የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር (ሴካፋ) ከቀናት በኋላ በኡጋንዳ አዘጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ተካፋይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እየተመራ እንደሚወዳደር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የዘንድሮው የሴካፋ ውድድር ከግንቦት 14-28/2014ዓ.ም እንደሚካሄድ ቢገለፅም፣ ውድድሩ የሚካሄድበት ቀን ሊቀየር ይችላል። ንጄሩ በተባለችው ከተማ ውድድሩ ሲካሄድ ስምንት አገራት ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። እነዚህ አገራት በሁለት ተከፍለው የሚጫወቱበት የምድብ ድልድልም ተደርጓል። በዚህም መሠረት ከተሳታፊዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በምድብ ሁለት መደልደላቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በምድብ ድልድሉ የዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓት ላይም በመጀመሪያው ምድብ፤ አዘጋጇ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ እና ጅቡቲ መደልደላቸው ታውቋል። በሁለተኛው ምድብ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በውድድሩ በአዲሱ አሰልጣኝ ፍሬው የሚመሩም ይሆናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ፍሬው ኃይለገብርኤል ዋናውን የሴቶች ቡድን ሉሲዎቹን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ስምምነት ላይ ደርሷል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ስብሰባ አሰልጣኙ የቡድኑን አሰልጣኝነት በኃላፊነት ተረክቦ ለሴካፋው ውድድር እንዲያዘጋጅ ውሳኔ ላይ ደርሷል።
አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን ስኬታማ ጊዜን ማሳለፉ የሚዘነጋ አይደለም። ከቡድኑ ጋር የሁለት ዓመታት ቆይታ የነበረው አሰልጣኙ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ቻምፒዮን እንድትሆን አድርጓል። ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ በኮስታሪካ በሚደረገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በቀጥታ ተሳታፊ ልትሆን ችላለች። በማጣሪያውም እስከመጨረሻው ዙር ከደረሱ አራት ቡድኖች መካከል አንዱ ነበር።
ቡድኑ በዓለም ዋንጫው ባይሳተፍም ተስፋ ሰጪ የሆነ ጠንካራ ቡድን በመመስረት ረገድ አሰልጣኙ ትልቅ ሚና ነበረው። በመሆኑም በሴካፋ የሚሳተፈውን ቡድን ውጤታማ እንዲሆን ተጨማሪ ኃላፊነት ለአሰልጣኙ መስጠቱን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014