ልጆች እንደምን ከርማችኋል ደህና ናችሁ ወቅቱ የሙከራ ፈተናዎች እየተሰጡበት ያለ ከመሆኑ አንጻር ፈተና እንዴት ነበር፤ እርግጠኛ ነኝ በጥሩ ሁኔታ ፈተናውን ሰርታችኋል። ደከም ያላችሁበት የትምህርት ዓይነት ካለ ደግሞ ለቀጣዩ በደንብ በማጥናት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ስሩ እሺ።
ልጆች ዛሬ ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሳነብ ካገኘሁት ላይ አንድ በሰሜን ወሎ ክልል ያለ ባለተሰጥዖና ጎበዝ ተማሪ የሆነ ታዳጊ ልጅ አስተዋውቃችኋለሁ።
ስሙ ህጻን ሳሙኤል ዳርጌ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በሰሜን ወሎ ዞን ራያና ቆቦ ወረዳ በሮቢት ከተማ ነው። እድሜው 12 ዓመት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የ9ነኛ ክፍል ተማሪ ነው። ይህ ደግሞ በጣም አስገራሚ ነው። ልጆች ህጻን ሳሙኤል ትምህርት የጀመረው በ4 ዓመቱ ሲሆን የትምህርት አቀባበሉ በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ በ7 ዓመቱ ስድስተኛ ክፍልን ሊያጠናቅቀ ችሏል። ይህ እንግዲህ በአንድ አመት ሁለት የክፍል ደረጃዎችን አጠናቋል እንደማለት ነው ።
ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ግን የትምህርት ቤቱ መመህራን ልጁ በጣም ህፃን ከመሆኑ የተነሳ በክፍሉ ካሉ ተማሪዎች ጋር በአካል መመጣጠን እንደማይችል ከዚህ በኋላ በአመት አንድ ክፍል ብቻ መማር እንዳለበት ወሰኑ። ልጆች መምህራኑ ይህንን ውሳኔ ባያሳልፉ ኖሮ ህፃን ሳሙኤል በ12 ዓመቱ 11ኛ ክፍል ላይ ነበር የምናገኘው።
ልጆች ህጻን ሳሙኤል 7 እና 8ተኛ ክፍልን ሲማር ከመላው ክፍል (ሴክሽን) አንደኛ በመውጣት ነበር ያጠናቀቀው። ህጻን ሳሙኤል ትምህርትን አብዝቶ የሚወድ ብዙ ጊዜውንም በጥናት የሚያሳልፍ ቢሆንም ከትምህርት ጊዜና ከጥናት ውጪ ደግሞ የተለያዩ ነገሮችን ለእናትና ለአባቱ ያደርጋል። ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከልም እናትና አባቱ የመንግስት ሰራተኞች በመሆናቸው ለስራ ውጤታማነት የሚያግዟቸውን እቅዶች ያወጣላቸዋል። በእቅዶቹ ላይ ማብራሪያ ይሰጣቸዋል እንዴት አድርገው ቢሰሩም ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያማክራቸዋል። በዚህም በስራ አፈጻጸማቸው በጣም ውጤታማ ናቸው ይላል ስለ ህጻን ሳሙኤል በማህበራዊ ሚዲያው የተገለጸው መረጃ።
ህጻን ሳሙኤል ከትምህርት ውጪ ያሉ መጻህፍትንም በማንበብ በኩል ጥሩ ልምድ አለው ለምሳሌ በዶክተር ሮዳስ ታደሰ የተዘጋጀውን አንድሮሜዳ መጽሃፍ ለማንበብ የፈጀበት ሁለት ቀናት ብቻ ነው። ህጻን ሳሙኤል አድጎ መሆን የሚፈልገውም የስነ -ፈለግ ተመራማሪ ነው። ምኞቱ እንዲሳካለትም እንመኛለን።
ልጆች እናንተም በትምህርታችህ ውጤታማ እንድትሆኑ ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙ ፊልምና ሌሎች መዝናናቶችን ቀንሳችሁ ማንበብ ላይ ትኩረታችሁን አድርጉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም