በዓለማችን ላይ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ቀዳሚውና ወሳኙ እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያም እየተፋጠነ የመጣውን የዲጂታል ሽግግር አስመልክቶ እንደ ቀሪው ዓለም ወሳኝ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጨምሮ በዘርፉ ጉልህ ድርሻ ያላቸው አካላት “የሳይበር ደህንነት” በአገራችን ቀዳሚውን ትኩረት የሚሻበትን ጉዳይ ሲያስቀምጡ የመጀመሪያው ምክንያታቸው በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን ማደግ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሌላው አመክንዮ ደግሞ የሳይበር ምህዳሩ የዘመኑ መወዳደሪያ መሆን መቻሉ፤ የተቋማትና የዜጎች በምህዳሩ የመጠቀም አቅምና ፍላጎት መጨመሩ፤ በሳይበር ምህዳሩ ላይ ዓለም አቀፍ ተጽእኖው መጨመር እንደሆነም ያስረዳሉ። በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ይህ ዘርፍ ልዩ ትኩረትን የሚሻ እንዲሆን አስችሎታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት የህዝብ ተወካይ እንደራሴዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች አስመልክተው ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት ከዲጂታል ቴክኖሎጂና የሳይበር ምህዳር ጋር በተገናኘም ማብራሪያ የሚሻ ጥያቄ ተሰንዝሮ ነበር። በዋናነት ጥያቄው የሚከተለውን ጭብጥ የያዘ ነበር።
የሳይበር ጦርነት ዓለማችንን እያሳሰበ የመጣ አዲስ የቴክኖሎጂ የጦርነት አውድማ ሆኗል፡፡ የዚህ አይነት ጥቃት በአይን የማይታይ እጅግ በረቀቀ ዘዴ በስውር በርቀት የሚሰነዘር በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ የዒላማዎቹን አሰራር የማዛባት የማወክና የማስተጓጎል ከፍተኛ አቅም ያለው በአገራት መካከል የሚካሄድ ዘመናዊ የጥቃት ዘዴ ነው። ከዒላማዎቹ ዋና ዋና ግዙፍ የልማት፣ የፋይናንስ፣ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ሲሆኑ መዘዙና ጉዳቱም ከፍተኛ መሆኑ የወቅቱ የዓለማችን ዋና የስጋት ጎራ ውስጥ ይመደባል። ለዚህም ነው ጊዜው አገራዊ የሳይበር ደህንነትና የሳይበር ጥቃት የሚባለው፡፡
የዚህ አይነት ጥቃቶችን ለመከላከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በቀደመው ጊዜ በ1999 ዓ.ም ተመስርቷል፡፡ ይህ ተቋም በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት በተደረገለት ከፍተኛ ትኩረትና ሪፎርም በሰለጠነ አኩሪና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፤ ተቋማዊ ቁመናና በአሰራር ስርዓት ለውጥ የተሰነዘሩብንን በርካታ የሳይበር ጥቃቶች በአስተማማኝ ሁኔታ መመከትና ማምከን ተችሏል፡፡
የሳይበር ጥቃት ሁሉንም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችን ኢላማ አድርጎ የሚሰነዘር በመሆኑ የሳይበር ደህንነት የኢንሳ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተቋማት ትኩረትን የሚሻ በመሆኑ በዓመታዊ እቅዳቸው ተካትቶ እንዲተገበር የአስሩ ዓመት የልማት እቅድ የሳይበር ጥቃትን ሊያካትት ይገባል፡፡ ዘመኑ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ነውና የዲጅታል ሉአላዊነታችን በሳይበር ጥቃት እንዳይደፈር የተሟላ ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ በኩል ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
ምን ዝግጅት ተደርጓል?
ከላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች ከሆኑት ከአንዱ ለተነሳው ጥያቄ ምላሻቸውን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ላይ ባለፉት 9 ወራት ብቻ 5 ሺ 860 ገደማ የቨርቹዋል ጥቃት ተካሂዷል፡፡ ይህ ማለት በጥቅሉ ስድስት ሺ ጥቃት ደርሶብናል፡፡ በሚሊየን ብር ያጣንበት አለ በቢሊየን ያዳንንበት አለ፡፡ ዋናው ፋይናንሻል ዘርፍ አይ ሲ ቲ መሰረተ ልማት እና በኢንፎርስመነት ኤጀንሲስ ፤ መንግሥት ተቋማት እና ፕሮጀክቶቻችን በብዙ መንገድ ይሞከራሉ” በማለት ያለውን ስጋት ለማብራራት ከመሞከራቸውም በላይ ጥቃቱን ለመከላከልና የዘርፉን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ማብራሪያ ሰጥተውበታል።
አስተዳደሩ ምን ይላል?
የሳይበር ደህንነት ላይ ኃላፊነት ወስዶ በቀዳሚነት የሚሰራው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በተወካዮች ምክር ቤት የተነሳውን ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ተከትሎ የሚከተለውን መረጃ ይፋ አድርጓል። በተለይ በኢትዮጵያ በ11 ወራት ከተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከ97 በመቶ የሚልቀውን በማክሸፍ የ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን ይፋ ያደረገው መስሪያ ቤት የሳይበር ጥቃቱ በፋይናንስ እና የሚዲያ ተቋማት ላይ በብዛት ኢላማ ያደረገ መሆኑም ነው የተናገረው።
የሳይበር ምህዳር በባህሪው ድንበር የለሽና ኢ-ተገማች በመሆኑ ዓለም በዚህ መጠነ-ሰፊና ተለዋዋጭ ወንጀል በየቀኑ በአማካይ 16 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ሀብት ታጣለች። የሳይበር ወንጀል በ2015 በዓለም ላይ 3 ትሪሊየን ዶላር ካደረሰው ኪሳራ በእጅጉ እያንሰራራ መጥቶ በ2021 ደግሞ 6 ትሪሊየን ዶላር አሳጥቷል። በየዓመቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው ዓለም አቀፍ የሳይበር ወንጀል በ2025 ከ10 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር በላይ ሊያሳጣ እንደሚችል ተገምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሰሞኑን በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5 ሺህ 860 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን በማስታወስም፤ በዓለም ላይ በየቀኑ በቢሊዮን ዶላር የሚያሳጣው የሳይበር ጥቃት ለኢትዮጵያም ፈተና መሆኑን ገልጿል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፤ የሳይበር ወንጀል በኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ። በዚህም በ2011 ዓ.ም 790፣ በ2012 ዓ.ም 1 ሺህ 80፣ 2013 ዓ.ም 2 ሺህ 900 የሳይበር ጥቃቶች መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት 11 ወራት ደግሞ 6 ሺህ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከየት እንደተሞከሩና የወንጀሉን ባለቤቶች በቀላሉ ለመለየት ባይቻልም ያነጣጠሩባቸው ተቋማት መለየታቸውንም ጠቁመዋል።
በሳይበር ጥቃቱ በተለይም በባንክና የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ማነጣጠሩን ጠቅሰው፤ የሚዲያ ተቋማትም ኢላማ መደረጋቸውን ተናግረዋል። የመንግሥት ቁልፍ መሰረተ-ልማቶች፣ የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ተቋማትም በርከት ያለ ጥቃት ተሞክሮባቸዋል ተብሏል።
ከተሞከሩ 6 ሺህ የሳይበር ጥቃቶች መካከል ከ97 በመቶ በላይ ሙከራዎችን በማክሸፍ የ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን ጠቅሰዋል። ሊደርስ የነበረውን አደጋ የማዳን አቅም እየጎለበተ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሳይበር ወንጀል ሁልጊዜም ኢ-ተገማች በመሆኑ መጠንቀቅ እንደሚገባ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከመደበኛ የሰራዊት ግንባታ ጎን ለጎን የሳይበር ጥቃትን የሚከላከል አቅም መገንባት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቢግ ዳታ እና ለሳይበር ጥቃት
እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መረጃ “ቢግ ዳታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድግ በመጠኑ በጣም ትልቅ የሆነ (የተዋቀረ ወይም ያልተዋቀረ) መረጃ” ሲሆን በውስጡም ውስብስብ የሆኑ የዳታ ስብስቦችን የያዘ የመረጃ ክምችት አይነት ነው። ይህ ከፍተኛ መረጃ ክምችት በቆዩ ወይም ባልዘመኑ የመረጃ ቋት (data base) እና በሶፍትዌር ሲስተሞች ሊሰራና ሊከወን የማይችልም ነው።
በተቋማት ውስጥ የዚህን መረጃ ጥራት ወይም አጠቃላይ ሁኔታ በመግለጽ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የመረጃዎች መጠን፣ ልዩነት፣ ፍጥነት፣ ትክክለኛነት የሚባሉ መለያዎችን ወይም ባህሪያቶችን ይጠቀማሉ።
በሳይበር ደህንነት የጥቃት መንገዶች መጨመር ጋር ተያይዞ ሚስጥራዊ መረጃን በማስጠበቅ የተቋምን የሥራ ክንውን፣ እድገትና አቋም ማስቀጠል ወይም ማስጠበቅ አስቸጋሪና ከባድ ሊሆን ይችላል። ዴታን ከጥቃት መከላከል ወይም መጠበቅም አንዱና ዋናው በሳይበር ደህንነት ፈታኝ ጉዳይ ነው።
የዚህ ከፍተኛ የሆነ ዳታ መጥፋት ወይም መበላሸት የደንበኛ እምነት ማጣትን፣ ለኪሳራ፣ አለፍ ሲልም የደንበኛ መረጃ ስርቆት ወይም መጥፋትን፣ ለከፍተኛ ኪሳራና አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የሲስተም መስተጓጎሎችን ወይም መቋረጦችንም ያስከትላል። ይህ የከፍተኛ መረጃ ክምችት በተሳሳተ ወይም አግባብ በሌለው አካል እጅ ውስጥ ሊገባ ወይም ለተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሊጋለጥ ይችላል።
ከዳታ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን ወይም የሳይበር ደህንነቱን ለማስጠበቅ የሚውሉ የቆዩ ወይም ያልዘመኑ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሲስተሞችና ቴክኖሎጂዎች ብቁ ስለማይሆኑ፤ ይህን ትልቅ ይዘት ያለውን ዳታ መቆጣጠር ወይም መቀበል ስለማይችሉ ሊበላሹ ወይም ሊጠፉ ይችላል። በዋናነት ደግሞ በሚከተሉት ምክንያቶች ተጋላጭ ሊሆን ይችላል። በባለሙያ ክህሎት ወይም እውቀት ክፍተት ጋር ተያይዞ ይህ መረጃ ለሌላ ጥቃት ሰለባ ሊሆንም ይችላል። የዳታ ምንጮቹ በጣም ብዙና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከመሆናቸው አንጻር እያደገ በሚሄድበት ሰዓት ውስብስብነቱ ደህንነቱን ማስጠበቅ ከባድ እንዲሆን ያደርገዋል። ትክክለኛ እና አላስፈላጊ የሆነ ዳታም የመረጃ ክምችትን መፋለስ እና ሥራን እንዲሰናከል ሊያደርግ ይችላል።
የከፍተኛ መረጃ የዳታ ብክለት ከመረጃ አመክንዮ መዛባት እስከ ዳታ መቀላቀል ወይም መቀየር እና መበላሸት የሚደርስ ጉዳት ያስከትላል። ከውስጥ ባለ ሰው ታስቦበትም ይሁን ሳይታሰብበት ሚስጥራዊ የሆኑ መረጃዎች ሊወጡ እና ለስርቆት ሊጋለጡ ይችላሉ። የሳይበር ወንጀለኞች ከከፍተኛ መረጃው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሲስተሞች ክፍተት በመጠቀም ስርቆት ወይም የዳታ ማጥፋት ጥቃቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ። ዳታ በሰዎች ጫና ወይም አሉታዊ ሥራዎች በተጨማሪ በተፈጥሮ አደጋዎች ዳታው ሊበላሽ ይችላል።
የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት
ከአምስት የህዝብ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚጠቀሙባቸው መተግበሪያዎች መካከል ከአራት በላይ የሚሆኑት (82 ከመቶ) የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት እንዳለባቸው የቬራኮድ (Veracode) ጥናት ይፋ ማድረጉን ይሄው የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ይነግረናል።
ይህ የተጋላጭነት መጠን ከሌሎች ሴክተሮች አንጻር በጣም ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት መሆኑን በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ላይ የተሰማራው “ቬራኮድ” ኩባንያ በጥናቱ መጠቆሙንም ይገልፃል። ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲነጻጸር ለመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ሴክተሮች ጥቅም ላይ የዋሉ መተግበሪያዎች ላይ የተገኙ ክፍተቶችን ለመጠገን በእጥፍ የመጠገኛ ጊዜ እንደሚጠይቅ ነው ተመራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት።
ከዚህ ባሻገር 60 በመቶ የሚሆኑት የህዝብ ቤተ-መጽሐፍት ላይ የሚገኙ ክፍተቶች ሳይጠገኑ እስከ ሁለት አመት እንደሚቆዩም የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ጊዜም ከሌሎች ሴክተሮች አንጻር ሲታይ እጥፍ ጊዜያት እንደሚቆይ እና ከአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ እስከ 15 ወራት የተራዘመ ጊዜ እንደሚጠይቅ ታውቋል። ይህን የጥናት ሪፖርት ሲዘጋጅ በህዝብ አገልግሎት መስጫ ፣ በማኑፋክቸሪንግ ፣ በፋይናንስ አገልግሎቶች ፣ በተለያዩ ምርቶች ችርቻሮ ላይ ባሉ ዘርፎች ፣ በሆቴል፣ በጤና አጠባበቅ እና በቴክኖሎጂ ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ተግባራዊ ከሆኑ ግማሽ ሚሊዮን መተግበሪያዎችን ከ20 ሚሊዮን በላይ መረጃዎች ላይ መንተራሱን ቬራኮድ ጠቁሟል።
የቬራኮድ ዋና የምርምር ኦፊሰር የሆኑት ክሪስ ኢንግ፣ በህዝብ አገልግሎት ዘርፍ ላይ በኃላፊነት ያሉ እና ፖሊሲ የሚያወጡ አካላት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና ከፍተኛ የህዝብ ሚስጥራዊ መረጃ የያዙ መተግበሪያዎች በመረጃ መዝባሪዎች ቀዳሚ ኢላማ መሆናቸውን ሊገነዘቡ እና የማስተካከያ ርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታም ከህዝብ እንደራሴዎች ለተነሳላቸው የሳይበር ደህንነት ስጋት ምላሽ የሰጡት የሚያመለክተው ጠንካራ የደህንነት መሰረተ ልማትና የመከላከል አቅም የማይገነባ ከሆነ አገሪቱ ልክ እንደቀሪው ዓለም ሁሉ “የሳይበር ደህንነት” ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሰጋት ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2014