የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ከተነገረ ቆይቷል፡፡ ኦሊምፒኩ ይካሄዳል ተብሎ ከታሰበበት ጊዜ ቢዘገይም በቅርቡ እንደሚካሄድ ግን ተጠቁሟል። ለዚህም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚወክሏቸውን ወጣት ስፖርተኞች ለመምረጥ የየራሳቸውን ውድድር ማድረግ ጀምረዋል።
ኦሮሚያ ክልል የኦሮሚያ ወጣቶች ኦሊምፒክን በሻሸመኔ ከተማ ከትናንት በስቲያ ማካሄድ በመጀመር ቀዳሚ ሆኗል። ክልሉ በኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ የሚሳተፉ ስፖርተኞቹን ውጤታማ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅቶችን እንደጀመረም ታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ከድር እንዳልካቸው ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ የኦሮሚያ ወጣቶች ኦሊምፒክ እየተካሄደ የሚገኘው በኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ክልሉን ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ ከማድረግ ባሻገር ወጣት ስፖርተኞች በአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ የሚሳተፉበትን እድል እንዲያገኙ ነው።
ይህ የወጣቶች ኦሊምፒክ በአገር አቀፍ ደረጃም ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በታዳጊና ወጣቶች ላይ በመሥራት ተተኪና ስኬታማ ስፖርተኞችን የማፍራት ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።
“ታዳጊ ወጣቶች ላይ ካልተሠራ እንደ ሃገር በዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ ስፖርተኞችን ማፍራት ይከብዳል” ያሉት አቶ ከድር፣ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድርን ማካሄድ እንዳስፈለገ አስረድተዋል። የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ይህም ተጨባጭ ውጤት እየታየበት መሆኑን ከዚህ ቀደም ክልሉ ያካሄደውን የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በምሳሌነት በማንሳት አብራርተዋል። በዚህ የወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድርም ክልሉን እንዲሁም ሃገርን ውጤታማ የሚያደርጉ ወጣቶች በብዛት ሊገኙ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የውድድርና ስልጠና ዳይሬክተር መኮንን በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ ኦሮሚያን ወክለው ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶችን ለመምረጥ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ስፖርተኞች ብቻ በሻሸመኔው ውድድር እየተካፈሉ ይገኛሉ።
ውድድሩ በአፍሪካና በዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክም ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት ወጣት ስፖርተኞችም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታልሞ እየተካሄደም እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ይህ ውድድር በጀት እንደ ልብ በሌለበትና በአጭር ጊዜ ዝግጅት መካሄዱ ፈተና እንደሆነም ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ወጣቶች ኦሊምፒክ የምታዘጋጅ ሃገር በመሆኗ በጥድፊያም ቢሆን ክልሉ የራሱን ውድድር እያደረገ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሃገር አቀፉ የወጣቶች ኦሊምፒክ እንደሚካሄድ ባለፈው ዓመት ቢያሳውቅም ሳይካሄድ ዘግይቷል። ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ውድድሩ የሚካሄድበትን ትክክለኛ ጊዜ ቢያሳውቅና ክልሎች በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ውድድር ቢገቡ የተሻለ ይሆን ነበር ባለው አጭር ጊዜ የተሻለ ውድድር ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ ነው።
በታዳጊና ወጣቶች ውድድሮች ላይ እንደምንጊዜውም የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፣ ክልሉ በጤና ምርመራ ወይም በሳይንሳዊ ዘዴ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል። ዓለም ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚጠቀመው ማግኔቲክ ሪሶናንስ ኢሜጂንግ(ኤም አር አይ) የተባለውን ቴክኖሎጂም ቢሆን ፍጹም እንዳልሆነ አስታውሰው፣ አገርን የሚወክሉ ወጣቶች ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከመሄዳቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም የራሱን የተለያዩ ማጣሪያዎች እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ለአስር ተከታታይ ቀናት በተለያዩ አስራ አምስት የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን፣ ከክልሉ የተውጣጡ ከሰላሳ በላይ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። ውድድሩ በደማቅ የተሳታፊዎች የሰልፍ ትርኢት ከተጀመረ በኋላ ባለ ሜዳው ሻሸመኔ ከተማና ባቱ ከተማ የመክፈቻ የእግር ኳስ ፍልሚያ አካሂደዋል። በዚህም ሻሸመኔ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በጨዋታ የበላይነት ከነበረው እንግዳው ቡድን ጋር ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። በእለቱ የወንዶች አስር ሺ ሜትር የአትሌቲክስ ውድድርም ፍጻሜ አግኝቷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም