ሰሞኑን የቤቱ በር ተዘግቶ መክረሙ ብዙዎችን አስደንግጧል። ለወትሮው በአካባቢው ሰው አይጠፋም። በደጃፉ ተቀምጠው ልጃቸውን የሚያጠቡት ወይዘሮ አላፊ አግዳሚውን ሰላም ሲሉ ይውላሉ። መንደርተኛውና የቅርብ ዘመዶች የማይጠፉበት አጸድ ዛሬ በዝምታ መዋጡ የተለመደ አልሆነም፡፡
የቤቱን በር ጠጋ ብለው ያስተዋሉ አንዳንዶች ከውጭ በኩል በትልቅ ቁልፍ መዘጋቱን አውቀዋል።እንዲህ የሚሆነው ወይዘሮዋ ከቤት ሲወጡና ራቅ ብለው ሲሄዱ ብቻ ነው።ከሰሞኑ ወይዘሮ አርጎ ልጃቸውን አዝለው ከቤት ሲወጡ አልታዩም።እንዲህ ቢሆን ኖሮ ከመንደርተኞች አንዳቸው እንኳን ያውቁ ነበር።ጉዳዩ ያስጨነቃቸው የቅርብ ሰዎች ለመፍትሄው አበክረው መከሩ፣ ተማከሩ ፡፡
ወይዘሮዋና የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሴት ልጃቸው ጋር ከአካባቢው ከተሰወሩ ሁለት ቀናት ተቆጥረዋል። እንዲህ መሆኑ በእጅጉ ያሳሰባቸው ጎረቤቶች ከእናትና ልጁ ጋር የሚኖረውን ሰው አስታወሱ። ይህ ሰው ለዓመታት አብሯቸው የዘለቀ ሠራተኛቸው ነው።በዓመት ሰባት ሺህ ብር እየተከፈለው የግብርና ሥራን ይከውናል።ወይዘሮዋ ጊዜው ሲደርስ የለፋበትን አይነፍጉትም።እሱም ቤተሰብ ሆኖ ግዴታውን በወጉ እየተወጣ የእጁን፣ የላቡን ዋጋ፣ ይቀበላል፡፡
የአካባቢው ሰዎች እሱን ጭምር ያለማየታቸው ይበልጥ አስደንግጧቸዋል። ያለአንዳች ምክንያት ሦስቱም እንደማይጠፉ ቢገባቸው የእነሱን ጥረት አቁመው ለወዳጅ ዘመዶች ተናግረዋል።ጉዳዩን የሰሙት የቅርብ ዘመዶች ሰዎቹ እነሱ ዘንድ ያለመምጣታቸውን ያውቃሉ። ለቀናት ድምጻቸው ሳይሰማ፣ መድረሻቸው ሳይታወቅ መጥፋታቸው ደግሞ አስደንግጧቸዋል፡፡
የቅርብ ዘመዶችን ያካተተው የሦስቱ ሰዎች ፍለጋ ተጠናክሮ ቀጠለ። ሰዎቹ ከቤት ደርሰው የተዘጋውን ቤት ለመክፈት ሞከሩ። ቤቱ በቁልፍ የተከረቸመ ነበርና በዋዛ አልተከፈተም። ምንአልባት ወይዘሮዋ ከሄዱበት ቢመለሱ የበሩ መከፈት መልካም አይሆንም። ዘመዶቻቸው ቁልፉን ሌሎች ዘንድ አስቀምጠው እንደሆን ጠየቁ።ጎረቤቶች ለማንም በአደራ እንዳልተዉ መለሱላቸው፡፡
የአካባቢው ነዋሪና የወይዘሮዋ ዘመዶች በቤቱ ላይ ዝርፊያ እንዳይፈጸም ቢሰጉ ለጥበቃው ተጉ።የሰዉን አለመኖርና የቤቱን መዘጋት ያስተዋሉ አንዳንዶች ስርቆት እንዳይፈጽሙ ያሰቡ ጉዳዩን ለአካባቢው ቀበሌ አስታወቁ።ቀበሌው ጥበቃውን በወጉ እንዲከውኑ እውቅናውን ሰጣቸው።ሰዎቹ ቤቱን እየጠበቁ፣ ንብረቱን ሊቃኙ ተስማሙ፡፡
አሁን የሦስቱ ሰዎች ድንገት ወጥቶ ያለመመለስ አሳሳቢነት ጨምሯል።ሰዎቹ በዚህ በኩል ሲያልፉ አየን፣ ያሉበትንም ሰማን የሚል አለመገኘቱ ሁሉንም ከጭንቀት ጥሏል። ከፍለጋው ጊዜያት ጥቂት ቆየት ብሎ ድንገት ወሬ ሰማን ያሉ ሰዎች መልዕክት ይዘው መጡ።አብሯቸው የሚኖረው ሠራተኛ መናኸሪያ አካባቢ መታየቱንና በዕለቱም ብቻውን እንደነበር ተናገሩ፡፡
ይህን የሰሙት ፈላጊዎች ውስጣቸው በተስፋ ሞላ። ቢያንስ የእሱ መኖር የሌላውን ሰላም መሆን ይናገራል ሲሉ አሰቡ። በስፍራው የደረሰውን የወይዘሮዋን የቅርብ ዘመድ ነዋሪዎቹ ቤቱ ተሰብሮ ውስጡ እንዲፈተሽ ጠየቁት። ዘመድዬው የሰዎቹን ጥያቄ ከልብ አድምጦ ወደቤቱ ተጠጋ።
ሰውዬው የተዘጋውን ቤት ቆም ብሎ አስተዋለው።በሩ የተዘጋው ከውጭ በኩል ነው።ይህንን ሲያውቅ ወይዘሮዋ በሩን በትክክል በቁልፍ ዘግተውት እንደሄዱ ገባው። ወዲያው እውነታውን ለጎረቤት አሳውቆ ምንም ስጋት እንደማይኖር ገለጸላቸው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በኋላ በሩ ተዘግቶ መቆየት እንደሌለበት ጫና ፈጠሩ። ዘመድዬው የሰዎቹን ሀሳብ አልተቃወመም። በቁልፍ የተከረቸመውን በር በአግባቡ ሰብረው ወደውስጥ እንዲዘልቁ ተስማማ። እንደታሰበው ሆኖ የተቆለፈውን በር ለመክፈት በርካታ እጆች ተባበሩ፡፡
በመኝታ ቤቱ…
ትልቁ ቁልፍ አጥብቆ የያዘው መሸጎሪያ ሲከፈት አፍታ አልፈጀም።የበሩን መበርገድ ያዩት ሰዎች ዋናውን በር አልፈው፣ በሳሎኑ ተራምደው ወደመኝታ ክፍሉ አመሩ።ገና ወደውስጥ ከማለፋቸው ለአፍንጫ የሚከብድ ክፉ ሽታ ተቀበላቸው።
ሰዎቹ ግራ እንደገባቸው ራመድ አሉና ወደውስጥ ከሚያሳልፈው ክፍል በር ላይ ቆሙ። በቅርብ ርቀት የተጠቀለለ ነገር ታያቸው ሰሌን ነው። ወደክፍሉ አለፉና ጥቅሉን ሰሌኑን ዘረጉት። ከስሩ ብርድልብስ አለ። አፋቸውን እንደሸፈኑ ብርድልብሱን በፍርሀት አነሱት። ዓይናቸው ያየውን እውነት ማመን አልቻሉም።
ወይዘሮዋና ትንሽዋ ልጃቸው አካላቸው ተመቶ እንዳልሆነ ሆነዋል። በሰሌንና በብርድልብስ የተጠቀለለውን የእናትና ልጅ የተለያየ አካል ማየት በእጅጉ ከባድና አሰቃቂ ሆነ። ስፍራው በድንገቴ ጩኸት ሲደባለቅ የሰሙ ሰዎች እየተሯሯጡ ቤቱን ከበቡት። ሁሉም የተመለከቱትን አምነው መቀበል ቸገራቸው፡፡
ጥቆማ ለፖሊስ ..
የአካባቢው ነዋሪዎችና የቅርብ ዘመዶች በእናትልጅ ላይ የተፈጸመውን ግድያ እንዳዩ ፈጥነው ወደ ፖሊስ ደወሉ። ፖሊስ የደዋዮቹን ጥቆማ እንደተቀበለ የሰዎቹን ድንጋጤና መርበትበት አጤነ። በከባድ ጭንቀት ውስጥ እንዳሉ ያስታውቃል። ፖሊስ በስፍራው ሲደርስ የቀበሌውን ሊቀመንበርና የአካባቢውን ነዋሪዎች አገኘ።ወንጀሉ ተፈጽሞበታል ከተባለው መኖሪያ ቤት ሲጠጋ የበሩ ቁልፍ ተሰብሮ ወለል ብሎ መከፈቱን አስተዋለ። ከሕግ አካላት እውቅና ውጪ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሲፈጸም በቂ መረጃዎችን ለመውሰድ ያስቸግራል። ለሥራው ፈታኝ ቢሆንም ባሉት እውነታዎች መረጃዎችን ለማግኘት የምርመራቡድኑ ወደውስጥ ዘለቀ፡፡
የፖሊስ ቡድኑ አባላት ክፉ ሽታ ለአፍንጫቸው እየደረሰ ወደ ሁለተኛው ክፍል ዘለቁ።የሆነውንም በግልጽ ተመለከቱ። ወይዘሮ እርጎ ኑርዬና ጨቅላዋ ልጃቸው ሰውነታቸው ክፉኛ ተጎድቶ በደም እንደተነከሩ ወድቀዋል። ድርጊቱ በምን ዓይነት መሣሪያ እንደተፈጸመ ለማወቅ ቡድኑ በጥንቃቄ ምርመራውን ቀጠለ፡፡
አስከሬኑን ማንሳት ለብዙሀን ፈታኝ ቢሆንም አስፈላጊው ጥንቃቄ ሳይጓደል የሟቾቹ በድን ከስፍራው ተንቀሳቀሰ። ይህኔ አካላቸው ተጠቅልሎበት የነበረው ብርድልብስ ብቻውን ቀረ።የፖሊሶቹ ዓይን ከሌሎች ሰዎች በተለየ በብርድልብሱ ላይ አነጣጠረ።ሁሉም በውስጡ አንዳች ነገር ደብቆ እንደያዘ ጠርጥረዋል፡፡
ፖሊሶቹ ሳያመነቱ ብርድልብሱን በጥንቃቄ ገለጡት። ጠቅልሎ የያዘው ምስጥር ግድያው የተፈጸመበትን ጥልቆ (መጥረቢያ) ነበር። ፖሊስ ያገኘውን ማስረጃ በጥንቃቄ አንስቶ ስለግድያው የሚኖረውን ጥርጣሬ የአካባቢውን ሰው ጠየቀ። አብዛኞቹ ነዋሪዎች የቀድሞው ግምታቸው ተቀይሯል።
ነዋሪዎቹ የወይዘሮዋ ሠራተኛ ሙሉጌታ አድ ማሱ ከእናትና ልጁ ጋር ተሰውሮ እንደነበር ሲገምቱ ቆይተዋል። አሁን ግን ነባሩ ሀሳባቸው ተወግዶ ግለሰቡን ዋንኛ ተጠርጣሪ አድርገውታል። ይህን እውነት በመረጃነት የመዘገበው ፖሊስ ተገቢውን ምርመራ ለማካሄድ ‹‹ይበጁኛል›› ያላቸውን ሀሳቦች ሰበሰበ።ወዳጅ ዘመድን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪ ተፈላጊውን ለመያዝ ትብብሩን አሳየ።
ፖሊስ የግለሰቡን መልክና ቁመና፣ አለባበስና አረማመዱን ከሌሎች ጠይቆ አሰሳውን ከአካባቢው ጀመረ። በበቂ ሁኔታ መረጃዎች ተሰባሰቡ። ከአካባቢው ሰዎች ለድርጊቱ መፈጸም መነሻ ይሆናሉ የተባሉ ምክንያቶች አንድ በአንድ ተዘረዘሩ፡፡
ፖሊስ ወይዘሮዋ በአካባቢው አልታዩም ከተባለበት ጊዜ አንቶ የግለሰቡን መሰወር ከጥርጣሬ አስገብቶ ፍለጋውን ቀጥሏል። ያለአንዳች ምክንያት ለቀናት እንደማይጠፋ ገምቶም እርምጃውን አፋጥኗል።ነዋሪው በየዕለቱ እየተሰበሰበ ይወያያል። ተፈላጊውን በእጅ ለማድረግ ፎቶግራፉን መያዝ እንደሚያስፈልግ አምኖም በየስልኩ ምስሉን ለመፈለግ ዘዴና መላ ፈጥሯል፡፡
ከመንደሩ ወጥቶ ዙሪያገባ አካባቢዎችን ማሰስ የጀመረው የምርመራ ቡድን ተፈላጊው ከአንድ ቀን በፊት ሀራ ገበያ የሚሸጡ ጥጆችን ይዞ መታየቱን ሰማ።ይህን መረጃ መነሻ አድርጎም ቆቦ፣ ትግራይና አጎራባች አካባቢዎች ሊሻገር ይችላል የሚለውን ግምት አጠናክሮ የአሰሳ ቡድኑን አሰማራ።
አዲስ መረጃ…
በድንገት ከፖሊስ ጆሮ የደረሰው አዲስ መረጃ የምርመራ ቡድኑን አባላት አንቅቷል።ግለሰቡ በትውልድ አገሩ ጉባ ላፍቶ ወረዳ ልዩ ስሙ ‹‹ላይ ገዶ›› ከተባለ ስፍራ እንደታየ መረጃ ተገኝቷል። ፖሊስ የኅብረተሰቡን የጸጥታ አካላትንና የወረዳውን ትብብር አጣምሮ ፍለጋውን ቀጠለ። እንደተባለው ግለሰቡ በስፍራው ከታየ ቦታው ድረሰ ሄዶ ለመያዝ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።ከፍተኛ ኃላፊነትን በሚጠይቀው የዘመቻ ሥራ እያንዳንዱ ባለድርሻ ኃላፊነቱን በጥንቃቄ መወጣት አለበት፡፡
ፖሊስ የደረሰውን መረጃ ከተፈላጊው ግለሰብ ጋር እያገናዘበ ወደጉባለፍቶ ወረዳ አቀና።ወረዳው ወንጀሉ ከተፈጸመበት ወረዳ ቀጥሎ የሚገኝ አካባቢ ነው።የአሰሳ ቡድኑ አባላት ከወረዳ ከተማው ደርሰው አስፈላጊውን የሥራ ክፍፍል ወሰዱ።ግለሰቡ ‹‹ይገኝበታል›› ከተባለበት ስፍራ ደርሰው እንዴት እንደሚይዙት ስልትና ዘዴ ቀየሱ። ሁሉም የተሰጣቸውን ግዳጅ ተቀብለው ሲለያዩ ከታላቅ ሞራልና ኃላፊነት ጋር ነበር፡፡
የንስር ዓይኖች…
ውሏቸውን በተፈላጊው ግለሰብ የትውልድ ስፍራ ያደረጉት አሳሽ ፖሊሶች አመሻሹን ወደቤተሰቦቹ መንደር ዘልቀው ስፍራ ይዘው አድፍጠዋል። ግለሰቡን ሲገባ አልያም ሲወጣ ጠብቀው ለመያዝ ራሳቸውን መደበቅና ምስጢር መጠበቅ አለባቸው። ጸጉረ ልውጥ መሆናቸውን ያዩ ሌሎች ተመልካቾች እንዳይጠረጥሯቸው ለመመሳሰል ሞክረዋል፡፡ አሁን ምሽቱ እየገፋ ጨለማው እየበረታ ነው።
የወንጀል መከላከል ቡድኑ በተፈላጊው ቤተሰቦች መኖሪያ እንደከበበ ነው። እስካሁን ተጠርጣሪውን ለመያዝ የሚያስችሉ ምልክቶች የሉም። ስፍራው ያለአንዳች ኮሽታ በጭርታ ዘልቋል። በተጠንቀቅ ዘብ የቆሙት ፖሊሶች እንደንስር ዓይን የሚወረወር ዕይታቸውን ሳያረግቡ በግቢው ላይ አፍጥጠዋል፡፡
ብርዱና የሌቱ ውርጭ ያልበገራቸው ብር ቱዎች በጥንካሬ እንደቆሙ ሌሊቱ ነግቶ ወፎች ተንጫጭተዋል። አሁን ባለንስር ዓይኖቹ ይበልጥ ነቅተው እንደ ነብር ማድባታቸውን ይዘዋል። ፖሊሶቹ ከተከበበው ግቢ አንድ አቅጣጫ የተለየ ነገር ውል ሲል አስተውለዋል።እርምጃቸውን አፍጥነው፣ ጆሯቸውን ተክለው ወደጠረጠሩት ስፍራ ተጠግተዋል፡፡
ከግቢው አንድ አቅጣጫ ውል ያለው ነገር ለፖሊሶቹ በግልጽ ታይቷቸዋል። ታዳኙ ሙሉጌታ ነበር። ፖሊሶቹ በሚገርም ፍጥነት መሣሪያቸውን ደግነው አካባቢውን በስልት ሸፈኑት። ዙሪያውን እንደተከበበ የገባው ተፈላጊ ከበባውን አምልጦ ለመውጣት ሩጫውን ቀጠለ። ፖሊሶቹ መሣሪያቸውን ሽቅብ እንደያዙ ‹‹እጅ ወደላይ፣ እጅ ወደላይ›› እያሉ ተጠጉት። የሰማቸው አይመስልም።በመጣበት ፍጥነት እየሮጠ አጥሩን ለመዝለል ሞከረ፡፡
ፖሊሶቹ የዘላዩን አቅጣጫ ተከትለው ወደ ሰማይ አከታትለው ተኮሱ።ተፈላጊው ተስፋ አልቆረጠም። የሞትሞቱን እየሮጠ ከበባውን ለመጣስ ጥረቱን ቀጠለ። ሙከራው ብዙ አልዘለቀም።እንዳሰበው ርቆ ሳይርቅ፣ በፖሊሶቹ ብርቱ ክንድ አርፎ በጥብቅ ካቴና ታሰረ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
አሁን ተፈላጊው ግለሰብ ጠፍቶ ከተደበቀበት ታስሶ በቁጥጥር ስር ውሏል።ፖሊሶች ተጠርጣሪውን ይዘው እንደተመለሱ ቃሉን ይሰጥ ዘንድ ጥያቄ አቀረቡለት።ሙሉጌታ አድማሱ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ አልካደም።ከአሰሪው እማወራ ጋር ለሁለት ዓመታት በአሰሪና ሠራተኛ ደንብ ተስማምተው አብረው ሲኖሩ ቆይተዋል፡፡
ተቀጣሪው ሥራውን ሲጀምር በዓመት ስድስት ሺህ ብር ይከፈለው ነበር። በቀጣዩ ዓመትም የአንድ ሺህ ብር ጭማሪ አግኝቷል። ሌላ ዓመት ሲጨምር የጠየቀው የደመወዝ ጭማሪ ግን ከአሰሪው ጋር አላስማማቸውም።ወይዘሮዋ የሚከፈለው ገንዘብ በቂ እንደሆነና ከዚህ በላይ መጨመር እንደማይችሉ አስታውቀውታል፡፡
ሙሉጌታ ከአሰሪው የተሰጠው ምላሽ እጅግ አበሳጭቶታል። አብሯቸው ቢኖርም በሁኔታው ከልብ እየተናደደ ነው። ይህን ስሜቱን ይዞ ሀራ ገበያ የዋለው ግለሰብ መጠጥ ጠጥቶ ማምሻውን ሲመለስ እናትና ልጁን ለመግደል እንዳልሳሳና በወቅቱ ድርጊቱን ሲፈጽም የሚያደርገውን እንደማያውቅ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
የሀሮ ፖሊስ ንዑስ ጣቢያ የግለሰቡን መዝገብ አደራጅቶ ወደሚመለከተው ለማሳለፍ በቂ መረጃዎችን በማስረጃዎች አስደግፎ በአግባቡ ሰነደ።ዶሴውን በወጉ አዘጋጅቶም ክስ እንዲመሠረት ወደ ዓቃቤሕግ መዝገብ አሳለፈ።ዓቃቤሕግ የቀረበለትን ማስረጃ በመመርመር ግለሰቡን ፍርድቤት አቁሞ ፍትሕ ይበየን ዘንድ ተከራከረ።
ውሳኔ…
የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሽ ሙሉጌታ አድማሱ ላይ የተከፈተውን የክስ መዝገብ ሲመረምር ቆይቷል፡፡ ተከሳሹ ወይዘሮዋንና ጨቅላ ልጃቸውን በጭካኔ መግደሉ በማስረጃዎች ተደግፎም ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ግለሰቡ ወንጀሉን በትክክል መፈጸሙን ባለመካዱና በማመኑ ለመጨረሻ ውሳኔ ፍርድቤቱ በቀጠሮ ተገኝቷል፡፡
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድቤት በሰየመው የመጨረሻ ችሎት ፍርዱን ለመስማት የተገኙት ታዳሚዎች የሆነውን እያስታወሱ፣ በተፈጸመው ድርጊት እያዘኑ ውሳኔውን ይጠብቃሉ፡፡ ችሎቱ በተከሳሹ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ጊዜ አልወሰደም፡፡ የቀረበለትን መረጃ ከማስረጃዎች አገናዝቦ ወር ባልሞላ ጊዜ ለውሳኔ ደርሷል፡፡ ፍርድቤቱ በዕለቱ በሰጠው ፍርድም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሃያ አምስት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014