ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያለው የተማረና ያልተማረ ወጣት የሚገኝባት ሀገር ናት። ይህ የሕዝብ ቁጥር መብዛት ታዲያ አንድም እንደ መልካም እድል የሚቆጠር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ስጋት ይታያል ። በርካታ ቁጥር ያለው ትኩስ ኃይል ወደ ሥራ ቢሠማራ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚያሳድግ በመሆኑ እንደመልካም አጋጣሚ ሊቆጠር ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ለዚህ የወጣት ኃይል በበቂ ሁኔታ የሥራ እድል መፍጠር ካልተቻለ በቁጥሩ ልክ ስጋቶች መፈብረካቸው አይቀሬ ነው።
ሀገሪቱ ካላት በርካታ ቁጥር ያለው ወጣት አኳያም ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር በርካታ ሥራ እየተሠራ ነው። ሰፊ የሰው ኃይል ለሥራ የሚያሠማሩ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ፣ ኢንዱስትሪዎች በመላው ሀገሪቱ እንዲስፋፉ መንግሥት ሳያሰልስ እየሠራ ይገኛል። ወጣቱ የተለያየ ስልጠና እንዲያገኝ በማድረግ ረገድም የሚሠሩ ሥራዎች ብዙ ናቸው። በእርግጥ ይህም ቢሆን በመንግሥት ብቻ የሚከናወን አይደለም። የግል ባለሀብቱ የራሱ የወጣቱም ድርሻ ጉልህ ነው። በራሳቸው ሰልጥነውና ሥራ ፈጥረው ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል የከፈቱና ለብዙዎች ሞዴል የሆኑ ወጣቶችም አሉ። ሆኖም ግን ወጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ከዚያም ወጥቶ መሥራትን ይጠይቃል። በተለይ ወጣቱ በራሱ ሥራን እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከምንም በላይ ለችግሩ እልባት ይሰጣል። ይህንን ማድረጉ ደግሞ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል። ወጣቱም ቢሆን በራሱ የሚያደርገው ትግል ወሳኝ ነው።
ስለሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሃሳብ ሲነሳ በብዙዎች ዘንድ ወደ አዕምሮ የሚመጣው በመንግሥት በኩል ለወጣቶች የሚመቻቸው የሥራ እድልና ወጣቶች በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ተጠቃሚ የሚሆኑበት የቢዝነስ አካሄድ ነው። ይሁንና ሥራ ፈጠራ የግድ መንግሥት ባመቻቸው የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆን ብቻ አይደለም። የራስን ቢዝነስ መጀመር ብቻም ሊሆን አይችልም። ከዚያም የላቀ ነው። በግልም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥሮ በመሥራት አዳዲስ ሃሳቦችንና አሠራሮችን በመፍጠር ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወንም ጭምር እንደሚያካትት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በተለይ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ አዳዲስ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ወጣቶች በብዛት እየተቀጠሩ ያሉ በመሆናቸው ተቋማቸውን ፈጠራ በታከለበትና በሁለንተናዊ መልኩ ሊለውጡ ይገባል። ስለ ሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሀሳብ ጠንቅቀው የሚያውቁትም ይህንን ተግባራዊ ሲያደርጉ ነው። ይህንን ተመርኩዞ በቅርቡ የኢንተርፕሪነርሺፕ ኢንስቲትዩት በራሱ ተነሳሽነት በትላልቅ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ወጣቶችና ለሌሎች አንጋፋ ሠራተኞች በሥራ ፈጠራ ፅንሰ-ሃሳብ ዙሪያ ስልጠናዎችን ሰጥቷል።
ስልጠናዎቹ በተለይ ወጣት የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች የእውቀት አድማሳቸውን በማስፋት በተቋማቸው ፈጠራ የታከለባቸውን ሥራዎች እንዲያከናውኑና ተቋማቸውን እንዲለውጡ የሚያግዝ ስለመሆኑ ተነግሯል።
አቶ ቦሩ ሻና በኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የሰለጠነና ፕሮግራም ማናጀር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያ በከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ለሚሠሩ ወጣቶችና ልምድ ላላቸው ሠራተኞች ስልጠና መስጠት የተፈለገበት ዋነኛ ዓላማ አስተሳሰቡ በውስጣቸው ሰርፆ እንዲገባና መንግሥት በኃላፊነት ደረጃ ያሉ ሠራተኞቹ በየመሥሪያ ቤቱ የተቀላጠፈና ኃላፊነትን የወስደ ሥራ እንዲያከናውኑ በመፈለጉ ነው።
ስልጠናው ከተለመደው አሠራር ወጥተው አዳዲስ አሠራሮችን በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት እንዲያመጡና ከችግሮች ፊት እየቀደሙ የማኅበረሰቡን ችግር እየፈቱ እንዲሄዱ የሚያስችልም ጭምር ነው። ከዚህ በፊት ሥራ ፈጠራ በብዛት የሚታወቀው በግል ሴክተር ቢሆንም የአሁኑ ግን አዲስ አሠራር ነው።
ኢንተርፕሪነሺፕ ሲባል ደግሞ ለግል ሴክተር ብቻ የተሰጠ አጀንዳና ቢዝነስ መሥራት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢንተርፕሪነርሺፕ ሁሉም ሰው በተሠማራበት የሥራ መስክ አዳዲስ እሴቶችን ጨምሮ ለሚያገለግለው ኅብረተሰብ በየጊዜው የተሻሻለ አሠራርና ሥራን የሚያመጣበት ነው።
የኢንተርፕሪንሺፕ ፅንሰ ሃሳብ ሰዎች ሥራን በፍቅር እየሠሩና ችግሮችን እየፈቱ ፈጠራን ያማከለ አሠራር እንዲኖር የማድረግ አስተሳሰብ ጭምር ነው። ሰውን በፍቅር የማገልገል፣ ችግሮ ሲፈጠሩ በፍጥነት እየቀረፉ የመሄድና ኃላፊነት እንዲሰማ የሚያደርግም ነው። ከዚህ አንፃር እሴት መጨመር በገንዘብ ብቻ የሚለካ ሳይሆን በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ፈጠራን ያማከለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው።
በዚህ ፅንሰ ሀሳብ ደምበኛም የሚማረርበት ሳይሆን በየጊዜው አዳዲስና የተቀላጠፈ አገልግሎት አግኝቶ የሚረካበት ነው። ከላይኛው አመራር እስከታችኛው እርከን ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችም በዚሁ አስተሳሰብ እንዲቃኙ የሚያስችል ነው።
አቶ ቦሩ እንደሚሉት፤ በሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ እንዲህ አይነቱ ስልጠና ለወጣቶችና ልምድ ላላቸው ሠራተኞች ሲሰጥ የመጀመሪያው ነው። በሀገር ደረጃ እንደስትራቴጂ ተቀምጦ ያለው የግል ሴክተሩ ኢኮኖሚውን እንደሚያነቃቃ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አዲስ የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብ የመንግሥት ሴክተር እንዲሻሻልና ፈጣሪ እንዲሆን በሴክተሩ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚሁ ፅንሰሃሳብ መነሻ መንግሥትም በራሱ ኃላፊነት ወስዶ ለግል ኢንተርፕሪነርሺፕ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ተደርጓል።
የግሉ ሴክተር ለብቻው ውጤታማና ሥራ ፈጣሪ ሊሆን አይችልም። በተመሳሳይ የመንግሥት ሴክተርም የተንዛዛና ብቁ ያልሆነ አገልግሎት መስጠት የለበትምና ይህ የሥራ ፈጣራ ፅንሰሃሳብ በሁለቱም ሴክተሮች ውስጥ መስረፅ ይገባዋል። በተለይ ደግሞ የመንግሥት ሴክተር የሥራ ፈጠራ ፅንሰሃሳብ በገባቸው ሰዎች ሊመራ ይገባል። ከዚህ አንፃር በተለይ ትኩስ ኃይል የሆኑት ወጣቶች ይህ እድል በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።
በአሁኑ ወቅት እየመጣ ያለው ወጣትም ሆነ ጊዜ እየተቀየረ ነው። በተመሳሳይ የዓለም አቀፍ ሁኔታም ተለዋዋጭ ነው። በዚያው ልክ ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገራት ጋር በተለያየ መስክ የምታደርገው ወድድርም ጨምሯል። የዛኑ ያህል ዘርፈ ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችም እያጋጠሙ ይገኛሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ተቋቁሞ ለመሄድ ደግሞ አሁናዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ መሥራት የሚችል የሰው ኃይል መገንባት ያስፈልጋል።
የመንግሥት ሴክተር ውስጥም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውና እምቅ ችሎታን ያነገቡ ነገር ግን በአግባቡ ያልተጠቀሙበት ወጣቶች አሉ። በተመሳሳይ በሚሠሩት ሥራ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠርላቸው አዳዲስ አስተሳሰቦችን የሚፈጥሩ ይኖራሉ። ወጣቶች ይበልጥ ለቴክኖሎጂ ቅርብ በመሆናቸውና አዳዲስ ነገሮችን የመቀበል ችሎታቸው የላቀ በመሆኑ ይህንን እያዩ መጠቀሙ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው።
ዘመኑ በፍጥነት አዳዲስ ነገሮችን በቶሎ የመያዝና ወደውጤት መቀየርን ይፈልጋል። የሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሃሳብም ይህንኑ የሚያቀነቅን ነው። እናም ከዚህ አንፃር ረጅም ዓመታትን የሠሩ ሰዎች ሳይሆኑ ገና በለጋ አዕምሯቸው የሥራውን ዓለም የተቀላቀሉ ወጣቶች አዳዲስ የሥራ ፈጠራዎችን የማምጣት ችሎታ አላቸውና ነገሩን እንዲረዱትና ወደተግባር እንዲገቡበት ማድረግ ከምንም በላይ ያስፈልጋል።
እንደ አቶ ቦሩ ገለፃ፤ የዚህ ሥራ ፈጠራ ፅንሰሃሳብ ስልጠና መጀመር በተለይ በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ችሎታ በማውጣት እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። ተቀጥረው ሲሠሩ ራሳቸውን በማየት የራሳቸውን ቢዝነስ ለመጀመርም በር ይከፍትላቸዋል። በተጨማሪም የፐብሊክ ሴክተር በጣም የታጨቀና አብዛኛው ሠራተኛም ከአቅም በታች እየሠራ ያለ በመሆኑ በዚህ የሥራ ፈጠራ ፅንሰሃሳብ አስተሳሰብ ወጣቶች አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል።
ደምበኛውም የተቀላጠፈና እርካታ ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርጋል። ከዚህ ባለፈ ወጣቶቹ የራሳቸውን ቢዝነስ ለመጀመርም እንደመንደርደሪያ ስለሚሆን ስልጠናው እንደመልካም አጋጣሚ ይቆጠራል።
የስልጠናው ፕሮግራም የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብን በፐብሊክ ሰርቪስ ሴክተሩ አገልጋዮች ውስጥ የማስረፅ ዓላማን ብቻ የያዘ አይደለም። ይልቁንም ሠራተኛው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን፣ ጠንካራ የሥራ ባህልን እንዲያዳብርና በዚሁ ደረጃ ሀገሪቱን እንዲመራት ማድረግም ጭምር ነው።
ጽንሰ ሀሳቡ በግሉ ሴክተር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ፕሮግራም አንዱ ነው። በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁና እየተመረቁ ያሉ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብ እንዲኖራቸውና በዚሁ ልክ እንዲሠሩ ከዩኒቨርሰቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም እየተሠራ ይገኛል።
ወጣቶች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ችሎታ ማውጣት እንዲችሉ የኢንተርፕሪነርሺፕ ስልጠና ፕሮግራሞች ይዘጋጃሉ። በሥራ ፈጠራ ዙሪያ በወጣቶች መካከል ውድድሮችም ይካሄዳሉ። በዚህ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችም በኢንስቲትዩቱ በኩል ይሰጣሉ። ወጣቱን ጨምሮ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው የሥራ ፈጠራ ፅንሰ ሃሳብን እንዲጎለብት በኢንስቲትዩቱ በኩል የተጀመረው ተግባር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሥራ ፈጠራ ውጤት እንዲጨምር ያደርጋል።
ሰዎች በሚሠሩባቸው የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ኃላፊነት ወስደው ሌላ አካል ከውጪ ይጠይቀኛል ብለው ሳይጠብቁ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያስችላቸዋል። ይህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚጨምረው እሴት ይኖራል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በብዙ ቁጥር ደግሞ ፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ ያለው ሥራና አሠራሮቹ በየዓመቱ እየተሻሻለና እየተቀላጠፈ ይሄዳል። ይህም የተደሰተና የለማ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ተገልጋዮች ችግራቸውን አይቶ መፍትሔ ሰጪ ትውልድ እንዲያገኙ ያግዛል። በተመሳሳይ በመንግሥት ሴክተር ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በተለይ ለግሉ ዘርፍ ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ትልቁን ኃላፊነት መንግሥት ይወስዳል። የድህነትና የሥራ አጥነት ችግርን በመቅረፍ ረገድም ሚናው የጎላ ነው።
አሁን ላይ የሚታየውን የውጪ ምንዛሪ እጥረትን መቅረፍ የሚቻለውም የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴዎች በብዛት ሀገሪቱ ላይ ሲኖሩ ነው። የሥራ ፈጣሪዎች ቁጥር ሲበዛ ደግሞ ምርታማነት ይጨምራል፤ የሀገሪቱ ዓመታዊ የተጣራ ምርት በየዘርፉ ይሰፋልም። ከዚህ ባለፈ ሥራ አጥነት ይቀንሳል። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ መተካትና የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ማዳን ያስችላል። እንዲሁም ወደ ተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ኢንተርፕራይዞች ይበዛሉ። ይህ ደግሞ አሁን የሚታየውን የውጪ ምንዛሪ ችግርን ያሻሽለዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱ ተወዳዳሪነትም ከፍ እንዲል ያደርጋል።
የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት በቅርቡ ባዘጋጀው የሁለት ዙር የሥራ ፈጠራ ስልጠና ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር በተደረገ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት 60 የሚሆኑ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙና በተለያዩ የሥራ ዕርከኖች ላይ የሚገኙ ወጣት ሠራተኞች ተሳትፈውበታል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2014