ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካም ሆነ የዓለም ሀገራት ጋር ስትነፃፀር ዝቅተኛ የከተማ ነዋሪ ያላት አገር እንደሆነች ይነገራል፡፡ በአገሪቱ ከመቶ አመታት በፊት ተመስርተው በመስፋፋት ላይ ያሉትም ሆኑ አዳዲስ የሚመሰረቱት ከተሞች በፕላን ካለመመራት በተጨማሪ በበርካታ ችግሮች የተተበተቡ መሆናቸውም ይገለፃል። ከዚህም የተነሳ የነዋሪዎቻቸውን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም።
ተብትበው ከያዟቸው ችግሮች መካከል የመሬት አጠቃቀም፣ ከተሞቹ አቅራቢያ ያሉ አርሶ አደሮች ህይወት አለመቀየር የሚፈጥረው ቅሬታ፣ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ፍልስት የተነሳ በቂ የስራ እድል አለመፍጠርና በከተማው ላሉ ነዋሪዎችም በቂ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመኖር ይጠቀሳሉ።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የከተማ ፕላን አዘገጃጀትና አተገባባርን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያካሄደ ሲሆን፣ ተወያዮቹ የችግሮቹ መነሻ ምክንያቶች የሚሏቸውን በማስቀመጥ የመፍትሄ ሀሳብ አቅርበዋል ።
የከተሞች አመሰራረትና በፕላን አለመመራት የፈጠረው ተፅእኖ
በዩኒቨርሲቲው የከተማ ልማት ስልጠናና ማማከር ዘርፍ የኧርባን የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር በላይ ፍሌ እንደሚሉት፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የወደፊቱን ታሳቢ በማድረግ ከተሞችን በእቅድ መምራት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ወሳኝ ነው። ከተሞች በፕላን ከተሰሩና በአግባቡ የሚመሩ ከሆነ የኢኮኖሚ እድገት ምንጭ፣ በአግባቡ ካልተመሩ ግን አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያቆረቁዙ ይሆናሉ። በኢትዮጵያም ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው አብዛኞቹ ከተሞች ለረጅም ጊዜ በተያዘ እቅድ ባለመመራታቸው ኢኮኖሚውን የሚደግፉ አይደሉም፡፡
እንደ ሀገር ከተሞችን ለመምራት በፕላን አዘገጃጀትም በአተገባበርም ረገድ ክፍተት መኖሩን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ያደጉት ሀገራት የከተሞች የእድገት መስመር ከግብርና ቀጥሎ ወደ ኢንዱስትሪ፤ ከኢንዱስትሪ መስፋፋት በኋላ ወደ አገልግሎት እንደሚሄድ ነው ያመለከቱት፡፡
በአፍሪካ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሳይዳብርና የሚፈለገው ደረጃ ላይ ሳይደርስ አገልግሎት ቀድሟል። አገልግሎት ዘርፉ እያደገ በአንፃሩ ማኑፋክቸሪንጉ ኋላ የቀረና የሚፈለግበትን ያህል የስራ እድል እየፈጠረ ባለመሆኑ ከተሞች እንኳን ከገጠር ለሚፈልሰው በስራቸው ላሉትም ስራ መፍጠር ተስኗቸዋል።
በአለም ላይ ያለው ተመክሮ በመጥቀስ የክትመት መጠኑ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድግ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ሮም መከተም ጀምራ የህዝብ ብዛቷን ሁለት ሚሊዮን ለማድረስ ሁለት ሺ አመት የፈጀባት ሲሆን፣ ኦስትሪያ በ400፣ ሸንጋይ በ20 አመት ተመሳሳይ ቁጥር ላይ ደርሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከአለም ህዝብ 54 በመቶ የሚኖረው በከተማ ሲሆን፣ ለሚቀጥሉት ሰላሳ አመታት ደግሞ በየቀኑ 280 ሺ ህዝብ ከተማ እንደሚቀላቀልም ይገመታል። ኢትዮጵያም ከአለም ዝቅተኛ የከተማ ነዋሪ ያላት ነገር ግን በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ አገር እንደመሆኗ እድገቱ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል።
‹‹ነገር ግን›› ይላሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ‹‹ዛሬም ድረስ በፍጥነት እየጨመረ የሚመጣ የህዝብ ብዛትን ከግምት ያስገባ ፖሊሲና እቅድ እየተዘጋጀ አይደለም። በዚህም የተነሳ የመሰረተ ልማት ተደራሽ አለመሆንና የከተሞቹ ለነዋሪዎቻቸው አለመመቸት የሁሉም ከተሞች መለያ ችግር እየሆነ መጥቷል›› በማለት ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋቅጋሪ ነገሪ እንደሚያብራሩት፤ የከተሞች መመስረትም ሆነ መስፋፋትና ማደግ ቁጥጥር እየተደረገበት በተቀናጀ መልኩ በእቅድ የሚመራ ካልሆነ ችግር መፍጠሩ አይቀርም።
አለም አቀፍ ልምድ እንደሚያሳየው፤ በአብዛኞቹ ከተሞች የሚመሰረቱት መንገድና የተፈጥሮ ሀብትን መሰረት አድርገው የረጅም ጊዜ እቅድ ሳይያዝላቸው ቀስ በቀስ በመሆኑ ፕላን የሚወጣው ከተሞቹን ለመምራት ሳይሆን የተመሰረቱትን ከተሞች ለማስተካከል ይሆናል። ይሄ ደግሞ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደሚታየው እያፈረሱ መገንባትን ያስከትላል።
በተጨማሪም የከተሞች በፕላን አለመመራት የአየር ንብረት ለወጥ ላይም ተፅእኖ ይፈጥራል። ከተሞች የሚይዙት ቦታ ከ10 በመቶ በታች ሆኖ ነገር ግን ከ70 በመቶ በላይ የአየር ብክለት ይፈጥራሉ። በግልባጩ ደግሞ በአየር ብክለት ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጠው ከከተማ ውጪ የሚኖረው ማህበረሰብ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ከተሞች የሚመሰረቱት በቅድሚያ ታስቦ ሳይሆን በአብዛኛው የተፈጥሮ ሀብትን በማየት፣ ለጦርነት አመቺ መሆኑን በመምረጥ እንዲሁም የንግድ መተላለፊያና የሀይማኖት ቦታዎችን በመከተል በመሆኑ በፕላን ለመመራት አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል›› የሚሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ጎንፋ ባልቻ ናቸው።
ዳይሬክተሩ እንደሚያብራሩት፤ ከተሞች በፕላን ባለመመራታቸው ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል ገቢ ለመሰብሰብ ብቁ አልሆኑም። በዚህም የተነሳ ከማእከላዊ መንግስት የሚሰጣቸውን በጀት ብቻ ጠብቀው የሚገነቡት መሰረተ ልማቶች ለነዋሪው በቂ አይደሉም።
የተመቻቸ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ደግሞ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው የተቀዛቀዘ ስለሆነ የስራ እድል ፈጠራው የነዋሪውን ፍላጎት የሚያሟላ አይሆንም። በተጨማሪም ከተሞች በከተማ አስተዳደር ባለሙያ ያለመመራታቸው ብዙዎቹ ጉዳዮች የፖለቲካ አቅጣጫ እንዲይዙ ማድረጉንና የተወሳሰበ ችግር እየፈጠረ እንደሆነም ይናገራሉ።
የከተሞች ኢኮኖሚያዊ እድገትና የስራ እድል ፈጠራ
የከተሞችን ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በተመለከተም ዶክተር በላይ እንደሚያብራሩት፤ በሀገሪቱ ያሉ ከተሞች 20 ከመቶ ህዝብ ይዘው ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ እድገት ያላቸው ድርሻ ከ45 እስከ 48 በመቶ ይደርሳል። በአንፃሩ ግብርናው 80 በመቶ ህዝብ ይዞ ከ36 በመቶ የዘለለ አስተዋፅኦ የለውም። በአብዛኛው የከተማ መስፋፋት ደግሞ ወደ ጎን በመሆኑ ከስራ እድል ፈጠራና ከምርታማነት አኳያ ሲታይ ችግር ያለበት ሲሆን፣ ከተሞች ለመኖሪያም ሆነ ለኢንዱስትሪ የሚሆን መሬት በሚፈልገው መጠን የማቅረብ እጥረትም አለባቸው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢ-መደበኛ ክትመት እየተስፋፋ ነው፤ ይህ ደግሞ ለመደበኛው ኢኮኖሚ እንቅፋት በመሆን ኢ-መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ ያደርጋል። በአፍሪካ አብዛኛዎቹ ከተሞች ወደብን፣ የንግድ ቦታዎችን፣ የተፈጥሮ ሀብቶችንና መንገዶችን መሰረት አድርገው በሂደት የተመሰረቱ ናቸው።
በዚህም የተነሳ ኢ-መደበኛ ንግድ በአፍሪካ በአብዛኞቹ ሀገራት ከ50 በመቶ በላይ በመድረሱ መመለስም ማስተካከልም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በኢትዮጵያም አብዛኞቹ ከተሞች በተመሳሳይ መንገድ የተመሰረቱ ቢሆንም፤ የኢ-መደበኛው ንግድ እንቅስቅሴ እስካሁን 22 በመቶ አካባቢ በመሆኑ ለማስተካከል ከሌላው የተሻለ ተስፋ ያለበት ሆኖ መታየቱን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ዋቅጋሪ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ከተሞች አብዛኛውን ለፍጆታም ሆነ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ እቃዎችን የሚጠቀሙት ከውጪ ሀገር በማስገባት ነው። በሌላ በኩል የተወሰኑ ግለሰቦች በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የተፈጥሮ መዕድናትን ወደ ውጪ በመላክና የቅንጦት እቃዎችን ከውጪ በማስገባት የተሻለ ህይወት ሲኖሩ ይታያል።
ነገር ግን በአቅራቢያቸው ያሉ ገጠሮች ያላቸውን ምርት በመጠቀም እሴት ጨምረው የስራ እድል በመፍጠር ያመረቱትንም ለአካባቢያቸው ነዋሪዎች አገልግሎት ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። በኢትዮጵያ የከተሞች እድገት 4 ነጥብ 5 በመቶ ሲባል ከእጥፍ በላይ እድገቱ የሚሸፈነው በአካባቢያቸው ካሉ ገጠሮች በሚመጡ አቅርቦት ሲሆን፣ ሰዎቹ በቀጥታ ስራ የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
በዚህም የተነሳ የህዝብ ቁጥር መጨመርና የስራ እድል ፈጠራ አቅም ማነስ በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች የሚታይ ችግር ከሆነ ቆይቷል። ከህዝብ ብዛቱ ጋር እየተመጣጠነ የሚሄድና የከተማውን ብቻ ሳይሆን ከገጠር ሊመጣ የሚችለውንም ስራ አጥ ታሳቢ ያደረገ የስራ እድል በመፍጠር በተለይ ወጣቱን አምራች ማድረግ ከከተማ አስተዳደሮች ይጠበቃል። ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ግን ፍልሰቱ ስለማይቆም ከተሞች የወንጀል መስፋፊያ የመሆናቸው እድል ሰፊ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የገጠር ለከተማ እና የከተማ ለከተማ ትስስር
ትስስርን አስመልክተው ዶክተር በላይ እንዳ ስቀመጡት፤ በኢትዮጵያ ያለው የገጠር ለከተማ እና የከተማ ለከተማ ትስስሩ በፖሊሲ አልያም በስትራቴጂ የተደገፈ ሳይሆን በቃል ብቻ የተያዘ ያለ ህግ ማእቀፍ በዘ ፈቀድና በፍላጎት የሚከናወን ነው። በዚህም የተነሳ በኢኮኖሚው ረገድ ከገጠር የሚመጣው ምርት በምን አግባብ ወደ ከተማ መድረስ አለበት?
በዚህ ሂደትስ ምን አይነት የስራ እድል መፍጠር ይቻላል? ከተማስ ከደረሰ በኋላ እንዴት እሴት ተጨምሮበት ምርቱ ለከተማው ነዋሪና በአካባቢው ላለው ለገጠሩ ህዝብ ተመልሶ አገልግሎት በመስጠት ከውጪ የሚመጡ ፍጆታዎችን መተካት ይችላል? የሚለው በህግ ማዕቀፍ እየታየ አይደለም። በገጠር ያሉ ስራ አጦችንም በተመለከተ ከተሞች ሲመጡ ከመቀበል ውጪ ባሉበት ለመርዳት ሲሰሩ አይታይም።
‹‹በአሁኑ ወቅት በመንግስት ትኩረት ተሰጥቷቸው በመስፋፋት ላይ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ቢሆኑ መፈተሽ አለባቸው›› የሚሉት ባለሙያው፣ ‹‹ፓርኮቹ በአስተማማኝ ሁኔታ ቋሚ የስራ እድል ሲፈጥሩ፣ እሴት በመጨመር ከምርታቸው የአካባቢውን ነዋሪ ተጠቃሚ ሲደርጉ፣ ለተቀጣሪዎች ተመጣጣኝ ክፍያና ለስራ ምቹ ሁኔታና መኖሪያ ቤት ሲያቀርቡ አይታይም›› ብለዋል።
የመፍትሄ አቅጣጫ
ባለሙያዎቹ የመፍትሄ ሀሳብ ያሉትንም ሲያቀርቡ ከተማ እንዳይፈጠርም ሆነ እንዳይስፋፋ ማድረግ ስለማይቻል አዲስ የሚመሰረቱትንና በማስፋፊያ የሚሰሩትን ነባር ከተሞች የረጅም ጊዜ እቅድ በማዘጋጀትና በፍጥነት ወደ ትግበራ በመግባት የመንግስትን ወጪን መቀነስ እንዲሁም የህዝብንም ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቃል። ከተሞችን ለመምራት የሚዘጋጁ ፓሊሲዎችና እቅዶችም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ከተማ እንደሚገቡ ታሳቢ ማድረግ አለበት። በከተማ አመራሮች በኩል የአመራር ክህሎት ክፍተት በመኖሩ አንዳንድ ጉዳዮች የትም ቦታ ከተሞች መመራት ያለባቸው በከተማ አመራር በሰለጠኑ ባለሙያዎች ብቻ መሆን አለበት።
በስራ እድል ፈጠራውም ከተሞች ከገጠር የሚፈልሰውን ስራአጥ በስራቸው ባሉ ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት መስጫዎች የተሻለ ክፍያ በመክፈል መያዝ ይጠበቅባቸዋል። እያንዳንዱ ከተማም በአካባቢው ካለው የገጠር አስተዳደር ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር በገጠር ላለው ዜጋ ባለበት የስራ እድል በመፍጠር እዛው እንዲቀር ማድረግ የግድ ይላል።
ለዚህ ደግሞ ከተሞች እቅድ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ የገንዘብና ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው። የአንዱስትሪ ፓርኮችንም በአስተማማኝ ሁኔታ ቋሚ የስራ እድል መፍጠራቸውን፣ እሴት በመጨመር መስራታቸውን፣ ለተቀጣሪዎች ተመጣጣኝ ክፍያና የመኖሪያ ቤት እጥረት ማሟላታቸው መፈተሽ ተገቢ ነው።
በከተማ ዙሪያ ያሉ ኢንዱስትሪዎችም እሴት በመጨመር ገጠሩን ከግምት ያስገቡና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርቶች ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል። ለተሳለጠ የንግድ እንቅስቃሴ፣ መሰረተ ልማቶችን በጋራ ለመጠቀምና ለልምድ ልውውጥ በከተሞችም መካከል የእርስ በእርስ ጠንካራ ትስስር መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በአንዳንድ ከተሞች የሚሞከሩ የፈጠራ ስራዎች ገጠሩን ማዕከል ያደረጉ ሊሆን ይገባል። በየትኛውም ደረጃ የሚሰሩ ግንባታዎችም የአየር ብክለትን ታሳቢ በማድረግ አረንጓዴ ልማት ያካተቱ መሆን አለባቸው እንዳለባቸውም ነው ባለሙያዎቹ ማራሪያ የሰጡት፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