ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ ችግሮች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ችግሮች ቀላል የማይባል ቁሣዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች አድርሰዋል፤በማድረስ ላይም ናቸው፡፡ የዜጎችም ህይወት እንደዋዛ ተቀጥፏል፡፡ የችግሮቹ መንስኤ ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ በመሆኑ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ከፊት ለፊታቸው የተደቀኑ መሰናክሎችን ለመጥረግ በተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው፡፡ ወጣቶች ለአገራዊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ቅድሚያ ተሰላፊ እንደመሆናቸው ሰሞኑን፤ የአዲስ አበባ ወጣቶች ወደ ባህር ዳር በማቅናት በጣና ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም እንዲሁም የጥላቻንም ሰንኮፍ ከስሩ ነቅሎ ለመጣል ተረባርበዋል፤ መክረዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የተመራው የአዲስ አበባ ወጣቶች ጉብኝት ከአራት መቶ በላይ ወጣቶችን ያሣተፈ ነበር፡፡ ዋና ዓላማውም የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ እያደረሰ ላለው ችግር ለማስወገድ አለኝታ ነታቸውን ከማሣየትም በላይ የዘለቀ ነው፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ትኩስ የሆነውን ወጣት ኃይል ለጥፋት የሚቆሰቁሱ ሴራዎች መሸረብ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በርካታ ወጣቶች የእለት ተግባሮቻቸውን በሚፈጽ ሙባቸው የትኛውም አካባቢዎች ከእውቀት ገበያው ዩኒቨርሲቲ እስከ ራስን ማደሻው መዝናኛ ቦታ ድረስ ይሣካም ይክሸፍ አያሌ የጥፋት ውዥንብሮች ተሞክረዋል፡፡
ጊዜና ወቅት እየጠበቁ ብልጭ ድርግም የሚሉ ብጥብጦች አሁን በአገሪቱ አዲስ ክስተት አይደሉም፡፡ ድርጊቶቹ ወጣቱን ማዕከል በማድረግ መለያየትን በመስበክ፣ አንድነትን በማሻከር፣ ብጥብጥ በመፍጠርና አገርን በማተራመስ የወጣቱን የወደፊት ሕልም የሚያጨልሙ ሴራዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበቤዎች የባህርዳር ጉብኝት ተልዕኮ በተንኮል ለተጠመዱ አካላት እንደማይሳካላቸው በተግባር ማሳየት የቻለ ነው፡፡
ምክትል ከንቲባው በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለተማሪዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ በወቅቱም ‹‹የአንዱ ህመም የሁላችን ህመም ነው፤ ሁለት ወንድማማቾችን በማጋጨት የሚገኝ ነገር ኪሳራ ብቻ ነው፡፡ በአንድነታችን ላይ የተቃጣውን የትኛውንም ዓይነት እንቦጭ በተባበረ ክንዳችን ልንነቅለው ይገባል›› ሲሉ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹ጣና ላይ ያለው ችግር የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ችግር ነው፡፡ የስኬታችን ምስጢር አንድነታችን ነው፡፡ የኦሮሞ ወጣቶች ‹ጣና ኬኛ› ብለው በውቢቷ ባሕር ዳር የጀመሩትን ገድል የጣና ሐይቅን ከችግር ለመታደግ ጅምሩ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል›› ብለዋል ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፡፡
ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስተያየታቸውን ከሰጡት ተሣታፊ ወጣቶች መካከል ወጣት ከድር አሰፋ ታደሰ ከአዲስ አበባ እንደገለጸው ‹‹ ጣና የሁላችንም ነው›› በጣና ሐይቅ ሕልውና ላይ ያንዣበበው ጠላት አረም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› ነውና ብሂሉ የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ሲደመር አሸናፊ ነውና፤ መቀራረብ፣ መጠያየቅ፣ መወያየት እና አንድ መሆን ስንችል አንድ የጋራ ሀብት ይኖረናል፤ኢትዮጵያ ይህ ሲሆን የጋራ እንጂ የግል ጠላት ሊኖረን አይችልም፤ጥላቻ፣ድህነት እንቦጭ፣ አሉቧልታ፣ ውሸት….ወዘተ በተደመረ አስተሳሰብና በተደመረ ክንድ ይንበረከካሉ፡፡
