ልጆች እንዴት ናችሁ? ባለፈው ሳምንት በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ምን አይነት የአጠናን ዘዴ መከተል እንዳለባችሁ ነግሬያችሁ ነበር። የነገርኳችሁን የአጠናን ዘዴዎች ተግባራዊ እያደረጋችሁ እንደሆነም አምናለሁ። በዚህም ጥሩ ውጤት እንደም ታመጡ እተማመናለሁ።
ለመሆኑ ልጆች ከመማሪያ መጻሕፍቶቻችሁ ውጭ ሌሎችን ታነባላችሁ? የምታነቡስ ከሆነ ምን አይነት መጻሕፍትን ነው የምታነቡት? ይህን ጥያቄ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት። ምክንያቱም ልጆች በአገራችን የንባብ ባህል እምብዛም ስላልዳበረ ነው።
እናንተም ብትሆኑ በአብዛኛው የመማሪያ መጻሕፍትን እንጂ ሌሎችን ዘወትር ታነባላችሁ ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል። ይህን ስል ግን ሁላችሁንም አይደለም። ጥሩ የንባብ ልምድ ያላችሁ ልጆች እንደምትኖሩም አውቃለሁ።
ታዲያ ልጆች የማንበብ ልምድ ገና በልጅነት ነውና የሚጀምረው ይህንን ልምድ ከወዲሁ ማዳበር አለባችሁ። ጠንካራ የንባብ ባህል ካላችሁ ወደፊት የእውቀት ደሃ አትሆኑም። እዚሁ አገራችሁ ላይ ተቀምጣችሁ ዓለምን መዞር ትችላላችሁ። ለነገሮች ያላችሁ አተያይም ይሰፋል። የእውቀት አድማሳችሁም ይጨምራል።
ልጆች የተሻለ የንባብ ባህል በቤታቸው ማዳበር እንዲችሉ የሚከተሉትን ስምንት መንገዶች መከተል በቂ ስለመሆኑ የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ወላጆችም እነዚህን መንገዶች ተከትለው የልጆቻቸው የንባብ ባህል እንዲዳብር ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራሉ።
1ኛ. ንባብ የእለት ተእለት ልምዳቸው እንዲሆን እርዷቸው
ልጆች ንባብን የእለት ተእለት ልምዳችው ካደረጉ ልተወው ቢሉ እንኳን አይችሉም። ምክንያቱም ማንበብ ዘወትር ጠዋት ተነስተው ፊታቸውን ታጥበው ቁርሳቸውን
እንደሚበሉት አይነት ልምድ ስለሚሆን ነው። ይህ ልምድ እየዳበረ በሄደ ቁጥር ደግሞ በርካታ መጻሕፍትን የማንበብ አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል። አእምሯቸውም በእውቀት እየዳበረ ይሄዳል። ስለዚህ ልጆች ንባብን የእለት ተእለት ተግባራቸው ማድረግ አለባቸው። ለዚህም የወላጆቻው እገዛ ወሳኝ ነው።
2ኛ. ልጆቻችሁ ፊት ለፊት አንብቡ
ልጆች ብዙ ግዜ ወላጆቻቸው የሚያደርጓቸውን ነገሮች ነው መልሰው የሚያደርጉት። ወላጆች መልካም ነገሮችን ልጆቻቸው ፊት ባደረጉ ቁጥር ልጆችም መልሰው መልካም ተግባሩን ይደግሙታል። ከዚህ በተቃራኒ ልጆች ወላጆቻቸው መጥፎ ነገሮችን ፊት ለፊታችው ሲያደርጉ ይህንኑ የመድገም እድልቸው የሰፋ ነው።
ስለዚህ ወላጆች ልጆቻችሁ የንባብ ባህልን እንዲያዳብሩ ከፈለጋቸሁ እናንተ አንብባችሁ ለልጆቻችሁ ማሳየት ይኖርባችኋል። ልጆቻችሁ ፊት ለፊት መጽሐፍ ባነበባችሁ ቁጥር ልጆቻችሁ እናንት ያደረጋችሁትን ለማድረግ ይነሳሳሉ። በዚህም ሳያስቡት ከመጻሕፍት ጋር የቅርብ ጓደኛነት ይፈጥራሉ፡፡
3ኛ. የማንበቢያ ቦታ አመቻቹ
የንባብ ባህልን ለማዳበር የማንበቢያ ቦታ ለልጆች ወሳኝ ነው። ይህ ሲባል ታዲያ የልጆች ማንበቢያ ቦታ በጣምም ጠባብ በጣምም ደግሞ ሰፊ፤ እንዲሁም በመጻሕፍት በተጨናነቁ ሼልፎች መሞላት አለበት ማለት አይደለም። የማንበቢያ ቦታው ልጆች በሚተኙባቸው ክፍሎች አመቺ ቦታዎች ላይ ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ግን ክፍሉ ለልጆች ለማንበብ አመቺና በቂ ብርሃን ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ነው።
4ኛ. ወደ ቤተመጻሕፍት ይውሰዷቸው
ቤተመጻሕፍቶች አዳዲስ ሀሳቦችን፣ እውቀቶችን ብቻ ሳይሆን፤ አዳዲስ መጻሕፍቶችንና ደራሲዎቻቸውን የመተዋወቂያ ትልቅ ስፍራዎች ናቸው። አብዛኛዎቹም ለልጆች የሚሆኑ መጻሕፍትን ያሟሉ ናቸው። አንዳንዴም ከንባብ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ፕሮግራሞችን ሊያዘጋጁ ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻችሁን ወደዚህ የእውቀት ማእከል የምትወስዷቸው ከሆነ መልካም የንባብ ባህል የማዳበር እድል እንዲሰጣቸውና ሌሎች ልጆችም እነሱን አይተው ንባብ እንዲጀምሩ ያስችላቸዋል።
5ኛ. ልጆች የሚፈልጉትን እንዲያነቡ እድል ይስጧቸው
ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ቤተመጻሕፍት ሲወስዷቸው እዛ ያሉ መጻሕፍትን ተዘዋውረው እንዲያዩና የሚፈልጉትን መርጠው እንዲያነቡ እድል ሊሰጧቸው ይገባል። ብዙ ጊዜ ልጆች ሰው ሰጥቷቸው ሳይሆን በራሳቸው መርጠው ማንበብ ይፈልጋሉ። ከዚህ አንፃር ወላጆች ልጆቻቸው ትክክለኛውን የማንበብ ደረጃ ወይም ርእሰ ጉዳይ ካሳሰባቸው ከመጻሕፍት ክፍሎች ውስጥ እንዲመርጡ እድል መስጠት ያስፈልጋል።
6ኛ. እለት በእለት የንባብ አጋጣሚዎች ይፍጠሩ
ንባብ ጥሩ መፅሃፍ መርጦ ቁጭ ብሎ የማንበብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የእለት ተእለት ሕይወት አንዱ አካል ጭምርም ነው። ስለዚህ ወላጆች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ልጆች እንዲያነቡ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ግን መሆን ያለበት ልጆች እንዳይሰላቻቸው በማድረግ ነው። ለምሳሌ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በመኪና አልያም በእግር ሲንቀሳቀሱ በመንገድ ላይ የሚያዩቸውን የማስታወቂያ ፅሁፎች ምን እንደሆኑ በመጠየቅና እንዲያነቡ በማድረግ ንባብን እንዲወዱ ማድረግ ይችላሉ።
7ኛ. የሚወዷቸውን መጻሕፍት ደግመው እንዲያነቧቸው አድርጉ
እርስዎ አንድን መጻሕፍት ደጋግመው ሲያነቡ ሊሰለችዎት ይችላል። ነገር ግን ልጆች የሚወዱትን መፅሃፍ ደጋግመው ማንበብ ይወዳሉ። ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ያመለጡዋቸውን ነገሮች በመፅሐፉ ታሪክ ወይም በምስሎቹ ላይ ማየት ይወዳሉ። እንደገና ማንበብ በገጹ ላይ የሚያዩትን ቃል ከሚሰሙት ቃላት ጋር እንዲያገናኙም እድል ይሰጣቸዋል። ውለው አድረው፣ ልጅዎ መጽሐፉን ለእርስዎ ማንበብ ሊጀምርም ይችላሉ።
8ኛ. ስለንባብ ይወቁ
መምህር ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን እርሰዎ የልጅዎ የመጀመሪያ አስተማሪ ነዎት። በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ምን ምን የማንበብ ችሎታዎች እንደሚጠበቁ ትንሽ ማወቅ የልጅዎን ንባብ ለመደገፍ ይረዳዎታል። ከዚህ አንፃር ልጆች የንባብ ባህል እንዲያዳብሩ ከተፈለገ ወላጆች ስለንባብ የተወሰነ ፍንጭ ሊኖራቸው ይገባል፤ ማንበብም ይጠበቅባቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30 /2014