የኢትዮጵያ ስፖርት በሚጠበቀውና በሚፈለገው ልክ ላለማደጉ በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል። ከእነዚህ መካከል ግን መንግስታዊ የሆነው የስፖርት ማህበራት አደረጃጀትና አሰራር ቀዳሚው ነው። በመሆኑም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተሰጠውን ኃላፊነት መሰረት በማድረግ ሲሰራበት የቆየውን አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት መመሪያ አሻሽሏል።
ሚኒስቴሩ የፌደራል መንግስት አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 37 1/ነ/ በተሰጠው ስልጣን፤ የስፖርት ማህበራቱን መመሪያ የማውጣት፣ የመመዝገብ፣ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት አለው። በዚህም መሰረት በብሄራዊ የስፖርት ሪፎርሙ እንዲሁም ስለስፖርት ባለሙያዎች በተመላከተው መሰረት መመሪያውን በማሻሻል ወደ ተግባር መቀየሩን አስታውቋል።
ተሻሽሎ የቀረበው ይህ መመሪያ ከመጽደቁ አስቀድሞ በተለያዩ የስፖርት ባለድርሻ አካላት ይፋ በማድረግና በማወያየት በሂደት እንዲዳብር ተደርጎ ነው። የስፖርት ማህበራት ማቋቋሚያ መመሪያ ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ 2014 ዓ.ም ጸድቆ ለሚመለከታቸው አካላት መሰራጨቱንም ሚኒስትሩ በመግለጫው ጠቁሟል።
የስፖርቱን መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍ ግማሽ መንገድ ይጓዛል የተባለለት መመሪያው፣ ተፈጻሚ የሚሆነውም በአገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ፓራሊምፒክ ኮሚቴዎች ላይ ነው። የደንቡ አስፈላጊነት፤ በዋናነት ከዚህ ቀደም የስፖርት ማህበራቱ አሰራርና አደረጃጀት ጥያቄ የሚያስነሳ ስለነበረ ነው። በመመሪያው አለመኖር ምክንያትም በምንም ዓይነት ሁኔታ ለሚፈጸም ጥፋት ተጠያቂነት ባለመኖሩ መመሪያው እንዲሻሻል ተደርጓል። መመሪያው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ልምድ እንዲሁም ከአገሪቷ ህግ አንጻር ተቀምሮ የተዘጋጀም ነው።
መመሪያው ትኩረቱን ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የፈቃድ አሰጣጥ ሲሆን፤ ሲሰራበት በቆየው ደንብና መመሪያ ውስጥ ያልነበረ አሰራር መሆኑ ታውቋል። ይኸውም የስፖርት ማህበራት እንዲያሟሉ የተቀመጠላቸውን መስፈርቶች በማሟላት ምዝገባ መፈጸም ነው። ከመስፈርቶቹ መካከልም በማህበራቱ ስር የሚገኙ የስፖርት ክለቦች ስያሜ፣ አርማ እና መዝሙሮች ከብሄር፣ ፖለቲካና ሃይማኖት ጋር የተያያዙ እንዳይሆኑ የሚያሳስብ ነው።
የፈቃድ እድሳቱ በየአራት ዓመቱ የሚደረግ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት እንዲጠናቀቅም እየተሰራ ይገኛል። ነገር ግን መስፈርቱን ያላሟሉ የስፖርት ማህበራት አራት ዓመት የማደራጃ ጊዜ ይሰጣቸዋል። ይህም ሆኖ መስፈርቱ መሟላት ካልቻለ ግን ማህበራቱ አገር አቀፍ ዕውቅና ማግኘት የማይችሉ በመሆኑ የክልል አሊያም ከተማ አስተዳደር ደረጃ ይቆያሉ።
አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራቱ በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ከመንግስት የሚያገኙት የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሁም የንብረት አጠቃቀም ኦዲት እንደሚደረግም ተመላክቷል። ከአቻ ተቋማት ጋር የሚኖራቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውን እንዲሁም ማህበራቱን የሚመሩት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስልጣንና የስራ ዘመን ላይም ሊሆኑ ይገባቸዋል ያላቸውን መመሪያው በግልጽ አስቀምጧል።
በአንጻሩ ማህበራቱ ዕውቅና እና እድሳት ሳያደርጉ ውድድሮችን ማካሄድ፣ በስራቸው የሚገኙ ክለቦች ስያሜ፣ አርማ እንዲሁም መዝሙር የብሄር፣ ሃይማኖትና ከሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነጻ ካልሆነ፣ በስፖርት ስም በሚደረጉ ተገቢ ያልሆኑ የውጪ ጉዞዎች ላይ፣… ክልከላ አድርጓል።
የተሻሻለውን መመሪያ ተከትሎም የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፤ የተሻሻለ መመሪያ የዓለም አቀፍ ስፖርት ማህበራት ህግ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ የተደነገገ መሆኑን ገልጸዋል። የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጨምሮ ማህበራቱን በሚመጥን ደረጃ የስፖርት አደረጃጀቱ እንዲከናወን የሚያደርግና የተናበበ መሆኑንም ነው ያስታወቁት። ከዚህም ባለፈ ማህበራቱ ስፖርቱን በመላ ሃገሪቷ እንዲያስፋፉና ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ የሚያደርግም ነው ብለዋል።
በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ ማህበራቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል። በርካታ አገር አቀፍ ማህበራት ትልልቅ ስያሜ እያላቸው ነገር ግን በሚመጥናቸው አደረጃጀት ያልነበሩበት፣ የስፖርት ስራ አስፈጻሚዎች ከተመረጡ በኋላ አለመውረድ፣ በዚህም ተጠያቂ የማይሆኑበት እንዲሁም ቡድን ከፍለው እርስ በእርስ ልዩነት የሚፈጥሩበት እንደነበር አብራርተዋል። በመሆኑም የተሻሻለውን መመሪያ ወደ ተግባር ከመለወጥ አንጻር ሚኒስቴሩ ያለውን ቁርጠኛነትም አረጋግጠዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም