ከአፍሪካ ሕዝብ 77 በመቶው ዕድሜው ከ35 ዓመት በታች የሆነ ወጣት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንደኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታም የወጣቱ ቁጥር ከዚህ አይተናነስም። የወጣቱ ቁጥር እንደ ብዛቱ በአንድ አገር ላይ ያለው አስተዋፅኦም የጎላ ነው። የወጣቱ ችግርም በሥራ አጥነት ከመሰቃየት ጀምሮ በርካታ ነው። የሴት ወጣቶች ችግር ደግሞ በእጅጉ ያይላል።
በተለይ ሴት ወጣቶች ገና በታዳጊነታቸው፣ በ10ና 15 ለጋ ዕድሜያቸው ከማግባት ጀምሮ አባት የሌለው ልጅ የማሳደግ ሃላፊነት ይወድቅባቸዋል። ወንዱም ሆነ ሴቷ የመማርና ተምረው የመሥራት ዕድሉን የሚያጡበት ጊዜ ቀላል አይደለም። ሆኖም በተፈጥሮና በማህበረሰቡ ዘንድ ለሴትነት ካለው አመለካከት ጋር ተዳምሮ በሴት ወጣቶች ላይ የሚያርፈው ጫና ይበዛል። እንደ “አንዲ ማማ” አይነት ድርጅቶች ደግሞ እነዚህን መሰል ችግሮች ለመፍታትና የወጣቶችን ሸክም ለማቃለል የተፈጠሩ ናቸው።
ገቢያቸው በወር ከሁለት ዶላር ወይም ከመቶ ብር በታች የሆነና ይሄንንም የማግኘቱ ዕድል የሌላቸውን እናቶች ያቀፈው “አንዲ ማማ” ስለወጣቶች ችግርም ግድ ብሎታል። አምስቱ የአንዲ ማማ መሥራቾች በዕድሜ ከ20 እስከ 35 ዓመት መሆናቸው የበለጠ አግዟቸው ነው ወደ ሥራ የገቡት።
እኛም ለዛሬ ወጣቶች አብዝተው ስለራሳቸው በሚያስቡበት ዕድሜ ዘመን ላይ ቢሆኑም ስለ ዕድሜ አቻዎቻቸው ማሰብ ግድ እንደሚላቸው የአንዲ ማማ ፕሮጀክት መሥራቾቹ ወጣቶች አርአያ ይሆናሉ በሚል በጎ አሳቢ ወጣቶቹንና የበጎ ዓላማ ተጠቃሚ ወጣቶችን ተሞክሮ ልናጋራችሁ ወድደናል።
ወጣት አንዱዓለም ኃብተጊዮርጊስ የ”አንዲ ማማ” ፕሮጀክት ሊቀመንበር ነው። እንደገለፀልን ከሆነ ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ እናቶች ላይ ቢያተኩርም፤ እናቶች የሚኖሩት ለልጆቻቸው እንደመሆኑ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩና እንዲያበቁ የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ማስቻል ነው ዋና ዓላማው። አገር ውስጥ ያለውን የእናቶችን ችግር በጥልቀት መረዳትን መነሻ አድርገው የመሰረቱት ይሄው ፕሮጀክት እናቶችን ይንከባከባል። ለትርፍ እንደመቋቋሙም መልሶ ወረቀትን በመጠቀም ተግባሩ ለበርካታ ወጣቶች በተለያየ መልኩ የስራ ዕድል እየፈጠረም ይገኛል።
እንደ አንዱዓለም ገለፃ ወጣቶቹ ስለወጣቱ እንዲያስቡ ያደረጋቸው መነሻ ትምህርት ጨርሶ ሥራ ዕድል አጥቶ ሲንከራተት ከማየታቸው ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ነው። የሚበሉትና የሚኖሩበት አጥተው ሌላው ቀርቶ የሚለብሱት ሁሉ አጥተው ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ወጣቶች መኖራቸው ቀደምና ጠለቅ ያለ የትምህርትና የሥራ ግንኙነት ለነበራቸው የአንዲ ማማ መሥራቾች ስለወጣቱ ችግርም በየፊናቸው በጥልቀት እንዲያስቡ መነሻ ሆኗቸው ቆይቷል። የቀደመ ትውውቅ ያላቸው እንደመሆናቸው ታዲያ ሰብሰብ ብለው በየውስጣቸው ስለወጣቱ ችግር እንዲወያዩ አደረጋቸው።
በተለይ ወጣት አንዱዓለም በአንድ ትምህርት ቤት ከጓደኞቹ ጋር ኳስ በሚጫወትበት ጊዜ የሰማውና ያየው ልቡን ነካው። ለተጫወቱበት ሜዳ መክፈል ግድ ነውና ለተጫወቱበት ሜዳ ለመክፈል የትምህርት ቤቱን አመራሮች ይጠይቃሉ። እናቶቻቸው ኑሮ ከብዷቸው ምግብ መብላት የማይችሉ ተማሪዎች አሉና ለእነዚህ በወር 400 ብር ስጧቸው ብለው ይመልሱላቸዋል። “እንዴት አንድ ተማሪ 400 ብር አጥቶ ምግብ ሳይበላ ይውላል? አንድ እናትስ እንዴት ይሄን የገዛ ልጇን መመገብ የሚያስችል አቅም እንኳን ታጣለች?” የሚለው መነሻ ሆናቸውና “አንዲ ማማ” ፕሮጀክትን መሰረቱ።
የእነዚህን ታዳጊ ወጣቶች እናቶችን ብናበለፅግ ልጆቹም ይበለፅጋሉ የሚል ዕይታ ተይዞም “አንዲ ማማ” ጥቅም ላይ የዋሉ ወረቀቶችን ሰብስቦና መልሶ ጥቅም ላይ ለሚያውሉ አካላት ወደ ማቅረብ ሥራው ተገባ። አምስቱ ወጣቶች የእናትን ድንቅነት ያነገበው ሀሳብ ቀድሞ በየውስጣቸው ይብላላ የነበረ ነበርና ተግባብተውበት ለመጓዝ ችግር አልነበረባቸውም። በዚህ ላይ ቀድሞ ትውውቅ ነበራቸውና ሀሳቡን በጋራ አዳብረውት ፈጥነው ነው ወደ ሥራ የገቡት። ወደ ሥራ ከገቡ አንድ ዓመት ከአራት ወራቶች አስቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና መጻሕፍትን ጨምሮ በብዙ ቶን የሚቆጠሩ የተለያየ ቀለም ያላቸውንና የሌላቸውን ወረቀቶች ከየተቋማቱ በመሰብሰብ በመልሶ ጥቅም ላይ ለሚያውሉ አካላት ማቅረብ ችለዋል። ወረቀት የሚገኝበት መንገድ ልክ ባለመሆኑ በተቋማት ዘንድ የባሕርይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ግንዛቤ ፈጠራ ላይም ሲሰሩ ቆይተዋል። ግንዛቤው ወረቀትን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል በየጊዜው ሀገራችን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባውን 200ሺህ ቶን ወረቀት የሚተካ ትልቅ ሀብት በመሆኑ ቆሼ መጣል፣ ማቃጠልና በውሃና በሌሎች ነገሮች ማበላሸት ተገቢ አለመሆኑን ማመላከት ላይ ያተኮረ ነበር። ወደ ትላልቅ ኢንዱስትሪ የሚለወጥና የገቢ ማስገኛ ምንጭ በመሆን እናቶችና ወጣቶችን የሚያበለፅግ ለመሆኑም ሥራቸውን ማሳያ አድርገው ሲያብራሩለት ነው የከረሙት።
ወረቀት በመሰብሰቡ፣ የተሰበሰበውን ወረቀት መልሶ እፁብ ድንቅ የሚባልላቸውንና የተዋቡ የቤት ውስጥና የቢሮ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶችን ጥቅም ላይ በማዋልና ለገበያ በማቅረቡ ለ63 እናቶች እንዲሁም ለ500ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የገቢ ምንጭ ለማድረግም ሲሰሩበት ነው አንድ ዓመት ከአራት ወራቸውን ያስቆጠሩት። የወጣቶቹ ሥራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዕድሜ አቻዎቻቸውን ተስፋ አለምልሟል። በአንድ ዓመት ውስጥ 1ሺህ 50 እናቶችን፤ እንዲሁም 500ሺህ የዕድሜ አቻዎቻቸው የሆኑ ወጣቶችን ለመድረስ የሚያስችለውን ሀሳብ በእቅድ ደረጃ መሰነቅ አስችሎታል። በአንዲ ማማ እናቶችም፣ ወጣቶችም በዚህ ሥራ በተሳትፏቸው መጠን ገቢ ያገኛሉ። እናቶች በእናትነት አምባሳደርነታቸው ብቻ ቁጭ ብለው ይጦሩበታል። የሚያማምሩትና ዋጋቸው እጅግ ውድ የሆነውን እንደ አበባ ማስቀመቻ፣ መመገቢያና የመሳሰሉትን የቤት ውስጥና ሌሎች መገልገያ ቁሳቁሶችን በማምረቱ ሂደት እናቶች ብቻ ሳይሆን በርካታ ወንድና ሴት ወጣቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል።
