በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከትናንት በስቲያ የተጀመረው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሴቶች ዋንጫ በተለያዩ ጨዋታዎች ቀጥሏል። በውድድሩ ለመሳተፍ ከቀናት በፊት ወደ ዩጋንዳ ያቀኑት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ትናንት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አከናውነዋል። ሉሲዎቹ ዛንዚባርን በመግጠም አምስት ለዜሮ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የሴካፋ ዋንጫ ጉዟቸውን በጣፋጭ ድል ጀምረዋል።
ገና ጨዋታው በተጀመረ አንደኛው ደቂቃ ላይ በአረጋሽ ካልሳ ግብ መምራት የቻሉት ሉሲዎቹ በሃያ ሰባተኛና ሃምሳ ሰባተኛ ደቂቃ ላይ አምበሏና የግብ ቀበኛዋ የሉሲዎቹ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ሎዛ አበራ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች መሪነታቸውን ማጠናከር ችለዋል። በሰባ አራተኛውና በሰማንያ ስምንተኛው ደቂቃ ላይም ቅድስት ዘለቀ ሁለት ግቦችን አክላ ሉሲዎቹ ጨዋታውን በቀላሉ ተቆጣጥረው የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው ሊወጡ ችለዋል።
የሉሲዎቹን ተተኪዎች የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመምራት ስኬታማ ጊዜን ያሳለፉት አዲሱ የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በዋናው ብሔራዊ ቡድንም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በድል መጀመር ችለዋል። ከበርካታ ወራት በፊት የወጣቶቹን ብሔራዊ ቡድን እየመሩ በ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ የውድድሩ አስተናጋጅ የነበረችውን ዩጋንዳን በፍጻሜ ጨዋታ በመርታት በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ የሆነውን ዋንጫ ማንሳት የቻሉት አሰልጣኝ ፍሬው በሴካፋ በርካታ ግብ የሚያስቆጥርና ጥቂት ግቦች ብቻ የሚያስተናግድ ጠንካራ ቡድን መስርተው አሳይተዋል። ከሴካፋው ጣፋጭ ድል በኋላም ያንኑ ቡድን እየመሩ በዓለም ከ20 አመት በታች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ እስከ መጨረሻውና አራተኛው ዙር መጓዛቸው ይታወሳል።
አሰልጣኙ በወጣቶች ቡድን ያስመዘገቡት ውጤት በዋናው ብሔራዊ ቡድንም ተመሳሳይ ስኬት ለማስመዝገብ ተስፋ እንዲጣልባቸው አድርጓል። ለዚህም ከሳምንታት በፊት ሉሲዎቹን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው የቡድን ስብስባቸውን ስኬታማ ከነበረው የ20 አመት በታች ቡድን በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን በማሳደግ ከነባሮቹና ልምድ ካካበቱት ጋር በማጣመር ሲዘጋጁ ቆይተዋል። በአጭር ጊዜ ዝግጅት ያዋሃዱት ቡድንም የመጀመሪያ ፍልሚያውን ትናንት በድል በመወጣት ፍሬውን አሳይቷቸዋል።
አሰልጣኝ ፍሬው በወጣቶቹ ቡድን በርካታ ግብ የሚያስቆጥር በአንጻሩ ትንሽ ግብ የሚቆጠርበት ጠንካራ የአጥቂና የተከላካይ መስመር ያለው ቡድን መስራት እንደሚችሉ አሳይተዋል። በዋናው ቡድንም ትናንት የተጋጣሚያቸው ዛንዚባር ብሔራዊ ቡድን ደካማነት እንዳለ ሆኖ ገና በመጀመሪያ ጨዋታቸው አምስት ግብ አስቆጥረው ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው ማሸነፍ መቻላቸው ገና ተገንብቶ ያላለቀው ቡድናቸው ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል።
በውድድሩ በምድብ ሁለት ከታንዛኒያ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደሉት ሉሲዎቹ ትናንት ያስመዘገቡት ድልና ያሳዩት እንቅስቃሴ ከቀጣይ ተጋጣሚዎቻቸው አቅም አኳያ ወደ ጥሎ ማለፍ ፍልሚያ ያልፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ቡድኖች አንዱ አድርጓቸዋል። ያምሆኖ በጥሎ ማለፍ ዙሩ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ቡድኖች ጥንካሬ ሉሲዎቹ በውድድሩ ለመቆየት የሚያደርጉትን ፍልሚያ ቀላል እንደማያደርገው ይጠበቃል።
ስምንት አገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው በሚፋለሙበት የዘንድሮው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በሁለኛው ምድብ አዘጋጇ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ርዋንዳ እና ጅቡቲ ተደልድለዋል። ዩጋንዳ በውድድሩ መክፈቻ እለት ርዋንዳን ሁለት ለምንም መርታቷ የሚታወስ ሲሆን ሁለተኛው ጨዋታ ቡሩንዲ ጅቡቲን ሶስት ለዜሮ በመርታት ተደ ምድሟል።
ለአምስተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ባለፈው ዓመት በጅቡቲ አስተናጋጅነት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ሲሆን ውድድሩ ሲቃረብ ጅቡቲ ጨዋታዎችን የምታስተናግድበት ኤል ሃጅ ሃሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ስቴድየም ግንባታ ባለመጠናቀቁ አዘጋጅነቷን ማንሳቷ ይታወሳል። በዚህ የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ያለፈው ውድድር አሸናፊ የሆነችውን ኬንያን ጨምሮ ሌሎች ጠንካራ አገራት አለመሳተፋቸው ይታወቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2014