አዲስ አበባ፡- ለፓርላማ የተመራው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ህግ ካልጸደቀና የቦርዱ አባላት ካልተሟሉ የአዲስ አበባ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ ማወቅ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የምርጫ ቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ የሆኑት ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በ2010ዓ.ም ይካሄድ የነበረው የአዲስ አበባ ምርጫ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ለአንድ ዓመት መራዘሙን፤ በአሁኑ ወቅትም ለፓርላማ የተመራው የምርጫ ድርድር ማቋቋሚያ አዋጅ ካልጸደቀና የቦርዱ አባላት ካልተሟሉ ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ ማወቅ እንደማይቻል ገልጸዋል።
የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ እንዳሉት፤ ቦርዱ ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ አዲስ አመራር ካመጣ ወዲህ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ በተለይም በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሥር በተቋቋመው የህግና የፍትህ ማሻሻያ ጉባዔ ላይ ምርጫ ቦርዱም ተሳትፏል፤ የብሄራዊ የምርጫ ቦርዱን የማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና እንዲረቀቅ አድርጓል፤ የአዋጅ ህጉንም ለፓርላማ ተመርቷል።
የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ የማሻሻያ አዋጅ ህጉን ፓርላማው እስኪያጸድቅ ድረስ እየተጠበቀ እንደሚገኝ፤ አሁን ባለው ሁኔታ የተቀየረው የቦ ርዱ ሰብሳቢ ብቻ በመሆኑና ሌሎች የቦርድ አባ ላት ባለመሟላታቸው ህጉ ከጸደቀ በኋላ ተቋሙ ውስጥ ባለው አዲስ የማደራጀት ሥራ ‹‹ሪፎርም›› አዲስ የቦርድ አባላት ለውጥ እንደሚደረግ ገልፀው፤ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ የትኛውንም ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል። የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ በአሁኑ ወቅት ነባሮቹ የምርጫ ህግና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የሥነ ምግባር ህግ እየተከለሱ እንዳሉ፣ ሊደረጉ የታቀዱት ምርጫዎች ቋሚ ኮሚቴው የተመራውን ህግ ሲያፀድቅና የቦርዱ አባላት ሲሟሉ ወደ ምርጫ እቅድ ሥራዎች እንደሚገባ፤ ነገር ግን ባልተሟላ ቦርድ አባላት የምርጫን ውሳኔ ማሳለፍ እንደማይቻልና በህጉ መሰረት የሚሾሙ የቦርድ አባላት ሳይኖሩ ምርጫን ማካሄድ ህጋዊ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
‹‹የቦርዱ አዲስ አደረጃጀት የተለያዩ ክፍልፋዮች ያሉት ሲሆን፤ የመጀመሪያው የምርጫ ህግ ማሻሻል፣ የተቋሙን መዋቅር መቀየር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሲሆኑ፤ ሁለቱ ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ምርጫ ቦርድ ይሠራቸዋል የሚባሉትና በህግ የሚሰጡ ኃላፊነቶች የሚከናወኑት የተቀየረውን የምርጫ ህግ መሰረት አድርገው ይሆናል። አሁን እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች የቦርዱ አጋር አካላት ከሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻልን ያካተቱ ናቸው›› ብለዋል የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ ከምርጫው በፊት ቦርዱ እያከናወነ ያለውን የለውጥ ሥራዎች አስመልክተው ሲገልጹ።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤቱ የተመራው ፓርላማው ሊዘጋ አንድ ቀን ሲቀረው እንደነበር አስታውሰው፤ ፓርላማው እንደተከፈተ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የአስረጂ መድረክ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸው የምርጫ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ብዙ አካላት በውይይት መድረኩ አለመገኘታቸውን ገልጸዋል።
አዋጁ በምክር ቤት የሚጸድቀው ያገባኛል የሚሉ አካላት በአስረጂ መድረክ ውይይት ካደረጉበትና አስተያየት ከሰጡበት በኋላ ነው የሚሉት ሰብሳቢዋ፤ ምርጫ የፓርቲዎችና የህዝብ ጉዳይ በመሆኑ እነዚህ አካላት በድጋሚ ውይይቱ ላይ እንዲገኙ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ እየተደረገ እንዳለ ተናግረዋል።
ሰብሳቢዋ የሚመለከታቸው አካላት የማይገኙ ከሆነ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን እንደሚያሸጋግርና ተወያይቶ አዋጁን እንደሚያጸድቅ አሳስበው፤ ውይይቱን ለማካሄድ የፊታችን ሰኞ በድጋሚ ጥሪ መደረጉንና ከውይይቱ በኋላ እስከ ቀጣይ ሳምንት ድረስ አዋጁ እንደሚጸድቅ ጠቁመዋል።
እስካሁን ለምክር ቤቱ የቀረበው አዋጅ ምርጫ ቦርዱን ስለማቋቋም የሚጠቅሰው ረቂቅ ብቻ እንደሆነና ሌሎች ተያያዥ ህጎችና አዋጆች ለምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ አለመድረሳቸውን ሰብሳቢዋ ጠቁመው፤ የምርጫ ሂደቱን ለማካሄድ የቦርድ አባላት መሟላት የሚለው ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል።
‹‹የምርጫ ቦርድ ተቋሙ አለ። አልተሟላም የሚባል ነገር የለም። በተነሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ምትክ አዲስ ሰብሳቢ ተተክቷል። ሌሎቹ የቦርድ አባላት ደግሞ በህጋዊነት ሥራ ላይ አሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው። አዲሷ ሰብሳቢም ከእነርሱ ጋር እየሠሩ አዲስ ቦርድ የሚተካ ከሆነም ይቀጥላሉ፤ ካልሆነ ደግሞ አልተሟላምና ተቀምጫለሁ የሚል ነገር አይኖርም። ስለዚህም የቦርድ አባላት እንዳሉ ነው ምክር ቤቱ የሚያውቀው›› ሲሉ ምርጫ ቦርድ አባላት አልታሟሉልኝም ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
አዲሱ ገረመው