ፀጉርን መሠራትና መዋብ በሴቶች በኩል እንደ ፋሽን እንደሚዘወተር መናገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው። ልዩ ልዩ የፀጉር አሠራር ስልቶችንና ፋሽን ጎልቶ የሚታየው የሴቶች ፀጉር አሠራር ላይ ነው። ነገር ግን እንደ ሴቶቹ የጎላና የሚዘወተር ባይሆንም የወንዶች የፀጉር አቆራረጥ ፋሽኖችንም የከተሜ ወጣቶች ሲከተሉ ይታያሉ።
በ1960ዎቹ መጨረሻ በአገራችን ከተሞች የነበሩ ወጣቶች ጎልማሶች ተማሪዎችና ሠራተኞች አፍሮ እና ጆንትራ የሚባሉ የፀጉር አቆራረጥ ስልቶች ይከተሉ እንደነበር በወቅቱ ከነበሩ ወጣቶች ጎልማሶች ፎቶግራፎች አይተናል፤ የዚያን ዘመን ትውልዶች ሲናገሩም ይሰማል።
እኛ በዘመናችን ያንን የፀጉር ስልት ብንከተል ሰው ሁሉ አራዳ ሳይሆን ወራዳ߹ በአራዳ ቋንቋ ፋራ ወይም ጅላጅል አድርጎ ሊቆጥረን ይችላል። ወንዶች በዘመናችን ፀጉራቸውን በጣም ቢያስረዝሙት የወቅቱ ፋሽን እና ስልት ስላልሆነ ሰውየው ምንሆነ ብለው ሊያስቡም ሊሰጉም ይችላሉ። የታዳጊዎች ቁንጮ የወጣቶች ጎፈሬ የጀግኖች ሹሩባ አሁን ፍሪዝ የምንለው ፋሽን ሆኖ የመጣው መፈረዝ በወንዶች ፀጉር ላይ ይታይ ነበር። የአፋር ወጣቶች እንደ ባህል ፀጉር በመፈረዝ ይታወቃሉ። ቢኒአሚር የሚባለውን የቀድሞ ቱሪዝም ኮሚሽን ፎቶ ያስታውሷል።
የወንዶች ፀጉር አሠራርና አቆራረጥ ምርጫ በከተሜዎች ዘንድ እንደ ሰዎቹ ፍላጎት እና እንደ ዕድሜያቸው የሚወሰን መሆኑን ያነጋገርናቸው የወንዶች ፀጉር አስተካካይ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔር ስብጥርና ብዙሃነት ጋር ሲታይ በአገሪቱ በርካታ የወንዶች ፀጉር አቆራረጥ ስልት እንዳለ ጠቅሰው፣ ይህን ግን የጸጉር አቆራረጥ በገጠር ከሚኖረው የአካባቢው የባህሉ ተከታይ ውጪ ከተሜዎች ሲተገብሩት እምብዛም አይታይም።
ከተሜዎች በፊልም እና በምዕራባውያን ስፖርት ጨዋታዎች ላይ ያዩትን የፀጉር አቆራረጥና አሠራር ስልት ፀጉራቸውን በመቆረጥና በመሠራት እንደ ፋሽን ለማድረግ ይሞክራሉ ይላሉ።
ወጣት በላይ ታደለ በመርካቶ አመዴ ገበያ መታጠፊያ አቅራቢያ ከሚገኘው ከረሜላ ህንፃ አራተኛ ፎቅ በወንዶች የውበት ሳሎን በፀጉር አስተካካይነት ይሠራል። የፀጉር አቆራረጥ እንደሰው ፍላጎት የሚወሰን ነው የሚለው በላይ፣ በተለይ ወጣቶቹ የተለያየ የፀጉር አቆራረጥ ስልቶችን ይመርጣሉ፤ ሙሉ ፍሪዝ ይሁንልኝ የሚሉ ወንዶችም አሉ ሲል ያብራራል። ፍሬንች ስታይል ብለው የሚመጡ አሉ። እንደ ባላቶኒ ዓይነት ይሠራልኝ የሚል አለ፤ ሥራው በእንደዚህ ዓይነት ስልት ነው በብዛት የሚሠራው ባይ ነው።
የፀጉር አቆራረጥ ስልቶችን ከበይነ መረብ ከቴሌግራም ከመሳሰሉት እናያለን የሚለው በላይ፤ እንደ ጭንቅላት አቀማመጣቸው መርጠን ፀጉራቸውን እያስተካከልን እናስውባለን ይላል። ያየነውን የፀጉር አቆራረጥ ስታይል ወይም ስልት እንተገብረዋለን። በኦን ላይንና በቪዲዮ እንደዚሁም በፎቶ እናሳያዋለን ከመረጠውና ከእሱ ጋር የሚሄድ ከሆነ ፀጉሩን እንደፍላጎቱ አስተካክለን እናስውባለን። ፍላጎት እና ምርጫ ካለው ያንን የፀጉር አቆራረጥ ስልት ይቀበላል። እናሳየዋለን ከወደደው አስተካክለን እንሠራለታለን ሲል ያብራራል።
በላይ የፀጉር አቆራረጥ ሥራውን የለመደውና ያዳበረው በልምድ ነው። ሠፈር ውስጥ ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው ጸጉር ይቆራረጡ ይስተካከሉም ነበር። አጠገባቸውም ፀጉር ቤት ስለነበር እዛ ልምዱን አግኝቷል፤ በዚህ ሥራ ወደ ስምንት ዓመት እንደሆነው ነው በላይ የሚናገረው።
እንደ በላይ ገለጻ፤ የፀጉር አቆራረጥ ስታይልና ፋሽን የሚከተሉት ቢያንስ ከ18 ዓመት እስከ 35 ዓመት የሚደርሱ ወጣቶች ናቸው። ከ35 ዓመት እና ቢያንስ እስከ 40ዎቹ ዓመት መጨረሻ የሚደርሱት ደግሞ ፍሪዝ ምናምን ወደሚለው ያደላሉ። ከዛ በላይ የሆኑት ደግሞ በብዛት መደበኛ የፀጉር አቆራረጥን ይመርጣሉ።
ሰው በወቅቱ ካለው ነገር ጋራ የሚዛመድ የፀጉር አቆራረጥ ስታይል ይከተላል። በኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን እንዲሁም ፊልም ድራማ የመሳሰሉት ነገሮች ሲመለከት ያንን የፀጉር አቆራረጥ ስልት ለመከተል ወደ እኛ መጥቶ ፀጉሩን ይስተካከላል ሲል ያብራራል።
እንደ በላይ ገለጻ፤ በብዛት በኳስ ጨዋታው አድንቀውት የፀጉር አሠራር ስልቱን የሚከተሉ በፊልም ላይ አይተው የወደዱትን ተዋናይ የፀጉር አቆራረጥ ስልት የሚከተሉ ብዙ ወጣቶች አሉ። አብዛኛዎቹ ግን በኳስ ጨዋታ ላይ ያደነቁትን ተጫዋች የፀጉር አሠራር እና አቆራረጥ ስልት ይከተላሉ።
በፊልም እና በኦን ላይንም አይተው ይሄን ፋሽን ተግብርልኝ ብለው በብዛት ፀጉራቸውን ለመሠራት ወደ ጸጉር ቤቱ እንደሚመጡም ይናገራል። ‹‹እኛም እያየን በሙያችን መሠረት እንደወደዱት እናስተካክልላቸዋለን ይላል።
አንዳንዶቹ የሚመርጡት የፀጉር አቆራረጥ ስልት አንዳንዴ ከጭንቅላታቸው ቅርጽ የማይሄድበትም ጊዜ እንዳለ ተናግሮ፣ ምርጫቸው ከራሳቸው ቅርጽ ጋር እንደማይሄድ እናስረዳቸውና ሌላ የአቆራረጥ ስልት እንዲመርጡ እንነግራቸዋለን ሲል ይናገራል። ለቅያሬ በመረጡት መሠረትም ከራሳቸው ቅርጽ ጋር እንዲዛመድ በማድረግ እንደሚያስተካክሏቸው ያብራራል።
በአራት ኪሎ ድንቅ ሥራ ህንፃ ሦስተኛ ፎቅ በአንቴ የወንዶች የውበት ሳሎን የሚሠራው አባይነህ ሽፈራው በፀጉር አስተካካይነት ከአስር ዓመት በላይ ሰርቷል፤ ሙያውን ያዳበረው በልምድ እንደሆነ ይናገራል። ሠፈር ውስጥ ፀጉር ቤት ስለነበረ በዚያ በተደጋጋሚ አስተካካዮቹ ለምሳ ሲወጡ ህፃናትም አዛውንትም ሲመጣ ፀጉር እያስተካከለ እንደለመደ ይገልፃል።
በብዛት ወደ እሱ ፀጉር ለመስተካከል የሚመጡት ወጣቶች እንደሆኑ የሚገልጸው አባይነህ፣ የሚመርጡት ቁርጥ በብዛት ዘመናዊ የሆነ ስልት መሆኑን ይናገራል። በአብዛኛው ፌድ የሚባል የአቆራረጥ ስልት እንደሚከተሉ ይናገራል፤ እሱም ልክ አንደ በላይ ትልልቆቹ መደበኛ የፀጉር አቆራረጥን እንደሚመርጡ ይጠቁማል።
አቆራረጡን ለማዘመን በይነመረብ እና ሌሎችንም በማየት ራሱን እያዳበረ እንደሆነ የሚገልፀው አባይነህ፤ ፀጉራቸውን ለማስተካከል ከሚመጡ ወጣቶች አብዛኞቹ በኳስ ጨዋታ፣ በፊልም፣ በድራማ ላይ በቴሌቪዥን ያዩትን የአቆራረጥ ስልት መርጠው አሳይተውኝ በፍላጎታቸው መሠረት አሰማምርላቸዋለሁ ሲል ያስረዳል። የግድ ባይመስልም በፊልምና በኳስ ላይ ያየሁትን እንደምርጫቸው አስተካክልላቸዋለሁ ባይ ነው።
ጸጉር አስተካካዮቹ ከቀለም ጋር በተያያዘ በብዛት የሚጠቀሙት ለፀጉር ማደግና መለስለስ የሚረዱ እንደ ቫይታሚን የሚያገለግሉ ቀለሞችን ነው። ለእዚህ ስራ አባይነህ እንደ ኮንዲሽነር ዓይነት ቀለምም ተመራጭ ነው፤ ይህም የበለጠ ፀጉሩን ያስውበዋል ያሳምረዋል። ካለው ፋሽን ጋር ደግሞ የበለጠ የሚሄድ እንደሆነም ነው የሚናገረው።
ብዙዎቹ ፀጉር አቆራረጥ የሚመርጡ ወጣቶች የራሳቸው ስልት እንዳላቸው ጠቅሶ፣ ይህንንም በኪስ ስልካቸው ይዘው ጸጉር ቤት እንደሚሄዱ ይናገራል። በዚህ በመረጡት የፀጉር አቆራረጥ ስልት መሠረት እንደሚስተካከልላቸው ነው አባይነህ የሚገልፀው።
በጸጉር አቆራረጥ አሁን ብዙ አማራጭ እንዳለም ገልጾ፣ የሚፈልጉትን የአቆራረጥ ስልት መርጠው ይዘው ለመምጣት ብዙም እንደማይቸገሩም ይናገራል። በግሉ የሚመርጠው የአቆራረጥ ስልት ብዙ እንዳልሆነም ተናግሮ፣ ደንበኛ ሁሌም ትክክል ነው ብሎ በማመን የወደዱትን የአቆራረጥ ስልት እንተገብራለን በማለት ያስረዳል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም