
አዲስ አበባ፡-ለዜጎች በሰላም መኖር ስጋትን የሚፈጥሩ፤ በሃገር ሕልውና ላይም አደጋን የሚደቅኑ አካላት ላይ መንግሥት መውሰድ የጀመረውንም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትናንት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከሰሞኑ በሃይማኖት ሽፋን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችና ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የፌደራል ፖሊስ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እያዋሉ ይገኛሉ፡፡ ተጠርጣሪዎቹም ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ይደረጋል።
ለዜጎች በሰላም መኖር ስጋትን የሚፈጥሩ፤ በሃገር ሕልውና ላይም አደጋን የሚደቅኑ አካላት ላይ መንግሥት መውሰድ የጀመረውንም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ሃገራችን በርከት ያሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትንና ሁነቶችን አስተናግዳለች
ያለው መግለጫው፤ የስቅለት፤ የፋሲካ፤ የታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር፤ የኢድ አልፈጥርና የፍቼ ጫምባላላ በዓላት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን ያስተናገድንበት ሳምንት እንደነበር አስታውሷል።
በዚሁ ወቅት በጎንደር ከተከሰተው አሳዛኝ ጥፋት እንዲሁም እሱን ተከትሎ በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከታየው ፍጹም ከኢትዮጵያዊነት ስነምግባር ያፈነገጠ ወንጀል ባሻገር በዓላቱ በመላ ሃገሪቱ በድምቀት ተከብረዋል። በዚህም በዓላቱ ኢትዮጵያውያን በፈተና ውስጥ ይበልጥ የሚጸና የአብሮነት እሴት እንዳላቸው ያሳዩበትና የሃገርንም ገጽታ ለመገንባት ያስቻሉ ናቸው ሲል መግለጫው አመልክቷል።
በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፉት እነዚህ በዓላት ከሃይማኖታዊ አስተምህሮታቸው ርቀው የጥፋት ማስተናገጃ እንዲሆኑ ለማድረግና በኢትዮጵያውያን መካከል የተዘረጋውን የአብሮነት ገመድ ለመበጠስ ያቀዱ ወንጀለኞች ብዙ ጥፋትን ለማድረስ በብርቱ የሞከሩበትም ወቅት መሆኑን መግለጫው አውስቶ፤ይህ ውጥናቸው ባሰቡት የጥፋት ልክና ባቀዱት የወንጀል ስፋት መጠን እንዳይሳካ ላደረጉት ኢትዮጵያውያን በሙሉ መንግሥት ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል ብሏል።
ሕዝብ የሰጣቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በጠንካራ ቅንጅትና እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል የተወጡ መላው የጸጥታ አካላትና ተባባሪ ተቋማትም ምስጋና ይገባቸዋል ያለው መግለጫው፤ለዜጎች በሰላም መኖር ስጋትን የሚፈጥሩ፤ በሃገር ሕልውና ላይም አደጋን የሚደቅኑ አካላት ላይ መንግሥት መውሰድ የጀመረውንም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
በዚህ ሂደት ለጽንፈኝነትና አክራሪ አመለካከት ቦታ እንደሌለው በተግባር ያረጋገጠው መላው ሕዝብ ከሰሞኑ እንደታየው ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ያሳየውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም