የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የሴቶች እግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) ትናንት በአዘጋጇ ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ ጨዋታ ተጀምሯል። ስምንት ሀገራት በሁለት ምድብ ተደልድለው ለአሸናፊነት በሚፋለሙበት በዚህ ውድድር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በዛሬው የጨዋታ መርሃ ግብር መሰረትም በምድብ ሁለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከዛንዚባር አቻቸው ጋር ሲገናኙ፤ በሌላኛው ጨዋታ ደግሞ ታንዛኒያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ይጫወታሉ።
12 አባል ሀገራት ያሉት የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው ይህ ውድድር በአህጉሪቱ ረጅም ዓመታትን በማስቆጠር ቀዳሚው ነው። ውድድሩ በሁለቱም ጾታ በተለያየ የዕድሜ ገደብ የሚካሄድ ሲሆን፤ የሴቶቹ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ 1986 በዛንዚባር አዘጋጅነት ነበር የተካሄደው።
ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ተቋርጦ በመቆየት እአአ በ2016 በድጋሚ ተጀምሯል። በ2018 እና 19 በተከታታይ ከተካሄደ በኋላም ለ2021 ጅቡቲ እንድታስተናግድ ቢደረግም በድጋሚ ሊሰረዝ ችሏል። በመሆኑም ለአምስተኛ ጊዜ የሚደረገውን የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ኡጋንዳ ለሁለተኛ ጊዜ የማሰናዳት ዕድሉን አግኝታለች። ትናንት በተጀመረው በዚህ ውድድር ላይም በመጀመሪያው ምድብ አዘጋጇ ኡጋንዳ ከሩዋንዳ ጋር ስትጫወት፤ የብሩንዲ እና ጅቡቲ ብሄራዊ ቡድኖችም ተገናኝተዋል።
ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ውድድርም በምድብ ሁለት ኢትዮጵያ ከዛንዚባር፤ ታንዛኒያ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ይጫወታሉ። በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እየተመራ ያለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከትናንት በስቲያ ወደ ውድድሩ ስፍራ ማቅናታቸው የሚታወቅ ነው። የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች አሸናፊና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ብሄራዊ ቡድን እስከመጨረሻው ዙር በማድረስ ተስፋ ያሳየው ወጣቱ አሰልጣኝ ቡድኑ በውድድሩ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀቱን አረጋግጧል። አስቀድሞ ሲመራው የቆየው የታዳጊዎች ቡድን ውድድሩን በዩጋንዳ ማድረጉን ተከትሎ ስለሜዳው፣ አየሩ እንዲሁም ስለቡድኖቹ አስቀድሞ መረጃው ያለው መሆኑ ለዚህ ውድድር እገዛ የሚያደርግለት መሆኑንም አስገንዝቧል።
አሰልጣኙ ከጉዞው አስቀድሞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም በወጣት ተጫዋቾች የተዋቀረ ቡድን ይዞ በውድድሩ ላይ እንደሚካፈልም ጠቁሞ ነበር። ቡድኑን የመምራት ኃላፊነት ከፌዴሬሽኑ መረከቡን ተከትሎ በሊጉ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ካላቸው ጥቂት ተጫዋቾች እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን (13 ተጫዋቾችን) በማሰባጠር ቡድኑን መስርቷል።
ይህንንም ያደረገበት ምክንያት በወጣቶች የተገነባና ለረጅም ጊዜ ግልጋሎት የሚሰጡ ተጫዋቾች ያሉት ብሄራዊ ቡድን እንዲኖር እንዲሁም ውድድሩ ለወጣት ተጫዋቾች ጥሩ ማሳያ ስለሆነ ቅድሚያ ለመስጠት መሆኑንም ገልጻል። አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በውድድር ላይ የቆዩ በመሆኑ ከግንቦት 10/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተጫዋቾቹ ተሰባስበው በቀን አንዴ ልምምድ በመስራት ቡድኑን በማዋሃድ ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ቆይቷል። ከ23ቱ ተጫዋቾችም ጉዳት ያስተናገዱት ሁለት ተጫዋቾች ማገገማቸውንና የተቀሩትም በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙም ናቸው።
34 ልኡካንን ያቀፈው ቡድኑ ሁለት ሰዓት በሚጠጋ በረራ ኡጋንዳ የደረሰ ሲሆን፤ ትናንት ረፋድ ላይ በጂንጃ ትምህርት ቤት ሜዳ የመጀመሪያ ልምምዱን ሰርቷል። ሉሲዎቹን የሚገጥመው የዛንዚባር ብሄራዊ ቡድን(የዛንዚባር ንግስቶች) የመጀመሪያውን ዋንጫ በሀገሩ ማስቀረት የቻለ ነው። በአንጻሩ በቀጣዮቹ ውድድሮች በከፍተኛ ልዩነት በመሸነፉ ከውድድር ውጪ በመሆን የዋንጫ ጉዞውን ለማሳካት አልቻለም።
ሉሲዎቹ እአአ በ2016 እና 2018 የሴካፋ ተሳትፏቸው ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁበት ውጤት ትልቁ ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል። ሁለተኛውን ጨዋታ ግንቦት 27/2014ዓም ከታንዛኒያ ጋር የሚያደርጉ ሲሆን፤ ግንቦት 29/2014ዓም ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ጋር የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ያከናውናሉ። የግማሽ እና የፍጻሜ ጨዋታዎቹም ሰኔ 02 እና 04/2014ዓም የሚደረግ መሆኑንም የተያዘው መርሃ ግብር ያመላክታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014