ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት እንዳላት በተደጋጋሚ ይነገራል። ለዚህ በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት ግን አጥጋቢ በሆነ መልኩ የሥራ እድል ሲፈጠር አይታይም። ለወጣቱ ኅብረተሰብ የሥራ እድል ለመፍጠር በመንግሥት በኩል የሚደረገውም ጥረት አርኪ አይደለም። የግሉ ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ቢታሰብም በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚጠበቅበትን ድርሻ አልተወጣም።
በኮቪድና በተለያዩ ሁኔታዎች የዓለም ኢኮኖሚ መንገራገጭ ብሎም የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግርም ለወጣቶች በሚፈለገው ልክ የሥራ እድል ለመፍጠር አላስቻለም። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችም ያለሥራ ለመቀመጥ ተገደዋል። በዛው መጠን በብዙ ወጣቶች ዘንድ ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራስን ሥራ የመፍጠር ፍላጎት ደካማ መሆንም ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል።
በነዚህ ችግሮች ውስጥ ታዲያ አሁንም ተስፋ ሰጪና የወጣቱን ሕይወት የሚቀይሩ የሥራ እድል ፈጠራዎች በፌደራልና በክልል ደረጃ እየተከናወኑ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ በሲዳማ ክልል ወጣት ተመራቂ ተማሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተከናወነ ያለው የሥራ እድል ፈጠራ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው።
አቶ ከፍያለው ከበደ የሲዳማ ክልል ሥራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገጠር ሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ክልሉ በገጠር ሥራ እድል ፈጠራ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተሻለ አፈፃፀም አሳይቷል። በዝግጅት ምዕራፍም ክልሉ በማይንድ ሴትና ኢንተርፕሪነርሽፕ ስልጠናዎች ላይ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን አከናውኖ ወደተግባር ገብቷል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግም ክልሉ በተለይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶች ላይ ትኩረቱን በማድረግ የሥራ እድል ፈጥሯል። በዚህም እስከ ዘጠነኛ ወር ድረስ 26 ሺ 373 ለሚሆኑ ወጣቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል። ይህ ሲባል ግን በጊዜያዊነት ለወጣቶች የሥራ እድል አልተፈጠረም ማለት አይደለም። በጊዜያዊነት የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ወጣቶች በመደገፍና በማብቃት ቆጥበው ወደቋሚ ሥራ እንዲመጡ ጠንካራ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ይህ አፈፃፀም በዓመቱ ከታቀደው ጋር ሲነፃፀር 78 ከመቶ መሆኑን ያሳያል። ከዘጠኝ ወሩ እቅድ አፈፃፀም ጋር ሲታይ ደግሞ 89 ከመቶ ያህሉን ማሳካት ተችሏል። የሥራ እድል የሚፈጠርላቸው ወጣቶችን ልየታ በሚመለከትም መቶ በመቶ ማሳካት ተችሏል። ልይታን በተለመደው መንገድ ብቻ ሳይሆን የዳታ ቤዝ ሥርዓት በመፍጠር ከታች የሚመጡ መረጃዎች በኮምፒዩተር ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ በመቻሉ ልየታውን በሚፈለገው ልክ ማሳካት ተችሏል። በዚህም ቀደም ሲል የነበረው የመረጃ ጥራትና ድግግሞሽ ችግር ተወግዷል።
ከዚህ ባለፈ ለወጣቶቹ የመሸጫና የማምረቻ ቦታዎች ድጋፎች ተደርገዋል። የብድር አቅርቦትና የብድር አገልግሎቶችም ተሰጥተዋል። የሂሳብ ዝርጋታና የኦዲት ሥራዎችም ተሠርተው ኢንተርፕራይዞችን ወደፊት የማሸጋገር ሥራዎችም ተከናውነዋል።
ምንም እንኳን ክልሉ የመሬት ጥበት ችግር ያለበት ቢሆንም በመንግሥታዊ ድጋፍ መሬቶቹ ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲውሉ በማድረግ በአግባቡ ተጠቅሟል። በተለይ ደግሞ በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚገኙ ሰፋፊ መሬቶችን ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ እንዲውሉ በማድረግ ለተሞክሮ የሚሆን ሥራዎችን አከናውኗል።
ለአብነትም በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በአጭር ግዜ 85 ሄክታር የሚሆን የትምህርት ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ መሬቶችን በዲግሪ ለተመረቁና ለ75 ወጣቶች በማቅረብ የትራክተር ድጋፍ ተደርጎላቸው በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ሌሎች የወል መሬት ያሉበትንም በውል ለሶስትና ለአራት ዓመታት ወጣቶቹ እንዲጠቀሙበት ተደርጓል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ በመንግሥት ድጋፍ እንደ ክልል 60 ሚሊዮን ብር በመያዝና ሁሉም ገንዘብ ወደታች እንዲወርድ በማድረግ ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲውል ተደርጓል። ከዚህ ቀደም የተሰራጩ ብድሮችም በብድር አስመላሽ ግብረ ኃይል እንዲመለሱ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል።
በዚህም እስከ ዘጠነኛ ወር ድረስ መመለስ ከሚገባው 100 ሚሊዮን ብር ውስጥ 44 ሚሊዮን ብር ያህሉን ማስመለስ ተችሏል። ይህ አምና ከነበረው አፈፃፀም ጋር ሲታይ ደግሞ የተሻለ ለውጥ አሳይቷል። በሌላ በኩል ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተመረቁ ወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት እስከ ዘጠነኛው ወር ድርስ 46 ሚሊዮን ብር ብድር ተሰራጭቷል። ነገር ግን አምና እስከዘጠነኛ ወር ድረስ የተሰራጨው የብድር መጠን 22 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የዘንድሮው አፈፃፀም ከአምናው በእጥፍ የተሻለ ነው።
ክልሉ በዚህ ዓመት 3 ሺ 500 ኢንተርፕራይዞችን ወደቀጣዩ ደረጃ ለማሸጋገር አቅዶ እስከ ዘጠነኛ ወር ድረስ 483 ያህል ኢንተርፕራይዞችን ብቻ ማሸጋገር ችሏል። ይህም ከተያዘው እቅድ አኳያ ሲታይ አፈፃፀሙ ጉድለት እንደሚታይበትና ለዚህ ጉድለት ምክንያቱ የባለሙያ ድጋፍ እጥረትና ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ መሆኑን አረጋግጧል። ይህንኑ ችግር ለመቅረፍም ባለሙያዎች እንዲቀጠሩ ተደርጓል። የባለሙያዎቹን ክህሎት ለማዳበ ርም ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሚደራጁ ኢንተርፕራይዞች በቶሎ እንዳይበተኑና ዘላቂነት እንዲኖራቸው በጥራት ረገድ ጠንካራ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለዚህም አንዳንድ ሪፎርሞች እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አንዱ እንደ ክልል የተዘጋጀው የብድር ጣሪያ ወይም የፓኬጅ ጥናት ሪፎርም ነው። በዚህ ሪፎርም ቀደም ሲል የነበሩትን ሀያ ሦስት ፓኬጆች አዳዲሶችን በማካተት ወደ አርባ ስድስት እንዲያድጉ ተደርጎ ወደ ሁሉም ወረዳዎች ወርዷል።
ይህ ሪፎርም ሊደረግ የቻለውም አሁን ባለው ሁኔታ የኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ቀደም ሲል የነበረው የገንዘብ ዋጋ አሁን ካለው ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ነው። ለአብነትም በዶሮ እርባታ የአንድ ቀን ጫጩት 15 ብር እያለ ነበር ፓኬጁ የተጠናው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የአንድ ቀን ጫጩት ዋጋ በመጨመሩ ዋጋው እንዲስተካከል ተደርጓል። በተመሳሳይ በሌሎች ፓኬጆች ላይም የዋጋ ማሻሻያ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ የማምረት ሥራ በፓኬጅ ውስጥ ያልነበረ በመሆኑ እንዲገባ ተደርጓል። በክልሉ ሦስት ወረዳዎች የሚሠራው የሐር ትል ማምረት ሥራ እንደ አንድ ፓኬጅ ተቆጥሮ ተካቷል። ፓኬጆቹን ክላስተር የማድረግ ሥራም ተከናውኗል። በዚሁ መሠረት የፍየልና በግ ማሞከቻ፣ የወተት ላም፣ የዶሮና የሰብል ክላስተሮች በሚል የመለየት ሥራም ተሠርቷል። ፓኬጆቹን በክላስተር የመለየት ሥራ የተከናወነውም በዋናነት ውጤታማነቱን ይበልጥ ለመጨመር ነው።
በክልሉ 538 የገጠር ቀበሌዎች ያሉ ሲሆን በነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ ባለሙያዎች ተመድበዋል። ይሁንና ባለሙያዎቹና በነዚህ ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ያሉት ሀብቶች የሚገኙት በተበታተነ ሁኔታ ነው። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም በዳሌ ወረዳ በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ ተበታትነው የነበሩ ባለሙያዎች ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጡ ተደርጓል። በሌላ አባባል ሦስትና አራት የሚሆኑ ቀበሌዎች ዘመናዊ በሆነና ለመረጃ አያያዝ በሚያመች መልኩ ወደ አንድ ማዕከል ታቅፈዋል።
በቀጣዩ 2015 ዓ.ም ከተማ ላይ ያለው የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ በገጠር ወረዳዎች ላይም ተግባራዊ እንዲሆን ታሳቢ በማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ኃላፊው እንደሚያብራሩት ከዚህ በፊት በክልሉ የሚገኙ ተመራቂ ወጣቶች በአብዛኛው ፔሮል ላይ መፈረምን ብቻ ነበር የለመዱት። ሥራቸውን እንደጨረሱ መንግሥት ሥራ ይፈጥርልኛል ብለው ነበር የሚያስቡት። ነገር ግን በአሁኑ ግዜ በተለይ በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ጠንካራ ሥራ በመሠራቱና ተደጋጋሚ ስልጠናዎችም በመሰጠታቸው በዲግሪ የተመረቁ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።
በዚህም ወደ 2 ሺ 673 የሚሆኑ የዲግሪ ምሩቃን ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ወደ ሥራ ገብተዋል። በተመሳሳይ ቁጥራቸው በርከት ያለ የዲፕሎማ ተማራቂ ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረዋል።
በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመለየትም ምሩቃኖች እንዲደራጁና እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎች እንዲጠቀሙባቸው ተደርጓል። በተለይ ደግሞ ወጣቶቹ በወርቅ፣ ሴራሚክና ማዕድናት ማውጣት ሥራ ላይ ተደራጅተው የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። በአንዳንድ የወርቅ ማዕድናት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ኩባንያዎች ወደ ቁፋሮ ከገቡ በኋላ ለወጣቶቹ በንዑስ ሥራ ተቋራጭ ዘርፍ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል። በአሸዋና ድንጋይ ማዕድንም ወጣቶቹ ቅድሚያ አግኝተው እንዲሠሩ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ በየትኛውም ካፒታል ሥራና በትላልቅ ፕሮጀክቶችም የሚሠሩትም ጭምር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን አጠናቀው ለወጡ ወጣቶች ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲሠሩ ተደርጓል። ትላልቅ የግንባታ ሥራዎችም ካሉ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወጣቶቹ የንዑስ ተቋራጭ ሥራ እንዲያገኙ ይደረጋል።
ለአብነትም በሀዋሳና አጎራባች ከተሞች ላይ በአረንጓዴ ስፍራ፣ በማፋሰሻ ቦይ፣ በኮብል ስቶንና በመንገድ ሥራዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው የመጡ ወጣቶች እንዲገቡ ተደርጓል። በተመሳሳይ በገጠርም ተመራቂ ወጣቶቹ በገጠር ተደራሽና ቀበሌን ከቀበሌ በሚያገናኙ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች ተደራጅተው እየሠሩባቸው ይገኛሉ።
ኃላፊው እንደሚገልፁት በክልሉ የሥራ እድል በገጠርና በከተማ የሚፈጠረው በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ሲሆን በዋናነት ግን በግብርናው ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም እስከ ዘጠነኛ ወር ድረስ ሥራ ከተፈጠረላቸው 26 ሺ 373 ወጣቶች መካከል 80 ከመቶ ያህሉ በግብርና ዘርፍ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው። ይህም የእንስሳት ሃብቱን፣ የወተት ላም፣ ከብት ማድለብ፣የአንድ ቀንና አርባ ስምንት ቀን ጫጩት፣ ዶሮ፣ እንቁላልና ስጋን ያካትታል።
በተለይ በእንስሳት ዘርፍ ይርጋለም ላይ ባለው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ አማካኝነት ወጣቶች ለፓርኩ የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት እንዲያቀርቡና እዛው በፓርኩ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ በማድረግ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፍም በተለይ በኮንስትራክሽን ሥራ ከወርቅ ማምረት አንስቶ እስከ መንገድ ግንባታ ድረስ ያሉ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በተመሳሳይ ሰፊ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ ወጣቶቹ ከፀጉር ሥራ ጀምሮ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ።
ከሦስቱ ዘርፎች በዘለለ 250 የሚሆኑ ወጣቶችን ወደ ከፋ ዞን በመላክ በቡና ልማት ዘርፍ እንዲሠማሩም ተደርጓል። ወጣቶችን ወደውጪ ሀገር በመላክ ተጨማሪ ሥራዎችን ለማሠራትም ክልሉ ከክልሎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ ይገኛል።
በቀጣዮቹ ሶስት ወራትም ክልሉ በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ይሆናል። እስከ ዘጠኝ ወር የተሠሩ ሥራዎችን በጥንካሬና በጉድለት ከገመገመ በኋላ በሦስት ወራት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ለየት ባለ መልኩ ገምግሞ ወደ ተግባር ገብቷል። ለዚህም ለእያንዳንዷ ቀን ስራዎችን ከፋፍሎ ሰጥቷል።
በበጀት ዓመቱ 38 ሺ 605 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስከ ዘጠነኛ ወር ድረስ 26 ሺ 373 ያህሉን ማሳካት ተችሏል። ቀሪውን ደግሞ ለማሳካት ለሶስት ወራት በማከፋፈል ተቀምጧል። ለሶስት ወር ከታቀደው ውስጥ ደግሞ 70 ከመቶ ያህሉን ማሳካት ተችሏል። በድጋፍና ክትትል ላይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014