ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ሳምንቱስ ጥሩ አለፈ? ሳምንቱን ትምህርታችሁን በትጋት በመከታተል እንዳሳለፋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆች ስለ ስብዕና ግንባታ ታውቃላችሁ? የስብዕና ግንባታ በመደበኛው ትምህርት ከምታገኙት እውቀት በተጨማሪ ከወላጆቻችሁ፣ ከመምህራኖቻችሁ እንዲሁም ከክፍል ጓደኞቻችሁ መልካም ስነ ምግባርን በመቅሰም የምታገኙት ትምህርት ነው።
ልጆች እናንተ በስነምግባር ታንፃችሁ እንድታድጉና መልካም ስብዕናን እንድታጎለብቱ ታዲያ የወላጆቻችሁና መምህራኖቻችሁ ክትትል ያስፈልጋችኋል። በተለይ ደግሞ ወላጆቻችሁ መጥፎውን ከጥሩ በመለየት የተገባ ባህሪ እንድታሳዩ ሊያስተምሯችሁ ይገባል። በተለይ ደግሞ ከታች የተዘረዘሩትን የልጆች አስር የስብዕና ማጎልበቻ መንገዶችን ቢከተሉ እናንተ ልጆች የተሟላ ስብዕና ይዛችሁ ታድጋላችሁ።
ልጆች፣ ዛሬ ለቤተሰቦቻችሁ አንዳንድ ሀሳቦችን ማካፈል መረጥኩ። እናንተም ብታውቋቸው አይከፋም ብዬ በማሰብ ላጋራችሁ ወደድኩ። መልካም ንባብ።
1ኛ፡- ለሚያደርጓቸው ነገሮች ጥንቃቄ ያድርጉ
እንደሚታወቀው ልጆች ብዙ ግዜ ልጆች የሚማሩት ከሚያዩቸው ነገሮች ነው። አብዛኛውን ነገር የሚማሩት ደግሞ ወላጆቻቸው የሚያደርጉትን ነገር በማየት ነው። ከዚህ አንፃር ወላጆች ልጆቻቸው ፊት ለሚናገሩትና ለሚያደርጉት ነገር ጥንቃቄ መውሰድ አለባቸው። በሌላ አባባል ወላጆች ልጆቻቸው ሊያደርጉ የማይፈልጓቸውን ነገሮች እነርሱም ማድረግ የለባቸውም።
2ኛ፡- ልጆችዎን ማወዳደርና መፈረጅ ያቁሙ
ወላጆች በማንኛውም መንገድ ልጆቻቸውን ማወዳደርና መፈረጅ የለባቸውም። ልጆች አሁንም ገና ነገሮችን እየተማሩ ያሉበት ደረጃ ላይ በመሆናቸው ወላጆች እነሱን ሲፈርጇቸው በቀላሉ ሊያምኗቸው ይችላሉ። እንደውም አመፀኛና ከዚህም በላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እነሱን ከሌሎች ልጆች ጋር ማወዳደርም ሞራላቸው እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ብቁ እንዳልሆኑ እንዲሰማቸውና በራስ የመተማመን መንፈሳቸው እንዲቀንስ ያደርጋል። ስለዚህ ልጆች ቢያጠፉ እንኳን ወላጆች ትክክለኛ ቃላቶችን ተጠቅመው ስህተታቸውን እንዲያርሙ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
3ኛ፡- በትኩረት ይከታተሉ
ወላጆች ልጆቻውን በትኩረት ሊከታተሏቸው ይገባል። በተለይ በአሁኑ ግዜ ልጆች ስልኮችና ላፕቶፖች ከእጃቸው ስለማይጠፉ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ልጆች አዘውትረው የሚያደርጓቸውን ነገሮች፣ ፍላጎታቸውንና ልምዳቸውን መከታተል የግድ ይላል። ከክትትሉ ባለፈ ታዲያ ልጆች አዳዲስ ነገሮችን እንዲማሩና እንዲያውቁ ማበረታታት ያስፈልጋል።
4ኛ፡- ጥሩ አድማጭ ይሁኑ
ወላጆች በሥራ መብዛትና በተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ለልጆቻቸው በቂ ግዜ ሲሰጡ እምብዛም አይታዩም። ከዚህ አንፃር ወላጆች በየትኛውም አጋጣሚ ለልጆቻቸው የተወሰነ ግዜ ሊሰጡ ይገባል። ይህም ልጆች ስለራሳቸው ለመናገርና ለመግለፅ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። ወላጆችም የልጆቻውን ችግር ሰምተው ሊያግዟቸው ይገባል። በዚህ ግዜ ታዲያ ልጆች በወላጆቻቸው በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያድርባቸው ያደርጋል።
5ኛ፡- በሚጠብቁት ልክ ልጆችዎን አይጫኗቸው
አብዛኞች ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑና ስኬታማ ሕይወት እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ። ይሁንና ወላጆች ልጆቻቸው እንዲሆኑላቸው በሚጠብቁት ልክ ጫና የሚያሳድሩባቸው ከሆነ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተው ጫናን መሸከም ባለመቻላቸው አመፀኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው መሆን የሚፈልጉት ነገር ላይ ማተኮር ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። አቅማቸውን በመለየት እነርሱን መንከባከብና ማበረታታም ይገባቸዋል።
6ኛ፡- ደምቦች ያውጡላቸው
ልጆችዎን ገና በትንሽነታቸው በኃላፊነት ያሳድጓቸው። ይህም የተፈላጊነትና የሥነሥርዓት ስሜት በውስጣቸው እንዲያድር ያደርጋል። ለዚህም ልጆች ሊከተሏቸው የሚገቡ ደምቦችን ያውጡላቸው። ለምሳሌ ለእንቅልፍ ወደ አልጋ የመሄጃ ሰዓት ያብጁላቸው። በየዕለቱ ጥርሳቸውን የሚያፀዱበትና የሚያጠኑበትንም ሰዓት ያስቀምጡላቸው። እንዲዝናኑ እና የራሳቸውን አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ ያድርጉ። ነገር ግን መከተል ያለባቸውን አንዳንድ ደንቦች ማወቅ እንደሚኖርባቸው ያሳውቋቸው።
7ኛ፡- የስክሪን መመልከቻ ግዜን ይገድቡ
በዚህ ግዜ ለወላጆች ፈተና እየሆኑ ከመጡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የልጆች በቲቪ፣ ታብሌትና ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ስክሪኖች ላይ መጠመድ ነው። የዚህ ዘመን ልጆች ትልቁ ሱስም በእነዚሁ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች መለከፍ ነው። በተለይ ደግሞ ልጆች እነዚህን መሳሪያዎች ተከልክለው እንዲያጠኑ ከተደረጉ በኋላ ዳግም ሲመለሱ ቆይታቸው ይጨምራል። ከዚህ አኳያ ወላጆች ልጆች በታብሌቶች፣ ቲቪና ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ላይ የሚኖራቸውን ቆይታ በሰዓት ሊገድብና ቁጥጥርም ማበጀት ይኖርባቸዋል። ልጆች እነዚህን መሣሪያዎች በሚጠቀሙበት ግዜም ከትምህርት፣ ለልጆች ከሚሆኑ መዝናኛዎችና ከቤተሰብ ጋር ሊያገኙ ይገባል።
ልጆች ሁል ግዜ በቪዲዮ ጌሞች ላይ ብቻ እንዳያሳልፉ ወላጆች አንዳንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉና ከስክሪን ውጪ ያሉ ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።
8ኛ፡- ምሳሌ ይሁኑ
‹‹የምታወራውን ሆነህ ተገኝ›› እንደሚባለው ወላጆቻቸው ልጆቻቸው የሚጠይቋቸውን ነገሮች ማድረግ አለባቸው። በተለይ ደግሞ በአነስተኛ የዕድሜ ደረጃ ላይ ያሉ ልጆች ወላጆቻቸውን ያሚያደርጉትን ሁሉ ያስመስላሉ። ወላጆች የሚያወሯቸውን ነገሮች በድርጊት ካልፈፀሙና ደምብ ካላስቀመጡ ልጆች ይህን ከቁም ነገር ላያስገቡት ይችላሉ። ስለሆነም ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም ባሕሪ ማሳየትና በዚሁ መንገድ እነርሱም ተቀርጸው እንዲያድጉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
9ኛ፡- ራስ መቻልን ያበረታቱ
ልጆችን በእንክብካቤ ማሳደግ የወላጆች ግዴታ ነው። ይህ ግን እስከዘላለሙ ሊቀጥል የሚችል ተግባር አይደለም። ምክንያቱም ልጆች አንድ ቀን ነገሮችን በራሳቸው ማድረግ መፈለጋቸው ስለማይቀር ነው። ስለሆነም ልጆች ከወላጆች ርዳታ እንዲላቀቁ ሁሌም በወላጆች ላይ እንዲንጠላጠሉ ማድረግ አያስፈልግም። ልጆች አንዳንድ ነገሮችን በራሳቸው እንዲያከናውኑና እንዲያስተናግዱ ማድረግም ተገቢ ነው። ይህም የኃላፊነት ስሜትን እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል።
10ኛ፡- የወላጅት ክህሎትዎን ይከልሱ
ወላጆች ከላይ የተደረደሩትን መፈፀም ብቻ ሳይሆን የወላጅነት ክህሎታቸውንም መከለስ ይኖርባቸዋል። ወላጆች በልጆቻቸው ባህሪ ወይም በሚሰጡት ምላሽ ምክንያት ስህተት የሰሩበት ግዜና ሊቀየሩት የሚችሉት ነገር ሊኖር ይችላል። ለዚህም ወላጆች ግዜ ወስደው የወላጅነት ክህሎታቸውን መከለስና ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም