ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ ‹‹አንድ የሙስሊም አባት የቀብር ሥነ-ስርአት እየተፈፀመ የቀብር ስነስርአቱን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ድንጋዮች ከአንድ መስጂድ ጎን ካለ ቤተክርስቲያን ተነስተዋል ››በሚል የግለሰቦች ግጭት መፈጠሩና ይህንንም ተከትሎ ግጭቱ ወደ ቡድን ፀብ ተሸጋግሮ የፀጥታ ችግር መከሰቱ ይታወሳል። ከዚሁ የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘም የሰው አካል ጎሏል፣ ነብስ ጠፍቷል ንብረትም ወድሟል።
የዚህ ግጭት ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ዋነኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ታዲያ ወጣቶች በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በተለያዩ ጊዜያትም ወጣቶች የጥፋት ሃይሎች አጀንዳ ማስፈፀሚያ ሆነው ህይወታቸውን ገብረዋል። በተሳሳተ አቅጣጫና በስሜት ተነድተውም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። የጥፋት ሃይሎች ለተመሳሳይ እኩይ አላማቸው ወጣቶችን አሁንም መሳሪያ ማድረጋቸው አይቀርምና ወጣቱ ሃይል ተታሎና በስሜት ተነድቶ ተጨማሪ ዋጋ እንዳይከፍል የብዙዎች ስጋት ነው። ስለዚህ አንድ ድርጊት ሲፈጸም ወይም ሊፈጸም ግርግር ሲታይ ወጣቱ ወደ ጉዳዩ ዘው ብሎ ከመግባቱ በፊት በማን ምን እየተደረገ መሆኑን ሰከን ብሎ ማሰብ፣ ጊዜና ሁኔታዎችን ማገናዘብ፣ ከስሜት ውጪ ሆኖ እያንዳንዱን ጉዳይ ማስላት ይኖርበታል። ሁልጊዜም ወጣትነት ችኩልነት እንደሆነ ይታሰባል። ይሁን እንጂ አሁን አገር ያለችበት ወቅት ደግሞ በስሜት የሚመራበት አይደለም። ረጋ ብሎ ሁሉንም ነገር መመርመር ያስፈልጋል። ለንግግር ቅድሚያ መስጠት ላይ ማተኮርን ይጠይቃል።
የአማራ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ ጌጡ ፤ ወጣቶች ከስሜት በወጣ መልኩ ረጋ ብለው እንዲያስተውሉ ነው የሚመክረው። እርሱ እንደሚለው በጎንደር የተከሰተው የፀጥታ ችግር በሃይማኖት አለመግባባት ምክንያት አይደለም። ለዚህም ማሳያው ከዚህ በፊት የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች በከተማዋ ለረጅም አመታት ተቻችለው መኖራቸው ነው። አንዳቸው ለአንዳቸው እየተጋገዙና እየተደጋገፉ ለረጅም አመታት ዘልቀዋል። የክርስትናም ሆነ እስልምና እምነት ተቋማት እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችም የፀጥታው ችግር በሃይማኖት ምክንያት የተፈጠረ እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።
ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ የተከሰተው የፀጥታ ችግር ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ ድብቅ አላማቸውን የማስፈፀም ፍላጎት ያላቸው የጥፋት ሃይሎች ሴራ ነው። በዚህም መጠነ ሰፊ የፀጥታ ችግር በከተማዋ ተከስቷል። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ውስጣዊ አንድነትን የመሸርሸር አላማም ያላቸው በመሆኑ የከተማዋን ፀጥታ አደፍርሰዋል።
በአሁኑ ጊዜ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በመረዳት ነገሮችን አስታርቆ በፊት የነበረውን አንድነት በይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል የጋራ ጉዳይ ስለሚሆን በዚህ ላይ እንደወጣት ማህበር የሚጠበቁ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከዚህ አኳያ በመጀመሪያ የእነዚህን እምነቶች ነባራዊ ሁኔታና ዳራ ምን እንደሚመስል ለወጣቱ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ለዚህም የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች ከዚህ በፊት በነበሩት የእምነት በአላት ላይ አንዱ በአንዱ በአል ላይ እየተገኘ ሲያደርግ የነበረውን የመረዳዳት የመደጋገፍ እና አብሮ የማክበር ተሳትፎ እንደማሳያ ማንሳት ይቻላል።
ከመጠላላት ይልቅ አንዱ በሌላኛው በአል ላይ ተገኝቶ አንደኛውን ሲደግፍ የነበረበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል። ለአብነትም የጥምቀት በአል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ሲከበር የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች ለክርስትና እምነት ተከታይ ወንድሞቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ ይጠቀሳል። የገና በአል ሲከከበርም የአስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች ድጋፍ ጎልቶ ይታያል።
