በርከት ያለ ቤተሰብ ያላቸው ባልና ሚስት የልጆቻቸው ዕድሜ ተከታታይ ነው። ልጆቹ በላይ በላይ በመወለዳቸው እኩዮች ይመስላሉ። ሁሉንም በፍቅር ሰብስበው የያዙት ጥንዶች ፈጣሪ ባደላቸው ፍሬዎች ተማረው አያውቁም። ቤተሰቡን በወጉ ለማሳደር፣ እንደአቅም አልብሶ፣ አብልቶ ለማኖር የቻሉትን ያደርጋሉ። ይህ ቤተሰብ በልጆች ብዛት አቅሙ ሲፈተን፣ ገቢው ከወጪው ሲገዳደር ዓመታትን ተሻግሯል።
ሕጻን ዘመረች ግራኝ ለቤተሰቡ ሰባተኛ ልጅ ናት። ልጅቷ በእህት ወንድሞቿ መሐል ስታድግ ችግርና ደስታን እኩል ተጋርታ ነው። እንደወጉ ዕድሜ ሲደርስ ትምህርት ቤት መሄድ በማይታሰብበት መንደር ያገኙትን ቀምሶና ተሻምቶ ማደር የተለመደ ነው።
እንግዳው …
አንድ ቀን ወደ እነ ዘመረች መንደር ብቅ ያለው ጎልማሳ ከአባትዬው ጋር ሲጨዋወት አረፈደ።ዘመረች አባቷና ሰውዬው ወደእሷ እያመላከቱ ሲያወሩ ደጋግማ አስተውላለች። ጉዳዩ በግልጽ ባይገባትም ጨዋታቸው በእሷ ዙሪያ እንደሆነ ገብቷታል። የትንሽዬዋ ልጅ ትንሽ ልብ ደጋግሞ እየመታ ነው። ዓይኖቿ ከአባቷና ከሰውዬው ሳይነቀሉ በአትኩሮት ማስተዋሏን ቀጥላለች ።
አቶ ግራኝና እንግዳው የስጋ ዝምድና የላቸውም። ሰውዬው ዛሬን ወደመንደሩ የዘለቀው ያገሩ ሰው የሆነውን አባት ሊያማክርና ያሰበውን ሊጠይቀው ነው።እንግዳውን በተለየ ዓይን የምታየው ሕጻን ከሁለቱ ሰዎች አዲስ ነገር የምትጠብቅ ይመስላል። አባቷ ሰውየው የሚለውን እየሰማ አንገቱን በይሁንታ ይወዘውዛል።
ጥቂት ቆይቶ አባቷ አቶ ግራኝ ወደ ሕጻን ዘመረች እያስተዋለ በነገረው ጉዳይ እንደተስማማ አረጋገጠ። ሰውየው ለአባትዬው ግራኝ ልጁን እንዲሰጠው ጠይቆት በእሺታ ተቀብሏል።በሃገሬው ባህል መሠረት ልጅህን ስጠኝ ሲባል አይከለከልም።እምቢተኝነት ነውርና ያልተለመደ ነው።አባት ሰውዬው ልጅህን ልውሰዳትና ልጄን ትዘል፣ትቀፍልኝ ሲለው ሊከለክለው አልቻለም። ጥያቄውን ተቀብሎ በሀሳቡ ተሰማምቷል።
አባት ልጁን ለመስጠት ሲወስን ሰውዬው ደግሞ በመሀላ ቃል ገብቷል፡፤ልጁን እያስተማረ በወጉ ሊያሳድግ፣ ሊንከባከባት በሽማግሌ ፊት ተስማምቷል።ውሎ ሳያድር ሕጻኗን ከቤተሰቧ የወሰደው አባወራ ቃሉን እንደሚጠብቅ ቃል እየገባ ዘመረችን ከቤተሰቡ ቀላቀለ።እንደአባት እንድታስበው እያሳሰበ፣ ወደፊት እንደሚያስተምራት እየነገረ ልጅቷን ሊያላምድ ከሌሎች ሊያዛምድ ሞከረ።
ሕጻን ዘመረች የመጣችበት ዓላማ አልተረሳም። ከአባወራው ሚስት ትዕዛዝ እየተቀበለች፣ የተባለችውን እየፈጸመች የሞግዚትነት ሥራዋን ጀመረች። ልጅቷ ልጅ ለማዘል ትከሻዋ አልዛለም።ከጠዋት አስከማታ ከእሷ ጥቂት የሚያንሰውን ሕጻን ይዛ ስትወዘወዝ ትውላለች። ዘወትር ቢደክማት፣ ሸክሙ ቢከብዳት ማንም ነገሬ አይላትም ።ሞግዚትነቷ ልጅ በማዘል፣ተሸክሞ በመዋል ተወስኗል።
የአባወራው ሚስት መተዳደሪያዋ የምግብ ቤት ሥራ ነው። ገንዘብ ለመቁጠር ፣ ደህና ገቢ ለማግኘት ስትሮጥ መዋል ግዴታዋ ሆኗል። በስሯ ላሉት ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል፣ነገን የተሻለ ሆኖ ለመገኘት እረፍት ይሉትን አታውቅም።ከልጅ ጋር ሥራ ወይዘሮ ሞግዚት ካገኘች ወዲህ ‹‹እፎይ!›› ብላለች።አሁን ቀኑን ሙሉ ልጇን አዝላ ከድካም የምታሳርፍ አጋር አላት ።ሕጻን ዘመረች በመማሪያ ፣በመቦረቂያ ዕድሜዋ ኃላፊነት ወድቆባታል። እንደ እኩዮቿ ልሁን ብትል የሚሰማት ‹‹እሺ›› የሚላት አታገኝም።
ዘመረች ልጆች ስታይ መቦረቅን ትሻለች ።እሷም እንደእኩዮቿ ዕቃ፣ዕቃ ብትጫወት፣ ገመድ ብትዘል ደስ ይላታል።ይህ እንዳይሆን የኑሮ ገመድ ጠፍሮ ከያዛት ወራት ተቆጥረዋል።ልጅነቷን በጉልበቷ ከፍላ፣ ደስታዋን በዕንባ ሲቃ ውጣ ቀናትን መግፋት ግዴታዋ ነው።
አራት ወራትን ያስቆጠረው የሕጻኗ ሞግዚትነት፣ ለሚታዘለው ልጅ ዕድሜና ምቾትን ጨምሯል። ለምታገለግላቸው አሳዳሪዎቿ አቅም ሆና ሥራ ያቀለለችው እናት አባቷ፣እህት ወንድሞቿ በዓይኗ ውል ሲሏት በናፍቆት ትሳቀቃለች። አንዳንዴ ለራሱ ጉዳይ ብቅ የሚለው አባቷ ከቤት እያስጠራ ያያታል።ይህኔ የልጅነት ዓይምሮዋ በደስታ ይሞላል።አባቷን ስታገኝ ሮጣ ትጠመጠምበታለች፣ በዚህ ሰዓት ከእሷ በላይ ደስተኛ የለም። ኩራት ይሰማታል፣ ፈገግታ ይውጣታል።ሁሉን ትረሳለች፣ አባቷ ጉዳዩን ጨርሶ ወደመጣበት ሲመለስ ደግሞ ሆዷ ይረበሻል፣ ብቸኝነት ባይተዋርነት ይወርሳታል።
የስምንት ዓመቷ ዘመረች አዝላ የምትውለው ሕጻን እንጀራዋ ነው። ልጁን ካልተሸከመች፣ አባብላ ካላስተኛች፣ እህል አትጎርስም፣ ዕንቅልፍ አታስብም። ይህ ሲሆን ማንም ስለእሷ መድከም አይጨነቅም። ሽክሙ ይከብዳታል፣ ልጅነቷ ያስቸግራታል ፣የሚል አሳቢ የላትም። ያልጠናው ትከሻዋ በየቀኑ ልጁን ያዝላል።ጫንቃዋ ፈጽሞ አያርፍም፤ ጉልበቷም አይዝልም።
ታህሳስ 8 ቀን 2006 ዓም
ቀኑን ሙሉ ሕጻኑን አዝላ ስትወዘወዝ የዋለችው ዘመረች አመሻሻ ላይ ድካም ቢጤ ተሰምቷታል። ፤ አንዳንዴ ሰውነቷ ሲዝል፣ ትከሻዋ ሲረታ እንቅልፍ ያዳፋታል። እንዲህ ሲሆን በጊዜ ጎንዋን አሳርፋ መተኛትን ትሻለች። ድካም የሚወርሰው አካል ፣ልጅነት የሚፈትነው ማንነት ግን በየቀኑ በሌሎች ይሁንታ እንደታዘዘ ነው። ትንሽዋ ሞግዚት ሁሌም ያሻትን ማድረግ ተችሏት አያውቅም።
በዛን ቀን ምሽት ዘመረች ልጁን አዝላ በግቢው ከወዲያ ወዲህ ስትል ቆይታለች። ሕጻኑ ሥራ ውላ የመጣች እናቱን የናፈቀ ይመስላል። ደግሞ ደጋግሞ እያለቀሰ ይነጫነጫል። እንደነገሩ ከትከሻዋ ያዘለችው ዘመረች ከፍ ዝቅ እያደረገች፣ ከወዲያ ወዲህ እየዞረች፣ ታባብለዋለች። አሠሪዋ ወይዘሮና ወላጅ እናቷ ከሌላ ክፍል ናቸው።
በድንገት የተሰማውን ‹‹ ጓ ›› የሚል ድምጽ ተከትሎ ያምባረቀው የሕጻኑ የለቅሶ ድምጽ ከቤት የነበሩትን ሰዎች ትኩረት ስቧል። አሁን ልጁ ከቀድሞው ይበልጥ አምርሮ እያለቀሰ ነው። ወይዘሮዋና ወላጅ እናቷ ካሉበት እየሮጡ ሲደርሱ ትንሹ ልጅ ከትንሽዋ ሞግዚት ትከሻ አምልጦ ከመሬት ወድቆ ነበር።
አያቱን ጨምሮ ወላጅ እናቱን ያስደነገጠው ድንገቴ ክስተት በዘመረች ላይ እርምጃ ለማስወሰድ አልዘገየም። ወድቆ የሚያለቅሰውን ሕጻን ከመሬት ያነሱት እናትና ልጅ ትኩረታቸው ወደ ሞግዚቷ ሆነ። እናት ቀድማ ዘመረችን በጥፊ አቃጠለቻት። ዘመረች እያለቀሰች ከመሬት ወደቀች።
የልጃቸው ቅጣት መነሻ የሆናቸው ወይዘሮ ለትንሽዋ ሞግዚት አላዘኑም። ልጅቷ ከወደቀችበት ሳትነሳ ትከሻዋን በእርግጫ እየረገጡ አሰቃይዋት። የእናትና ልጁ እልህ በቀላሉ የሚበቃ አይመስልም። ለተጨማሪ ቅጣት ዘመረችን እያዋከቡ፣ እያዳፉ ወደመኝታ ክፍል ወሰዷት።
የእናትና ልጁን አስደንጋጭ ቁጣና ድንገቴ ቅጣት መቋቋም የተሳናት ህጻን እየተንገላታች ከመኝታ ክፍሉ ገብታለች። ከደረሰባት ድብደባ ሁሉ ከጆሮ ግንዷ ያረፈውን ከባድ ጥፊ የቻለችው አይመስልም። ፊቷን በትናንሽ እጆችዋ እያሻሸች፣ ጆሮዋን ደጋግማ እየዳሰሰች እንዲምሯት፣ እንዲተዋት በለቅሶ ትማጸናለች። ንዴት ውስጥ ያሉት እናትና ልጅ ፈጽሞ ሊሰሟት፣ሊራሩላት አልፈቀዱም። ያሻቸውን ሲጨርሱ በሩን ከውጭ ቆልፈውባት ። ከአጠገቧ ራቁ።
ማግስቱን ማለዳ…
ማልዳ ከዕንቅልፏ የነቃችው ወይዘሮ ከወዲያ ወዲህ እያለች ትንቆራጠጣለች። ለእሷ በዚህ ሰዓት ከመኝታ መነሳት አዲስ አይደለም። በጠዋት ተነስታ ለሆቴል ሥራው ትዘጋጃለች። ለሠራተኞቿ ድርሻ ሰጥታ ትቆጣጠራች። ዛሬ ግን ስሜቷ ከዚህ ተለይቷል። ሥራ የመሥራት ፣ ድርሻ የማከፋፈል ፍላጎት የላትም። ፊቷ ላይ ጭንቀት ይነበባል። ገጽታዋ ተለይቷል። ጥቂት ቆይታ ከአንዲት ጎረቤቷ ደጃፍ ተገኝታ በሯን አንኳኳች።
ሴትዬዋ በጠዋቱ ከቤቷ የደረሰቸውን ወይዘሮ እንዳየች ደንገጥ ብላ ምክንያቷን ልታውቅ ፈለገች። የማለዳዋ እንግዳ በፊቷ ድንጋጤና ኃዘን እየተነበበ የልጇ ሞግዚት ምሽቱን እንደጠፋችና እሷ ዘንድ መጥታ እንደሆነ ጠየቀቻት። የተጠየቀችው ወይዘሮ በሁኔታው ደነገጠች። ሞግዚቷ ዘመረች ትናንት ምሽት ልጁን እንዳዘለች ወደቤቷ ዘልቃ ነበር። እንደተለመደው ከልጆችዋ ተጨዋውታ ተመልሳ ሄዳለች።
ወይዘሮዋ ከሴትዬዋ መልሱን እንዳገኘች ወደቤት ፈጥና ተመለሰች። በስፍራው ደርሳም ሠራተኞቿን ዳግም አፋጠጠች። ሠራተኞቹ ልጅቷን ከትናንት ምሽት በኋላ ፈጽሞ እንዳላይዋት፣ እንዳላገኝዋት እየማሉ አረጋገጡ። ወይዘሮዋ በእነሱ መልስ አልረካችም። ያገኘቻቸውን ሁሉ እየጠየቀች፣ ካዩዋትና ያለችበትን ካወቁ እንዲያሳውቋት ተማጸነች።
ከአባትዬው ጋር …
ረፋዱን ካለበት መኖሪያው ‹‹ወይጦ›› ወደተባለው መንደር ያቀናው የዘመረች አባት የሚፈልጋቸውን ከብቶች ተመልክቶ ጉዳዩን ፈጥኖ ጨርሷል። ወደአገሩ ለመመለስ በቂ ጊዜ እንዳለው ሲያውቅ እግረመንገዱን ልጁን ለማየት ወደምትገኝበት መንደር አቀና።
እስከዛሬ በሰፈሩ ደርሶ ልጁን ሲቃኝ ዘመረች አጠገቡ ለመገኘት ጊዜ አትፈጅም። ካለበት ደርሳ ከአንገቱ ትጠመጠማለች። ከፊቱ ቆማ ናፍቆቷን ትወጣለች። ዛሬ ግን ይህ አልሆነም። አባት ከስፍራው ከተቀመጠ ቆይቷል። እስካሁን ትንሽዋ ልጁ ብቅ አላለችም። ዓይኖቹ እየተንከራተቱ በጉጉት ጠበቃት፣ አሁንም ብቅ አላለችም። ጊዜ ወስዶ ታገሰ። ለውጥ አላገኘም።
ጥቂት ቆይቶ ወደአሠሪዎቿ ቤት ዘለቀ። ከስፍራው ሲደርስ ወይዘሮዋን አገኛት። ሰላምታ እንደተለዋወጡ ልጁን እንድታገናኘው ጠየቃት። የወይዘሮዋ ፊት ላይ ድንጋጤ ተነበበ።
ዝምታዋን ያስተዋለው አባት ደጋግሞ ስለልጁ ጠየቃት። ወይዘሮዋ ጉዳዩን ማስተባበል አልቻለችም። ልጁ ዘመረች ከትናንትና ምሽት ጀምሮ ከቤት ጠፍታ መሄዷን አረዳችው። አባት በሰማው ጉዳይ በእጅጉ ደነገጠ። ትንሽዬ ልጁን ከሞቀ ቤቷ አምጥቶ፣ ከእህት ወንድሞቿ ነጥሎ ለችግር እንደጣላት ገባው። አባት ጊዜ አልፈጀም። በአካባቢው ካሉ ዘመዶቹ ዘንድ እየዞረ ፈለገ። ጉዳዩን የሰሙ ሁሉ በየቦታው አሰሷት፣ ፈለጓት። ዘመረች አልተገኘችም።
በፍለጋው ተስፋ የቆረጠው አባት ወደቤቱ አልተመለሰም። አመሻሹን ከፖሊስ ጣቢያ ደርሶ ጉዳዩን አመለከተ። ሁኔታውን የሰሙት የፖሊስ አባላት በቂ መረጃ ወስደው ትንሽዋን ሞግዚት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አጠናቀቁ። ቡድን ተዋቅሮ አሰሳው ተጀመረ። የሚያጠራጥሩ ስፍራዎች ተፈተሹ። የሚጠረጠሩ ሰዎች ተጠየቁ።
ከፖሊስ ጋር…
ፖሊስ ወዳጅ ዘመድን ይዞ፣ ከአካባቢውን የቀበሌ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥብቅ ፍለጋውን ቀጠለ። ፈላጊዎች ድምጻቸውን እያጉሉ፣ በጩኸት እየተጣሩ ዘመረችን ሊያገኙ ተሰማሩ። በሞተር ሳይክሎች ጉድጓድ ጉድባዎች ተፈተሹ። በድምጽ ማጉያ የታገዘው ፍለጋ ጠነከረ።
ማንም ሕጻንዋን አላገኘም። ዘመረችን የበላ ጅብ ሳይጮኸ ጀንበር ጠለቀች። ጨለማው አይሎ ፣ ምሽቱ ሲበረታ ፈላጊዎች ተስፋ ቆረጡ። ወዳጅ ዘመዱ በኃዘን አንገቱን ደፋ። የፖሊስ እይታና ትኩረት ግን ከሌሎች ሁሉ የተለየ ሆኖ አመሸ።
የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን መርማሪ ምክትል ሳጂን ወንድይፍራው አሸብርና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የፍለጋ አቅጣጫውን ቀየሩት። ከአሠሪዋ መኖሪያ ተገኝተው በስፍራው ያገኙዋቸውን ሠራተኞችና ወይዘሮዋን በጥያቄ አጣደፉ። የተለየ ምላሽና ፍንጭ አላገኙም። የፖሊስ መረጃ በሠራተኞቹ ብቻ አልተወሰነም። ባገኘው ፍንጭ ታግዞ የሕጻንዋን አሠሪ ወይዘሮ ጥበብ በሞላው ፖሊሳዊ ጥያቄዎች እያዋዛ ከእውነታው ለመድረስ ጣረ።
ምሽት ከአንድ ቀን በፊት…
ከሞግዚቷ ትከሻ ላይ የሕጻኑን መውደቅ ያወቁት እናት ልጅ። ዘመረችን በድብደባ እያዋከቡ ከቀጧት በኋላ መኝታ ቤታቸው አስገብተው ዘግተውባታል። ዘመረች በእናት ልጁ ከባድ ያለ ድብደባ የከፋ ሕመም ላይ ወድቃለች። በሁኔታው የተናደዱት እናትና ልጅ ስለሞግዚቷ ጉዳትና ለቅሶ አልተሰማቸውም። ከተዘጋው በር ጀርባ ካለው ክፍል ተቀምጠው ቡና እየጠጡ አምሽተዋል።
ጥቂት ቆይተው የተዘጋውን ክፍል በርግደው ገቡ። ዘመረች ከሰዓታት በፊት ስታለቅስና ስትጮህ እንደቆየችው ሆና አላገኝዋትም። በዝምታ ተኮራምታ ተኝታለች። ሁለቱም ዕንቅልፍ እንደጣላት ጠርጥረው እየተናደዱባት ነው።
ዘመረች የእነሱን መምጣት አውቃ ፈጥና አልተነሳችም። ጠጋ ብለው አስተዋሏት። ትንፋሽና ሳግ የላትም። የልጅ ገላዋ አልሞቃቸውም። ጠጋ ብለው ዳሰሷት። አልተንቀሳቀሰችም። እናትና ልጁ ክፉኛ ደነገጡ። ዘመረች ባልጠና አካሏ ላይ ባደረሱባት ድብደባ ሕይወቷ አልፏል። ሁለቱም ባሉበት ደነዘዙ።
ምክክር..
ከጥቂት መረጋጋት በኋላ እናትና ልጁ በጥንቃቄ መከሩ። የሕጻንዋን አስከሬን በመኝታ ቤቱ መስኮት ጥለው ማስወገድ እንዳለባቸው ወሰኑ። ሀሳባቸው በስምምነት ጸድቆ ድርጊቱን ፈጥነው ፈጸሙት። የዘመረች አስከሬን በመስኮቱ ተወርውሮ ከመኖሪያ ቤቱ ተወገደ። ማለዳውን ከስፍራው አንስተው ከገደል ጨመሩት።
ወደቤት ሲመለሱ የቤቱን እንጀራ ጋጋሪዎችና ውሀ ቀጂዎች ጠርተው የማታውን ድርጊት ትንፍሽ እንዳይሉ በጥብቅ አስጠነቀቁ። ሠራተኞቹ ትዕዛዙን በፍራቻ ተቀበሉ። ለጠየቋቸው ሁሉ ስለልጅቷ ‹‹አላየንም፣ አልሰማንም›› ሲሉ ቆዩ።
ፖሊስ የወንጀሉን መፈጸም በበቂ ማስረጃዎች እንዳረጋገጠ ተጠርጣሪዎቹን እናትና ልጅ ለፍርድ ለማቅረብ መዝገቡን ወደ ዓቃቤ ሕግ አስተላለፈ። ጉዳዩ ተጣርቶ የቀረበለት ዓቃቤ ሕግም ሁለቱን ሴቶች ለሕግ አቅርቦ ውሳኔ ለማሰጠት የክስ መዝገቡን አንቀሳቀሰ።
ውሳኔ…
ሰኔ አምስት ቀን 2006 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነፍስ ባጠፉት እናት ልጅ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ እናት እና ልጅ በፈጸሙት ድብደባ ሕይወት መጥፋቱን አረጋግጦም ጥፋተኝነታቸውን ለይቷል።በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም ተከሳሾቹ እናትና ልጅ እያንዳንዳቸው፣ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡
መልካምሥራአፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014