ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው በርካታ የግብርና ምርቶች መካከል አረንጓዴ ወርቅ የተባለው ቡና በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በዘንድሮው የበጀት ዓመት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአስር ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ ውጭ ገበያ ከተላከው ቡና ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት እንደተቻለ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ላለፉት ሰባት ተከታታይ አመታት አጠቃላይ ኤክስፖርቱ እድገት ያላሳየ እንደሆነና በአሁኑ ወቅት አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በተለይም ቡና ከፍተኛ እምርታ ማስመዝገብ የቻለ መሆኑን አንስተዋል።
ቡና በዘንድሮው በጀት ዓመት እምርታ ያሳየ ስለመሆኑ እና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ልማትና ግብይት የተመዘገበው ውጤት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቡና በስፋት እየተተከለ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት እየተፈተነችበት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማቃለል የምትችለው ወደ ውጭ ገበያ በምትልከው ምርቶች በመሆኑ ምርታማነት ላይ አተኩሮ መሥራት የግድ እንደሆነም አመላክተዋል። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም በተለይ በግብርናው ዘርፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ ጠቀሜታዎችን ማስመዝገብ የቻለና በቀጣይም ውጤታማ ሥራ ሊሠራበት የሚገባ እንደሆነም ይታመናል።
ቡና በአሁኑ ወቅት ትርጉም ያለው ለውጥ እያስመዘገበ ያለና ለአገር ኢኮኖሚም በጎ አስተዋፅኦውን እያበረከተ ይገኛል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቀሱት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ ቡና በስፋት መተከል መቻሉ አንዱ ሲሆን በግብይት ሰንሰለቱም የተሠሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ስለመኖራቸው ባለሙያዎች ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቡና ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የጀመረው ካለፈው ዓመት ጀምሮ እንደሆነና ለዚህም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ያነሱት የቡና አምራቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሁሴን አምቦ ናቸው።
እንደሳቸው ማብራሪያ፤ በቡና የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችና በሕገወጥ ንግድ ዙሪያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በርካታ ሥራዎችን እንደሠራ ነው ያነሱት። በተለይም ቡና አልሚዎች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ኢሲኤክስ) ሳይገቡ ደረጃውን የጠበቀ ቡና በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉና ዘርፉ ከምርት ገበያው ውጭ መሆኑ አሁን እየታየ ያለውን ውጤት ከማስመዝገብ ባለፈም አርሶ አደሩም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል።
የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል አንዱ የ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› መርሃ ግብር ነው። በቡና ግብይት ሰፊ ድርሻ ባለው በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ፕሮግራም ትልቅ መሻሻል ታይቷል። ይህም ለዘርፉ ውጤታማነት ሁለተኛው ምክንያት ነው። ፕሮግራሙ በተለይም ገበሬውን ከጉድጓድ አውጥቶ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል።
በጥራት የተዘጋጀው ቡና ለውጭ ገበያ እየቀረበ ገበሬው የተሻለ ገቢን እያገኘ ሲሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት በታሪክ ከ50 ብር ተሻግሮ የማያውቀው አንድ ኪሎ ጀንፈል ቡና በአሁኑ ወቅት እስከ 150 ብር ደርሷል። ለዚህም በግብይት ሰንሰለቱ መሀል ገብቶ ጥራቱንና ዋጋውን የሚበጠብጥ አካል ባለመኖሩ ነው።
ይሁንና ቡና ከፍተኛ ትኩረት፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚፈልግ በመሆኑ ችግሮች ሲፈጠሩ በቶሎ ለችግሮቹ መፍትሔ በመስጠት ዘርፉ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ የግድ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ሁሴን፤ ለዚህም መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት መሠረት ከላይኛው አመራር ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ ባለሙያዎች በቅርብ ሆነው ልማቱንና ግብይቱን መከታተል ያለባቸው መሆኑን አመላክተዋል።
ቡና በመጠን ሳይባክን ጥራቱም ሳይጓደል አርሶ አደሮች በቀጥታ ለአቅራቢዎች፤ አቅራቢዎች ደግሞ ለላኪዎች ማስረከብ የሚችሉበት አሠራር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርግቶ መስራት በመቻሉ በግብይት ሂደት የነበረውን የተንዛዛ አሠራር ማስቀረት ተችሏል። ከዚህም ባለፈ መነሻውና ምንነቱ የታወቀ የቡና ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣ የራሱን አስተዋጽኦ ተጫውቷል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብይቱን የማዘመንና ፍትሃዊ የማድረግ እንዲሁም እሴት የመጨመር ተግባርን በማከናወን አገሪቷ ከዘርፉ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል ግብ ይዞ እየሠራ መሆኑን የገለጹት በቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ናቸው። እንደሳቸው ገለጻ አጠቃላይ ግቡን ሊያሳኩ የሚችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ሲያስረዱ፤ የኢትዮጵያ ቡና በተለይም በአሁኑ ወቅት ላስመዘገበው ውጤት ምርቱ ሳይባክን ከምርት እስከ ኤክስፖርት መዳረሻ ድረስ በትክክል መውጣት የሚያስችለውን ሥራ መሥራት በመቻሉ እንደሆነ አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት መመዝገብ እንዲችል አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከሠራቸው ሥራዎች መካከልም አንደኛው አገራዊ ግብረ ኃይልን የማጠናከር ሥራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደራሽ ቁጥጥር በማድረግ ቡና እንዳይባክን ማድረግ ተችሏል። ሦስተኛው በሶፍትዌር ሲስተም በመገንባት ሁለቱን በመደገፍ ቡናው ሳይባክንና ከመጣበት ቦታ በቀጥታ ወደ መዳረሻው እንዲደርስ የማድረግ ሥራ ነው።
ከግብረኃይል አንጻር በተለይም ከፌዴራል ፖሊስ፤ ከጉምሩክ ኮሚሽን፤ ከአዲስ አበባ ከንግድ ቢሮ፤ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ምዕራብና ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን የተጠናከረ የቅንጅት ኮሚቴ በማዋቀር ኮሚቴዎቹም ከታች ያሉትን ግብረኃይሎች በማጠናከር ትርጉም ያለው ሥራ ተሠርቷል።
እስካሁን በነበረው አሠራር የኢትዮጵያ ቡና የላላ ቁጥጥር የነበረውና በትክክልም ቡናው የት እንደደረሰ የማይታወቅበት ሁኔታ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በምርት ገበያ ላይ ኮንትሮባንዱ በዝቶ ቡናው ወደ አገር ውስጥ ይመለስ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን የነበሩ ችግሮችን ማቃለል ችሏል። በተለይም የተለያዩ የጥራትና ቁጥጥር ሶፍትዌሮችን በመገንባት የአገሪቷ ቡና የት እንደሚገኝ፤ ከየት እንደተሰበሰበና የት እንደደረሰ በመከታተል እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራት ያለውን ምርት ማምረት፤ ግብይቱን ዘመናዊ ማድረግ፤ የዘርፉ ተዋናዮችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥና በዚህም አገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል በማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
የምርት ጥራትን በተመለከተ በቀዳሚነት አርሶ አደሩ ጋር ያለውን ክፍተት የመድፈን ሥራ እየተሠራ ነው። ለአብነትም ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ለሦስተኛ ዙር እየተካሄደ ነው። ምርቱን በጥራት በማምረት የተሻለ ገቢ እንዲገኝ እየተሠራ ሲሆን ከዚህም ባለፈ አርሶ አደሮች የራሳቸውን ምርት በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ መላክ የሚችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ከካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በተጨማሪም ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው ቡና እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት አርሶ አደሩ ዕውቀት እንዲኖረው ያስችለዋል።
ግብይቱን በማዘመን በተለይም በግብይት ሰንሰለት ውስጥ የነበረውን አላስፈላጊ ሂደት በመቁረጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲፈጠርና አርሶ አደሩ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህም ባሻገር አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ውጤት እንድታገኝ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል።
ቀልጣፋና ዘመናዊ የግብይት ሂደት በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ቡና በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ተደርጓል። ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለውም በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ በመግለጽ፤ አንደኛው የነበሩ ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት ሪፎርም የተካሄደ ሲሆን ሁለተኛው ሪፎርሙን ሊደግፉ የሚችሉ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎች መሻሻላቸው እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በዚህ ሂደትም ከዚህ ቀደም አርሶ አደሩ ቡናውን የሚሸጠው ለደላላ ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ስድስት አማራጮች ተቀምጠውለት በሚያመቸው መንገድ መሸጥ እንዲችል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውለታል። ስድስቱ አማራጮችም አንደኛው በምርት ገበያ፣ ሁለተኛው ለአቅራቢ፣ ሦስተኛው ከአካባቢው ባለሀብት ጋር በመተባበር በተሻለ ዋጋ መሸጥ የሚችልበት አማራጭ ሲሆን፤ አራተኛው አርሶአደሩ ፈቃድ አውጥቶ በቀጥታ ቡናውን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ይችላል። አምስተኛ ከህብረት ሥራ ዩኒየን ጋር በጋራ በመደራጀት በዩኒየኑ አማካኝነት ቡናውን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ይችላል። ስድስተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ለቡና ቆይዎች ቡናውን መሸጥ የሚችልበት አማራጮች ናቸው።
እነዚህ ሁሉ የገበያ አማራጮች ከዚህ ቀደም ያልነበሩና በሪፎርሙ የመጣ ለውጥ እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ በአካባቢው ለሚገኝ ባለሀብት ቡናውን በመሸጡ ከባለሀብቱ በርካታ አገልግሎቶችንና ድጋፍ ያገኛል። ለአብነትም አዳዲስ ዝርያዎችን ከማግኘት ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደርጋል። አርሶ አደሩ ከባለሀብቱ በሚያገኘው ድጋፍም የተሻለ ምርት በመሰብሰብ በተሻለ ዋጋ ቡናው የሚሸጥ ሲሆን በዚህም አርሶ አደሩን ጨምሮ ባለሀብቱና አገሪቷም ከዘርፉ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።
ሌላው ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንዲታይ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የላኪና አቅራቢ ግንኙነት አንዱ ነው። በላኪና አቅራቢ መካከል የነበሩና ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ ተጠቃሚ ሆነው የቆዩ ሰንሰለቶችን ማስቀረት ተችሏል። እነዚህ በመካከል የገቡ አላስፈላጊ አካላትን ማስወገድ መቻሉ አንደኛ የቡና ጥራት እንዲኖር አስችሏል።
የቡና ጥራትን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ደረጃ አንድ ቡና 83 በመቶ ጥራቱን ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፤ ደረጃ ሁለት ስድስት በመቶ፣ ደረጃ ሦስት 44 በመቶ፣ ደረጃ አራትና አምስት ደግሞ ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል። ደረጃ አንድ፣ ሁለትና ሦስት ቡና ሲሸጥ ጥራት ያላቸው በመሆናቸው በድርድር በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣሉ። ይህም በቀዳሚነት የቡና ጥራት እንዲጠበቅ ከማስቻል ባለፈ አርሶ አደሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚ በመሆን ቡናውን በተሻለ ዋጋ እየሸጠ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በኪሎ 10 ብር ሲሸጥ የነበረው ቀይ እሸት ቡና በአሁኑ ወቅት እስከ 50 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ጀንፈል ቡና ደግሞ ከ100 ብር በላይ ደርሷል። አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ቡናውን በዚህ ዋጋ ሸጦ እንደማያውቅ ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አቅራቢው ቡናውን ከአርሶ አደሩ ገዝቶ ለላኪዎች ያቀርባል። ላኪውም ጥራት ያለው ቡና ሲቀርብለት በተሻለ ዋጋ ቡናውን ገዝቶ ወደ ውጭ ገበያ ይልካል። በዚህም ሳይተዋወቁ የቆዩት ላኪና አቅራቢዎች ተዋውቀው ተግባብተውና ተናበው እየሠሩ በመሆናቸው ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ከምርትና ምርታማነት እንዲሁም ከግብይት ሥርዓቱ በተጨማሪ ቡና ውጤታማ መሆን እንዲችልና አገሪቷም ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ነባር ገበያ ውስጥ የመቆየትና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለግ ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2014