በበርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ጸጋዎቿ ከምትታወቀው ሲዳማ ክልል የምትገኝ ሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት ያለባት ከተማ ናት። ከተማዋ በአሁኑ ወቅት በፈጣን የዕድገት ግስጋሴ ላይ የምትገኝና በአረንጓዴ መልከዓምድር አቀማመጧ፤ በፏፏቴዎቿና በፍልውሃዎች የታደለች ለመሆኗም በርካታ ምስክሮች አሏት። ልዩ ልዩ ውበት ያላቸው ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉ መዳረሻዎቿም ትኩረት የሚስቡ ልዩ የተፈጥሮ ስጦታዎቿ ናቸው።
ከተማዋ በተፈጥሮ የታደለችውን ጸጋ ጠብቃ በመጠቀም ለትውልድ ማስተላለፍ እንድትችል ከተማ አስተዳደሩ ሕዝቡን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ስለመሆኑ የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሚልኪያስ ብትሬ ነግረውናል። ይሁን እንጂ ‹‹ማንኛውም መሠረተ ልማት ከኅብረተሰቡ ተሳትፎ ውጪ ውጤታማ መሆን አይችልም›› በማለት ያስረዳሉ።
እንደሳቸው ገለጻ፤ ሀዋሳ ከተማ በመሠረተ ልማት የምትታማ አይደለችም። እያንዳንዱ መሠረተ ልማት ከተማው በራሱ ከሚያመነጨው ገቢ ተሰብስቦ የሚሠራ ነው። ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በከተማው ነባር እና ከአስር ኪሎ ሜትር በላይ የሆኑ የአስፓልት መንገዶች በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ከቴክኒክና ሙያ እስከ ዶሮ እርባታ ያለው የአስፓልት መንገድ ባለፈው ዓመት መጠናቀቅ ችሏል።
ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ የሆነውና ከታቦር ተራራ ዙርያ አቋርጦ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል አካባቢ የሚያበቃው መንገድም በአሁኑ ወቅት የማጠናቀቅ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል። ሌሎች አዳዲስ የአስፓልት መንገዶችንም እንዲሁ በተያዘው በጀት ዓመት ለመሥራት በተለያዩ አካባቢዎች ሥራው የተጀመረ መሆኑን አቶ ሚልኪያስ ይጠቅሳሉ።
ከተጀመሩት የአስፓልት መንገዶች መካከልም ስምንት ኪሎ ሜትር የሚደርስ የአስፓልት መንገድ የሚገኝበት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሥራው ተጀምሯል። በተለይም አልፎ አልፎ በከተማዋ የጎርፍ ችግር የሚስተዋል በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ ትላልቅ ድሬኔጆችን መገንባት ተችሏል። አጠቃላይ ትልቅ የውሃ አቅም መሸከም የሚችሉ አዳዲስና ትላልቅ ድሬኔጆች ተገንብተዋል።
በከተማዋ አዳዲስ ከተገነቡት የውሀ መውረጃዎች በተጨማሪ ነባሩንም በተለይም ጎርፍ በሚያስቸግርባቸው አካባቢዎች የመጠገን ሥራ ተሠርቷል። ለአብነትም ዳቶ ሴራሚክ ከሚባለው አካባቢ እስከ ዳካ ድረስ የሚሄደው መንገድ የውሀ ማውረጃ ሥራውም ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ሌሎች ጎርፍ የሚያስቸግርባቸው አካባቢዎችንም እንዲሁ በመለየት የውሀ ማውረጃ እየተሠራ ነው።
አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን ብቻ መሥራት ሳይሆን ነባሮችንም የመጠገንና የመንከባከብ ሥራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሚልኪያስ፤ ይህም በከተሞች ከሚሠሩት መሠረተ ልማቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል። በዚህ ረገድም በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የተበላሹና ሰዎችን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የውሀ ማወረጃዎችን በአዲስ የመተካት ሥራ ተሠርቷል። ክፍት የነበሩ ፕሪካስቶችን መሸፈን የተቻለ ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 16 ሺ ፕሪካስቶችን ለመሸፈን ታቅዶ ስድስት ሺ ነባር ፕሪካስቶችን መጠገንና መሸፈን ተችሏል። ከእነዚህም መካከል ከከተማ አስተዳደሩ እስከ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አደባባይ ባለው አካባቢ የተሠሩት ሥራዎችና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሀዋሳ ከተማ ተጠናክረው የቀጠሉ ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ሚልኪያስ፤ ለዚህም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ የነበረ መሆኑን አንስተዋል። መሠረተ ልማት ከኅብረተሰቡ ተሳትፎ ውጪ ውጤት ሊያመጣ የማይችል በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል። ኅብረተሰቡ በተለይም የመሠረተ ልማቶችን ከመጠበቅና ከመንከባከብ አንጻር ከተማዋ የኔ ናት የሚለውን አስተሳሰብ ማጎልበት እንዲችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርቷል። በዚሁ መሠረት ማኅበረሰቡ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በተያዘው በጀት ዓመት በኅብረተሰቡና በባለሀብቱ ተሳትፎ ብቻ ከ50 ሺ ካሬ ሜትር በላይ የአረንጓዴ ልማት ሥራ መሠራት ተችሏል። ይህም የማኅበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ ማሳየት ከሚችሉ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው። የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ከማከናወን ባሻገርም የተሠሩትን የልማት ሥራዎች የመጠበቅና የመንከባከብ ተግባር ከኅብረተሰቡ የሚጠበቅ መሆኑን አቶ ሚልኪያስ ይናገራሉ።
ከከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን ለመጥረግ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣ መሆኑን ጠቅሰው ኅብረተሰቡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመሆን የልማት ሥራዎችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ እየሠራ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በዚህም ወጪ ከመቆጠብ ባለፈ ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲሠሩ ያስችላል።
ሀዋሳ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማ ግብርናን በማስፋት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች መሆኑን የተናገሩት አቶ ሚልኪያስ፤ የከተማ ግብርና ማንኛውም ዘመናዊ ከተሞች ማከናወን ያለባቸው ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። በከተማ ግብርና መሳተፍ ከተሞች በአረንጓዴ ልማት ሥራ ላይ ከሚያሳድሩት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በምግብ ራስን ለመቻል የጎላ ድርሻ ያለው ነው።
በአሁኑ ወቅትም በሀዋሳ ከተማ ሰፋፊ ይዞታ ያላቸው ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የተለያዩ ተቋማትን ለከተማ ግብርና መጠቀም የግድ ነው። ከተቋማት በተጨማሪም ሰፋፊ ይዞታ ባላቸው ግለሰቦች ግቢ ውስጥ የጓሮ አትክልቶች መልማት እንዲችሉ ሰፊ ንቅናቄ ተፈጥሯል። በቀጣይም ሥራው መሬት መንካትና ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንዲችል በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ከተሞች በራሳቸው አቅም ብቻ ውጤት ማምጣትና መሠረተ ልማትን ማስፋፋት የማይችሉ መሆኑን አቶ ሚልኪያስ አንስተው፤ ከተማ አስተዳደሩ ከማኅበረሰቡ በተጨማሪ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ማኅበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራት መቻላቸውን ነግረውናል። ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ ለአብነትም ጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ 100 ወጣቶችን ከጎዳና አንስቶ ስልጠና በመስጠት ለሥራ የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሰቁሶችን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ሊያቋቁማቸው ችሏል።
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተጨማሪ የኅብረተሰቡን ችግር መሠረት ያደረጉ ተግዳሮቶችን ነቅሶ በማውጣት በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተጠናከረ ሥራ እየሠራ ያለበት ሁኔታ አለ። በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ የሚሠራቸው በርካታ ማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በሀዋሳ ከተማ እየታዩ ካሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መካከል ውስንና ውድ የሆነውን የመሬት ሀብት ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር አንዱ ነው። በሀዋሳ ከተማ ካዳስተር ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ቆየት ያለ ሲሆን የላቀ ውጤት ማስመዝገብም ችሏል። ከተማዋ በዘርፉ ውጤታማ ሥራ መሥራት በመቻሏም ሌሎች ከተሞች ከሀዋሳ ከተማ ተሞክሮ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ከተማ አስተዳደሩ በተለይም በ2013/14 ለሕጋዊ ካዳስተር ሥራ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሠርቷል። በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ወደ ሕጋዊ ካዳስተር ሥርዓት ያልገቡ ክፍለ ከተሞችን ለማስገባት ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ከዚህ ቀደም ከነበሩ አምስት ክፍለ ከተሞች በተጨማሪ ታቦርና ሐይቅ ዳር የተባሉ ሁለት ክፍለ ከተሞች ወደ ሕጋዊ ካዳስተር ሥርዓት እንዲገቡ ሽፋን የማስፋት ሥራ ተሠርቷል።
ለሕጋዊ ካዳስተር ሥራው አጋዥ የሆኑ መሣሪያዎችን በማስገባት ሰፋፊ ሥራዎች ስለመሠራታቸው ያነሱት አቶ ሚልክያስ፤ በበጀት ዓመቱ ለሥራው አጋዥ የሆኑ ጂሲፒ እንዲሁም ሌሎች ሥራውን ሊያግዙ የሚችሉ መሣሪያዎችን ማቅረብ ተችሏል። የኅብረተሰብ ቅሬታ ሰሚና ታዛቢ ኮሚቴዎችን በማደራጀትም እንዲሁ 46 ኮሚቴዎች በበጀት ዓመቱ ተደራጅተዋል። በዚህ ምክንያትም በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ሥራው ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠናቀቅ የቻለ ሲሆን በዘጠኝ ወር አፈጻጸም አምስት ሺ ይዞታዎችን ለማረጋገጥ ታቅዶ አራት ሺ ይዞታዎችን ማረጋገጥ ተችሏል። በቀጣይ ቀሪ ጊዜው የዕቅዱን መቶ በመቶ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
መሬትን ዘመናዊ በሆነ መንገድ የማስተዳደር ሥራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለይም ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራት መቻላቸውን አቶ ሚልክያስ ያስረዳሉ። ‹‹ኅብረተሰቡ ያልደገፈው ማንኛውም የልማት ሥራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም›› በማለት ነበር። ይሁንና ሕጋዊ ካዳስተርን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደት በተለይም ከደንብና መመሪያ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ክፍተቶች የሚታዩ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ የተለያዩ የካሳ ክፍያና ሌሎች ቅሬታዎችንም ያነሳል።
በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ተገቢ የሆነ የካሳ ክፍያዎችን በመፈጸም የመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ ጥያቄዎችን እየመለሰ የሚገኝ ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመትም በአረንጓዴ ልማትና በመንገድ ከፍታ ምክንያት የተነሱ 1200 ሰዎች ምትክ መሬት እንዲያገኙ ተደርጓል። ይሁንና ሁሉንም ጥያቄ በአንድ ጊዜ መመለስ የማይቻል በመሆኑም በተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ምክንያት ተነሺ የሆኑ ሰዎች በሂደት ምትክ ቦታ እንዲያገኙ እየተሠራ ነው። በተለይም ሕጋዊ ካዳስተርን ተግባራዊ በማድረግ ኅብረተሰቡ ደህንነቱ የተረጋገጠና የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን አንስተዋል።
ሀዋሳ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገችና እየሰፋች የምትገኝ እንደመሆኗ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችና የማስፋፊያ ሥራዎች ይስተዋሉባታል። በተለይም በመንገድ ሥራና በአረንጓዴ ልማት ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወነ ያለ ቢሆንም በከተማዋ ሰፊ ቁጥር ያለው አገልግሎት ፈላጊ በመኖሩ ከተማ አስተዳደሩ ፈጣንና የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየሠራ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
ከተሞች የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዲችሉ ሕጋዊ ካዳስተር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ ሚልኪያስ፤ ዘርፉ ገቢ ማመንጨት እንዲችል የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ከገቢ ጋር በተገናኘ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከተማ አስተዳደሩ ከሕጋዊ ካዳስተር አገልግሎት 26 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት የቻለ ቢሆንም ከተማው ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ በቀጣይ ከዚህም በላይ ገቢ ማግኘት ይቻላል። ገቢው በማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ብቻ የተገኘ ሲሆን ሌሎች መደበኛ ገቢዎችን ጨምሮ ሕጋዊ ካዳስተርን ተግባራዊ በማድረግ በተሰጠ አገልግሎት ብቻ በዘጠኝ ወር ውስጥ በድምሩ 40 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል። በቀጣይም ሕጋዊ የካዳስተር ሥራውን በሁሉም ክፍለከተሞች አጠናክሮ በመሥራት ከዚህ በተሻለ መጠን ገቢ ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014