አገር ስራዬ ብላ ካፈራቻቸው ማንነቶች፤ ስራዎቻቸው በአግባቡ ለትውልድ ያልተላለፉላቸው ብሔራዊ አርበኞች፣ አቻ የለሽ ጀግኖች ብዙዎች ናቸው። ከጀግኖቹም መካከል ቀዳሚዎች ያሉ ሲሆን አንዱም በ “አይበገሬው ጀነራል”ነቱ (ዶጋሊው ላይ ባስገኘው ድል ምክንያት ያገኘው መጠሪያ ነው) የሚታወቀው፤ ታሪክ ፀሀፊዎቹ እነ በርክሌይ ሳይቀሩ “ከአፄ ቴዎድሮስ ሞቱ በኋላ አቢሲኒያ ያፈራችው ታላቅ መሪ”፤ ባለ ውለታነታቸውም እንደዛው። ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ “Alula, Dogali and Ethiopian Unity” በሚል ጽሁፋቸው “ከአሳዛኙ የአፄ ቴዎድሮስ የመቅደላ ፍፃሜ በፊትም ሆነ በኋላ አፄ ቴዎድሮስን የመሰለ አንድ ሰው ቢኖር አሉላ አባ ነጋ ብቻ ናቸው፡፡” በማለት ምስክርነታቸውን የሰጡላቸው ያሉለት አሉላ አባ ነጋ ናቸው።
ደራሲያ፣ የታሪክ ጸሐፍት፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ስነቃላችን … ስንትና ስንት ጀግኖቻችንን ሲያነሱ፣ ሲያወድሱ፣ ሲያሞግሱና ለትውልድ ሲያቀብሉ የኖሩ (ይህ የሚቀጥል ይሆናል) ሲሆን አንዱና ቀዳሚውም አሉላ እንግዳ (በፈረስ ስማቸው አሉላ አባ ነጋ) ናቸው።
የውጪዎቹ (ጠላቶቻችን ሳይቀሩ) ጥናትና ምርምር አድራጊዎች፣ የፖለቲካል ሳይንስ አጥኚዎች፣ የታሪክ ፈልፋዮች ስለ ስመ ጥር ኢትጵያዊያን ያላነሱት የሌለ ሲሆን፤ አንዱም የቀይ ባህሩ አንበሳ፣ የዶግዓሊው ጦርነት (ጥር 26፣ 1887) ባላምባራስ፣ የራስ አሉላ አባ ነጋ ሕይወትና ስራ ነው። (በዋናነት የሚጠቀሱት ሁለት ዓበይት ጦርነቶች ደግሞ የ1875 የጉንደት እና የ1876 የጉራዕ ጦርነቶች ናቸው፡፡) ለመነሻና ማስታወሻ ያህል የሚከተለኩትን (ከዘሪሁን አበበ ይግዛው የተዋስናቸውን) ሁለት አንቀፆች እንመልከት፤
በ1805 የኦቶማን ቱርክ የግብፅ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው አልባኒያዊው ሙሐመድ ዓሊ ወደ አፍሪካ መምጣት ለብዙ ክስተቶች ምክንያት ሆኗል፡፡ […] ከ1805 እስከ 1849 ስልጣን ላይ የቆየው ሙሐመድ ዓሊ በዋናነት የተሳካለት ግብፅ ራሷን የቻለች እና ከኦቶማን ቱርኮች ነፃ የሆነች አገር መመስረቱ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የኦቶማን ግዛቶች የነበሩ የቀይ ባህር እና የህንድ ውቅያኖስ አዋሳኝ ጠረፎችንም በግብፅ ስር ለማድረግ ጥሯል፡፡ […] ዋና እና የከረሩ ጦርነቶች የተካሄዱት ግን የሙሐመድ ዓሊ የልጅ ልጅ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ (1863-1879) ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ነበር፡፡
የአያቱን የመስፋፋት ሃሳብ ለማሳካት ደፋ ቀና ብሎ፤ ብዙ ደክሞ እና በአሜሪካውያን እና በአውሮፓውያን በአማካሪዎች እና በቅጥረኛ ወታደሮች ታጅቦ ኢትዮጵያን ለመውረር ቆርጦ የነበረው ኬዲቭ ኢስማኤል ፓሻ ዓላማው ከግዛት ማስፋፋት [ያ]ለፈ ነበር፡፡ […] በዋናነት የሚጠቀሱት ሁለት ዓበይት ጦርነቶች ደግሞ የ1875 የጉንደት እና የ1876 የጉራዕ ጦርነቶች ናቸው፡፡ በሁለቱም ጦርነቶች ወራሪዎቹ ግብፆች እና አጋዥ ቅጥረኛ ወታደሮች እና አማካሪ ጄኔራሎች ሽንፈትን ተጎንጭተው ተመልሰዋል፡፡ ድልም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ሆነ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ድሎች በስተጀርባ ደግሞ የአንድ ሰው ስም ሁሌም በጉልህ ይነሳል፡፡ አሉላ አባ ነጋ!!
የአለም አገራት መሪዎች ጀግኖቻችንን ጨምሮ በስመጥር ኢትዮጵያዊያን ሲደመሙና ሲበሳጩ ስለ መኖራቸው ምንም አይነት ጥርጣሬን የማያጭር እውነታ ሲሆን፤ ለዚህም ለአሉላ ከጀነራልነት የዘለለ ማእረግን የሰጠችው እንግሊዝ ተጠቃሽ ነች።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያልተካሄደ የጦርነት አይነት የለም። እኛን ለመድፈር በዛ በኩል ያልመጣም የለም። ሊውጠን ያላሰፈሰፈም በጭራሽ የለም። አይኑር እንጂ ሁሉም ምሱን እያገኘ ያልተመለሰ የለም። ለመጣው ፋሺስት ሁሉ ምሱን ሲሰጡት ከኖሩት መካከል ደግሞ አንጋፋው የጦር አበጋዝ አሉላ አባ ነጋ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን አርበኞች የተጋረጡባቸውን አደጋዎች ከመመከትም ባለፈ በማክሸፍ፤ ሲጋልብ የመጣን የውጪ ጠላት በመደምሰስና በመቅበር በኩል አለም ያውቃቸዋል። እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ ድሎች ደግሞ ሁሉም በሚባል ደረጃ በጊዜና ቦታ የሚገለፁ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል፣ ልክ እንደ አድዋ (1888 ዓ.ም) ሁሉ፣ ጉንደት እና ጉርአ ተጠቃሾች ናቸው። ይሁኑ እንጂ እነዚህ ለአሉላ ግን ብቸኞቹ የድሎቹ ስፍራዎች አይደሉም።
ድሎች ሁሉ ያለ አሉላ እና ጦራቸው የሚታሰቡ አይደሉምና አስፈላጊ ከሆነ ግብፆችን ዋቢ አድርጎ መነጋገር ይቻላል። መልሳቸው “ጀግናው አሉላ አባ ነጋ!!!” እንደሚሆን ቢታወቅም፤ “ማን ነው አይቀጡ ቅጣት የቀጣችሁ?” ብሎም መጠየቅም ይቻላል። ከቱርኮቹስ አንፃር??
“ቱርኮች ምጽዋን መያዛቸውን የሰሙት አጼ ዮሐንስ የጦር አዛዣቸው ለነበሩት ራስ አሉላ ’እስክመጣ ድረስ ተጨማሪ ቦታ እንዳይዙ ነቅታችሁ ጠብቁ’ ብለው መልዕክት ላኩ[።] ራስ አሉላ ግን ’ለጌታ ድግስ እንጂ ጦር አያቆዩትም’ ብለው ቱርኮችን ተዋግተው ድል አረጉ፡፡” ተብሎ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪው ሲያስተጋባ የነበረውን የአሉላን የጦር ሜዳ ውሎና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጀግንነት እዚህ አሰብ አድርጎ ማለፉ ስለ ውለታቸው ሲባል ተገቢ ይሆናልና አድርገን ብናልፈው አይከፋም።
ማሞ ውድነህ በ1847 በተምቤን ዙቁሊ ሚካኤል መወለዳቸውን የመዘገቡላቸው አሉላ አባነጋ ተዋጊ አርበኛ፣ ማራኪ ጦረኛ ብቻ አይደሉም። አሉላ የጦር መሪ ብቻም አይደሉም። አሉላ ማራኪ አንበርካኪም ብቻ አይደሉም። ታሪካቸው እንደሚያስረዳው አሉላ አባ ነጋ ሁሉንም ነበሩ። የተዋጣለት አስተዳዳሪ፣ የተሳካለት መፍትሄ አመንጪ፣ ይህ ቀረሽ የማይባሉ ዲፕሎማት፤ …. ስትራተጂስት፤ “…እኔ የሮማ ጠቅላይ ገዥ ሆኜ ስሔድ ያን ግዜ ጣሊያኖች ሰሐጢ ድረስ ሊመጡ ይችላሉ። አንዴ ክንዴን አሳይቻቸዋለሁ እንደገና ከመጡም እደግማቸዋለሁ! ራሱ ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ኖሯል፤ ይኖራልም…” በሚለው ዘመንን ተሻጋሪ አባባላቸው አለም የሚያውቃቸው ነበሩ።
“የምኒልክ ሰራዊት አንቀሳቃሽ ሞተር” በሆነው አሉላ ጉዳይ ላይ ገፋ አድርገው እንደሄዱት፣ እንደ ፕሮፌሰር ንጉሴ አየለ (ተደጋግሞ በሚገለፅላቸው “Ras Alula and Ethiopia`s Struggle Against Expansionism and Colonialism: 1872-1897” ስራቸው) ገለፃ ራስ አሉላ በስተኋላ ወደ ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ (ኋላ አፄ ዮሐንስ 4ተኛ) ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሹመትን በሹመት በመደረብ ወደ ፊት ገሰገሱ፡፡ በመጀመሪያ እልፍኝ አስከልካይ ቀጥሎም አጋፋሪነትን ተሾሙ፡፡ በ1873 ደጃዝማች ካሳ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ሲባሉ አሉላ የሻለቅነትን ማዕረግ የንጉሱ ሊጋባነት ማዕረግን ደርበው ያዙ፡፡
ኢትዮጵያን ካቀኑት፤ እንደ አገርም ካቆሙት መካከል አንዱና ፊት መሪው አሉላ ሲሆኑ፤ ለዚህም፣ አሁን አሁን ነገር አለሙ ሁሉ ተደበላለቀ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ስማቸውን ሳታነሳ ውላና አድራ አታውቅም ነበር። በተለይ በዘመነ ደርግ ታሪካቸው ልዩ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ከሚደረግላቸው ባለ ታሪኮች መካከል አሉላ ቀዳሚው ነበሩ። በማስተማሪያ መጻሕፍት ውስጥ ሁነኛ ቦታ ካላቸው ስመ ጥር ስብእናዎች መካከል አንዱ እኝሁ እያወራንላቸው ያሉት ብሄራዊ አርበኛና የጉራዕው አንበሳ፣ የጉንደቱ ሳቢሳ አሉላ አባ ነጋ ናቸው።
ሁለቱ አበይት ጦርነቶች (የ1875 የጉንደት እና የ1876 የጉራዕ) ሲሆኑ፤ በሁለቱም ጦርነቶች ወራሪዎቹ ግብፆች፣ አጋዥ ቅጥረኛ ወታደሮች እና አማካሪ ጄኔራሎች ሽንፈትን ተጎንጭተው ተመልሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በቀይ ባህሩ አንበሳ ራስ አሉላ አባ ነጋ ነው። (አዳራሽ ውስጥ ብንሆን “አንድ ግዜ እናጨብጭብለት እስቲ” ሳንል የምንቀር አይመስለኝም።)
ስለ አሉላ ባለ ውለታነት በዚህ ጽሑፍ ዳግም እናስታውስ እንጂ ማንነታቸው ሲገለፅ፣ ገድላቸው ሲብራራ፣ ስራዎቻቸው ሲተነቱ … ዛሬ አዲስ አይደለም። በስራዎቻቸው የታሪክን ከርስ በደንብ አድርገው ከሞሉት መካከል አንዱ እሳቸው ናቸው። በአለማችን በስማቸው ሳይቀር ተፅእኖ የፈጠሩ አርበኞች አሉ ከተባለ፤ ያለ ምንም ጥርጥር አሉላ ከፊት ይቆማሉ።
ለዚህ ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጃቸውን አሉላ ማለታቸውን (ስለ አሉላ የሰሯቸውን ስራዎች ትተን) እንደ አንድና ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በአንድ ወቅት፣ ዘሪሁን አበበ ይግዛው የተባሉ በ”አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ፣ የህዳሴ ግድባችንን የመሰረት ድንጋይ መጣል አስመልክተው “የ‘ጉ’ ቤት ለግብፆች” ሲሉ ባሰፈሩት፣ የመሀዲስቶች ውጋት፣ የፋሺስቶች ጣሊያን መቅሰፍት የሆነው ጀግናው አሉላን አስታዋሽ መጣጥፍ ላይ እንዳሰፈሩት፤ አሉላ በ”ጉንደት—- ጉራዕ— “ የፈፀሙት ጀብድ በ”ጉባ—-”ም ተደገመ የሚል የደስ ደስ ያለው ዜና መሳይ ጽሑፍ ሲሆን፤ ሀሳቡ ታሪካዊ መሰረት ያለው መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል። (ሁለቱ “ጉ—”ዎች – የጉንደት፣ የጉራእ መሆናቸውን፤ የመጀመሪያው ከመጋቢት 7 ቀን እስከ መጋቢት 9 ቀን 1876 መካሄዱን ልብ ይሏል)፤ ሶስተኛው “ጉ—” የአባይ መገደቢያ ስፍራን የሚመለከተው “ጉባ”ን ባገናዘበ መልኩ ታሪክን በማገናኘት የቀረበ ጽሑፍ ነው። ለአጥኚና ተመራማሪ የተመቸ ደስ የሚል “ቀመር”። (በወቅቱ የጉራዕው ጦርነት – ግብፅ ኢትዮጵያን ለመያዝ የተነሳችበት አበይት ምክንያት አባይን ከነ ምንጩ የግብፅ ወንዝ ለማድረግ ከነበራት ቅዠት የመነጨ እንደ ነበር ልብ ይሏል፡፡)
በርእሳችን ስለ ራስ አሉላ እንግዳ ያልተነገሩ ጉዳዮችን ይዘን እንደ መጣን ተናግረናል። “ያልተነገሩ” የሚለው “በአግባቡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያልተላለፉ” ከሚለው ጋር በተለዋዋጭነት እንዲነበብ እያሳሰብን ወደ አልተነገሩቱ እንዝለቅ።
አሉላ ካልተነገሩለት ስራዎቹ መካከል የተሳተፈባቸው ዋና ዋና ጦርነች፤ ከእነ ማን ጋር እንደተፋለመና እነ ማንን ድል እንዳደረገ አለመታወቁ ነው። ከጦርነቶችና ድሎቻቸው እንጀምር።
በአገር አንድነት፣ ሉአላዊነት፣ ዳር ድንበር መከበር፣ በሕዝቦች አንድነትና በኢትዮጵያ ታሪክ የማይደራደሩት “የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጠቅላይ መሪ” (በ”መስከረም”፣ “በኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት ትግል የአሉላ አባ ነጋ ሚና” ርእስ ስር እንደ ሰፈረው) ራስ አሉላ ከ24 በላይ በሆኑ ግዙፍ ጦርነቶች ላይ የተሳተፉ (በመምራት) ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከየካቲት 7 እስከ 9፣ 1876 (ከኦቶማን – ግብፅ ጋር) በጉራዕ፤ መጋቢት 8 እስከ 11፣ 1889 (ከመሀዲስቶች ጋር) ጋላባት፤ ከጥር 7 እስከ 18 (ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር) መቀሌ፣ 1886፤ የካቲት 2፣ 1896 (ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር) አድዋ እና ሌሎች በርካቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ “ሲጋልብ የመጣን አህያ ቀርቀብ አድርገህ ጫነው” እንዲል ስነቃላችን፤ ሁሉም በአሉላ ድል አድራጊነት የተጠናቀቁ ናቸው።
ሌላው ስለ አሉላ ለዚህ ትውልድ ያልተነገረው (ሊነገረው ሲገባ) መሰረታዊ ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፏቸውና ከውጪ መንግስታት ተወካዮች ጋር ያደረጓቸው ኦፊሴላዊ ስብሰባዎች (1879–1896) ሲሆኑ፤ ከሐምሌ አጋማሽ 1879 ጀምሮ እስከ ሀምሌ 1896 ድረስ ብቻ አገራቸውን በመወከል ከ24 በላይ ኦፊሴላዊ ስብሰባዎችን አድርገዋል።
ካደረጓቸው ኦፊሴላዊ ስብሰባዎች መካከል የግሪክ ቆንሲል፣ የብሪታኒያ መልእክተኛ፣ የፈረንሳይ መልእክተኛ፣ የኢጣሊያ መልእክተኛ፣ የሩሲያ መልእክተኛ፣ የብሪታኒያ ግብፃዊያን መልእክተኛ፣ የኢጣሊያ ወኪሎች፣ በኤርትራ የኢጣሊያ ገዥ፣ የብሪታኒያ ወኪል እና ሌሎች በርካቶች የሚገኙ ሲሆን፤ በአንዳቸውም ስብሰባና ውይይቶች የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው አልሰጠም።
ዶ/ር ንጉሴ አየለ የአድዋ 100ኛ አመትን አስመልክቶ በተዘጋጀው ልዩ እትም (“መስከረም” መጽሔት፤ በእውነቱ ለአሉላ እንደዛ አይነት ልዩ የመዘክር ስራ ተሰርቶ የሚያውቅ ስለ መሆኑ ይህ ጸሐፊ አያውቅም) ላይ እንዳሰፈሩት ይህ ሁሉ ቁርጥ የሆነ የአሉላ ኢትዮጵያዊ አቋም እስከ መጨረሻው የዘለቀ ሲሆን “ከአድዋ ድል በኋላ በ1897፣ የኢጣሊያኖች፣ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች ከኢትዮጵያ ጋር ስለ ድንበር ለመደራደር፤ የኢትዮጵያን ነፃነትም ለመቀበል ተገደዋል።”
