በጎ ፍቃደኝነት ሰዎች ትርፍ ወይም ጥቅም ሳይፈልጉ በራሳቸው ተነሳሽነት ሌሎችን ለማገዝ የሚያከናውኑት ተግባር ነው። ይህን በጎ ተግባር ሰዎች በራሳቸው ፍቃድ ሲያከናውኑ ታዲያ ዘርን፣ ፆታን፣ የቆዳ ቀለምን፣ ሃይማኖትን፣ ቋንቋንና ፖለቲካን መሰረት አድርገው አይደለም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው የበዛ በጎ ፍቃደኞች እንደየፍላጎታቸው በየጊዜው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ይሳተፋሉ። በኢትዮጵያም ቀደም ሲል ስለ በጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛና በመንግስት በኩልም የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ግዜ በዚህ አገልግሎት የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ወጣቶች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። እስከ አሁንም በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል። በዚህም ብዙዎች ከአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በዚህ የክረምት ወቅት ወጣቶች በስፋት ከሚሳተፉባቸው ጉዳዮች አንዱ ይኸው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ነው። ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ከፍ እያለ በመምጣቱም በአገልግሎት የመሳተፍ መጠናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
አምና በተከናወነው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም 19 ሚሊዮን ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ 23 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ወጣቶች በአገልግሎቱ ተሳትፈዋል። በዚህም መንግስትና ህዝቡ ሊያወጡ ይችሉ የነበረውን 12 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል። ዘንድሮም ይህንኑ አገልግሎት ለማከናወን እቅድ ታቅዶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሂዲን ናስር እንደሚሉት ባለፈው አመት በተከናወነው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 19 ሚሊዮን ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ 23 ሚሊዮን ገደማ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ተሳትፈዋል። በዚህም መንግስትና ህዝብ ሊያወጡ ይችሉ የነበረውን 12 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል።
የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተቀናጀ መልኩ ለመስጠት የእቅድ ዝግጅትና ሌሎችም አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል። የተዘጋጀው እቅድም ለሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ የፌዴሬሽን አደረጃጀትና በላድርሻ አካላት እንዲወርድ ተደርጓል። ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችን ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አቅደው ለትግበራ ዝግጁ ሆነዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በአስራ አንድ የተለያዩ ዘርፎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሰጥ ሲሆን በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከ19 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ይሳተፉበታል። በሚከናወነው በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም መንግስትና ህብረተሰቡ ሊያወጡ የሚችሉትን 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ለማዳን ታቅዷል። አገልግሎቱም ከሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንዲከናወን መርሃ ግብር ተይዞለታል።
እንደ ሃላፊው ገለፃ የዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በአረንጓዴ አሻራ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ሰላም፣ መንገድ ደህንነት፣ ኮቪድ-19 መከላከልና ሌሎችም የጤና አጠባበቅ ስራዎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ያተኩራል።
በተጨማሪም የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልና ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ በሌሎች አስራ አንድ ዘርፎች ላይ ያተኩራል።
በዋናነት ደግሞ የወጣቶችን እርስ በእርስ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና አጠቃላይ የወጣቶች ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዲኖረው በሰላም ዙሪያ ያተኮሩ ግንኙነቶችም ይካሄዳሉ።
አገልግሎቱ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት ከአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ጎን ለጎን በወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ይከናወናሉ። ሀረር፣ ድሬዳዋና ጅግጅጋ ከተሞች ላይ የሚከናወኑ ሌሎች ፕሮግራሞችም አሉ። የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙም በቅርቡ ይጀመራል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ አገር አቀፍና ሁሉም ወጣት የሚሳተፍበት እንደመሆኑ ክልሎችም እቅዱን ተቀብለው ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በማቀድ ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። ለአብነትም በአማራ ክልል 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሌሎች ክልሎችም እንደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አገልግሎቱን ለማስጀመር ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። እቅድ የማወያየት ስራም በዚህ ሳምንት ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በክልሎች ያሉ ወጣቶች ከችግኝ ተከላ ጎን ለጎን በሚበሉ ተክሎችና ፈጥነው በሚደርሱ በጓሮ አትክልት ምርቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች ተከናውነዋል። በፍራፍሬ መልክ ችግኞች ተተክለው ለረጅም ግዜ የሚፈሉ ችግኞች እንዲሆኑም ተመሳሳይ ስራዎች ተሰርተዋል።
እንደ አገርም 70 ከመቶ የሚሆኑ ወጣቶች በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ይሳተፋሉ። በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አደረጃጀት ደግሞ እስከ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣት አደረጃጀቶች በአገልግሎቱ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ለእቅዱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።
ኃላፊው እንደሚገልፁት አገሪቱ ካለባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር ሁሉም ወጣቶች በዘንድሮው በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የበኩላቸውን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ደግሞ አገሪቱ ከፍተኛ የሰላም ችግር ያለባት በመሆኗ ይህንኑ ችግር ለመፍታት ወጣቶች በወሰን ተሻጋሪ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉ እቅድ ተይዟል።
ይህም ለገፅታ ግንባታና ወጣቶች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲስተካከል ትልቅ ፋይዳ አለው። ለዚህም በኢትዮጵያ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙት ሀረር፣ ድሬዳዋና ጅጅጋ ከተሞች ተመርጠዋል። በተመሳሳይ በሌሎች ክልሎች ላይም የወጣቶች የእርስ በእርስ ግንኙነት፣ የልምድና የባህል ልውውጥ እንዲሁም በሰላም ዙሪያ የነበራቸውን አንድነት የሚያጠናክሩበት ስራዎችም ይከናወናሉ። ለአብነትም የአማራ ክልል ተወላጅ ወጣቶች ወደ ሌሎች ክልሎች በመሄድ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲያደርጉና በሰላም ዙሪያ እንዲወያዩ ፕሮግራሞች ተይዘዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በደምብ እንዲቀጥል በማድረግ በተለይ አሁን ካለው አገራዊ ችግር በመነሳት አገር አቀፍ የወጣቶች የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ይህም ወጣቶች ከምንም ነገር ነፃ ሆነው ስለወቅታዊ የአገራቸው ሁኔታ በነፃነት የሚያወሩበትና የሚመክሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚሁ መርሃ ግብር ውስጥ ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችም አብረው የሚሰሩ ይሆናል።
ከዚህ አንፃር የዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ፋይዳው ብዙ ነው። ከአስራ አንዱ መርሃ ግብሮች ውስጥ አንዱ ወጣቶች በሰላም ጉዳይ የሚመክሩበት፣ አጫጭር የፓናል ውይይቶች የሚያካሄዱበትና ስለሰላም የሚያወሩበት በመሆኑ አገልግሎቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል።
ይህ አገልግሎት ብዙ ጊዜ በጀት ተኮር አይደለም። ወጣቶችም እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን አስተባብረው ነው አገልግሎቱን የሚሰጡት። ነገር ግን ለአንዳንድ ጉዳዮችና ስራ ማስኬጂያ አዲስ አበባን ጨምሮ የክልል አስተዳደሮች የሚመድቧቸው በጀቶች ይኖራሉ።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ መሳተፍ ለሚፈልጉ ወጣቶች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ባሉ በወጣት አደረጃጀቶች አባላትና በሌሎች ግንኙነቶች (ኔትዎርኮች) ና መገናኛ ብዙሃን (ሚዲያዎች) ን በመጠቀም ቅስቀሳዎች ይደረጋሉ። ከዛም ወጣቶች እንደየፍላጎታቸው በተለያዩ መርሃግብሮች ላይ ተሳትፈው አገልግሎቱን ይሰጣሉ። ወጣቶቹ ለዚሁ አገልግሎት ሲጠሩ እየተገናኙ የበጎ ስራውን ያከናውናሉ።
ለአብነትም ደም ልገሳ ቢሆን የተለያዩ ፕሮግራሞች ይያዛሉ። በክልል ከሆነ እንደወረዳውና እንደየአካባቢው ሁኔታ ወጣቶች ደም ይለግሳሉ። የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤቶች የሚሰሩ ከሆነ ደግሞ ቀድመው የተለዩት ላይ ወጣቶች ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ያፈሳሉ።
ሌላው አካል ደግሞ ቤቶቹን ለመስራት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ያሟላሉ። ይህም እርስ በእርስ የሚተሳሰር ነው። ችግኝ ተከላም በተመሳሳይ በእያንዳንዱ ቦታ ላይ ፕሮግራሞች ይያዛሉ። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋነኛ ስራም ወጣቶች ቀርበው እንዲሰሩና እንዲያግዙ ማድረግ ነው።
ከስድስትና ከሰባት አመታት በፊት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሳተፉ ወጣቶች ቁጥር ከሁለትና ከሶስት ሚሊዮን አይበልጥም ነበር። በአስተሳሰብም በኩል በጎ ፍቃድን ከጥቅም የማስተሳሰር ሁኔታዎች ይታዩ ነበር። ይሁንና ዛሬ ወጣቱ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ ያለው አስተሳሰብ እየተቀየረ መጥቷል። ተነሳሽነቱም ጨምሯል። ማህበረሰቡም ስለ በጎ ፍቃድ አገልግሎት እያወቀ መጥቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተሻሻለ መምጣት የመሪዎች አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው። ለአብነትም ባለፉት አመታት በፌዴሬሽኑ በኩል የአቅመ ደካማና አረጋውያን ቤቶች ይሰሩ ነበር። ነገር ግን ስራው ያን ያህል አልነበረም። መሪዎች በዚህ ስራ ሲሳተፉበት ግን ሞዴል ሆኖ ሌሎችም እየተከተሉት ስራው እያደገ መጥቷል።
በተመሳሳይ በአረንጓዴ አሻራ የመሪዎች ተሳትፎ እያደገ በመምጣቱ የዛኑ ያህል መሪዎቹን ተከትሎ በዚህ መርሃ ግብር በበጎ ፍቃደኝነት የሚሳተፈው ወጣት ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መጥቷል። በዚህም በክብረ ወሰንነት የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ በአንድ ጀምበር ለመትከል ተችሏል። ይህም የበጎ ፍቃድ አስተሳሰብ በወጣቱና በማህበረሰቡ ዘንድ እየዳበረ እንደመጣ ያሳያል።
ይህ በጎ ተግባር ዘለቄታዊነት እንዲኖረው ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው ስለነገዋ አገራቸው የሚጠቅም ነገር ዛሬ ላይ የሚያስቀምጡ ከሆነ ከራሳቸው አልፈው ሌላውንም መጥቀም ይችላሉ። ሁሉም ወጣቶች በዚህ ደረጃ የሚሳተፉ ከሆነም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከታሰበው በላይ እያደገ የሚሄድበት እድል ይኖራል። ከዚህ አኳያም ወጣቶች በነቃ ሁኔታ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ይመከራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014