የገዘፈ ሰብእና ያላቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ሊነሱ የሚችሉባቸው ምክንያቶች አያሌ ሲሆኑ፤ የዛሬው እንግዳችንም የዚሁ ሰብእና ተጋሪ ናቸው። ሁለገብ ሰብእና ያላቸው ሰዎች ሊታወሱ የሚችሉባቸው ስራዎቻቸው በርካታ ሲሆኑ ከእነዚህም አንዱ የሕይወት ዘመናቸውን በደራሲነት፣ ጋዜጠኝነት፣ ተርጓሚነትና በሌሎችም የሙያ ዘርፎችና መንግሥታዊና ማህበራዊ ሃላፊነቶች ያሳለፉትና በዋግ አውራጃ (የወሎ ክፍለ አገር) የተወለዱት ማሞ ውድነህ ናቸው። (የተወለዱበትን አመት ምህረት አልፎ አልፎ የተለያየ ሆኖ ይገኛል፤ በመሆኑም ማጣራትን ይፈልጋል። እዚህ የተጠቀሰው አብዛኛዎቹ ምንጮች የተጠቀሙበት ነው።)
ሥራዎቻቸው በስለላ፣ በታሪክ፣ በልቦወለድና ተውኔት ላይ የሚያተኩሩት፤ በ1954 የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን፤ “ሁለተኛው የዓለም ጦርነት” በሚል ርእስ (የመጨረሻቸው “የደረስኩበት” የሚለው ግለ-ሕይወት ታሪካቸው ነው) የደረሱትን ማሞ ውድነህ (1923 እስከ 2004 ዓ.ም) በኢትዮጵያ የድርሰትና አጻጻፉ ዓለም ክብረወሰኑን የያዙ ሲሆን፤ ይህም ሊሆን የቻለው በእስከ ዛሬው የአገራችን የድርሰት ዓለም ያልተደፈረው የ59 መጻሕፍት (የሰሯቸውን ስራዎች በተመለከተ ከ53 እስከ 59 ባሉት ቁጥሮች መካከል የሚዋዥቁ መረጃዎች ናቸው ያሉት። ይህ ጽሑፍ፣ በእንግሊዝኛ የጻፏቸውም ስላሉ፣ ከፍተኛውን ቁጥር መውሰድን መርጧል) ደራሲና ተርጓሚ በመሆናቸው ሲሆን፤ ይህም እስከ አሁን ሳይደፈር ባለበት ይገኛል።
የጋዜጠኛ ማሞ “አዲስ ዘመን” ፣ “ፖሊስ እና እርምጃው”፣ “ህብረት” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጦች ላይ መስራታቸውን ልብ ይሏል፤ ስራዎች በጥቅሉ ሲገለፁ ይሰማል እንጂ በአብዛኛው በስም የሚታወቁ አይደሉም። በመሆኑም፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እያዋዛን የምንጠቅስላቸው መጻሕፍት በሙሉ የማሞ ሲሆኑ፤ የመጀመሪያዎቹ አስሩ – ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ የሴቷን ፈተና፣ ከወንጀለኞቹ አንዱ፣ ቬኒቶ ሙሶሊኒ፣ የገባር ልጅ፣ ሁለቱ ጦርነቶች፣ አደገኛው ሰላይ፣ ዲግሪ ያሳበደው፣ ካርቱም ሔዶ ቀረ?፣ እና የ፮ቱ ቀን ጦርነት ስለመሆናቸው ለመናገር ጋዜጠኞች ሳንቀር ስንቸገር ይታያል።
ለአስራ ሁለት አመታት የኢትዮጵያ ደራሲዎች ማኅበርን በሊቀ-መንበርነት የመሩት ማሞ ከደራሲና ጋዜጠኝነትም በላይ የሚዲያ ተቋም እስከ ማደራጀት ድረስ የዘለቀ አቅም የነበራቸው ሰው ነበሩ። ከዚሁ አኳያም፣ በአንድ ወቅት ”አዲስ ዘመን እያለሁም የፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ጄነራል ጽጌ ዲቡ ለንጉሱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ፖሊስና እርምጃው ጋዜጣን እንዳቋቁም ታዘዝኩ።” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በኤርትራ ክፍለ ሀገር ፕሬስ መምሪያን እንዲያቋቁሙ ወደ አስመራም መላካቸውን መናገራቸውም ይታወሳል።
