በኢትዮጵያ ሁለተኛው የፍጥነት መንገድ ከሞጆ ተነስቶ፣ መቂ፣ ባቱና አርሲ ነጌሌን ታኮ ሀዋሳ ይደርሳል። ይህ ፕሮጀክት በአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ላይ የራሱ የሆነ አወንታዊ ውጤት ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። 202 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ግንባታ ከሞጆ – መቂ፣ ከመቂ – ባቱ፣ ከባቱ – አርሲ ነጌሌ፣ ከአርሲ ነጌሌ – ሀዋሳ በሚል በአራት ኮንትራቶች የተከፈለ ነው።
ግንባታው በ2008 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ ሲጀመር በ2013 ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ግብ ተቀምጦለት ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ አልቻለም። የመንገዱ አካል የሆኑት ክፍል አንድ ሞጆ – መቂ እና ክፍል ሁለት መቂ – ባቱ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ይታወቃል። ክፍል ሶስት ባቱ – አርሲ ነጌሌ 57 ኪሎ ሜትር እና ክፍል አራት የአርሲ ነጌሌ – ሀዋሳ 52 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል። የሞጆ ሀዋሳ የመንገድ ፕሮጀክት በአጠቃላይ እና አርሲ ነጌሌ ሀዋሳ ፕሮጀክት በተለይ ዘመኑ የደረሰበት የመንገድ ግንባታ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ የተደረገበት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
የፕሮጀክቱ አራተኛው ክፍል የሆነው የአርሲ ነጌሌ – ሀዋሳ የመንገድ ፕሮጀክት በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እየተገነባ ያለ ሲሆን፤ የማማከር ስራውን ደግሞ ቤጂንግ ኤክፕሬስዌይ ሱፐርቪዥን እና ውሃን ጂኦክ ኢንጂነሪንግ ኮንሰልተንሲ የተሰኙ ድርጅቶች በጋራ እየተገበሩት ይገኛሉ።
መንገዱን ለመገንባት የሚውለው ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት እና በቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የሚሸፈን ነው። ከመንገዱ አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 85 በመቶ በቻይናው ኤግዚም ባንክ የሚሸፈን ሲሆን፣ 15 በመቶ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው። መንገዱ 31 ነጥብ 6 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባ ነው።
ግንባታው በቅርቡ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክት አመራሮችና ሠራተኞች ትምህርታዊ ጉብኝት ተደርጎበታል:: የአርሲ ነጌሌ – ሀዋሳ የመንገድ ፕሮጀክት ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ የመንገድ ግንባታው ዘርፍ አሁን የደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ የተደረገበት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፕሮጀክቱን የጎበኙት የአስተዳደሩ ባለሙያዎች እና አመራሮች እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱን እየገነባ የሚገኘው ድርጅት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንገድ ግንባታውን እያከናወነ መሆኑን ተመልክተዋል። ፕሮጀክቱ በሌሎች ፕሮጀክቶች ለተሰማሩት የፕሮጀክት አመራሮችና ሰራተኞች አዲስ እውቀት ያስጨብጣል።
ጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል ኢንጂነር ቤዛዊት ግርማ አንዷ ናት። ኢንጂነሯ በመንገድ አስተዳደሩ የጥናት ቡድን ውስጥ ትሰራለች፡፡ ፕሮጀክቱ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተተገበረበት መሆኑን መመልከቷን ትናገራለች። የአርሲ ነጌሌ ሀዋሳ የመንገድ ግንባታ በታላቁ የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚካሄድ ነው። የሻላ እና ሀዋሳ-ሀይቆችን ጨምሮ በአካባቢው በርካታ ሀይቆች የሚገኝበት ነው። በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች ለግንባታ አመቺ ያልሆኑ ጂኦሎጂካል ክስተቶች ይስተዋልባቸዋል። በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ አፈር ለመደርመስና ለመሰንጠቅ ተጋላጭ ነው። በዚህ አካባቢ የሚገኝ መሬት ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ሲያገኘው የመደርመስ ባህሪይ አለው።
እንዲህ አይነት አፈር ላይ የሚሰሩ ግንባታዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። ይህንን ችግር ለመለየት እና በቅድሚያ ለመከላከል ተቋራጩ የተጠቀመው ቴክኖሎጂ በመንገድ ግንባታው ዘርፍ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ አመላካች መሆኑን መመልከቷን ነው ኢንጂነር ቤዛዊት ያመለከተችው።
የፕሮጀክቱ ትግበራ ከመጀመሩ አስቀድሞ መልክአ ምድራዊ ካርታ እና ሳይት ምርመራን መሰረት በማድረግ የፕሮጀክቱ ግንባታ በሚካሄድበት ክልል ውስጥ የሚገኙ አስቸጋሪ ቦታዎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል። በልየታ ሂደት ረግረጋማ አካባቢዎች ተገኝተዋል፤ ተቋራጩ በእነዚህ ረግራጋማ እና ለግንባታ አመቺ ባልሆኑ አካባቢዎች በተገኙ መረጃዎች ዙሪያ ተጨማሪ ጥናቶች እንዲካሄዱ ቻይና ድረስ በመላክ በመረጃው ላይ ተጨማሪ ምርመራ መካሄዱን በትምህርታዊ ጉብኝቱ ወቅት ከተሰጠው ማብራሪያ ኢንጂነሯ ተረድታለች።
እንደ ቤዛዊት ገለጻ ኮንትራክተሩ የምርመራ ውጤቶችን መሰረት በማድረግ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ እና የራዶን ፍተሻዎችን በማድረግ የጂኦሎጂካል ሁኔታዎችን በጥልቀት በመቃኘት ችግሩን ለይቷል። የተለየ ሁኔታ በሚታይባቸው አካባቢዎች ጥልቅ ቁፋሮ እና የጂኦሎጂካል ምርመራዎችን በማካሄድ ችግሮችን ለመለየት ጥረት አድርጓል። ከብዙ ምርመራዎች በኋላ ፕሮጀክቱ በሚገነባባቸው አካባቢዎች ውስጥ በርካታ ሊሰነጠቅ እና ሊደረመስ የሚችል አፈር ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። እነዚህን መረጃዎች መሰረት በማድረግ የተሻለ የግንባታ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ እና አሉታዊ ተጽእኖዎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ወስዷል።
ሊደረመስ የሚችል አፈር የራሱ የሆነ ባህሪያት ያሉት ሲሆን፣ እንደዚህ አይነት አፈር የተለያዩ አደጋዎችንም ሊያስከትል ይችላል፤ በተለይም ግንባታው ከተካሄደ በኋላ መንገዱ የመንሸራተት እድሉ ከፍተኛ ነው። እንዲህ አይነት አፈር ብዙ የተደከመበትን፣ ገንዘብና ጉልበት የወጣበትን ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ከጥቅም ውጪ ሊያደርግ ይችላል። ይህንን ችግር ለመከላከል ተቋራጩ የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰዱን በጉብኝቱ ወቅት መረዳቷን ኢንጂነር ቤዛዊት ትናገራለች።
ከነዚህ የመፍትሄ እርምጃዎች አንዱ ሊደረመስ የሚችለውን አፈር ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ በማድረግ ለግንባታ አመቺ በሆኑ ቁሳቁስ ተተክቷል። ሌላኛው እርምጃ ደግሞ ከላይ ያለውን የመደርመስ ባህሪይ ያለውን አፈር በማንሳት ከስር ያለውን አፈር በሀይል መጠቅጠቅ ነው። በዚህ ግንባታም ተጨማሪ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ሊደረመስ የሚችል አፈር የማስተካከል ስራ ተሰርቷል።
የአፈር መሰንጠቅ መንገዱ በሚገነባበት አካባቢ ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ ነው። በተለይም አርሲ ነጌሌ አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ የመሬት መሰንጠቆች በስፋት ይስተዋላል። እነዚህ ችግሮች በቀጣይ በመንገዱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ አመላካች ነበርናም ችግሩን ለመቀነስ የሚያስችል የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ያስፈልግ ነበር።
እንደነዚህ አይነት ችግሮችን በቅድሚያ ለመከላከል ተቋራጩ የተጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች በቀጣይ በአገራችን በሚካሄዱ የመንገድ ግንባታዎች ጥቅም ላይ ቢውሉ መሰል ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ኢንጂነር ቤዛዊት አብራርታለች። ዘመኑ የደረሰባቸው እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ወደ አገሪቱ መግባታቸው በስራ ላይ ያሉ እና በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡ ተቋራጮች ጥሩ እውቀት እንዲቀስሙ እድል ይፈጥራል።
ግንባታው በሚካሄድበት ገጸ ምድር ላይ ብቻ ሳይሆን ከርሰ ምድር ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ተቋራጩ በቅድሚያ በመለየት ችግሩን ለመቀነስ ከግንባታው አስቀድሞ የመፍትሄ እርምጃ መውሰዱ ለአገር በቀል ተቋራጮች ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው የምትለው ደግሞ ትምህርታዊ ጉብኝቱ ላይ የተሳተፈችው ሌላኛዋ ኢንጂነር ሀያት አለማ ናት። ኢንጂነሯ በከርሰ ምድር ውስጥ የሚከሰቱ ክስተቶችን ለማስቆም ምንም እንኳ ሰው ሰራሽ የምህንድስና እርምጃ ሊወሰድ ባይችልም የአደጋን ኪሳራ ለመቀነስ የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚቻል ተቋራጩ በተግባር አሳይቷል ትላለች።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመዱ ቴክኖሎጂዎች በስራ ላይ ውለው ማየቷን የምትናገረው ሀያት፤ በአገራችን ለመንገድ ስራዎች ትልቁ እንቅፋት እየሆነ ያለው የመሬት መንሸራተት መሆኑን ትጠቅሳለች። ይህ ችግር በሚገነቡ መንገዶች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ተቋራጩ በቅድሚያ ጥናት በማካሄድ ቀድሞ ለችግር ተጋላጭ ሊሆን ይችላሉ ብሎ ባሰባቸው ቦታዎች ላይ ጥናቶችን በማካሄድ መሬት መንሸራተት እና መሰንጠቅ ሊከሰት የሚችልባቸውን ቦታዎች ለመለየት የተጠቀመው ቴክኖሎጂ ለሌሎች ተመሳሳይ ችግር ለሚስተዋልባቸው የመንገድ ግንባታዎችም የሚጠቅም ትልቅ ተሞክሮ ነው። ቴክኖሎጂው መንገዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ከጥቅም ውጪ እንዳይሆን ይረዳል።
ሀያት እንደምትለው ተቋራጩ የሚደረመስ መሬት ለማከም ከተጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች ባሻገር በመንገዱ ላይ የሚገነቡ ድልድዮችን ለመገንባት ዘመኑ የደረሰባቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞባቸዋል። ለድልድይ ግንባታዎችም እንዲሁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀሙ ባሻገር በዝናብ ወቅት ከድልድዮቹ ወደ ውሃ ማፋሰሻዎች የሚገባው ውሃ አካባቢውን በማይበክል እና የድልድዩን ደህንነት በማይጎዳ መልኩ እንዲወገድ የሚያስችል ስራ አከናውኗል። የተለመደው የውሃ ማፍሰሻ ዘዴ ቀጥ ያለ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴ ሲሆን፤ ይህም ለአካባቢ ብክለት መንስኤ ሲሆን ነበር።
እንዲህ አይነት ማፋሰሻዎች የሞጆ ሀዋሳ አይነት የጽዳት ሰራተኞች በሌሉባቸው ረጃጅም መንገዶች ላይ ሲገነቡ ማፋሰሻው በቀላሉ በቆሻሻ ይዘጋል። በድልድዮቹ ላይ ውሃ በመሰብሰብ የድልድዩ ደህንነት ላይ ችግር የሚያስከትል ነው። አሁን የአርሲ ነጌሌ ሀዋሳ ፕሮጀክት ላይ ተግባራዊ የተደረገው ግን ውሃ እንዳይሰበሰብ ብሎም በዚህ ምክንያት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመቀነስ የውሃ ማስወገጃ አቅጣጫ ወደ አግድም እንዲሆን መደረጉን ታነሳለች።
በአጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ በአይነቱ ልዩ ከመሆኑ ባሻገር ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ እስከ ፕሮጀክት ትግበራ ድረስ ዓለም የደረሰበት ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለበት እንደመሆኑ በዘርፉ ለተሰማሩ የፕሮጀክት አመራሮችና ሰራተኞች የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያስገኝ መሆኑን ያብራሩት የአስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች፤ ይህ ፕሮጀክት በሌሎች ፕሮጀክቶች ለተመደቡ አመራሮችና ሰራተኞች አዳዲስ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ የሚያስገኝ መሆኑንም ተናግረዋል። በጉብኝቱ ወቅት ያገኙትን እውቀት፣ ልምድ፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቀጣይ በሚሰሯቸው አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመተግበር የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
በአገራችን በድልድይ ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ የእውቀት ሽግግር በማምጣት በቀጣይ ሌሎች የዓለም አገሮች የደረሱበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ በር የሚከፍት መሆኑን ያስረዱት ባለሙያዎቹ ከተሰማሩት ባሻገር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ግንባታው አካባቢ በመሄድ እውቀት፣ ልምድና ክህሎት እንዲቀስሙ ሊደረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014