ታክሲ ውስጥ ነው፤ ወደ ሃያ ሁለት እየሄደ፣ ፊቱን ወደ ግራ አዙሮ በመስተዋቱ ውስጥ ወደ ውጪ ያስተውላል፤ አዲሳባን እያየ:: ቆነጃጅቷን፣ ጉዷን፣ ትናንቱን ዛሬውን ሳይቀር ተመለከተ:: ሁሉንም ነገር ልብ ብሎ ማየት ይወዳል፤ በተለይ ቆንጆ፤ እንደ አብዛኛው ሰው ቆንጆ አይቶ ቆንጆ ብሎ ብቻ አያቆምም፤ ቁንጅናዋን በተለያዩ መንገዶች ይገልጸዋል::
ቆነጃጅት ሲመለከት አዲሳባ ትገርመዋለች፤ አንዲት ፉንጋ እንዳይገባባት አዋጅ የወጣባት ትመስለዋለች:: ወደዚያ ወደዚህ ሲል ውብ ብቻ ነው የሚያየው፤ ይገርመዋል::
ሥራ ሲፈታ መሄጃው ወደ ትናንት ነው:: በዛሬው ውስጥ ያልኖረው ትናንት አለ:: የታክሲዋ ኋላ ወንበር ላይ ሆኖ ሀሳብ ወሰደው፤ መክሊት መጣችበት:: ዝም ካለ ከእሷ ሌላ የሚያስባት የለችም::
መክሊት የሕይወቱ ምርጥ ትዝታው ናት:: በትናንቱ ላይ የቀለማት ውብ ስዕሉ ናት:: እንደ እሷ ደስታን የሰጠው ማንም የለም:: ገነትን በእውን ነው ያሳየችው:: እያንዳንዱ ተፈጥሮዋ ይገርመዋል፤ ለመላዕክትነት ተፈጥራ በማይታወቅ ምክንያት ሰው የሆነች ይመስለዋል::
ከእግዜር ፍጥረት ሁሉ በእሷ የሚደነቅ ይመስለዋል:: በፍቅሯ ረክቷል:: በውበቷ ነፍሱ ስቃለች:: ከእሷ ጋር ያሳለፈው ጊዜ አዳምና ሄዋን ገነት ውስጥ ያሳለፉት ጊዜ ይመስለዋል:: እሷን ፍለጋ አምስት ዓመት ለፍቷል:: በየቀኑ ከማማርና ከመቆንጀት ባለፈ ግን እንከኗን ሊደርስበት አልቻለም:: በዘመኑ ሁሉ የምታስገርመው ናት:: ሰው እንዴት ያለ አንዳች እንከን ይፈጠራል? ሲል ራሱን ደጋግሞ ጠይቆ ያውቃል::
ስታወራ ትገለዋለች፤ ስትስቅ ታስደንቀዋለች:: ዝም ስትል፣ ስትኮሳተር በዚህ ሁሉ ውስጥ ያፈቅራታል:: ለአስር ሰው የሚበቃ ረጅም አንገት፣ ጀርባዋ ላይ የተጎዘጎዘ ረጅም ጸጉር፤ ጠዋትና ማታ የሚቀባባ አይንና ከንፈር አላት:: እንደ ሰንበሌጥ የቀጠነ ወገብ አላት:: በመቃ አንገቷ ላይ ሃምሳ ግራም የአንገት ሀብሏን አድርጋ እንደ ጥርኝ ዝባድ ከርቀት የሚያውደውን ሽቶዋን ተቀብታ ወደ እሱ ስትመጣ የሚማርከው ምንም አልነበረም::
አምራና ተውባ እየሳቀች ከእግር እስከ ራስዋ አፍጠው ወይም በዘዴ በዘዴ በሚመለከቷት ወንዶች መሐል አልፋ ከንፈሩን ስትስመው የሚሰማውን ኩራት መቼም አይረሳውም:: በሕይወቱ በእሷ ነው የተባረከው:: ማንም ያልሳቀውን ሳቅ ስቋል:: በእሷ የተነሳ ማንም ያላዘነውን አዝኗል:: እሷ ገነቱም ሲኦሉም ናት:: ያልዋሸችው ጊዜ አልነበረም:: ከነውሸቷ ነበር የሚያፈቅራት:: ከማንም ጋር ውላና አድራ ስትመጣ ስቆ ነበር የሚቀበላት::
ለመጀመሪያ ጊዜ ስትተዋወቀው በውሸት ነበር:: እንደ እሷ በውሸት የተካነ አያውቅም:: ጭፈራ ቤት ጥግ ይዞ ከወንድ ጋር እያያት እናቴ ታማ ሆስፒታል ነኝ ብላው ታውቃለች::
አንድ ቀን ለሥራ ጉዳይ ከከተማ ወጣ ብሎ ነበር፤ ጉዳዩ ቶሎ ተጠናቀቀና እመለሳለሁ ሳይላት ድንገት ቤት ይመለሳል፤ ቤት ሲደርስ ግን ያጋጠመውን ማመን አልቻለም፤ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ከወንድ ጋር ስትባልግ አገኛት:: ከዛን ጊዜ ወዲህ አይቷት አያውቅም:: በሥራዋ አፍራ ነው መሰለኝ እንደወጣች አልተመለሰችም::
እንዲያም ሆኖ ግን በመሄዷ ዛሬም ድረስ ይከፋል:: እንደዛም እየሆነች ባሏ ሆኖ መኖርን ይፈልግ ነበር:: እንዲህ እያሰበ ከጎኑ የሆነ ደስ የሚል ሽቶ አወደው:: አልዞረም፤ ከነሀሳቡ ነው፤ አዲሳባን እያያት:: መክሊትን እያሰበ:: እንዲህ የምታውደው እሷ ነበረች፤ ጠ ይሟ መክሊት::
‹ከኋላ ሂሳብ› የሚል ድምጽ ሰማ:: የረዳቱን ድምጽ ነበር:: እሱን እንደሆነ አልጠፋውም:: በረዳቱ ድምጽ ከሀሳቡ ወጣ:: አጠገቡ አንዲት ወጣት ተቀምጣ አየ:: መላ ሰውነቷ በዝምታ ውስጥ የሚስቅ መልከ መልካም ናት:: ከመላዕክት ጎን የተቀመጠ መሰለው፤ ቆንጆ ማየት ይወድ የለ፤ እስካሁን ሳያያት በመቅረቱ ተቆጨ:: ልጅ ናት፤ አንድ ፍሬ፤ ሃያዎቹ ግድም:: ፊቷን በከፊል ፣ እጆቿን ተመለከተ፤ እንደ ንጋት ሰማይ ፍክት ያለ ቆዳ አላት:: ማንም የሚያየው ውበት፤ ተገርሞ ሳያበቃ..
‹ጀለሴ ሂሳብ ክፈይና ትመሰጫለሽ› ሲል የታክሲው ረዳት ድምጽ ከአትኩሮቱ አላቀቀው:: የድምጹ ከፍ ማለት እና ከሀሳቡ ያበነነው መሆኑ አናዶታል::
ምን አባክ ትጮሃለህ በሚል አስተያየት እያየው ሂሳቡን ከፈለ::
አጠገቡ የተቀመጠችውን ወጣት በቆረጣ ማየቱን ቀጠለ:: በዝምታ እየሳቀች አገኛት:: በዝምታ የሚስቅ ብዙ ውበት አላት:: የሰከነ ግን ደግሞ የሚያረካ፣ ዝም ያለ ግን ደግሞ የሚናገር ተፈጥሮ:: የሆነ መባነን ወደማይፈልግበት ውብ ህልም ውስጥ ከተተችው:: መጀመሪያ መክሊትን ያያት ቀን እንዲህ እንደ አሁኑ ሆኖ እንደነበር አስታወሰ::
እናም ቆንጆዋን ተመለከታት፤ እንደ ቅድሙ ናት፤ በዝምታ በሚስቅ ፊት:: ሽቶዋ ነፍሱ ድረስ ገባ:: ታክሲው ውስጥ የተከፈተው የዘጠኝ ሰዓቱ ዜና ስለ ወቅታዊው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ያወራል:: ከአስራ ሁለቱ ተሳፋሪ ግማሹ ጆሮውን ለዜናው የሰጠ መስሎታል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጠር ችግር ተስቦ ተስቦ አገር ቤት ይገባልና ትክክል ናቸው ሲል አሰበ:: የተቀሩት ደግሞ በቀጥታ ስለ ኑሮ መወደድ፣ ስለ ሥራ መጥፋት፣ ስለመልካም አስተዳደር ችግር፣ ወዘተ የሚያስብ አድርጎ ቆጥሮታል::
እሱ ግን አጠገቡ ስላለችው ቆንጆ ያሰላስላል:: የእሷን ሀሳብ አምላክ ይወቀው ግን እንደ ቅድሙ ናት፤ በብዙ ውበት በብዙ ዝምታ::
ዝም ብሎ ሊለያት አልፈለገም፤ ሁሉም ሴቶች አንድ አይደሉም፤ ምናልባት በዚች ቆንጆ እባረክ ይሆናል ሲል አሰበ:: ዝምታዋ አስፈራው፤ ወንድ ላለማናገር ምላ ከቤት የወጣችም መሰለው:: የሆነው ይሁን እንጂ ዛሬ ሳያናግራት አይቀርም::
የሰዓቱን ዜና ታኮ ወሬ ቢጀምርላት ጥሩ እንደሚሆን አሰበ:: ግን ብዙ አለፋም የሆነ ሀሳብ መጣለት:: ለምን ስለቁንጅናዋ..ስለ ተቀባችው ሽቶ አድንቄ አልነግራትም ሲል አስቦ ‹ሽቶሽ በጣም ደስ ይላል› አላት::
‹አመሰግናለሁ› ፈገግታ በመከነበት ፊት መለሰችለት::
‹ሽቶ የሚወዱ ሴቶች ምን አይነት ስብዕና እንዳላቸው ታውቂያለሽ? ሲል ጥያቄ በማስከተል ጨዋታውን አቀጣጠለው::
‹አላውቅም› ስትል መለሰችለት እንዲነግራት በመጓጓት ወደ ጎን ዞራ እያየችው:: ፊቷ ላይ ጉጉት ተፈጠረ:: እንደ ዛሬ ወሬ ለመስማት ጓጉታ አታውቅም:: አይን አይኑን እያየች ጠበቀችው፤ ወሬ በአይን ይገባል በሚል ስሜት አይነት::
‹ሽቶ በጣም ነው የምወደው..› አለችው በድጋሚ ሳይጠይቃት በፊት::
እያሸነፋት መሰለው:: በዚች ሴት መባረክ አለበት:: ማሸነፊያ ቃላት በመራረጥ ላይ ሳለ ስልኳ ጮኽ::
ቦርሳዋን በርብራ አነሳችው::
‹የኔ ማር የት ነሽ? የሚል የአንድ አፍቃሪ ወንድ የሚመስል ድምጽ ሰማ::
‹የጓደኛዬ እናት ታመው ሆስፒታል ነኝ›:: ስትል መለሰችለት::
ጠላት:: የወደዳትን ያህል ተጸየፋት:: ቆንጆ ሆና መልካም ሴት እግዜር አልፈጠረ ይሆን? ሲል ራሱን እየጠየቀ ያለመውረጃው ትቷት ወረደ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)