑም ገቢ የሚባል የሌላቸው አቅመ ደካማ አረጋዊያን ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ሴት ሲሆኑና የቤተሰብ ኃላፊነት ሲደረብባቸው ችግሩን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል። ጎንበስ ቀና ብለው ኑሯቸውን መደጎም ቀርቶ ውሃ ቀድተው መጠጣት ለማይችሉት ደግሞ የህይወት ፈተናው የከፋ ይሆናል፡፡
ነዋሪነታቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03 የሆነው እናት ወይዘሮ ዙርያሽ አብደላ ይሄን ችግር እየተጋፈጡ ካሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል አንዷ ናቸው፡፡
‹እኔና ልጆቼ ምንም ገቢ አልነበረንም፡፡ የዕለት ጉርሳችንን መሸፈን የማንችልና ከምንበላበት የማንበላበት ቀን ይበልጣል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ተካፍሎ የመብላት ባህል ያላቸው በመሆኑ በደጋጎች ድጋፍ ህይወታችንን ማቆየት ችለናል›› ይላሉ ወይዘሮ ዙርያሽ።። ይሄ ባይሆን ችግራቸው እንደሚበረታና በሕይወት መሰንበት አንችልም ነበር ይላሉ፡፡
ወይዘሮ ዙርያሽ የበርካታ ልጆች እናት እና የመጀመሪያ ባለቤታቸው በሞት የተለይዋቸው ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ፤ ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ ላይ ወድቆ ቆይቷል። ይሄም ብቻ ሳይሆን ባደረባቸው ህመም የተነሳ ከተቀመጡበት የማይንቀሳቀሱ ጽኑ ህመምተኛ ሆነዋል፡፡
ይባስ ብሎም የወይዘሮ ዙርያሽን ኑሮ ያከበደባቸው ደግሞ የ16 ዓመቷ ልጃቸው በመኪና ግጭት አደጋ ምክንያት አስተሳሰቧ በመቃወሱ እንደሆነ ይናገራሉ። ልጃቸው ግጭት የደረሰባት የ10 ዓመት ልጅ ሳለች ነበር፡፡ በወቅቱ አያት ሆስፒታል ህክምና ተደርጎላታል፡፡ አሁን በሕይወት ብትኖርም እንኳንስ እሳቸውን ልታስታምም ለራሷም የሚሆን አቅም የላትም ፡፡ ልጅቱ የሚያስታምማት፤ የሚንከባከባት እና የሚጠብቃት ትፈልጋለች፡፡
ወይዘሮ ዙርያሽ ጎንበስ ቀና ብለው ልጆቻቸውን ማሳደግ ቀርቶ ውሃ ቀድቶ መጠጣት የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው ‹‹በቦሃ ላይ ቆረቆር›› እንዲሉት ተረት ኑሯቸው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖባቸዋል፡፡ ‹ምስጋና ይድረሰውና ለፈጣሪ አሁን ላይ ነፃ የሕክምና ወረቀት አለኝ› ሲሉም ለህክምና የሚከፍሉት ሁለት ሺህ ብር አጥተው ሕመማቸው ፀንቶባቸው ሕይወታቸውን ሊያጡ የነበረበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡
ጊዜ የራሱን መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ እምነት ቢጥሉም ሌላ አስደንጋጭ ጉዳይ ገጠማቸው፡፡ ከአመታት በፊት የሚኖሩበት አካባቢ ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ይኖሩበት የነበረው ቤት በመፍረሱ ከነልጆቻቸው ጎዳና መውጣታቸውንም አይዘነጉትም ፡፡ ጎንበስ ቀና ታደርጋቸው የነበረችው የመጀመርያ ልጃቸው በዚሁ ወቅት ራሷን ለማዳን ብላ ብን ብላ ጠፍታለች፡፡ አጎቷ ጋር ሄደች የሚል ወሬ ቢሰሙም እስከ አሁን የት እንዳለች አያውቁም፡፡
አሁን ላይ ሁሉም ነገር በአንዲቱ የ18 ዓመት ዕድሜ ያላት ልጃቸው ላይ ነው የወደቀው፡፡ ጎንበስ ቀና የምታደርጋቸው ይህችው ልጅ ናት፡፡ ዘንድሮ 12ኛ ክፍል ደርሳላቸዋለች፡፡ በለስ ቀንቷቸውም የሚኖሩበት ቀበሌ ለፈረሰባቸው ቤት ምትክ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋል ፡፡
‹‹ለተደራራቢ ችግር ተጋልጬ ነው እየኖርኩ ያለሁት ›› የሚሉት ወይዘሮ ዙርያሽ እየኖሩበት ያለውን አንድ ሜትር በአንድ ሜትር ቤት እንደ ማሳያ ያነሳሉ፡፡ የሚኖሩባት ቤት በጣም ጠባብና ጽዳቷም የተጓደለ ነው፡፡ ሆኖም እሷ ከመኖርያ ተቆጥራ በወር 600 ይከፍሉበታል፡፡ ይሄን ማድረግ የቻሉት እሳቸው ‹የድሆች አባት ብለው በሚጠሩት› አንድ የግል ድርጅት ድጋፍ ነው፡፡
ምንም አቅም ኖሯቸው የሚሰሩለት ሥራ ባይኖርም ድርጅቱ ገቢ ስለሌላቸው ብቻ በወር 1ሺህ 200 ብር በመስጠት ኑሯቸውን እየደጎመላቸው ይገኛል ፡፡ 12ኛ ክፍል ለደረሰችው ልጃቸውም እንዲሁ ከትምህርቷና እሳቸውን ከማስታመም ጎን ለጎን በምትሰራለት ሥራ ድጋፍ ያደርግላታል፡፡ በተጨማሪም በሴፍትኔት መርሐ ግብር ታቅፈው በሚያገኙት ድጋፍ የእሳቸውንና የልጆቻቸውን ሕይወት ማሰንበት ችለዋል፡፡
በተለይም በቅርቡ የተጀመረው የበጎ ፍቃድ ስራዎች የወይዘሮ ዙርያሽ አይነት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ አለኝታነቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ወጣቶች እየተባበሩ አቅመ ደካሞችን ሲረዱና ሲደግፉ ሲያዩ ወ/ሮ ዙርያሽ ደስታቸው ወደር ያጣል፡፡ ልጆቻቸው ተምረው ባይጦሯቸውም በጎ ፍቃደኖቹ የልጆቻቸውን ቦታ ተክተው ‹‹ምን እናድርግልሽ ››እያሏቸው ነው።
የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ተቋም የበጋና የክረምት ተብሎ በመከፈል በሁለት መልኩ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገልግሎቶች እንደ ሀገር በርካታ ወጣቶች እየተሳተፉና እንደነ ወይዘሮ ዙርያሽ ያሉ እናቶችን እየደገፉ ይገኛሉ፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2014