በተመሳሳይ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢድ አል አረፋ በአል ሲከበር የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ ወጣቶች ድጋፍ ሁሌም አለ። ሌሎች በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበሩ በአላት ላይም ይህ መከባበርና ድጋፍ ይታያል። ይህ ድጋፍ በሁለቱም እምነት ተከታይ ወጣቶች በተለይ በአላቱ ሲከበሩ መንገዶችን በማፅዳትና በሌሎችም ተግባራት ይገለፃል።
ይህ ታዲያ ጠንካራ እሴት በመሆኑ ወደፊትም በዚህ መልኩ መቀጠል እንዳለበትና አብሮ መስራት ያለበት በመሆኑ በዚህ ሰበብ የሁለቱን እምነት ተከታዮች ወንድማማችነት ለማጋጨት እየተሰራ ያለውን ሥራ ማረም እንደሚገባ በመረዳት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። መድረኮችን በማመቻቸት ወጣቶችን የማወያየት ስራዎችም እየተሰሩ ነው። ወጣቶች በሚገኙባቸው የውይይት መድረኮች ላይም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ አመራሮች እንዲገኙም ተደርጓል።
እንደ ወጣት አባይነህ ገለፃ፤ በሁለተኛ ደረጃ ወጣቶች ራሳቸው የመረጃ ምንጭ መሆን ስላለባቸው ነባር የሆነውን የከተማዋን እሴትና መልካም ባህል እንዲጠፋና ከጎንደር አልፎ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች እኩይ ተግባሩ እንዲሰፋ የሚያደርጉ የጥፋት ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታረሙ ወጣቶች በፍጥነት መረጃ እንዲሰጡና አካባቢያቸውን በተደራጀ መንገድ እንዲጠብቁ ስራዎች እየተሰሩ ነው። እንዲህ አይነቱ ድርጊት ዳግም እንዳይከሰትም ከፀጥታ ተቋማት ጋር የጋራ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
የአካባቢን ሰላም የሚያደፈርሱ ችግሮች ሲፈፀሙ ብዙ ጊዜ እርምጃ የሚወሰደው ዘግይቶ እንጂ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አይደለም። ነገር ግን ስራዎች መሰራት ያለባቸው እንዲህ አይነት የፀጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱም ጭምር ነው። አስቀድሞ ችግር ሊከሰትባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን ለይቶ ምን አይነት ሁኔታዎች ይመጣሉ የሚለውን እያሰቡ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱ አንዱ ትምህርት የተወሰደበት ነው። ከዚህ አኳያ ይህንኑ መሰረት በማድረግ በሁሉም አካባቢ ያሉ ወጣቶች በሌሎች አካባቢዎችም እንዲህ አይነቱ ችግር እንዳይፈጠር በተደራጀ መንገድ ይህን ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
የጠላትን አጀንዳ ከማስተጋባትና የውስጣዊ አንድነትን የሚከፋፍል ተግባር ከመስራት ይልቅ አሁን ያሉትን ችግሮች መፍታትና የውስጣዊ አንድነትን ከመቼውም ግዜ በላይ ማጠናከር እንደሚገባ በመረዳት በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም የዞን ወጣቶች ጋር በመግባባት ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋር በመሆን በጋራ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውና ይህ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ለመቆጣጠር በጋራ እየተመከረ ነው።
አጥፊዎችን በሚመለከት አንዱና በመሰረታዊነት መፍትሄ ያመጣል ተብሎ የሚታሰበው በየትኛውም ወገን ያሉ አጥፊ አካላት በጥፋታቸው ልክ ቅጣት ሲያገኙ ነው። ከማህረሰቡ የተደበቀ ነገር የሌለ በመሆኑ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አካላትን ወጣቶች አስቀድመው በመለየት ለሚመለከተው የፀጥታ አካል መረጃ እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ መረጃ ከመስጠት ባሻገር በእያንዳንዱ ከተማ በተለያየ መንገድ ገብተው ድብቅ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የሚሞክሩና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ፀጉረ ልውጦች ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች የሚሰሩትን ስራም በተመሳሳይ ለፀጥታ ተቋማት መረጃ መስጠት እንዳለባቸው በየአካባቢው ላሉ ወጣቶች በማህበሩ በኩል ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው።
ስለሆነም ሰው በሰራው ጥፋት ልክ መጠየቅ አለበት። በዚህም የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ጎንደር ከተማ ላይ የተከሰተው ችግር ወደሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ሰዎች አልተጠየቁም የሚሉ ምክንያቶች እንዳይመጡና የተፈጠረው ችግርም ዳግም እንዳይከሰት ስራዎችን መስራት ተገቢ ይሆናል። የፍትህና የፀጥታ ተቋማትም በዚሁ መንገድ ከወጣቶች ጋር እየሰሩ ነው።
ወጣት አባይነህ እንደሚለው እንዲህ አይነት የፀጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ ወይም እንዳይፈጠሩ መንግስት መስራት አለበት። የደህንት ተቋማትም በተገቢው መንገድ የት ቦታ ምን አይነት ችግር አለ በሚል መረጃዎችን እንዲለዩና የተለዩ መረጃዎች ደግሞ በአግባቡ ክትትል እንዲደረግባቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ችግሩ እንኳን ቢፈጠር ሳይሰፋና ምንም አይነት ጉዳት ሳይፈጠር መቆጣጠር የሚቻልበት እድል መኖር አለበት። ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ማህበረሰቡን በተገቢው ሁኔታ አነቃንቆ በሁለቱም ወገን ያሉ ጥፋተኞች በአግባቡ የሚጠየቁበት አሰራር ሊኖር ይገባል።
ተገቢው የሆነ የተጠያቂነት ስርአት እንዳለ ሆኖ ተጠያቂነቱ እውነታን መሰረት ያደረገና ሌላውንም ህብረተሰብ ሊያስተምር በሚችል መንገድ መሆን ይኖርበታል። ችግር የፈጠሩ አካላት መጠየቅ መቻል አለባቸው። በዚህ ፅንፈኛ ተግባር የተሰማሩ ሰዎችም ከድርጊታቸው መታረም አለባቸው። እንደዚህ አይነት ማህረበረሰብን ከማህረሰብ ፤ እምነትን ከእምነት ጋር ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ትክክለኛ መረጃን መሰረት አድርጎ እርምት መውሰድና ማስተካከል፣ የህግ የበላይነት እንዲኖር ማድረግ እንዲሁም ዜጎች በነፃነት ወጥተው እንዲገቡ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።
እንደ አማራ ክልል ወጣቶች ማህበር አደረጃጀት በርካታ ነገሮች ሲከሰቱ ቀድመው የሚሰለፉት ወጣቶች ናቸው። በተለያዩ ምክንያች በሚከሰቱ ችግሮች ተጎጂ የሚሆኑትም እነዚሁ ወጣቶች ናቸው። ከዚህ አንፃር ወጣቱ ከስሜታዊነት በዘለለ ምክንያታዊነትን ማስቀደም አለበት። ወጣቶች የነገ አገር ተረካቢዎችና መሪዎች ናቸው ሲባል በተደጋጋሚ ቢደመጥም ምክንያታዊ የሆነ ወጣት የዛሬ አገር ተረካቢና መሪ በመሆኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ በተረጋጋና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ችግሮችን በደምብ አጢነው ከመንግስት ጎን በመሆን እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ አለበት።
ወጣቱ ከመንግስት ጎን መሆን አለበት ሲባል ግን ከሁሉም በላይ ሰላም፣ የህግ የበላይነትና የዜጎች ሰብአዊ መብት ስለሚቀድም ይህን ታሳቢ በማድረግ ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ጥፋተኛ የሆነ አካል በሰራው ጥፋት ልክ እንዲቀጣ ወጣቶች ሚዛን ላይ ቆመው መታገል ይኖርባቸዋል።
በጎንደር ከተማ ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ፅንፈኛ አካላትና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ጎንደር ላይ የተፈጠረው ድርጊት ከአማራ ክልል ውጪ በሌሎች አካባቢዎች ባሉ የእምነት ተቋማት ላይም ሌላ ችግር እንዲፈጠር እየተደረገ ያለው ጥረት መታረም ያለበት ድርጊት መሆኑን የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ያምናል።
እንዲህ አይነቱ ድርጊት በጋራ ለመኖር፣ አገራዊ አንድነት አጠናክሮ ለመቀጠል፣ ኢትዮጵያዊነትንም ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ አይደለም። ከዚህ አኳያ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መቀጠል ፅንፈኛ አካላትን፣ ድብቅ አጀንዳ ያላቸውንና ውስጣዊ ወይም አገራዊ አንድነት እንዲሸረሸርና እንዲዳከም የሚሰሩ ሰዎችን አላማ እንደማገዝ ይቆጠራል።
ስለሆነም ነገሮችን ቆም ብሎ ማየትና በየትኛውም መንገድ ለሰው ክብር መጨነቅ ይገባል። እርስ በርስ መከባበር ካለ ደግሞ እምነታቸውም አብሮ ይከበራል። ግጭቱን የኦርቶዶክስና የእስልምና እምነት ተከታዮች አድርጎ መውሰድ፣ ከአንዱ አካባቢ ወደሌላው እንዲስፋፋና እንዲዛመት የማድረግ ድርጊት ሊታረም ይገባል። ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች በጀመሩት መንገድ ህዝባቸውን የማስተማር ስራቸውን አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይ የፀጥታ ተቋማትም ህግን የማስከበር፤ የፍትህ ተቋማትም ተገቢው ፍትህ እንዲሰፍን ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም