በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ የራሱንና የባለቤቱን መታወቂያ ለማሳደስ ቄራ አካባቢ ወዳለ አንድ ወረዳ ይሄዳል። ቀኑ መታወቂያና መሰል የወሳኝ ኩነት ጉዳዮች የሚታዩበት ነበር። ማልዶ ሄዶ ተራ ይዟል፤ ባለጉዳዩ ግን ብዙ ነው።
ጉዳይ ለማስፈጸም ብዙ እንግልትና ጣጣ እንዳለም ሰምቷል፤ ሁሉም ሥራ ሰው በሰው፣ በጉርሻ እንደሚፈጸም፣ ጉዳይ እናስጨርስ ባይ ደላሎች ስለመፈጠራቸውም ሰምቷል፤ እናም በቀላሉ ማስፈጸም እንደሚቸገር ገመተ።
ሠራተኞች ሥራ እንደጀመሩም ተራ ጠባቂዎቹ ቆመው ጉዳይ ወደ ሚፈጸምበት ክፍል የሚገባው የሚወጣው እየበዛ መጣ፤ መረጃ ልጠይቅ ብሎ እዚያው የሚሰምጠው፣ በሥርዓቱ አስተናግዱን እያለ ገብቶ በምሬት የሚያመለክተው በዛ።
ባለጉዳይ አስተናጋጆቹ በሥራ ቢጠመዱም ባለጉዳዮች በተራቸው መሠረት ሲጠሩ ግን ብዙም አይሰማም። ሁኔታው የማንን ጉዳይ ነው የሚፈጽሙት ያሰኛል። በአንጻሩ ጉዳያቸው ያለቀላቸው በፈገግታ ተሞልው ይወጣሉ። ሁኔታው ለጓደኛዬ እንቆቅልሽ ሆነበት።
ከእልህ አስጨራሽ ጥበቃ በኋዋላም ተራው ይደርስና በአንዱ መስኮት የእሱንና የባለቤቱን መታወቂያዎች ይሰጣል፤ ባለቤቱ እዚያው ባለጉዳዮች ማስተናገጃ ክፍል ተቀምጣ እየተጠባበቀች መሆኗንም ያስረዳል። መጠበቁን ቀጠለ፤ የሚያስታውሰው አጣ፤ ደጋግሞ ረሳችሁኝ ቢልም ጠብቅ ብቻ ሆነ ምላሹ። ከብዙ ምጥ በኋዋላም መታወቂያው ታደሰለት።
የእከሌስ ብሎ የባለቤቱን መታወቂያ ጉዳይ ጠየቀ፤ ባለቤቱ መሆኗን ሳይገልጽ፤ ያገኘው መልስ ግን ፋይሉ የለም የሚል ሆነ፤ እየሳቀ ምን እያልክ ነው ሲል ጉዳይ ፈጻሚውን ጠየቀው። እኛ ምን እናውቃለን፤ ማህደር ክፍል ጠይቅ ሲል መለሰለት። ባለቤቴ እኮ ናት፤ የእሷ ማስረጃ ለብቻው የት ሄደ ሲል መረር ባለመልኩ አሁንም ጠየቀ። ጉዳይ ፈጻሚው መልስ ሳይሰጠው ሌሎች ማስተናገዱን ቀጠሉ።
በእዚህ መሐል ሰፈር ውስጥ በአይን ብቻ የሚያውቀው በወረዳው የሚሠራ ኃላፊ ያገኛል። ጉዳዩን አስረዳ፤ ግለሰቡ ቁጭ በል ብሎት ፈገግ እያሉ ጉዳዩ ወደሚታይበት ክፍል ገባ፤ ከዚያም ጠብቅ ብሎት ሄደ። መታወቂያው ብዙም ሳይቆየው ታድሶ ተሰጣቸው።
ይህ እንግዲህ መታወቂያ ማሳደስን የተመለከተ ነው። አዲስ መታወቂያ ማውጣትም፣ የጠፋ መታወቂያ ማስተካት፣ የመሬት አስተዳደርና እኔ ሌሎች ከወረዳ ድጋፍ የሚያስጠይቁ ወዘተ ጉዳዮችም አይደሉም፤ በቀላሉ ሊፈጸም የሚችል መታወቂያ ማሳደስ ነው።
የመልካም አስተዳደር ችግሩ አዚህ ደረጃ ደርሷል። ከየአቅጣጫው የሚሰማው ቅሬታም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ውስብስብ ያልሆነውን ተራ ጉዳይ በማወሳሰብ ባለጉዳይን ለእንግልት በመዳረግ መብቱን በገንዘብ እንዲገዛ ማድረግ ተለምዷል።
መታወቂያ በቀላሉ ማግኘት ይቸገራል የተባለው በቀላሉ እያገኘ ፣ በቀላሉ ሊፈጸም የሚችለው መታወቂያ ማሳደስ ግን አንዴ ፋይል ጠፋ፣ የሚፈርመው ኃላፊ የለም፤ ኮኔክሽን የለም እየተባለ እንዲመላለስ ወይም እንዲንገላታ ይደረጋል። እነዚህ ችግሮች አንዳንዴ ሊፈጠሩ ቢችሉም ሲደጋገሙና መደበኛ እስኪመስሉ መድረሳቸው ግን ያሳስባል። ውስብስብ ችግሮችስ እንዴት እየተፈቱ ይሆን?
አንዳንድ ባለጉዳዮች ይህን ችግር በቀላሉ የፈቱ መስሏቸው የሚሄዱበት ሕገወጥ መንገድ ነው ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ። ባለጉዳዮች ስራ አስፈቅደው እንዲሁም ራቅ ካለ አካባቢም የመጡ ፣ ከወረዳ የሚፈልጉት ሰነድ ለብርቱ ጉዳይ የሚፈለግም ሊሆን ይችላል። በእዚህ ላይ የማንገላታቱን ዳርዳርታ ነቅተንበታል ይላሉ፤ እናም ሂሳብ መሥራት ውስጥ ይገባሉ፤ ገንዘቡ በትራንስፖርቱም በምኑም በምኑም መውጣቱ አይቀርም ብለው የሻይም ይበሉት ሌላ ገንዘብ ሰጥተው ማስፈጸም ውስጥ ገብተዋል፤ አምጡ ለማለት ቀድሞውንም የበረቱት አገልግሎት ሰጪዎቹ ፤ ባለጉዳዮች በፈጠሩላቸው ምቹ ሁኔታ ዘረፋቸውን በሌላው ባለጉዳይ ላይም ጭምር ወደ መፈጸም ገብተዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሩን የተረዱ አገልግሎት ፈላጊዎች ብድግ ብለው ጉዳይ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መሄድ ትተዋል፤ ጉዳይን በዘመድና በትውውቅ ማስፈጸም ተለምዷልና ጉዳይ ሲኖራቸው የሚሄዱበት መሥሪያ ቤት ዘመድ፣ ወዳጅ ፣ ትውውቅ ያለው ሰው ፍለጋ ይማስናሉ፤ ይህ የቆየ ሕገወጥ ተግባር አሁንም እንዳለ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ጉዳይን በማወሳሰብ ኪራይ ወደ መሰብስብ ተሸጋግሯል፤ ዛሬ ያለጉርሻ የማይንቀሳቀሱ አገልግሎት ሰጪዎች የሉም እስከማለት ተደርሷል። ይህ ሕገወጥ ተግባር አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ባሉ ሠራተኞች ይሁን በውጪ ደላሎችም እየተሠራ መሆኑ ደግሞ ችግሩን የከፋ አድርጎታል።
በዚህ ዘመን ሕጋዊ ጉዳይን ከማስፈጸም ሕገወጥ ጉዳይን ማስፈጸም ቀሏል እየተባለም ነው፤ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና አሁን የደረሰበት ደረጃ ለዜጎች ብቻ አይደለም ለሃገርም ስጋት ነው። ሕገወጦች ብዙ ገንዘብ ለአገልጋይ ተብዬዎች በመክፈል / ይህ በሰንሰለት ጭምር የሚሠራ ነው/ ለሰሚውም ሊታመን የማይችል ወንጀል እየተፈጸመ ነው። የመሬት ባለቤትነት ምንም አይነት ማስረጃ የሌላቸው ሰዎች በተለያየ ምክንያት በእጃቸው የነበረን የመንግሥት መሬት ይዞታዬ ብለው በሚሊዮኖች በሚቆጠር ብር መሸጣቸውን ስንሰማ የመልካም አስተዳደሩ ችግር የት እንደደረሰ መረዳት አያስቸግርም።
መንግሥት ይህን የሕዝብና የሃገር ጠንቅ ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ ከሕዝቡ በቂ መረጃዎችን ሰብስቦ ወደ ትግበራ መግባቱ ትክክልም ወቅታዊም ነው። ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ጉባኤውን ባካሄደ ማግስት የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሠራባቸው ካሉት መካከል የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው። በእዚህ ችግር ላይ ከኅብረተሰቡ ጋር ወርዶ ተወያይቷል፤ ኅብረተሰቡ አሉብኝ ያላቸውን ችግሮች በዝርዝር አስታውቋል፤ መንግሥትም እነዚህን ችግሮች በሚገባ ለይቶ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ነው።
በአዲስ አበባም በወረዳ በክፍለ ከተማ እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፤ ችግሮቹን ለመፍታት እቅድ አውጥቶና ቀነ ገደብ ጭምር አስቀምጦ እየሠራ ነው። እንዳያያዙ ከሆነ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በኩል ብዙ ለውጥ ማሳየት ይችላል።
መንግሥት ብቻውን ችግሩን ይፈታዋል ተብሎ መታሰብ ግን የለበትም። መንግሥት ከሕዝብ ውጪ አመርቂ ተግባር ሊሠራ እንደማይችል በመንግሥት ተከናወኑ የተባሉ ፕሮጀክቶችን፣ ሰላም የማስፈንና የሃገር ሉዓላዊነትን የማስከበር ሥራዎች ሁሉ መለስ ብሎ መመልከት ይቻላል። የመንግሥት አቅም ሕዝብ ነው።
የሕዝቡን አልፎም ተርፎም የመንግሥትን ችግሮች ለመፍታት የሕዝብ ሚና መተከያ የለውም። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ሕዝቡ ይህን በመንግሥት ዘንድ የታመነበትን ሚናውን መወጣት ይጠበቅበታል።
ሕዝቡ /ባለጉዳዩ. ችግሩን ምንም ሳይፈራ ለመንግሥት ጮክ ብሎ እንደተናገረው ሁሉ አገልግሎቱን በዘመድ ወዳጅ በትስስር ከማስፈጸም፣ በገንዘብ ከመግዛት በመውጣት መንግሥት ደመወዝ እየከፈላቸው በኪራይ ሰብሳቢነት የተሠማሩትን የአገልግሎቱን ቀበኛ አገልጋይ ተብዮች ራቁታቸውን ማስቀረት ይኖርበታል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከተሠማራው ክፍል ማን በሕገወጥ ተግባር እንደተሠማራ ማን እንዳልተሠማራም መጠቆም ይኖርበታል። ዘመኑ ጥቆማዎችን ለመስጠት ምቹ አንደመሆኑ በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌሎች መንገዶች ጥቆማዎችን በመስጠት የመንግሥት ጥረት እንዲሳካ ማድረግ አለበት። ተገልጋዮች አገልግሎት ሰጪዎች ነገሮችን ለማወሳሰብ ሲሞከሩ ይህን ችግር ሊያዳምጥ ለሚችል አካል ሪፖርት ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።
ተገልጋዩም በእዚህ ሕገወጥ ተግባር ውስጥ መግባቱን እየተመለከትን ነው። መብቱን በገንዘብ ከገዛ በእዚህ ሕገወጥ ተግባር ገብቷል ማለት ነው። በተለይ ጉዳይ እንዲያልቅላቸው ብለው ለአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች ጉርሻ ተገልጋዮች ከዚህ ሕገወጥ ተግባር መታቀብ ይኖርባቸዋል፤ እንግልትንና ወጪን ለመቀነስ ብለው አገልግሎትን በገንዘብ የሚገዙ ተገልጋዮች ችግሩን ይበልጥ እያወሳሰቡት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ይህ ተግባር ጤነኛውን አገልጋይ እየበከለ ነውና ማቆም ይኖርባቸዋል።
ባለጉዳዮች ጉቦ ከመስጠት አይደለም ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ዘመድ፣ የሚታወቅ ሰው ከመፈለግም መውጣትም ይኖርባቸዋል። አስፈላጊዎቹን ሰነዶች ይዘው ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመሄድ መገልገል ነው ያለባቸው። ይህ ሲሆን መንግሥት ለጀመረው መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር መሳካት ሚናቸውን መወጣት ይችላሉ።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014