ስፖርትና እድሜ የማይነጣጠሉ የውጤታማነትና የስኬት መታያና ምክንያት ናቸው። አንዳንዶች በለጋ የወጣትና ታዳጊነት ዘመናቸው ስፖርቱ ውስጥ በመግባት በብርታታቸው ከራሳቸው አልፈው የአገራቸውን ስም ያስጠራሉ። ሌሎች ደግሞ ስክነትና እውቀትን ተላብሰው በጎልማሳነታቸውም የአገር ኩራት የመሆን ዕድል ይኖራቸዋል። የተቀሩት ደግሞ ለጥቂት ጊዜ የበራች የብቃት ጀምበራቸው ብዙም ሳያስጉዛቸው ትጠልቃለች። በእርግጥ ስፖርት በእድሜ ሊገደብ የሚችለው፤ ቅልጥፍና፣ ጥንካሬና ልበሙሉነትን መሰረት ላደረጉትና በተወዳዳሪነት ሕይወታቸውን ለሚመሩት ስፖርተኞች ነው።
በዘመናዊው ዓለም ስፖርትን ከህጻናት መጀመር ለውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። ለዚህም ነው ታዳጊዎች በተማሪነት ሕይወታቸው በተለይ ከ13 ዓመታቸው ጀምሮ በስፖርቱ ያላቸው ብቃት በተለይ ጎልቶ ሊታይና የወደፊታቸውን የሚያመላክታቸው። ከ16- 25ዓመት ደግሞ ወርቃማውን አቅማቸውን የሚያሳዩበት ዕድሜ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያመላክታሉ። በአንጻሩ 32ከመቶ የሚሆኑ ስፖርት ባለሙያዎች ይህ ዕድሜ ካለፈ በኋላ በተሻለ ሁኔታ ስኬታቸውን በውድድር ሜዳዎች ያንጸባርቃሉ።
በመላው ዓለም አራት ቢሊዮን የሚሆኑ ተሳታፊዎች እንዳሉት የሚነገርለት ተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስ እድሜ ተጽእኖ ከሚያደርግባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ነው። ታዳጊና ወጣቶች በብዛት አቅማቸው ጎልቶ በሚታይበት በዚህ ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱ ግልጽ ነው። በፊፋ አዘጋጅነት የሚካሄደውን ታላቁን ውድድር እግር ኳስን ማዕከል አድርጎ የተሰራ አንድ ዳሰሳዊ ጥናትም(ትኩረቱን በእድሜ ላይ ያደረገ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት) ይህንኑ ይመሰክራል።
ተጫዋቾች አስቀድመው ወደ ውድድር ሊገቡ እንዲሁም ከ30 ዓመት በላይ ሊቆዩ ቢችሉም፤ ባለፉት 60 እና 70 ዓመታት ውጤታማነታቸው በይበልጥ የሚታይበትና መካከለኛ የሚባለው ዕድሜያቸው ከ24-27 ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ አማካይ የሚባለው የእግር ኳስ ተጫዋቾች እድሜ ከ24-29 መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ግብ ጠባቂዎች ከ25 እስከ 29 ዓመት፣ አጥቂዎች ከ25- 28፣ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ከ25-27 እንዲሁም ተከላካዮች ከ24-26ዓመታቸው ያለው ጊዜ በመካከለኛ ይመደባል።
እድሜ እንደየ ስፖርት ዓይነቱ የስፖርተኞችን ብቃት ሊጨምርና ሊቀንስ እንደሚችለው ሁሉ፤ በአንድ ስፖርት ውስጥ ባለ የተለያየ ውድድር የሚኖረው ውጤት ላይም በተመሳሳይ ተጽእኖ እንደሚኖረው አጥኚዎች ያረጋግጣሉ። እአአ ከ2000 እስከ 2020 የተካሄዱ ስድስት ኦሊምፒኮችን እንደማሳያ በመውሰድ ባከናወኑት ጥናት መሰረት እንደ ዋና፣ አትሌቲክስ፣ ቦክስ እና የመሳሰሉት ስፖርቶች ውስጥ በሚካተቱ የውድድር አይነቶች የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ዕድሜ ለውጥ እንደሚኖረው አስተውለዋል። በዋና ስፖርት አጭር በሚባለው 50 ሜትር እንዲሁም በረጃጅሞቹ 800 እና 1ሺ500 ሜትሮች በእድሜ ገፋ ያሉት ይበልጥ ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል። በአንጻሩ መካከለኛ ርቀት በሆኑት 200 እና 400 ሜትሮች ወጣት በሚባለው የእድሜ ገደብ ውስጥ ያሉ ተወዳዳሪዎች አቅማቸውን በይበልጥ ማሳየት ችለዋል።
የአትሌቲክስ በተለይም የሩጫ ስፖርትም በተመሳሳይ ዕድሜ የውጤታማነት ምክንያት ሆኖ ሊቀመጥ እንደሚችል ጥናቱ ያመላክታል። አጭር ርቀት በሚባሉት 100 ሜትር እና 200 ሜትር ውድድሮች እድሜያቸው እስከ 40 የሚደርስ አትሌቶች ተሳክቶላቸዋል። በዚህ ርቀት የክብረወሰን ባለቤትና በኦሊምፒክም እጅግ ስኬታማ የሆነው የምድራችን ፈጣኑ ሰው ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ በሁለቱም ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው የ30ኛ ዓመት ልደት ሻማውን ባጠፋ ማግስት መሆኑ ማሳያ ይሆናል። ከ400-800 ሜትር ባሉት ርቀቶች ደግሞ እድሜያቸው እስከ 24 የሆኑ ወጣት አትሌቶች በብዛት ተሳታፊና ውጤታማ ሲሆኑ፤ ከ1ሺ500 ሜትር በላይ ባሉ ርቀቶች የሚሳተፉ አትሌቶች እድሜም ጭማሪ ያሳያል። እንደ አጭር ርቀት ሁሉ በረጅሙ የአትሌቲክስ ስፖርት ማራቶንም እድሜያቸው 30 እና ከዚያ በላይ የሆኑት የሜዳሊያ ሰንጠረዡን የመቀላቀል እድላቸው የሰፋ ሆኖ ተገኝቷል።
በርካታ ስፖርቶች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ስፖርተኞች እድሜያቸው መጨመሩን ተከትሎ እንዳለፈው ጊዜ ሰውነታቸውን ማዘዝም ሆነ እንደልባቸው መንቀሳቀስ እያዳገታቸው ይሄዳል። በተጨማሪም ጉዳቶችን በቀላሉ ማስተናገድና በቶሎ አለማገገምን ስለሚደጋግሙ ቀስ በቀስ ከስፖርቱ ውጭ ወደመሆን ይሸጋገራሉ። በተቃራኒው አንዳንድ የስፖርት ዓይነቶች ደግሞ እድሜ ሲጨምር ስኬትን ወደማጎናጸፍ ይሸጋገራሉ። በተለይ እንደ ጎልፍ፣ ቦውሊንግ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ክብደት ማንሳት በመሳሰሉት ስፖርቶች ተሳታፊዎች እድሜያቸው ሲጨምር ወደ ስኬታማነት ማማ የመጓዛቸው ሁኔታ ይጨምራል። እንደ ቦክስና ክብደት ማንሳት ባሉ ስፖርቶች ደግሞ እንደ ሚዛኑ መጨመር የተወዳዳሪዎቹ እድሜም ጨምሮ ተገኝቷል። ለዚህም ምክንያት የሚሆነው ክብደት ሲጨምር ከፍጥነት ይልቅ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው ጥንካሬ በመሆኑ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2014