ዛሬ ከነበርንበት፣ የራሳችንን ባለውለታዎች ከምንዘክርበት አካሄድ ለጊዜውም ቢሆን ወጣ እንበልና ከውጪው አለም ለኛ ሲሉ፣ ለኢትዮጵያ ሲሉ ያልሆኑት የሌላቸውን፣ ድሩሲላ ዱንጂ ሂውስተንን የመሳሰሉትን (በተለመደው አገላለፅ፣ ”የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጆች” የምንላቸውን) በማንሳት ልፋትና ስለ ኢትዮጵያ የነበራቸውን ስሜትና ራዕይ እንጋራ።
የዛሬዋ የ”ባለውለታዎቻችን” ተስተዋሽ፣ ምናልባትም ይህ ጸሐፊ ”ከኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጆች መካከል ሰው ጥራ” ቢባል ቁጥር 1 ላይ የሚያስቀምጣት የብዕር አርበኛ ስትሆን፤ ምክንያቱም አርበኝነቷ ከብዕር፣ እምነቷም ከእውነት፣ ማስረጃዎቿም ከመረጃ የመነጩ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ርእሷም ሆነ ርእሰ-ጉዳይዋ ኢትዮጵያና የጥቁር ሕዝቦች የጋራ ማንነት መሆኑ ነው።
በአካዳሚው ደብርም ሆነ አድናቂዎቿ ዘንድ ”ራሷን በራሷ ያበቃች የታሪክ ተመራማሪ፣ ጋዜጠኛ፣ መምህር፣ ሙዚቀኛ …፤ በአሜሪካ የአፍሪካን-አሜሪካን ስርአተ ትምህርት ውስጥ በአዘጋጅነት፣ በተለይም “The Wonderful Ethiopians.” በሚለው ማስተማሪያ ቴክስት አርቃቂነት የተሳተፈች፤ አድር ባይ ብዕርን ሁላ ያስተነፈሰች አፍሪካ-አሜሪካዊቷ ድሩሲላ …” በሚል የምትታወቅ፤ ግዙፍ ሰብእና ያላትና ስራዎቿ ለምእተ አመት አራት ፈሪ በሆነው በዚህ እድሜያቸው እንኳን ገበያውን ከመምራት ያልቦዘኑላት ሰው ነች።
”የአፍሪካ ሕዝብ ምንም አይነት ታሪክ የሌለው፤ ያልሰለጠነ …” የሚለውን የነጮች ዘረኛ አስተሳሰብን አምርሮ በመቃወም በአፍጢሙ የሚደፋው (ልክ የአድዋው ድል እንዳደረገው)፣ ዱቦይስ (W.E.B. DuBois) ”The Negro” (1915) ስራ በጎ ትፅእኖ ስር የወደቀችው ድሩሲላ፤ በኢትዮጵያ ማንፀሪያነት በአጠቃላይ የጥቁር ሕዝብን ማንነት የተመለከቱ ሶስት (መጽሐፍ I (Book I), መጽሐፍ II, መጽሐፍ III) ስራዎቿን (Peggy Brooks-Bertram ከዚህኛው በተጨማሪ ሌሎች ስድስት ስራዎች (ሁሉም ከ1915 እስከ 1926 ባለው ጊዜ ውስጥ የተፃፉ) አሏት፤ የሁለተኛ ቅፅ ርእስም ”Origin of Civilization from the Cushites” ነው፤ ይህም በ1998 ተገኝቷል ነው የሚሉት) ስትሰራ ያለምንም የከፍተኛ ትምህርት ዲግሪ፣ ያለ ምንም የገንዘብ እርዳታና ረዳት … ነበር። (Thabiti Asukile በ”Drusilla Dunjee Houston (1876-1941)”, (February 12, 2007)፤ Brooks-Bertram (2002, xlii)ም ዛሬ እንዲህ እንደ ቀልድ የተዘነጋችው ድሩሲላ በነበረችበት ወቅት በኦክላሆማ ማንም የማይደርስባት ማህበረሰብ አንቂ፣ አስተማሪ፣ የተዋጣላት ደራሲ … ነበረች በማለት መዘንጋት የለባትም ከሚል ቁጭት ጋር ማንነቷን ይገልፃሉ።