በተመሳሳይ ወጣቶችን በተለያዩ መንገዶች ለመነጣጠል የሚጠነሰሱ የተንኮል ሴራዎችን በጋራ መመከት አገራዊ ግዴታችን ነው፤ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ማጎልበትና መጠበቅ ይገባናል፡፡ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ በማገዝ በኩል ከእኛ በሚጠበቀው ልክ አስተዋጽኦ እያበረከትን አይደለም፡፡ የአገሪቱን ሰላም በመጠበቅ ረገድም ወጣቱ ‹‹የውዴታ ግዴታ›› ያለበት መሆኑን አንስቷል፡፡
እንደ ወጣት ከድር አሰፋ ገለጻ፤ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአዎንታም ይሁን በአሉታ በሚፈጠሩና በሚሰሙ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ወጣቱ ተቀራርቦ አይወያይም፡፡ የመፍትሄ አካል እየሆነ አይደለም፡፡ ችግሩ ሰፊና የአገሪቱ ወጣቶች እንጂ በአንድ አካባቢ አልተወሰነም፡፡ በመሆኑም የተጀመረው የወጣቶች ተቀራርቦ የመወያየት ባህል እንዲለመድ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ወጣት ጉልበቱን፣ አዕምሮውንና ጊዜውን ርባና በሌላቸው የአሉባልታ ወሬዎች ማባከን ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ተሳታፊ የነበረችው ወጣት ፍሬወይን ተስፋዬ ‹‹ላም ባልዋለበት…›› እንዲሉ ያልታሰቡና ያልተደረጉ ጉዳዮች የእውነት ያህል ገንግነው በህዝቦች መካከል ቅራኔን እንደሚያሳድሩ ትናገራለች፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ባህር ዳር ሄደው በተፈጠረው የወጣት ለወጣት ግንኙነቱ እንቦጭን ለማስወገድ ከተበረከተው አስተዋጽኦ በላይ የተፈጠረው መለያየትን የማሸነፍና ጥላቻንም የመንቀል ስኬት ይጎላል፡፡ በባህር ዳር ቆይታ አገራዊ ማንነት ተቀንቅኗል፡፡ አሁን ሰላምን መስበክ ተጀምሯል፡፡ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብላለች፡፡
ወጣት ብርሃኑ አድማሱ ከባህርዳር ወጣቶች የተወከለ ተሳታፊ ሲሆን የወጣት ለወጣት ግንኙነቱን አስመልክቶ ሀሳብ አስተያየቱን አጋርቶናል፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣቶች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በርካታ ቁም ነገሮች መቅሰም ችያለሁ፡፡ በአሉባልታ የሰማኋቸው የጥላቻ ስሜቶች ምንጫቸው ያልተለዩ ከመሆናቸውም በላይ ሥራዬ ብሎ በሚቀምር አካል የሚነዙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ህዝቡ የተዋለደና አንድ ሆኖ የኖረ በመሆኑ ወንድሙን ወንድሙ ሊጨክንበት አይችልም፡፡ ከዚህ ባለፈ የአገሪቱ ወጣት ሆን ተብለው የሚሰሩለት የጥላቻ ታሪኮች መኖራቸውን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አገርና ታሪክ የሚያበላሹ የአስተሳሰብ ውጤቶች ሲያጋጥሙት ምክንያታዊ ሆኖ እውነታውን መለየት ተገቢ ነው፡፡
‹‹በማህበራዊ ሚዲያ ያገኘናቸውን ሁሉ እንዳለ ከተቀበልናቸው ህይወታችንንም ሆነ አገራችንን ለከፋ ችግር እናጋልጣለን፡፡ በወገናችን ላይም እውነትነት በሌለውና ውሃ በማያነሳ ሃሳብ የከፋ ጥላቻ ማሳደራችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ተቀራርበን ስንወያይ የጥላቻን ድንበር በማፍረስ ፍቅርና አንድነታችን ከራሳችን አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ይሆናል፡፡ ሰላም የማንኛውም ነገር መሰረት በመሆኑ የአዕምሯችን ቅኝት መሆን አለበት›› ሲል ወጣት ብርሃኑ አድማሱ ተናግሯል፡፡
በአጠቃላይ ትናንት የአገሪቱ መለያ ደማቅ ምልክት የሆኑ ማንነቶች በመመናመን ላይ ይገኛሉ፡፡ ልዩነቶቻችን የመዋደዳችንንና የመነፋፈቃችንን ተፈጥሯዊ ስበት እንዲንር ያደረጉት ነበር፡፡ አሁን ላይ መሰረት አልባ በሆኑ ጥላቻዎች ጥላሸት እየተቃቡ አለፍ ሲልም በደም እየታጠቡ መጥራት ቀርቶ ይበልጡኑ ሲጨቀዩ ይስተዋላል፡፡ ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች ድረስ ያልተቋረጡ ግንኙነቶች በመፍጠር የአገራቸውንና የሕዝቦቿን ታሪክ ሳይበረዝ ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል እንቦጭም ሆነ ድህነት የሕዝቦች መማረሪያ ተባይ ሳይሆን መማሪያ ክስተት ሆኖ ያልፋል፡፡