ሌላው ብዙዎቻችን በጉራእ እና ጉንደት ብቻ ስለምናውቃቸው፣ “የጦር ብልሀት ስለነበራቸውና እና የተዋጣለት ዲፕሎማትም ስለነበሩት”፣ ስለ አሉላ እንግዳ በሚገባ ያልተነገረውና ለትውልድ ያልተላለፈው በውጭው አለም የፈጠሩት ተፅእኖ ነው።
በዚሁ ከላይ በጠቀስነው መጽሔት ላይ በሚገባ ተብራርቶና በመዘርዝር (ቢቢሊዮግራፊ) መልክ እንደ ቀረበው፣ ከተነገረላቸው ይልቅ ያልተነገረላቸው የሚበዛው ራስ አሉላ፣ በመላው አለም ማለት ይቻላል፣ ርእስና ርእሰ ጉዳይ ሳይሆኑ ያለፉበት ጊዜ አለመኖሩ ነው። አዎ፣ በጀግንነታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው፣ በፅኑ ኢትዮጵዊነታቸው ውልፊትን የማያውቁት፣ በዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸው የአገራቸውን ጥቅም በማስቀደም የሚታወቁት፤ በሳል የጦር መሪው፤ ስለ ራስ አሉላ እንግዳ ያልፃፈ የፕሬስ፣ ያላስተጋባ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አልነበረም (ዝርዝሩን ከመጽሔቱ ይመለከቷል)። እሳቸውን እያነሳ ያልተወያየ የአገራት መሪ፣ ስለ እሳቸው ያለውን እውቀት ያልወረወረ የታሪክ ፀሀፊም ይሁን የፖለቲካ ተንታኝ አልነበረም።
134ኛ ዓመት መታሠቢያቸውን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ፅሁፍ መግቢያ ላይ “ከዶጋሊው ድል በኋላ ጣሊያን ቀርቶ መላው አውሮፓ በፍርሃት ንዷል። ይህንንም ለማረጋጋት በኢጣሊያ ሮም ከተማ ውስጥ “Termini” ከሚባል ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት ባለ “piazza dei cinquecento’ በሚባል ትልቅ አደባባይ ላይ በዶጋሊ ጦርነት ለሞቱ 500 የኢጣሊያ ወታደሮች ሰኔ 5 ቀን 1887 እ.ኤ.አ የመታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው፡፡ ራስ አሉላ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ሐውልታቸውን ሰርተው ጀግንነታቸው በውጪ አገር ዜጎች ሳይቀር አሁንም ድረስ እንደተተረከ ቀጠለ፡፡” በሚል የሰፈረውም እያልን ላለነው መረጃም ማስረጃችንም ነው።
ባጭሩ፣ አሉላ ድፍን የነጩን አለም ያንቀጠቀጡ፣ ቆፍጣናና የጀግኖች ቁና የነበሩ ሰው ናቸው። ይህ “በጉራዕ እና በጉንደት …” ከሚሉት ግዙፍ (ግን ደግሞ ጥቂት) ድሎቻቸው በስተቀር፣ በሚገባ አልተነገረላቸውም። ስራቸው እንደ አንድ የኢትዮጵያ መስራች አባትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፉ ዘንድ አላደረጋቸውም። ይህን ማድረግ ደግሞ የዚህ ትውልድ ስራ ነውና ሳይርቅ በቅርቡ …. ማለት ያስፈልጋል።
አሉላ በምኒልክ አድዋን ዋና ከተማቸው አድርገው የትግሬን ብዙውን የ7ሰሜን ክፍል እንዲገዙ ሾመዋቸዋል፤ የካቲት 15፣ 1897 ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስም በዚሁ ስልጣናቸው ላይ ነበሩ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014