በተለይም ”ክላሲክ” የተባለውን፣ እኛ ዛሬ እዚህ ድሩሲላን በባለውለታነት እናነሳ ዘንድ ምክንያት የሆነን ዘላለማዊ ስራዋ (መጽሐፍ I)ን ተከትሎ የጎረፈላት አድናቆት ለማመን ከሚቻለው በላይ ሲሆን፤ የስራው ተወዳጅነትም ሆነ ተጠቃሽነት (Reference) እስከዛሬም እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አልታየም። ይህ ስራዋ በብዙዎች ”እፀብ ድንቅ” የተባለላት (Thabiti Asukile) ሲሆን፤ በአድናቆት ላይ አድናቆትን ሁሉ አትርፎላት ዝናዋ ይናኝ፤ በተለይም በጥቁር ሕዝቦች፤ በምሁራንና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ አግራሞትና አድናቆት፤ በነጮቹ ዘንድ የልብ መሸበርና የወኔ መራድ፤ የስሜት መሸርሸር፣ የስነልቦና ድቀት … ሁሉ ይፈጠር ዘንድ ምክንያት ሆኗል።
የጥቁር ሕዝቦችን መብቶች የተመለከቱ፤ ፀረ-ዘረኝነት አቋምን የሚያራምዱ ከ3ሺ በላይ ርእሰ አንቀፆችን የጻፈችበት የ”Oklahoma Black Dispatch” ጋዜጣ ኤዲተር የነበረችው በዘመኗ ድምጽ ሌላቸው ሴቶች ልሳንና የተዋጣላት ሞዴል (quintessential race woman) የነበረችው ድሩሲላ ስራዋ አሉ የተባሉ የዓለም ምሁራንን ሁሉ ፈትኗል፤ እጃቸውን አፋቸው ላይ አስጭኖም ጉድ አስብሏል። የኋላ ኋላ፣ ሳይወዱ በግድ እውነቱ ይቀበሉ ዘንድ አስገድዷቸዋል። ይገደዱ እንጂ፣ በተለይ የነጭ የበላይነት ሰባኪ ምሁራን ስራዎቿን ”የተጋነነ” በሚል ከማጣጣል ባለፈ ተራ ዘለፋ ውስጥ እስከመግባት ድረስ ሄደው እንደነበር በታሪክ ሰፍሮ ይገኛል። አይውጡት አይተፉት ነገር ሆኖባቸው፤ የተጠቀመቻቸው ሰነዶችና ያቀረበቻቸው መረጀና ማስረጃዎች እማይወለዱ ሆነው እንጂ ስራዎቿን በነጭ ቢሰረዙት በወደዱ ነበር።
ይህንን አለምዓቀፍ የኃይማኖት እና ሰብአዊ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ስመ-ጥር ቤተመጻሕፍት፤ የዘርፉ ልሂቃን እስካሁን ድረስ በስስት የሚያዩትና ከጓዳ ይወጣ ዘንድ እማይፈቅዱት ስራዋን … ነጮችን ለማበሳጨት፤ ጥቁሮችን ለማስደስት ሳይሆን ዘረኝነትን በመቃወም እውነቱን ለአለም ለማሳየት ነው የጻፍኩት ያለችለት ይህ፣ ለ100 አመት አራት ፈሪ የሆነው ስራዋ ከላይ በጠቃቀስናቸው በጣም ጥቂት አድናቆቶች ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም።
ይልቁንም፣ በኦንላየን (አማዞን) ገበያ ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንኳን ብንመለከት በአሁኑ ሰአት፣ ገበያውንም እየመራ ያለው ይኸው በተለያየ የህትመት ደረጃ/ጥራት ለገበያ የቀረበው የ100 አመቱ ”መጽሐፍ I” (ጌታቸው ተስፋዬ ጎጂ በተባሉ ሰው ”ፒራሚድ ገንቢዎቹ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን!” (2002 አ.ም) በሚል ርዕስ ተጎራርዶ ተተርጉሟል)፣ በከፍተኛ ዋጋ ($62) እየተቸበቸበ የሚገኝ ሲሆን፤ ”ምድር አንቀጥቅጥ” ላልነው ማሳያችን ደግሞ መጽሐፉ ከአስር አመት በፊት በሕዝብ ጥያቄ እንደገና እንዲታተም ሲጠየቅ፣ ባልተለመደ፣ የአሜሪካ መንግሥት የእስከ ዛሬ አቋም ባልሆነ ሁኔታ ”አይቻልም” በሚል መከልከሉና የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ መሆኑ ነው።
በእሷ ላይ ተፅእኖ ከመፍጠርም አልፎ ከላይ የጠቀስነውን ስራዋን (መጽሐፍ 1) ትሰራ ዘንድ ቀስቃሽ ምክንያት ለሆናት ለግንባር ቀደም ፓንአፍሪካኒስቱ፤ የአፍሪካ ፍልስፍናዎች (ኔግሪቲዉድ፣ ኢትዮፒያኒዝም፣ አፍሮፖሊታኒዝም …) አቀንቃኝና አራማጁ W.E.B. DuBois የ”አመሰግናለሁ” ደብዳቤ የላከችው ድሩሲላ፤ ነጮቹንና ጥቁር ጠል የባለይነት ስሜታቸውን በማዳመር ዘረኝነታቸውን አይን ከሰበከት እያገላበጠች በአጭርና ገላጭ ሐረጋት በመግለፅም አብዝታ ትታወቃለች።
በጥንት አረቢያ፣ ፐርሺያ፣ ባቢሎናዊያን፣ እንዲሁም በህንድ በሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች መካከል አንድነትን በመፍጠር ላይ የተመሰረተው፤ ያ አንድነትም የጥንቱ የኢትዮጵያ ኩሽ ዘር መሆኑ ላይ የሚያተኩረውና በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች በባህል አንድ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ የሚደርሰው የአፍሪካ-አሜሪካዊቷ ድሩሲላ ታሪክ እንኳን ተጽፎ ተወርቶም የሚያልቅ አይደለም። በመሆኑም ወደ ስራዎቿ እንመለስና በዚህ አምድ፣ በባለውለታነት ትነሳ ዘንድ ወዳስቻላት ስራዋ፤ በስራዋም ተለይታ ትታወቅ ዘንድ ወዳ’በቃት፤ ስመ-ገናናም ወዳ’ደረጋት ”መጽሐፍ I” እንመለስ።
ለመሆኑ የምዕራብ ቨርጂኒያ ነዋሪዋ ድሩሲላ ስለ ኢትዮጵያ በሶስት ቅፆች ምን ምን ጉዳዮችን ጻፈች፤ ስለ ምንስ አንስታ ስለ ምንስ ሳታነሳ ቀረች …? የሚሉት ከሴትየዋ ሁለገብ ሰብእና አኳያ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ሲሆኑ፤ ለዛሬ ግን በ1926 ለንባብ ያበቃችውን Wonderful Ethiopians of the Ancient Cushite Empire (ይህ ከሶስቱ የመጀመሪያ ቅጽ በፈጠረው ተጽእኖ ምክንያት ሁለቱ ቅፆች በጉጉት ቢጠበቁም እስካሁን እምጥ ይግቡ ስምጥ የታወቀ ነገር የለም። (በተለይ፣ እራሷ ሂውስተን ”ሶስተኛው ቅጽ ከሁሉም የተለየ….” ማለቷን ተከትሎ ሁለቱ ቅፆች የት እንደ ገቡ አለመታወቃቸው አድናቂዎቿን እስከ ዛሬ ከቁጭትና ብስጭት ድባብ ሊያወጣ አልቻለም።)
ድሩሲላ ስለ ኢትዮጵያ ያላለችው ምንም የለም። ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊነት ተንትናለች። የአለሙ ሁሉ መነሻ ስለ መሆኗ አበጥራ በማያነቃንቁ መረጃና ማስረጃዎች በማጠናክር፤ በተዋጣለት የአጻጻፍ ብቃት ፍንትው አድርጋ አሳይታለች። የአለም ሥልጣኔ መነሻ ምንጭ ከየት ተነስቶ የት ድረስ እንደ ዘለቀ አመልክታለች። የኢትዮጵያን ውለታ እኔ ነኝ ባሉ የታሪክ፣ የቲኦሎጂ፣ አርኪኦሎጂ …. ተመራማሪዎች፤ ሳይንቲስቶች …. ጥናቶች፤ ፎቶግራፎች፣ ካርታዎች አስደግፋ ለአለሙ አሳይታለች።
”የአለማችን የክፍለ-ዘመኑ ምርጥ” ሲል ታሪክ የመዘገባት ድሩሲላ ስለ ኢትዮጵያ ያልገለጠችው ምንም እውነት የለም። ያልተናገረችውም አንድም ታሪክ አይገኝም። ለዚህም ነው ይህ ጽሑፍ ርእሱን ”ከፈጠሪ በታች፤ ከሰው ሁሉ በላይ …” ሲል የሰየመው።
ድሩሲላ የኢትዮጵያ ጠላቶች ብዙ መሆናቸውን በግልፅ ተናግራለች። ይህንን የሚያደርጉት ከተራ ግብዝነት ተነስተው መሆኑንም በሚገባቸው ቋንቋ ነግራቸዋለች። መፍትሄው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አክብሮ፣ አድንቆ፣ እውነቱንም ተቀብሎ (በግድም ቢሆን) መኖር መሆኑን ምንም ወደ ኋላ ሳትል እቅጩን ነግራቸዋለች – የዛሬ 96 አመት። ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለው የሚቀጥሉ፤ ልክ እንደ እስከዛሬው ሁሉ አንገቷን አስደፋለሁ ብለው የሚያስቡ ከሆነም እዳው ገብስ እንዳልሆነ፤ ውጤቱም እንሱ እንደሚያስቡት በእነሱ የበላይነት የሚደመደም እንዳልሆነና የመጨረሻው ድል የኢትዮጵያ እንደሚሆን መረጃና ማስረጃዎችን አንድ፣ ሁለት … በማለት ቆጥራ ታሳያለች – የዛሬ 96 አመት።
እውቁ አለም አቀፍ ምሁር (noted historian and bibliophile) አርተር (ARTHUR A. SCHOMBURG) እጅግ ከመደነቅና ማድነቅም ባለፈ ስራዋ በጣም የተብራራና ሰፊ መሆኑን ”illuminating and comprehensive book.” በማለት እንደገለፁት የድሩሲላ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች ከሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን ማንነታችንን በወጉ የማናውቅ ነን፤ በውጪ አካላት ሴራ በቀላሉ ተጠልፈን ለመውደቅ የምንንገዳገድ ግን ደግሞ የማንወድቅ ነን። መከራንና ስቃይን በጥበብ በማሳለፍ ወደ ነበርንብት ሰላማዊ ሁኔታ የምንመለስ ልዩ ሰዎች ነን።
እንደ ሌላው ተማርረንና ተስፋ ቆርጠን አገራችንን ለውድቀት አሳልፈን የምንሰጥ፤ ስደትን መምርጫችን የምናደርግ አይደለንም። አዛኝ፣ ሩህሩህ ነን፣ አትንኩኝ ባይም ነን። የግዛት ወሰናችን ከአፍሪካም አልፎ እስከ ስፔን ድረስ ሁሉ ዘልቆ የነበረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በንግድ እንቅስቃሴዋ (ከህንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ጠረፎች) የመሪነት ሚናን ስትጫወት፤ የተከበሩ ማእድናትን ለአለም ገበያ ስታቀርብ፤ በኪነ-ህንፃ ፊት መሪ የነበረች (”በዳቦድና በዳካ የሚታዩት ቤተመቅደሶች የተገነቡት በኢትዮጵያዊው ንጉስ ኤርጋሜነስ ዘመን ነው” ያለች ሲሆን፤ ይህም ከብዙ ማሳያዎቿ አንዱ ነው) … አገር ነች።
ስለ ኢትዮጵያ እውነቱን ለማወቅና ትክክለኛ የህሊና ዳኝነት ለመስጠት የሚያጠኑ ተመራማሪዎች ከዘመናችን መጻሕፍት አጥጋቢ መረጃዎች ሊያገኙ ያልቻሉበት ዋናው ምክንያት ፊታቸውን ወደ ጥንታዊያኑ ያረጁና ያፈጁ መዛግብትና ማህደራት ያለማዞራቸው ሲሆን፤ ወደ ጥንቱ መጻሕፍት ፊታቸውን መልሰው ቢሆንና ለጥቅም ባይገዙ ኖሮ ተዝቆ የማያበቃ የምስክርነት ማስረጃዎችን ባገኙ ነበር (ፒራሚድ ገንቢዎቹ …፣ ገጽ 53)።
ዳሩ ምን ያደርጋል፣ የአሁኑ ዘመን ጸሐፊዎች ለጥቅም ያደሩ በመሆናቸው እውነቱን ፈልፍሎ ለማውጣት አይችሉም … የምትለው ድሩሲላ፣ ኢትዮጵያዊያንን በወታደራዊ ጀብድ የሚችላቸው አልነበረም፤ የተዋጣላቸው መርከበኞች ነበሩ፤ በግብርናው፣ ባህላዊ ህክምናው፣ ኬሚስትሪና ፊዚክሱ … አለምን ያሰለጠኑ ሲሆን፤ የሥነጽሑፍ ተጽእኗቸው አለም አቀፍ ነው። በሥነፊደል፣ በቀለም ስራ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ድል በማድረግ፣ ለአገር በመሞት … የሚደርስባቸው የለም።
ይህንን መጽሐፍ የጻፍኩት (አላማው) ኢትዮጵያዊያንን ለማግነን፤ ወይም እነሱ ኩራት እንዲሰማቸውና እንዲኩራሩ ሳይሆን ያለፈ ማንነታቸውን አውቀው፣ አያት ቅድመ አያቶቻቸው የሰሩትን ተገንዝበው የበለጠ እንዲሰሩ ማድረግ ነው የምትለው ድሩሲላ መሸንቆጧንም አልተወችም። በ”Wonderful Ethiopians of the Ancient Cushite Empire” ላይ እንደሰፈረው፤
እኛ ኢትዮጵያዊያን ታሪክን መርምረን እራሳችንን ለማወቅ የማንጥር፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን ምን ምን ሰርተው እንዳለፉ ለማወቅ ምንም ደንታ እንኳን የሌለን፤ ከአለሙ ሁሉ በላይ፣ የአለሙ አይን ገላጭ ሆነን እያለ አንዱን እንኳን ለአለም እንዳላበረከተ ሁሉ የራሳችንን መልሰን ከሰው ፈላጊ ሆነን የቀረን ነን፤ ወታደራዊ ጀግንነታችን የት ድረስ እንደነበር እንኳን ለማወቅ ምንም ጥረት የማናደርገ …..፤ ግን ደግሞ እግዚአብሔር አብዝቶ የሚወደንና እሚጠብቀን ሰዎች ነን – እንደ አፍሪካ-አሜሪካዊቷ ድሩሲላ ዱንጂ ሂውስተን ጥልቅ ምርምርና ጥናት።
ዛሬ የናቅናቸው ኢትዮጵያዊያን ዘመናት ያሳለፉትን የግብፅ ፒራሚዶች የገነቡ፣ አፈራቸው ግብፅን ያለማ፣ የኮሚዩኒኬሽን ሥርዓትን በመዘርጋት የታወቁ፣ የስልጣኔን መሰረት ያስቀመጡ ህዝቦች ለመሆናቸው አይነ ልቦናችንን ከፍተን የግድ መቀበል ያለብን ጉዳይ ነው የምትለው ድሩሲላ፣ የከላውዴዊያኑ ጥንታዊ ባህል ከጥንታዊው ኩሽ የኢትዮጵያ ኢምፓየር የተገኘ፤ የሁሉም ነገር መነሻ አባይና ዳርቻው ነውም ነው የምትለው።
ኃያል ነን ባዮቹና የእንግሊዝ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ … ሕዝቦች በሌላው ላይ ተፅእኖ ለማድረስ የሚሞክሩት፤ በደልም የሚፈፅሙት ታሪክን ባለማወቃቸው፤ ግብዝነታቸው ነው የምትለው ድሩሲላ እኛ እውነቱን ብንገልፅ ይማራሉ፤ ችግሩም ይወገዳል ስትልም መፍትሄውን ታስቀምጣለች።
ድሩሲላ ስራዎቿን በማይነቃነቁ መሰረቶች ላይ መትከሏ የነቃፊዎቿን ልሳን ለመዝጋት እጅጉን ጠቅሟታል። ሄሮዱተስን ጨምሮ፣ ስራዋን ሰር ኤች ጆንሰን እንዳለው …፣ በንሰን እንደፃፈውና ራውሊንሰን እንዳረጋገጠው …፣ የኤሊየት ስሚዝን ጥናትና ምርምር ተመርኩዞ ዌልስ እንደ መሰከረው …፣ በሳንስክሪት ሰፍሮ እንደሚገኘው … በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ምእራፍ …. ላይ እንደሚነበበው…፣ ሂረን በምርምር ስራው እንደደረሰበት…፣ እንደ የፕቶሎሚያክ ጸሐፍት አገላለፅ …፣ በሳይክሎፔዲያ ኦፍ ቢቢሊካል ሊተሬቸር ላይ እንደ ሰፈረው …፣ ባልድዊን ዳዩዶረስን ጠቅሶ እንደፃፈው …፣ ሶሎንም ሆነ ፕሌቶ ይህን የተቀበሉት …፣ ኒብሁር እንደሚለው …፣ እንደ ሬክሉስ አገላለፅ …፣ ሳይስ ባገኘው መረጃ መሰረት …፣ ዶነሊ እንዳረጋገጠው …፣ እንደ ደ ሩዥ አስተሳሰብ …፣ አልደንድሮፕ …. ሲል ጽፏል፤ Duncker-History of Antiquity በተባለው መጽሐፍ (ቅፅ 1) ላይ እንደሰፈረው …፣ አሜሊያ ቢ ኤድዋርድስ A Thousand Miles Up The Nile በተባለው መጽሐፏ ላይ እንዳሰፈረችው ….፣ ሰር ጂ ጋርድነር በ…. መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው … እና ሌሎች በርካታ በአለማችን ”አንቱ” የተባሉ ምንጮችን ተጠቅማለች። ይህም ስራዋ ምእተ አመትን አስቆጥሮ እንኳን ተፈላጊነቱ ሳይቀንስ እንዲዘልቅ አድርጎታል።
በመጨረሻም፣ አፍሪካ-አሜሪካዊቷ ድሩሲላ ዱንጂ ሂውስተን ስራዋን በሚገባ ሰርታ፤ ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን እውነቱን ተናግራ ወደ’ማይቀረው ሄዳለች። ስራዎቿም በአለም የመጻሕፍት ደብራት ሁሉ ነግሰዋል (ከኢትዮጵያ ውስጥ በስተቀር)። ወደ ፊት ከዚህ ከዛሬው በተሻለ እናስታውሳታለን፤ ስራዎቿም በየቤተመጻሕፍቶቻችን ይቀመጣሉ ብለን እናስባለን። ለዛሬው፤ ”ነፍሷን በገነት ያኑርልን” እያልን እንሰናበታለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2014