የ29 ዓመት ወጣቷ ብርቱካን አድማስ እንዲህ ዓይነቱን የስራ ዕድል አንዲ ማማ ከፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል አንዷ ነች። ብርቱካን በዚህ የወጣትነት ዕድሜ ዘመንዋ በበርካታ ነገሮች ተፈትናና ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። ተወልዳ ያደገችው ደቡብ ጎንደር፣ ፋርጣ ወረዳ፣ ቱማቦ በሚባል አካባቢ ነው። ወደ አዲስ አበባ የመጣችው በ15 ዓመቷ ሲሆን ያመጣቻት አስተምራታለሁ ብላ አክስቷ ነበረች። ሆኖም የቤት ሰራተኛ አድርጋ ስላስቀረቻት የዚህ የዚህ በክፍያ አልሰራም ወይ በሚል በየሰው ቤት እየሰራች በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከ ስምንተኛ ክፍል እራሷን አስተምራለች። ሆኖም ጽኑ የትምህርት ፍላጎት ቢኖራትም በሰው ቤት ሥራ ከዚህ በላይ መማር አልቻለችም። ኑሮ ሲከብዳት በሕገወጥ ደላላ አማካኝነት ለሥራ ቤሩት ሄደች። ስትሄድ በቤት ውስጥ ሥራ ያጠራቀመችውን ብር ለሁለት ዓመት ቆይታዋ ግማሽ ክፍያ ዘጠኝ ሺህ ብር ከፍላ ነበር። ከሄደች በኋላም ቀሪውን ዕዳዋን ለሕገወጡ ደላላ ከፍላ ጨርሳለች። ሆኖም ሥራው ፍፁም አልተመቻትም። ዘጠኝ ሺህ ብሩን አገሬ ብሰራበትስ ብላም ተቆጭታ ነበር። ከማመናጨቅ ጀምሮ በስድብና ድብደባ የተሞላ በመሆኑ በአንድ ዓመት ከ10 ወሯ ጠፍታ ወደ አገሯ ተመለሰች።
ተመልሳ ስትመጣ ምንው ባልተመለስኩ እስከማለት የሚያደርስ ከበድ ከበድ ችግሮች ፈትንዋታል። ሥራ ከማጣት ባሻገር ለግለሰብ የምትከፍለው የቤት ኪራይ እስከማጣት ደርሳለች። ይሄም አንሷት ለልጇ የምትሰጠው ቁራሽ አጥታም ነበር። አንዲ ማማ የደረሰላት በዚህ ችግሯ ወቅት ነው። የኮልፌ ቀራኖዎ ክፍለ ከተማ ነዋሪ በመሆንዋ ወደ አንዲ የገባችው በወረዳው አማካኝነት በ”የደሃ ደሃ” ተመልምላ ነው። በአንዲ ማማ ታቅፋ መሥራት ከጀመረች ስምንት ወር ሆንዋታል። ወደ ሥራው የገባችው የአንድ ወር ስልጠና ወስዳ ነው። በወር ውስጥ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል ወረቀት ተመዝኖ ይሠጣትና ትጠቀልላለች። የመመግቢያ ሣህኖችና የቆሻሻ ቅርጫት እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን ትሰራለች። በወር እስከ 1ሺህ 500 ኪሎ የሰራችበት ወቅት አለ። በበኩልዋ የሥራ ዕድሉን በማግኘትዋ ወደ ተሻለ ሕይወት ተሸጋግሪያለሁ ብላ ታምናለች። ባለቤትዋ እያገዛት ጭምር በወር 2ሺህ ብር ለቤት ኪራይ እየከፈለች ልጅዋን ማስተማርና ማሳደግ ችላለች። አንዲ ታላቅ ራዕይ ይዞ በመነሳቱም ተስፋዋ በእጅጉ ለምልሟል።
ሌላዋ የ24 ዓመት ወጣት የሺሀረግ ፍትጉ ስትሆን በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል ያገኘች ነች። ከዚህ ዕድሜዋ ስምንቱን ዓመታት በሰው ቤት ሥራ ነው ያሳለፈችው። እንጀራ እናቷና አባቷ የራሳቸውን ኑሮ ነው የሚኖሩት። ሰው ቤት እየሰራች እስከ ስምንተኛ ክፍል ብትማርም ከባዱ የድህነት ጫና ከዚህ በላይ መግፋት አላስቻላትም። ምግብ ቆልፈውባት ሄዳው ምትፈልገውን ሳታገኝ ብዙ መከራዎችን በማለፍ ነው የእስካሁኑ ዕድሜዋን ያሳለፈችው። በሰው ቤት ሥራ ሁሉ ነገር ተቆጥሮና ተቆልፎ ነው የሚኬደው። በአንዲ ማማ ከታቀፈች ሰባት ወሯ ነው። አንድ ኪሎ ሲጠቀለል 100 ብር፤ ሲረከቡ ደግሞ 1ሺህ 200 ብር ይከፍሏቸዋል። በሚያዝያ ወር ብቻ 3ሺህ 700 ብር አግኝታለች። 2ሺህ 200 ብሩን ለቤት ኪራይ ትከፍላለች። ባለቤቷም ያግዛታል። ሆኖም አሁን ላይ ከቀድሞው በእጅጉ የተሻለ ኑሮ እየኖረች ነው።
ወጣት መቅደስ ተሾመ የአንዲ ማማ መሥራችና ምክትል ፕሬዚዳንት ናት።በአካወንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች። የተለያዩ የሙያ ትምህርቶችንም ተምራለች። ከትምህርት ቤት ስትወጣ ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተቀጥራ ስትሰራም ቆይታለች። መቅደስ በዚህ መካከል ነበር ውስጧ ሴቶችን አግዢ እያለ ለሚጠይቃት ጥያቄ መልስ መስጠት እንዳለባት ያሰበችው። በእሷ ዕድሜ ያሉ ወጣት ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ለማገዝ ብዙም ያሉበት የዕድሜ ደረጃ ይፈቅዳል ተብሎ ባይታሰብም ይሄንኑ በውስጧ ተፀንሶ ይወተውታት የነበረውን ሀሳብ መሰረት በማድረግ ከቀሩት ከአራቱ የአንዲ ማማ መሥራቾች ጋር ተወያየችበት። አሁን ለሌሎች የዕድሜ አቻዎችዋ ሥራ በመፍጠርዋ እርካታ ይሰማታል።
ወጣት ምዕራፍ ገ/እግዚአብሄር የአንዲ ማማ መሥራችና የኮሚዩኒቲ ኢምፓወርመንት ምክትል ፕሬዚዳንት ናት። በዚሁ ዓመት 30ኛ ዓመቷን ትይዛለች። ወጣቷ በዋናነት የምትሰራው ሴቶች ላይ ሲሆን ሴቶች በኢኮኖሚ መብቃት አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም አላት። ለቤተሰብና ለአካባቢ የሚደርሰው አንድ እናት ስትረዳ ነው። አንድ እናት ከቤት ተረዳች ማለት ሙሉ ቤተሰብ ተረዳ ማለት ነው። ይሄን በዋናነት ይዛ ምን ያህል እናቶችን ረዳች የሚለው ላይ ነው የምታተኩረው፤ እየተሯሯጠች ያለችው ይህንኑ ከማሳካት አኳያ ነው።
የአንዲ ማማ አባላት አሁን ላይ 63 እናቶችን በኢኮኖሚ እያበቁ ሲሆን መድረስ የሚፈልጉት 1ሺህ 50 እናቶችን ነው። እነዚህን መድረስ 1ሺህ 50 ቤተሰብ መድረስ ማለት። አንድ በኢኮኖሚ በቃች ማለት ከልጆችና ባሏ ጀምራ ቤተሰብኗ ረዳች ማለት ነው።
እዚህ ለመድረስ ጠንክረው እየሰሩ ነው። ፓኬጆቻቸው ለየትና በተን ያሉ ሲሆኑ አንደኛው እንደ ማርኬቲንግ አምባሳደርነታቸው እናቶች ምንም ነገር ሥራው ላይ ሳይገቡ ከቤታቸው ሆነው ይደገፋሉ። ወረቀት ከየተቋማቱ የሚሰበስቡ የጽዳት ሠራተኞችም እንዲሁ ደሞዛቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የሚደገፉበት አለ። ‹‹ልንሰራበት ያሰብነው ነገር ሩቅ አይደለምፐ፤ አጠገባችን ነው ያለው›› የምትለዋ ወጣት ምዕራፍ በተለይ ትኩስ ጉልበቱም፣ ጊዜውም፣ ዕውቀቱም ያላቸው ወጣቶች ከዚህ አጠገባቸው ላይ ካለው ነገር ተነስተው፤ በተለይ ከችግር መውጫ ቀዳዳው የጠፋባቸውን የዕድሜ አቻ ወጣቶችን፤ በተለይም ሴቶችንና እናቶችን አካባቢውን ማገዝ እንደሚቻል “አንዲ ማማ”ን ማሳያ አድርጋ ሀሳቧን አሳርጋለች። ሰላም!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014