የሃይማኖት ኮሚቴ ውስጥ በመሳተፍ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላምን ለማምጣት ጥረት ካደረጉት ጎምቱዎች መካከል አንዱ የሆኑት ማሞ ውድነህ በስራዎቻቸው ሁሉ ማለት በሚባል ደረጃ ለአገርና ሕዝብ አንድነት ልዩ ትኩረትን ሰጥተው ይሰሩ (ይደርሱ) የነበረ ሲሆን፤ እሱም ስለማህበራዊ ኖሮ (ለማህበራዊነት)፣ ስለአብሮነት፤ ስለመረዳዳት፤ በተለይም በማህበረ-ባህላዊ እሴቶች ላይ ሲሰሩ የነበር።
ማሞ ከላይ በጠቀስንላቸው የትኩረት ነጥቦች ላይ በሚገባ ብዕራቸውን የሰነዘሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ሥነ ጽሑፋዊ ምርቶቻቸውም መካከል “እድርተኞቹ”፣ “እቁብተኞቹ፣” “ማህበርተኞቹ” … የሚሉት ቀዳሚ ተጠቃሾች፤ ከሌሎቹም በብዛት የሚታወቁላቸው ናቸው።
በእስከዛሬው የአገራችን የድርሰትና ጸሐፍት ዓለም ውስጥ ማንም ደራሲ የማሞ ውድነህን ያህል ለማህበረ-ባህላዊ እሴት ልዩ ትኩረትን ሰጥቶ ስራዎቹን ለንባብ ያበቃ ደራሲ ይህ ጸሐፊ አያውቅም፤ ነካ ጣል ነካ ጣል ካልሆነ በስተቀር። ይህም፣ ከላይ እንዳልነው ማሞን ከሌሎች ለየት ይሉ ዘንድ ያስገድዳልና ዛሬ እዚህ ስለመነሳታቸው፤ በተደጋጋሚው ስለመዘከራቸው አንዱ ምክንያት ነው። በተለይ፣ በዚህ በአሁኑ፣ ሁሉ ነገር ችግር ባለበት ዘመን፣ እነዚህ ሶስት መጻሕፍት ተደግመውና ተደጋግመው ሊነበቡ የሚገባቸው መሆናቸውን ሳይጠቅሱ ማለፍ ሀላፊነትን መዘንጋት ነው የሚሆነውና ሶስቱ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ አንጡራ እሴትና አገር በቀል እውቀት ላይ የተመሰረቱ ድርሰቶች ማህበረ-ባህላዊ ፋይዳቸው እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
እዚህ ላይ ከርእሶቹ ጀምሮ፣ ልዩ ትኩረትን ለ“እቁብ” እና “እቁብተኞች”፤ ለ“ማህበር” እና “ማህበርተኞች”፤ “እድር” እና “እድርተኞች”… መስጠት ማለት፣ በተለይም ጉዳዩን ከሥነሰብእና ሥነማህበረሰብ (ሶሺዮሎጂ፣ እና አንትርፖሎጂ) አኳያ ለተመለከተው ማሞ ምን ያህል ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን እንደ ሕዝብና ማህበረሰብ እንቀጥል ዘንድ ዋልታና ካስማ በመሆን የያዙንን መሰረታዊያን በሚገባ እንደለዩዋቸው የሚያሳይ ነው። በተለይም፣ ከላይ በርእስ እና ርእሰ-ጉዳይነት ይዘው በስፋት የሄዱባቸው እነዚህ ሶስቱ ሰበነክ (ሂዩማኒስቲክ) ጉዳዮች አንዱን ከአንዱ መለየት በማይቻልበት ደረጃ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ምን ያህል የህልውናችን መሰረት እንደሆኑ፤ የአብሮነታችን ማሰሪያ ገመድ፤ ከሁሉም በላይ የአንድ ኢትዮጵያዊነታችን መለያ እንደሆኑ መገንዘብ የሚቻል ብቻ ሳይሆን፤ ማሞ ምን ያህል ከጊዜ ቀድሞ የማየት አቅም እንዳላቸው ሁሉ ያሳያልና ሰውየው የዋዛ አልነበሩም፤ ውለታቸውም እንደዛው።
በእነዚህ ሶስት ስራዎች ውስጥ አብሮነት በሚገባ ተንፀባርቋል። የመተጋገዝና መረዳዳት አስፈላጊነት ሊገባን በሚችል ሁኔታ ተብራርቷል፤ እቁብ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ በራሱ መንገድ ተዘርዝሯል። ሀዘንን መካፈልና ሥነልቦናዊ ፈይዳው (በተለይ ለሀዘንተኛው) በቀላሉ የሚታይ አይደለምና የማሞ እነዚህን የማህበረሰብ ምሰሶዎች ቀድመው ማየታቸው፤ አይተውም በማህበረሰቡ ውስጥ ይሰርፁ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፉ ዘንድ … በሶስቱና እራስ ራሳቸውን በቻሉ መጻሕፍት የሄዱበት ርቀት፣ በተለይ ዛሬ ላይ ሆኖ እነዚህ የማህበረሰብ ምሰሶዎች እየላሉ መሄዳቸውን ለተመለከተ የማሞ አስቀድሞ የማየት ችሎታን እንድናደንቅ ያደርጋልና ደራሲው በችሎታቸውም፤ በውለታቸውም ሊደነቁ ይገባል። (በተለይም እነዚህን ስራዎች ከአገርም ሆነ አገረ መንግሥት ግንባታ፤ ትውልድ ቀረፃ፤ እሴት ተከላ … አኳያ ለተመለከታቸው ፋይዳቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።)
ጉዳዩን መሰረት ለማስያዝ በማሰብ ወደ መስኩ ምሁራን ይዘነው ብቅ ብለን ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ (Urban Anthropology) ዶክትሬት (ፒኤች.ዲ) ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ ወደሚገኙትና በሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህር ወደ ሆኑት አቶ ብሩክ ሽፈራው ዘንድ በመሄድ ጉዳዩን እንዲያብራሩልን ጠየቅናቸው። እሳቸውም፤
ደራሲ ማሞ ውድነህ ያነሷቸው ጉዳዮች እንደኛ ላለ ማህበረሰብ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች፣ ማህበራዊ ድርጅቶች (Social organizations) ናቸው። መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት ለግለሰቡም ይሁን ለአካባቢው ማህበረሰብ በማይደርሱበት ሁኔታ ሁሉ የሚደርሱለት እነዚህ ተቋማት ናቸው። የሬሳ ሳጥን የሚገዛው እኮ እድር እንጂ መንግሥት አይደለም። እነዚህ ተቋማት ፋይዳቸው ብዙ ነው። አብሮነትን፣ መረዳዳትና መተሳሰብን፣ ሃሳብና መረጃ መለዋወጥን፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበትን ወዘተ ብቻ ልንመለከት እንችል ይሆናል፤ ግን የእነዚህ ማህበራዊ ተቋማት ፋይዳ ከእነዚህም ያለፈ ነው። አጥፊን የመመለስ፣ የአባላትን ብልሹ አካሄድና ባህርይ (ካለ) የማረም፤ በችግር ጊዜ እርስ በእርስ ዋስ የመሆን፤ እርስ በእርስ የመተማመን መሰረቶች፤ ለክፉ ቀን ፈጥነው ደራሽ፤ የማህበራዊ ቁጥጥር (Social control) ተግባራትን የሚወጡ፤ የግጭት አፈታትም ሆነ መፍታት አቅማቸው ጠንካራ የሆኑ … ተቋማት ናቸው። በመሆኑም በቀላሉ የሚታዩ ሳይሆኑ፣ መልካም ትውልድን ከመፍጠርና አገር ከመገንባት አኳያ ሁሉ ታይተው፣ ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ወሳኝ ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊ … ተቋማት ናቸው። በማለት ነበር የመለሱልን።
እዚህ ላይ እነዚህ ሶስቱን የማህበረሰብ አብሮነትንና የጋራ ህልውናን ከማፅናት አኳያ ጠበቅ አድርገን ያዝናቸው እንጂ ማሞ ከፍ ብለን ከጠቀስናቸው የመጀመሪያዎቹ አስር ስራዎች ቀጥሎ ያሉት ሌሎች አስሮቹም (የደቡብ ሱዳን ብጥብጥ፣ ብዕር እንደዋዛ፣ ሞንትጐመሪ፣ የኤርትራ ታሪክ፣ የኛው ሰው በደማስቆ፣ የ፪ ዓለም ሰላይ፣ ምጽአት-እሥራኤል፣ ሰላዩ ሬሳ፣ የ፲፯ቱ ቀን ጦርነት፣ እና የካይሮ ጆሮ ጠቢ) ማህበረሰብን ከማንቃት፣ ማስተማርና ማሳወቅ ላይ ያልተመሰረቱ አይደሉም። ይህ ደግሞ አንዱ የሥነጽሑፍ አላማ ነውና ማሞን ያስመሰግኗቸዋል።
ከድርሰት ስራዎቻቸው ጎን ለጎን ስምንት ትያትሮችን ለመድረክ ያበቁት ማሞ ውድነህ በትርጉም ስራዎቻቸውም አንቱ የተባሉ ሲሆን፤ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት፣ ሾተላዩ ሰላይ፣ የካይሮው ጆሮ ጠቢ ወዘተ እና ሌሎችም የተርጓሚነት ጥጋቸውን የሚያሳዩ ናቸው። በተለይ ምንም በሌለበት፣ በዚያ በ“ጨለማ ዘመን” የአገራቸው ሕዝብ፣ (በተለይ አንባቢው) በውጭው ዓለም ምን እየተደረገ እንደሆነ፣ የስልጣኔያቸው፣ የተንኮላቸው፣ የአኗኗራቸው … ሁኔታ ምን እንደሚመስል እንዲረዳ፤ በአይነ ልቦናውም እንዲመለከት፤ በእግረ ልቦናውም ወደዚያው እንዲያመራ ምን ያህል በድርሰቶቻቸው ይለፉ እንደነበር የትርጉም ስራዎቻቸው ራሳቸው ይናገራሉ። በበርካቶች ዘንድም ማሞ ውድነህ ሳይታክትና በተከታታይ ጸሐፊነቱ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ አይን ገላጭ ነው መባላቸውንም እዚህ ሊነሳላቸው የግድ ይላል። (በነገራችን ላይ፣ የሊዮን ዮሪስ “ኤክሶደስ” ወደ አማርኛ ከመለሱ በኋላ ርእሱን በተመለከተ 300 ምሁራንን በ“ምን ልበለው?” ዙሪያ ማነጋገራቸውን፤ በመጨረሻም “ምጽአተ-እስራኤል” የሚለው ማለፉን ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? ይህ ራሱ አንዱ የማሞ ልዩ መለያ ነውና አርአያነቱ የሚደነቅ ነው።)
ከእነዚህ ቀጥለው ያሉት 20ዎቹም (የበረሃው ተኰላ፣ ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ፣ ጊለን-የክፍለ ዘመኑ ሰላይ፣ የኦዲሣ ማኅደር፣ ከታተኞቹ፣ ከሕይወት በኋላ ሕይወት፣ ስለላና ሰላዮች፣ ምርጥ ምርጥ ሰላዮች፣ ዕቁብተኞቹ፣ አሉላ አባነጋ፣ የሰላዩ ካሜራ፣ ሰላይ ነኝ፣ በዘመናችን ከታወቁ ሰዎች፣ ዕድርተኞቹ፣ ሾተላዩ ሰላይ፣ ማኅበርተኞቹ፣ በረመዳን ዋዜማ፣ የበረሃው ማዕበል፣ ኬ.ጂ.ቢ.፣ ሲ.አይ.ኤና ጥልፍልፍ) ሲሆኑ፤ ሁሉም ከላይ የጠቀስነውን የደራሲውንና የሥነጽሑፍ ዓላማ የሳቱ አልነበሩም።
የወይዘሮ አልማዝ ገብሩ ባለቤት፣ የሶስት ሴቶችና የሶስት ወንዶች ልጆች አባት የሆኑት ማሞ በሰፋፊና ተንታኝ የጋዜጦች ላይ ጽሑፎቻቸውም ይታወቃሉ። በቀይ ባህር ጉዳይ፣ በግብፅና አጠቃላይ የአረቡ ዓለም ፖለቲካ፣ ስለ አፍሪካ ቀንድ፣ በሰሜኑ የአገራችን የተዛባ ታሪክ አረዳድ ዙሪያ፣ በወራሪ የውጭ መንግስታት ምክንያት በኢትዮጵያ በተካሄዱ ጦርነቶችና በኢትዮጵያ የድል የበላይነት መጠናቀቃቸውን … በተመለከተ ሳያሰልሱ የጻፉ ቋሚ አምደኛ ነበሩና በዚህም ለአሁኑና ለመጪውም የመረጃ ምንጭ የሆኑ ስራዎችን ትተው ማለፋቸው ሌላው የባለውለታነታቸው ጥግና ገፅታ ነው።
መቼም ማሞ ጎልተው የሚታወቁበት ዋናው ዘርፍ ሥነጽሑፍ ነውና ስለ ባለውለታነታቸው ማረጋገጫዎቹ ከላይ የጠቀስናቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ስራዎቻቸውም (የበረሃው ተኰላ፣ ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ፣ ጊለን-የክፍለ ዘመኑ ሰላይ፣ የኦዲሣ ማኅደር፣ ከታተኞቹ፣ ከሕይወት በኋላ ሕይወት፣ ስለላና ሰላዮች፣ ምርጥ ምርጥ ሰላዮች፣ ዕቁብተኞቹ፣ አሉላ አባነጋ፣ የሰላዩ ካሜራ፣ ሰላይ ነኝ፣ በዘመናችን ከታወቁ ሰዎች፣ ዕድርተኞቹ፣ ሾተላዩ ሰላይ፣ ማኅበርተኞቹ፣ በረመዳን ውዜማ፣ የበረሃው ማዕበል፣ ኬ.ጂ.ቢ.፣ ሲ.አይ.ኤና ጥልፍልፍ ሲሆኑ፣ ዩፎስ-በሪራ ዲስኮች፣ መጭው ጊዜ፣ ዮሐንስ፣ የአሮጊት አውታታ፣ እኔና እኔ፣ ኤርትራና ኤርትራውያን፣ ሞት የመጨረሻ ነውን?፣ የደረስኩበት-፩፣ የደረስኩበት-፪፣ ….) ናቸውና ማሞ ከትውልዳቸውም ባለፈ ለመጪዎቹ ሁሉ የተረፉ ስለመሆናቸው፤ ስለ አገርና ወገን፤ ባህልና ታሪክ … ስላላቸው አቋም አንባቢ ከስራዎቻቸው ሊገነዘብ ይችላል።
የካቲት ተወልደው የካቲት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ማሞን ልዩ ከሚያደርጓቸው ማንነቶች አንዱ የእድሜ ልክ ጸሐፊነታቸው ሲሆን፤ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሲጽፉ ኖረዋል። ይህም በራሱ የጥንካሬአቸው ማሳያ ነውና እውነትም ማሞ ብርቱ ነበሩ። (በነገራችን ላይ የካቲት ወር ካበረከተልን ፍሬዎች መካከል ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጐበኛ፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፣ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ማሞ ውድነህ …. እንደሚገኙ ያውቃሉ?)
የʻአምስት ዓይናው’ ማሞ ውድነህ አስከሬን፣ እንደሳቸው በሥነጽሑፍ ምርታቸው፤ በታሪክ ተመራማሪነትና ተርጓሚነታቸው … የባለውለታነት ማማውን በተቆጣጠሩት የአገር ባለውለታዎች፣ ከደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁና ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን መካነ መቃብር አጠገብ ያረፈ ሲሆን፤ በተለይም የህብረተሰቡን “እጅ ይዘው” ወደ ንባብ በማስገባት በኩል የማሞ ውድነህ ስራዎች ተወዳዳሪ እንደ ሌላቸው በስራዎቻቸው ላይ ፍተሻን ያደረጉ ሲመሰክሩላቸው ይሰማልና ይህንንም ከስራዎቻቸው ጎን ለጎን እንደ አንድ አገራዊ ውለታ፤ ትውልድ የመገንባትና የመቅረፅ፤ አንባቢ ትውልድ የመፍጠር ሀላፊነታቸውን እንደተወጡ ያሳያል።
ህልፈተ ሕይወታቸው በተሰማ ሰሞን “ሶል” የተባሉ አድናቂያቸው “ንባብን የወደድኩት በእሳቸው የስለላ (espionage) መጻሕፍት ነበር። ምኑ ተጠቅሶ ያልቃል። ፊልድ ማርሻል ሮሜል በየበረሀው ተኩላ”፤ “የእኛ ሰው በደማስቆ”፤ “ሰላዩ ሬሳ” … ኧረ ስንቱ፤ “ሳይላክ የቀረ ደብዳቤ” አይረሳኝም። እንዴ፣ ደብዳቤው ቢደርስስ ኖሮ? ማሞ በመጽሐፋቸው ፍፃሜአቸውን በአሳዛኝ አደረጉብን ያልናቸው ሁሉ ሮሜልን ሳላውቀው በመጽሐፉ ላይ አዝኜለት ነበር። አይ ልጅነት። አባታችን፣ ነፍሶን በገነት ያኑርልን።” በማለት ሀዘናቸውን መግለፃቸው ጎን ለጎን አንባቢ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ የተወጡትን ሃላፊነት የመሰከሩላቸውን እዚህ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።
“ዲግሪ ያሳበደው፣ የስድስቱ ቀን ጦርነት፣ ካርቱም ሄዶ ቀረ፣ ጊለን የክፍለ ዘመኑ ሰላይ፣ ምጽአተ እስራኤል፣ የኛ ሰው በደማስቆ፣ የበረሐው ተኩላ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ የካይሮው ጆሮ ጠቢ፣ ብዕር እንደዋዛ … የተሰኙትን መጻሕፍት በእጅ ይዞ መታየት ምንኛ ክብር እንደነበረ ማን ይዘነጋል?” የሚለውንና በethiopianchurch.org ላይ ሰፍሮ የሚገኘውንም አስተያየት ከዚሁ ጋር በተያያዥነት ማንሳት ይቻላል።
ደራሲውና ጋዜጠኛው ሁለገብ በመሆናቸው የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ ከነፊታውራሪ አመዴ ለማ ጋር በመሆን ያገለገሉት፤ የዶጋሌ ጦርነት 100ኛ ዓመት መታሰቢያም ስለ ጀግናው አሉላ አባ ነጋ የፃፉትን ታሪካዊ መጽሐፍ ያበረከቱት፤ የዓድዋ ድል 116ኛ ዓመት በሚከበርበት ማለዳ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፤ ለድርስት ያላቸውን ልዩ ቦታ፣ ክብርና ፍቅር “ድርሰት የመጀመሪያ ሚስቴ (ባለቤቴ) ነች። ወይዘሮ አልማዝ ሁለተኛ ሚስቴ ነች” ብቻ ሳይሆን፤ “ሁለተኛዋ ባለቤቴ የመጀመሪያ ባለቤቴን አጥብቃ ነው የምትወዳት፤ የምታከብራትም” በሚለው ለየት ያለ አገላለፃቸውም ይታወቃሉ።
በመጨረሻም ማሞ ውድነህ ታመው አልጋ ላይ በዋሉበት ወቅት ጋሽ ስብሀት ገብረእግዚአብሔርም ታሞ ሆስፒታል ነበርና “… እኔም አሞኛል፤ አንተም አሞሀል። ሁለታችንንም እግዚአብሔር ይማረን . . .” በማለት የጻፈላቸው ደብዳቤ ሳይደርሳቸው ሁለቱም ማረፋቸውን በወቅቱ ጥበቡ በለጠ መዘገቡን ጠቅሰን እንሰናበት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014