«ሱፉን ግጥም አድርጎ ተከርክሞ ፀጉሩ
መልዓክ መስሎ ታየኝ አይ ያለው ማማሩ»
አንድ ሰሞን በብዙዎች ተወዶ ይደመጥ ከነበረው የአስቴር አወቀ ዜማ ግጥም ላይ የተቀነጨቡ ስንኞች ናቸው። በሱፍ መዋብ ዘንጦ መታየት ጥንትም የነበረ አሁን ያለ ነው። የሱፍ አልባሳት/ሙሉ ልብስ/ እንደየዘመኑ ሁኔታ በተለያየ መልኩ የየዘመኑን ፋሽን በተከተለ መልኩ እየተዘጋጁ ዘመነኛው እንዲለብሳቸው ለገበያ ይቀርባሉ።
ለወንዶች ግንባር ቀደሙ መዘነጫ፤ እጅግ ወሳኝ ቦታ ላይ እምር ብለው የሚገኙበት ሱፍ ልብስ በእርግጥም ብዙዎችን ያሳምራል። ለዚህም ነው ፋሽንነቱ ዘልቆ ምዕተ አመትን ተሻግሮ ዛሬም በተለያየ ዲዛይን ተሠርቶ መለበሱ። ለልብስ ቅድ ባለሙያዎችና ለዲዛይነሮች ምስጋና ይገባቸውና ዛሬ ሱፍ ተለብሶ የማይሰለች ታይቶ የማይጠገብ እንዲሆን አድርገው አዳዲስ መልክ አላብሰው እያዘጋጁ ለገበያ ያቀርቡታል። ፋሽን ተከታዩም በየሱቁ ያየውን መርጦ ይዋብበታል።
ቀድሞ የሰብል መሰብሰቢያውን ወቅት መጠናቀቅ ተከትሎ የፍስሀና የደስታ ጊዜ በመሆኑ ተመርጦ በተለይ በጥር እንዲሁም የትንሳኤን በዓል ተከትሎ በአብዛኛው በሚያዝያ ወር ሠርግና ሠርገኛው ይበራከታል። የከተሞች ጎዳናዎች፣ መናፈሻ ስፍራዎች፣ አዳራሾች አዳዲስ አልባሳት በተጎናፀፉ ሙሽሮች፣ በተመሳሳይ አልባሳት ባማሩ ሚዜዎች፣ በመኪና ጥሩንቧና በሠርግ ዘፈን የሚደምቁበት ወቅት ነው።
እኛም ያለንበት የሚያዝያ ወር የሠርግ ወር እንደመሆኑ ይህን መሠረት አድርገን በሠርግ ወቅት ወንዶች ደምቀውና ተውበው የሚታዩበትን የሱፍ ልብስ/ሙሉ ልብስ/ በፋሽን አምዳችን መዳሰስ ወደድን። ከዚህ በፊት በዚሁ አምድ የሴት ሙሽሮች አልባሳት (ቬሎ) እና የሴት ሙሽሮች ሚዜዎች። አልባሳትን በተመለከተ አንድ ጽሑፍ አቅርበናልና ዛሬ ትኩረታችን የወንዶች የሠርግ አልባሳት በተለይም ሱፍ ላይ አድርገናል።
በተለይም ወንዶች በዚህ ወቅት በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ለብሰው አምረው የሚታዩባቸው አልባሳት ወይም ሱፍ አልባሳት/ሙሉ ልብስ/ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ መደብሮች ውስጥ በስፋት ለሽያጭ ይቀርባሉበፒያሳ፣ አራት ኪሎና ቦሌ መንገድ ላይ እነዚህ የወንዶች አልባሳት (ሱፎች) ለደንበኞቻቸው እይታ በሚመች መልኩ በየሱቆቹ ለገበያ የቀረቡ የወንዶች ሱፍ አልባሳትን ተዘዋውረን ተመለከትን።
ሱቆቹ ውስጥ በዓይነት በሱፎች ስሪት ጨርቅና በጥራት ደረጃቸው ተጠቃሚው አቅሙን ባገናዘበና በምርጫው ይለብሳቸው ዘንድ ተደርድረዋል። ፒያሳ ከአራዳ ሕንፃ ፊት ለፊት ከሚገኝ የተዘጋጁ ሱፎች/ሙሉ ልብሶች/ መሸጫ መደብር ውስጥ ነን። ሙሽሮች እንዲሁም ሚዜዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚገመቱ ለሠርግ ሥነ ሥርዓታቸው ይሆን ዘንድ ልብሶችን የሚለኩ ወጣቶችን ተመለከትኩ ጠጋ ብዬም አወራኋቸው። ሙሽራው ከሚዜዎቹ በተለየ መልክ የተለየ ነጣ ያለ ቀለም ያለው አብረቅራቂ ሱፍ ለመለካት በእጁ ይዞ አወራን።
አቶ ተመስገን ተሻለ ይባላል፤መኖሪያው እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ሲሆን፣ በዚሁ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ሠርጉን ሊያደርግ ሽርጉድ ላይ መሆኑንና ከሙሽራዋ ጋር የሚደምቅበትን ሱፍ ልብስ ለመግዛት መምጣቱን ገለፀልኝ።
በእርግጥ ሙሽሮች ለአንድ ቀን ብቻ የሚለብሱት የሠርግ ልብስ በአብዛኛው በኪራይ መልክ የሚጠቀሙ ቢሆንም አቶ ተመስገን ግን የተሰረገበትን ልብስ ወደፊትም ለታሪክ ማስቀመጥ በመፈለጉ ለመግዛት እንደወሰነ ይገልፃል። የወንድ ሙሽራ አልባሳቱ እንደ ተሠሩበት ጨርቅ ጥራትና የተመረቱበት አገር ዋጋቸው ይለያያል። የሙሽራ አልባሳቱ ከ4000 እስከ 12000 ድረስ ዋጋ ወጥቶላቸው ለተጠቃሚ የቀረቡ ሲሆን፤ ሙሽራውም ኪሱን በሚለካ ዋጋ መርጦ ሙሽራዋ ፊት የሚቀርብበትን ሱፍ ይገዛል።
አቶ ወንድወሰን ስሜ ከአቶ ተመስጌን ሚዜዎች አንዱ ነውለሙሽራው ሱፍ ልብስ ለማጋዛት በመደብሩ ተገኝተዋል፤ አቶ ወንደወሰን ለሚዜዎች የሚሆን ልብስ ጠይቀው ዋጋው እጅግ ተወዶባቸዋል፤ በዚህም የተነሳ በኪራይ አልባሳት ለመጠቀም መወሰናቸውን ነገሩኝ። በተለያዩ የልብስ መሸጫ ሱቆች ላይ ተዘዋውረው ማየታቸውን የሚገልፁት አቶ ወንድወሰን፣ የሱፍ ዋጋ በፊት ከሚያውቁት በእጥፍ ጨምሮ እንዳገኙት ያስረዳሉ።
እዚያው ፒያሳ አካባቢ የወንዶች ሱፍ አልባሳትና የተለያዩ ልብሶች መሸጫ ከሆነው ሌላ መደብር ገባን። መደብሩ የዘመኑ ዲዛይነሮች የተጠበቡባቸው አልባሳት ለሽያጭ የቀረቡበት ነው። አስተናጋጆች ገበያተኛውን በፈገግታ ይቀበላሉ፤ ይሸኛሉ። የድምጽ መቅጃ ይዜ መቅረቤን ባይወዱትም ቤቱ ውስጥ የሚሸጡ ዋና ዋና አልባሳትና ዋጋቸውን ግን ከመንገር ግን አልተቆጠቡም። ቤቱ ውስጥ ከቱርክ የሚመጡ የወንዶች ሱፍ አልባሳት በብዛት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ አልባሳቱ በአማካይ ከ7 ሺ እስከ 15 ሺ ድረስ ለሽያጭ መቅረባቸውን አብራርተውልኛልየሙሽራ እና የሚዜ አልባሳቱ በሚያምር መልኩ ተሰድረው ሲታዩ የወጣላቸው ዋጋ ከፍ ማለትን ያስረሳሉ።
በዚህ ወቅት የገበያ ሁኔታው የተሻለ መሆኑንና ሠርገኞች አልባሳቱን እየገዙ እንደሚጠቀሙ አስተናጋጁ አበዱል ቃድር (ትክክለኛ ስሙ አይደለም) ይናገራል። በሱቁ ወቅቱ ሰበብ ተደርጎ የተጨመረ የዋጋ ጭማሪ እንደሌለና አልባሳቱ ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው የወጣላቸው ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን ያስረዳል።
የልብስ ሽያጭ ባለሙያዋ ወጣት ሲፈን አየለ፤ የአልባሳቱ ዋጋ ከሌሎች አንፃር ሲታይ ብዙም ጭማሪ እንደለሌው ትገልፃለች። በተለይ እርሷ በምትሸጥበት ሱቅ ውስጥ የሚገኙ ሱፍ አልባሳት በጥራት ደረጃቸው ከፍ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ ዋጋቸውም በዚያው ልክ ውድ ሊሆን እንደቻለም ታስረዳለችነገር ግን እንደሰው ፍላጎት እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ በሌሎች ሱቆች ማግኘት እንደሚቻልም ትጠቁማለች ።
የሙሽራና ሚዜ አልባሳቱ በሁለት መልክ ለተጠቃሚ የሚቀርቡ ሲሆን፣ በአብዛኛው በኪራይ ይገኛሉ፡፡ሱቅ ተዘጋጅተው ከሚሸጡቱ የሙሽራ አልባሳት በተጨማሪ በተለያዩ የሠርግ አልባሳት የሚያከራዩ ድርጅቶች ተበራክተዋል። በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ባገኘነው መረጃ የወንድ ሙሽራ ልብስ ከ1 ሺ እስከ 3ሺ ብር የሚገኝ ሲሆን፣ የሚዜ ሱፍ ከ500 ብር እስከ 1ሺ ብር ድረስ ለኪራይ ቀርበዋል።
አቶ ተመስጌን ከአመት በፊት የሚያውቃቸው የሙሽራ አልባሳት እንዳሁኖቹ በተፈለገ መልኩ እጅግ ባያምሩም፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ይሸመቱ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከሁኔታዎች መቀያየር አንፃር የአልባሳቱ ዋጋ መጨመር የሚጠበቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣ አሁን ያለው ዋጋ ግን እጅግ መጋነኑን መታዘባቸውን ገልፀውልናል።
ተጠቃሚዎች አልባሳቱ በሽያጭና በኪራይ መልክ በሱቅና የሙሽራ አልባሳት ማከራያ መደብሮች ለተጠቃሚዎች እንደምርጫቸው እንዲጠቀሙ በስፋት መቅረባቸው በጄ ቢያስብልም፤ የዋጋው አልቀመስ ማለት ሠርገኛው ከሱፍ አልባሳት በተለየ ሌላ አማራጭ እንዲያስብ ያደርገዋል የሚል አስተያየት አስቀምጠዋል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም