ሁሌም በሰዎች ተፅእኖ ጉዳዮችን የምንመለከት፣ ሌሎች አስበውና አልመው ባወጡት መርሀ የምንመራ፣ በሰዎች አስተሳሰብ እራሳችንን የምንመረምር፣ ከግል ስብዕናና አቋም የራቅን ብዙዎች አለን። እንዴት የራሳችንን ቀለም አደብዝዘን ሌላን ለመሆን እንጥራለን ጎበዝ? ስለምን ያልሆነውን የሌሎችን ማንነት እንላበሳለን? እኛነታችን እኛው የሰራነው፣ መነሻና መድረሻችን እኛው ያሰመርነው ዓላማና ግብ የለየን፤ ያንን ለማሳካት የሚያስችል ቁመናን የተላበስንና በራስ መተማመን ያጎለበትን መሆን ይገባናል።
ሰዎች ብዙውን ጊዜ በራሳቸው መንገድ ርቀው የመጓዝ ልምድ የላቸውም። ያለ ሌሎች እርዳታ አንድም እርምጃ መራመድና ፍላጎታቸውን አልያም አላማቸውን ለማሳካት የሌሎች እርዳታ የግድ ነው ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው። በእርግጥ ከሰዎች ጋር የግል ዓላማችንን ለማሳካት መተጋገዝና መረዳዳት ሊኖርብን ይችልላል። ነገር ግን በሁለት እግራችን ለመቆምና ዓላማችንን ለማሳካት የሌሎች ጥገኛ መሆን አይኖርብንም።
“ምን ነገር በራሴ እወጣዋለሁ” ብለን በራስ መተማመናችንን ማጎልበት ለራሳችን ዋጋ መስጠት ይኖርብናል። አዎን እኔ ያለማንም እርዳታ ጉዳዮችን በራሴ መንገድ የመመርመርና የራሴን አቋም የመግለጽ ሙሉዕነት የተላበስኩ ነኝ ብሎ ማመን ይገባናል። በዚህ መንገድ ርቀው መሄድ የሚችሉት ደግሞ በራስ መተማመናቸው ከፍ ያለና ስኬታማም ናቸው። ልኬታችንን አውቀን በዚያ ልክ እራሳችንን በሚገባን ቦታ ማስቀመጥም ይገባል። እኛን በሚመጥን ልክ ስለኛ የሚሆን ለእኛም የሚበጅ ምን እንደሆነ እኛው ለእኛው መምረጥ ይኖርብናል።
ሰዎች የእኛን ምርጫ ሊመርጡልን ዓላማና ግባችንን ሊያሳኩልን ሳይሆን እንድናሳካ የሚያግዙን እንጂ ለሌሎች ግብና ዓላማ ማሳኪያ ቁስ ሊያደርጉን አይገባም። ጎበዝ ድንበር ይኑረን እንጂ፤ ለራሳችን የምናሰምረው ለልኬታችን የሚስማማ በእኛ ልክ ወደኛ የከለልነው ወደሌሎችም ተሻግረን የማንሄድበት ድንበር እናብጅ።
እኔ ያልኩት ድንበር ይሄ ከጎረቤታችን ጋር በአጥር የከለልነው የኔ ወሰን ይሄ ነው፤ የአንተ ደግሞ ወዲያ እያልን የምንለውን አይደለም። ድንበር የምለው፤ በስብዕናችን ውስጥ እኛን መስለን እኛ ሆነን በራሳችን የምንቆምበት ከሌላ የምንለይበት የራሳችን ማንነትና አቋም የምናንፀባርቅበት ማንነት ነው። ያ ድንበር በእኛና በሌሎች መካከል ያለ እኛ የራሳችንን የምንፈልገውና ያሻን በራሳችን ዛቢያ የምንከውንበት ከሌሎች ተፅዕኖ ነፃ ሆነን በራሳችን የራሳችን ቀለም የምንፈካበት ድንበር ነው።
አዎን እኛ በራሳችን ልክ የራሳችን የምንለው ድንበርማ ያሻናል። ሰዎች ከራሳችን አቋምና መርህ በአጋጣሚ ቀርበው የእነሱን ሊጭኑብን የምንገባ መሆን የለብንም። በእርግጥ ከእኛ የሆነውን ለሌሎች አንሰጥም፣ እኛም ጋር የጎደለውን ከሌላው አንቀበልም እያልኩ አይደለም። እያልኩ ያለሁት በሌሎች ትርኪ ምርኪ ወይም ሚዛን የሌለው ሃሳብና እቅድ አንመራ ነው። የራሳችን አቅጣጫና ግብ ይኑረን ነው።
የራሳችን መስመር እናብጅ፤ ያ መስመር ደግሞ እኛው ለእራሳችን በምንሰጠው ዋጋ ልክ መሆን ይገባዋል ነው። ታዲያ ይሄን መስመር ስናሰምር በልካችን ይሁን ሌሎች እንደኛ ያሰመሩትን ድንበራቸው የማንገፋ እኛም ሰፍቶ የሚያስቸግረን ሳይሆን በእኛው ልክ የተለካ ይሁን ነው። በሌላ አባባል በልካችን በአቋማችንና በመርሀችን መደራደር የለብንም ማለት ነው።
ያ የእኛ የሆነው መርህና ያሰመርነው ድንበር ለሌሎች አሳልፈን የማንሰጥ የሌሎችም መብት እና መርህ የምናከብር በዚያም ውስጥ በጥበብ የምንኖር መሆን ይኖርብል። እኛ ሰዎች ስንባል የእኛነታችን መገለጫ የሆነው ስብዕና የተላበሰ፣ በሰዎች እኩልነት የሚያምን፣ መብትና ግዴታውን ለመወጣት የሚጥር፣ አገራዊ ፍቅሩን በተግባር የሚያረጋግጥ፣ ፅኑ የሆነ ዜጋ የራሱ መርህ ያለው የማይብረከረክ አቋም የተላበስን ልንሆን ይገባል።
በመርህ የሚመራና በራስ መተማመኑ ከፍ ያለ ዜጋ የማይደራደርባቸው፣ በማያወላዳ መልኩ ለግቡ መሳካት ያስቀመጣቸው ጉዳዮች መሳካት ሁሌም የማይታክት ቆራጥ ነው። በዚህ በቡድን በሚፈረጅበትና አንድ የራስ የሆነ አቋም መያዝ ግድ በሚልበት ወቅት በተለይ የራስን ያልተበረዘ አዎንታዊ እሳቤን ይዞ መቆም በራስ መተማመን ማሳያ ነው።
ሰዎች በጋራ የፈረጁት ጉዳይ በራሳችን በተለየ አተያይ የምንመለከት ስንቶቻችን ነን። አዎን ተሰባስበው አንድን ጉዳይ በተመሳሳይ መልኩ ሲኮንኑ ሲያወግዙና አንድ የሆኑ ያህል ጉዳዩን ተገቢ ባልሆነ መልኩ እየተመለከቱት እንኳን አይ ልክ አይደላችሁም፤ እስኪ በዚያ መልክ ደግሞ ተመልከቱት ማለት እንዴት ይሳነናል። እኛም በሰዎች ምልከታ የእኛን አመለካከትና እይታ ሸፍነን መመሳሰሉ ቀሎናል።
እንዴት ሁልጊዜ ትችትና ነቀፋ ዋነኛ መርሀችን ይሆናል፣በጎን አለመመልከት ደግሞ የዘወትር ልማዳችን ይሆናል ጎበዝ? ያየነውን ስህተት የምናነውረውን ያህል የሚሰራውን በጎ ነገር እንዴት ቢያንስ ጥሩ ነው ማለት ያቅተናል። ጎበዝ እስኪ ቆም ብለን አካሄዳችን እንመልከት፤ ትችታችን ገደብ አላለፈም? ጉዳዮችን በበጎ ተመልክተን ከምንሰጠው አስተያየት ይልቅ ትችትና መዛለፋችን አልበዛም? እንዴት በዚህ መልኩ በመንጋ ስንፈርድና በደቡ ስንዛለፍ አይ ይሄ ነገር ቆም ብለን በሌላ መልኩ እንመርምረው ማለት ያቅተን።
ወንድሜ በጎ ዜና እንደ ኮሶ መሮህ የሽብር፣ የመለያየት፣ የጦርነትና ግጭት ወሬ እንደ ማር የሚጣፍጥህ ከሆነ ባልሰማኸውና ባላየኸው እንዲሁ ባሉ ብቻ የራስህን አቋም አሽቀንጥረህ ጥለህ የሌሎችን አቋም ላይ ከቆምክ ጤነኝነት አይደለምና እራስህን መርምር። ጥሩ ንግግርን ንቀሽ የማይጠቅምሽ ላይ ካዘወተርሽ፣ እውነታን አሳንሰሽ ያልተጨበጠው ላይ ጊዜሽን ከፈጀሽ አንቺ ከከሳሪዎቹ ተርታ ነሽ።
ጎበዝ ነገሮችን በንቃት እንመልከት እንጂ። የራሳችን የሆነ መርህ በራሳችን ሁኔታዎች አይተን የምንመዝን እንሁን እንጂ። እኛ እስከመቼ የሰዎች ሀሳብ ተሸካሚ የሰዎችን ቀመር ቀንበር የምንሆነው። ባሉ ብቻ ሳታመዛዝን አንተም ፈራጅ ከሆንክ ያየኸውን ጉዳይ በጎነት አንዴም ሳታወራ ነገሮችን ሁሉ በትችትና በነቀፌታ የምትመለከት ከሆነ ሚዛን ስተሀል።
ሚዛን ከሳትክና በራስህ የማትመራ ከሆነ ሁሌም ወሬህ ፅልመትን አግዝፎ የሚያሳይ ብርሃንን የከለለ ከሆነ ወዳጄ አንተ አደጋ ውስጥ ነህ። እንዴት መልካም ነገር መልካም መሆኑን መመስከር ሳትችል በጎ አስተያየቱን መለገስ ይሳንሀል። ይህ ፈፅሞ የሚጣረስ ነውና እራሰህን ከራስህ ጋር አስታርቀው።
በአንፃሩ ደግሞ መጥፎው ከመልካሙ አብልጠህ ማግዘፍ በየትኛው አተያይ ልክ ሊሆን ይችላል ብለህ አሰብክ። ጤናማ አተያይ መላበስ ሚዛናዊ ምልከታ እጅጉን ያስፈልጋል። ልኬት የተዛባ ነገር በትክክለኛ ክብደቱ ለማወቅ ያግዛል። ጉዳዮችን በሚዛን መመልከት ጥሩ ነው። ጎበዝ እራሳችንን ከዚህ የተዛባ ምልከታ እናርቅ። ፅልመትን ደጋግሞ ማመላከት ከብርሀናማ ሕይወት ያርቃል። በጎ ከምንለው አስሳሰብ፤ ሰላም ከምንለው የፍስሀ መነሻ በብዙ ያርቃል። በራስ መተማመናችን በማጎልበት የሌሎች ሀሳብና እሳቤ ማረፊያ እንዳይሆን እራሳችን ላይ መስራት ይኖርብናል። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2014