ሁለት አስርት አመታትን በተሻገረው የጋዜጠኝነትና የሕዝብ ግንኙነት ሙያዬ እንዳለፉት አራት አመታት በእጅጉ ተፈትኖ አያውቀውም። ለአገራችን ብዙኃን መገናኛዎችም እንደነዚህ አራት አመታት ያለ ፈተና ገጥሟቸው አያውቅም። በተለይ ሙያዊ ስነ ምግባራቸው አክብረው የሚሰሩ ሚዲያዎች በየዕለቱ የቱን መረጃ እንዴትና መቼ እንደሚዘግቡት በአርትኦት ኮሚቴ ስብሰባዎቻቸው መዋዘገባቸው የማይቀር ሆኖ ይሰማኛል። በተለይ የአዲስ ዘመንና የሪፖርተር ጋዜጦች ርዕሰ አንቀጽ ጸሐፍት ላይ ፈተናው የከፋ ነው። እኔም ለዛሬ የ”አዲስ ዘመን”፤ የ”ነጻ ሀሳብ” እየተሰናዳሁበት የነበረው አጀንዳ “ፖለቲካዊ መቤዠት” የሚል ነበር። ሆኖም በጎንደር፣ በስልጢ ዞን ወራቤ፣ በአዲስ አበባ በዓርቡ የመጨረሻ የጎዳና አፍጥር፤ በእለተ ኢድ አልፈጥር ደግሞ ደረጃው ቢለያይም በድሬዳዋና በሁሉም ክልሎች የተስተዋሉ ነውረኛ፣ አደገኛና አሳፋሪ አዝማሚያዎች የእጄን አጀንዳ አስጥለው በሰሞነኛ ጉዳዮች ላይ እንድጽፍና ወደኋላ ተመልሼ መጣጥፎቼን እንድቀራርም አስገድደውኛል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በከብቶች በረት ከተወለደበት ሰዓት ጀምሮ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል ከመሰደድ እስከ ሞት፤ ጽኑ መከራና ስቃይን ተቀብሏል። በተለይ በመጨረሻው ሰዓት ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የሆነ ስቃይ ፣ መከራ ፣ እንግልትና ግርፋትን ተቀብሎ ፤ በጲላጦስ ከወንበዴዎች ጋር ተፈርዶበት ፤ በቀራንዮ አደባባይ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ፤ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጥቶ አዳምንና ዘሩን ከሞት ወደ ሕይወት ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ፣ ከባርነት ወደ ነፃነት መልሶ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ፤ በማቴ 28፥5 ላይ “እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ወረደ፣ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፣ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና። እንደተናገረው ተነስቷልና በዚህ የለም ኑና እዩ አላቸው።” ተብሎ እንደተገለጸው፤ ብርሃንን ተጎናጽፎ በታላቅ ኃይልና ስልጣን በክብር ተነስቷል። በዚህ ታላቅና የክርስትና ራስ በሆነው የትንሳኤ ሰሞን ነው በጎንደር ለዛውም 44ቱ ታቦት ቅድስት ከተማ እየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ህያው ያደረገውና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው በወገኑ የተገደለው። በዚህ ያላፈርን ፣ ያላጠርንና መደበቂያ ያላጣን በምን እናፍራለን!?
ረመዳን በእስላማዊ ቀን አቆጣጠር ቅዱስ ቁራን ለነብዩ ሙሐመድ የተገለጠበት የተቀደሰ ዘጠነኛ ወር ነው። ከእስልምና አምስቱ አምዶች አንዱ የሆነው ጾም የሚያዝበት የተቀደሰ ወር ነው። የጀነት በር የሚከፈትበት፤ የጀሀነም ደጆች የሚጠረቀሙበት ልዩ ወር ነው። ጾም ከተፈታ በኋላ ያሉ ሶስት ተከታታይ ቀናት ወይም ሻዋል እንዲሁ የተባረኩ ናቸው። በዚህ ታላቅ ወር ነው በአዲስ አበባም በወራቤም አሳፋሪ ነውር ያየነው። ያ ልዩነት አንገታችንን የደፋነው ። “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት፤” ብለን ከመላው ዓለም እንግዳ ጠርተን በኢትዮጵያዊ ወግና ማዕረግ በክብር አስተናግደን መመለስ ሲገባን ያሳዘናቸው። እምነታችንን እንደማንኖረው ገመናችን የተጋለጠው። እርቃን የቀረው። በሁለቱም እምነቶች ያዋረዱን ጥቂቶቹ ቢሆኑም ሁላችንም በአንድም በሌላ በኩል ከደሙ ንጹሕ አይደለንም።
በእነዚህ ሰሞነኛ አገራዊ ነውሮች እንደገና ለማፈር፣ ለማጠርና መደበቂያ ለማጣት የግድ የጥቂት ግፈኞችን ማንነት መጋራት አያስፈልግም። የተገኙበትን ብሔርም ሆነ ሃይማኖት ስለማይወክሉ። በግሌ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋም እንደ አፍሪካዊም በሀፍረት አንገቴን ደፍቻለሁ። ከፍ ሲልም እንደ ሰው ቅስሜ ተሰብሯል። ሕመሙ አጥንቴን ዘልቆ ተሰምቶኛል። እንደ እግር እሳት ዕለት ዕለት ይለበልበኛል። ሆኖም ከእኔ ሕመም ስቃይና ሀፍረት በላይ የክልሉ ሕዝብ፣ መሪው ፓርቲ፣ ተፎካካሪዎችና አክቲቪስቶች በተፈፀመው አረመኔአዊ ድርጊት ይበልጥ አፍረዋል፤ ተዋርደዋል ብዬ አምናለሁ። ያላፈረ ቢኖር እሱ ሰውነቱን ይጠራጠር።
በጎንደር የሆነው ያሳፈረንንና ያሳዘነንን ያህል። የአዲስ አበባውና የወራቤው ያለ ልዩነት አሳፍሮናል። በሰማዕታት ሀውልት ላይ፣ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ፣ በመስጅዶች ፣ በዜጎችና በአገር ሀብትና ንብረት ላይ የጥፋት እጅ የሚያስነሳ ምን አይነት ሃይማኖታዊ ቀናዒ ነው !? በድሬዳዋና በሌሎች ክልሎችም የተስተዋሉ እኩይ ድርጊቶች አንገታችንን አስደፍተውናል። ይሄን ስል የሀፍረት ደረጃን ለማውጣት ወይም ሒሳብ ለመተሳሰብ አይደለም። መጠኑ ይነስም ይብዛም የእኔም ሆነ የእነሱ ሀፍረት አንድ ቦታ ላይ ይገናኛል ለማለት እንጂ። የሰሞኑን ኃፍረት ፣ ውርደት የሁላችንም ነው። የሀፍረታችን ፣ የውርደታችን ፣ የቅሌታችንና የነውራችን መጠን ይለያይ ይሆናል እንጂ እንደ ሕዝብ እንደአገር ሁላችንም ከሰውነት ተራ ወጥተናል፤ ጎለናል ፡፡
ጣት መቀሳሰሩና ታርጋ መለጣጠፉ ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ነጥብ ከማስቆጠር አንጻር ጥቅም ሊኖረው ይችላል። ይህ ግን ለአገርም ሆነ ለሕዝብ አይበጅም። ዘላቂ መፍትሔን አያመጣም። አሁን እሳት ከማጥፋትና ከዘመቻ ስራ ወጥተን ስትራቴጂካዊ መፍትሔ ላይ ማተኮር አለብን። ለመሆኑ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ መልሰን መላልሰን ለተንደረደርንባቸው የውርደት ቁልቁለቶች መግፍኤዎች ምንድናቸው!? ገለልተኛና ከስሜታዊነት የነፃ ተቋም (ለዛውም ካለን) በቀጣይ በጥናት የሚደርስበት ሆኖ ከዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች አራቱን እንደሚከተለው አነሳለሁ።
1ኛ . ትንትናችን በስሜት የተቃኘ መሆኑ፦
የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን/ መስራች አባል አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በዚያ ሰሞን “አርትስ” ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው “ትላንትም ሆነ ዛሬ እንደ አገር እንደ ሕዝብ የገጠሙንን ፈተናዎች ለመሻገር ሳይንሳዊ ጥልቅ ትንተና ያስፈልጋል። ትንተናው ግን በግዕብታዊነትና በስሜት ሊሆን አይገባም፡፡” ብለው ነበር። ዛሬ ለምንገኝበት ውርክብ የዳረገን የ60ዎቹ ትውልድም ሆነ እሱን ተከትለው የተቀፈቀፉ ነፃ አውጭ ፓርቲዎች በስሜትና በደም ፍላት ተመስርቶ የተደረገ ትንተናና የደረሰቡት የተሳሳተ ድምዳሜ ነው ማለት ይቻላል። በተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ተንጠልጥሎ የሚሰጥ የመፍትሔ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ለውጥ ውጤቱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው፡፡
የመደብ ትግልን በማንነት ጥያቄ አሳክሮ የተወጠነው ዘውጌ’ዊ ፌደራሊዝምም ሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከተዘፈቅንበት አዘቅት ሊያወጣን ይቅርና ለከፋ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ዳርጎን አርፎታል። ካርል ማርክስ “ ታሪክ ራሱን ሲደግም መጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ በማስከተል በአስቂኝ ሁኔታ” ያለው እንዳይሆን አበክሮ ማስተዋል ይጠይቃል። እንደ አገር የገጠሙንን ሰሞነኛ ችግሮች በስሜታዊነት ሳይሆን በሰከነ መንፈስ እና ከፓርቲ አጀንዳ ይልቅ አገርን በማስቀደም ቁጭ ብሎ መተንተንና ሀቀኛ ድምዳሜ ላይ መድረስና የመሻገሪያ ድልድይ መገንባት ያሻል ፡፡
2ኛ. ለችግሮቻችን አገረኛ መፍትሔ አለመሻታችን፦
ላለፉት 50 ዓመታት እንደ መስኖ ውሃ እነ ሌኒን፣ ስታሊን ፣ ማርክስ ፣ ኤንግልስ ፣ ማኦ ፣ ማኪያቬሊ ፣ ወዘተ . በቀደዱልን የርዕዮተ ዓለም ቦይ መፍሰሳችን አልያም ሲገድቡን መገደባችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ሆኖም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዛሬም ጥያቄዎቻችን አለመመለሳቸው ችግሮቻችን አለመፈታታቸው ሳያንስ ይበልጥ ተወሳስበው ውላቸው ጠፍቷል። ለዚህ ነው ለአንደኛው ችግር መፍትሔ ስናበጅ ሌላው እንደ እንቧይ ካብ ከጎን የሚናደው። ከሌኒን ኮርጀን የብሔር ጥያቄን እንደፈታን ስናስመስል አገራዊ ሕልውና አደጋ ላይ የወደቀው። ከሶቪየት ገልብጠን የዕዝ ኢኮኖሚን ስንተገብር ፈጠራ የኮሰመነው ኢኮኖሚ የደቀቀው። ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓንና ከቻይና እንዳለ ቀድተን ልማታዊ መንግስት ስናነብር አገር የጥቂቶች ሲሳይ ሆና ያረፈችው፡፡
ለነገሩ ጠንካራ አገራዊ አንድነትና ተቋማት በሌሉበት ልማታዊ መንግስት አይታሰብም። እነዚህ ማሳያዎች ችግሮቻችንን በተናጠል እና በተኮረጀ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖሊሲ ለመፍታት ያደረግነው ሙከራ መክሸፉን ያሳጣሉ። ለዚህ ነው አገር በቀል ወደ ሆነና ዙሪያ መለስ እይታ ማተኮር የሚያስፈልገው። ለዚህ ነው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር “መደመር” ቁጥራቸው ቀላል ባልሆነ ልሒቃን አገርን ፣ ትውልድንና ዘመንን የዋጀ ምላሽ ተደርጎ የተወሰደው። ፅንሰ ሀሳቡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ በ”ቲንክ ታንክስ” ፣ በሙያ ማህበራት ፣ በዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት ፣ ወዘተ . ሲተች ሲሔስ ደግሞ ይበልጥ የጋራ አካፋይ ሆኖ ሊወጣ ይችላል በሚል ዕምነት፡፡
3ኛ. የተረኮቻችን ምርኮኛ መሆናችን፦
ሰለሞን ሥዩም የተባሉ ፀሐፊ በፍ-ት-ሕ መፅሔት ከአንድ አመት በፊት ባስነበቡ መጣጥፍ ታሪካችን ሶስት የትርክት ዘውጎችን መፍጠሩን ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡን ጠቅሰው ሞግተዋል። አክሱማዊ ፣ ሴም ኦሪየንታላዊ እና ስር-ነቀላዊ ናቸው። ሶስተኛው የስድሳዎቹ ትውልድ የፈጠረው ነው። የታሪኩንም የፖለቲካውን ትርክት ከስሩ ለመቀየር ነው የሰራው። ትርክት ቀድሞ በተቀመጠ ድምዳሜና ብያኔ ላይ የሚዋቀር መሆኑ የውርክቡ መግፍኤ ነው። የዚህ ትውልድ ቅርሻ የሆኑ “ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጭዎች” በተለይ ባለፉት 27 አመታት ታሪክን በሸውራራ ትርክት ለመቀየር ያደረጉት ጥረት በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸው ነበር ማለት ይቻላል ፡፡
በእነዚህ የፈጠራ ትርክቶች በዜጎች መካከል ጥላቻን ፣ መጠራጠርንና ልዩነትን ጎንቁለው ማሳደግ ችለዋል። በተዛባ ትርክት ለቆሙ የጥላቻ ጣኦታት እንድንሰግድ መስዋዕት እንድንገብር አድርገዋል። ላለፉት በርካታ አመታት በተለይ ለውጡ ከባተ ወዲህ ሰሞነኛውን ጨምሮ የተስፋዋን ምድር ወደ አኬልዳማ ቀይረው ዳግም ቅስማችንን ሰብረው አንገታችንን አስደፍተውናል። ሆኖም ዛሬም ከዚህ የጥላቻ አዙሪት ለመውጣት ተረካችንን እንደገና መበየን እና ቂም በቀል የሚያወርሱ ጣኦቶቻችንን ከአእምሮ ጓዳችን አውጥተን ማንከባለል በየከተሞች ያቆምናቸውን የጥላቻ ሀውልቶች እንደገና ስለፍቅር ስለይቅርታ መቅረፅ አለብን ከዚህ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን ሳይሸራረፍ የማረጋገጥ ግዴታም አለብን ፡፡
4ኛ. ከውስጥ ወደ ውጭ ማነፅ፦
ለዘመናት ዕርቅን ፣ ፍቅርን ፣ ሰላምን ፣ ይቅርታን፣ አንድነትንና ፈሪሀ ፈጣሪን በአደባባይ የሚሰብኩ ወካይ የሆኑ ቱባ ቱባ ባህሎችና ሃይማኖቶች ባሉበት እንዲሁም ከሕዝቡ አብዛኛው ሃይማኖተኛ በሆነበት አገር ሰሞነኛውን አይነት አረመኔአዊ ግፎች መልሰው መላልሰው የሚጎበኙን ለምን እንደሆነ ግራ ያጋባል። መስቀልን ፣ ኢ-ሬቻን ፣ ፍቼ ጨምበለላንና ኢድ አልአደሀን በአደባባይ ባከበርንበት ልክ መገኘት ለምን እንደተሳነን ያስቆዝማል። ለዚህ ውድቀት ላለፉት 50 አመታት የመጣንበት ፖለቲካዊ ሀዲድ የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፤ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚሰብኩንን ሆነው አለመገኘታቸው ለደረስንበት የሞራል ዝቅጠትና ጉስቁልና ሌላዊ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ በባህላዊ ወረቶቻችንንም (cultural capitals) ሆነ ዕምነቶቻችንን የትውልዱን ሰብዕና ማነፅ፣ ምግባሩን መግራት እንዲችሉ ራሳቸውን መፈተሽ፤ ስለ አገልግሎታቸው ስነ ዘዴ ቆም ብሎ ማሰብ ማንሰላሰል ወቅታዊ ጥሪ ሊሆን ይገባል። ባህላዊም ሆኑ ሃይማኖታዊ ትእምርቶቻችን የትውልዱን ሰብዕና ላይ ላዩን የሚቀባቡ ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያንፁ፤ የአስተሳሰብ ልዕልናን የሚያቀዳጁ ሆነው እንዲያገለግሉ እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ልዑል አምላክ ልብ ይስጠን ! መውጫውን ይግለጥልን ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com