አዲስ አበባ፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በገጠሙት የመዘግየትና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በመገናኛ ብዙሀን ይሰሩ የነበሩ ዘገባዎች መቀዛቀዛቸውን የታላቁ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ “የሀገራችን ሚዲያ ለሀገሩ ግድብ” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው የመገናኛ ብዙሀን የምክክር መድረክ ላይ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር እንዳሉት፤ ህዝቡ ላለፉት ስምንት ዓመታት ድጋፉን በሙሉ ልቡ እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ መገናኛ ብዙሀን የተጫወቱት ሚና ቀላል የሚባል ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በግንባታው መዘግየትና በተከሰቱ ተያያዥ ችግሮች ምክንያት የቀድሞውን ዓይነት ስራ አይታይም። ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ ፍቅርተ ገለጻ፤ ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያዎች፤ እንዲሁም ሌሎች ለግንባታው አንድ ሆነው በመሰለፍ ወቅታዊ መረጃዎችን በማቀበል ሰፊ ስራ በመስራታቸው ህብረተሰቡም የግድብ ባለቤትነት ስሜቱ ጎልብቶ ሁሉም አሻራውን ለማኖር በቅቷል። በዚህም 12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ከመቻሉም በላይ፤ ግንባታውም ዛሬ ላይ 65 በመቶ ደርሷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ በተጠናከረ መንገድ ቀጥሎ የተጀመረው ስራ ይጠናቀቅ ዘንድ የመገናኛ ብዙሀን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ዘንድሮ በገጠመን የግንባታ መዘግየት ምክንያት መቀዛቀዙ በሁላችንም ላይ የታየ ነው፤ ይህንን ለማሻሻልም ባለፉት ወራት መንግስት ችግሮቹን ፈትሾ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ለማድረስ ጥረት አድርጓል፤ በመሆኑም፤ መገናኛ ብዙሀን ከመቀዛቀዝ ወጥተው ከጎናችን በመሰለፍ ለህዝቡ መረጃ ማድረስና የህዝቡን አመኔታ ተስፋ ሰጪ በሆነ መልኩ መመለስ ይገባል” ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የሚዲያውን ሚና አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ተሻገር ሽፈራው እንዳሉትም፤ የመገናኛ ብዙሀን ተከታታይ ዘገባ ለግድቡ ግንባታ ህዝቡ እንዲነሳሳ በማድረግ በኩል ሰፊ ሚና ተጫውተዋል። ከዚህ በኋላም ስራውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ተሳትፎ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስም ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሀን ባለፈው አንድ ዓመት በግድቡ ዙሪያ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች እየቀነሱ፤ ጣዕማቸውንም እያጡ እንደ ተባራሪ ዜና እየተቆጠሩና ችላ እየተባሉ መምጣታቸውን የሚናገሩት ዶክተር ተሻገር፤ መገናኛ ብዙሀኑ በዚህ ልክ ትኩረት ከነፈጉት ህዝቡም ስለሚዘናጋው በቀጣይ ወቅታዊ መረጃዎችን በማቀበል አጀንዳውን መልሰው ማምጣት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
በበርካታ አገራዊ የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ልዩነት ቢኖርም የህዳሴው ግደብ ግን ከፍተኛ አገራዊ መግባባትን የፈጠረ ነው ያሉት ጽሁፍ አቅራቢው፤ ይህ መግባባት ደግሞ በሁሉም መገናኛ ብዙሀን ላይ ሲታይ መቆየቱን በመጠቆም፤ በቀጣይም “እንደ አንድ ልብ መካሪ ፤ እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ” በመሆን የተጀመረውን ስራ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳተፉት የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች መካከል ጋዜጠኛ ሂርፓ ሰርቬሳ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሀን በአንድ አገር ውስጥ ለሚሰሩ ማናቸውም ስራዎች ሚናቸው የጎላ ነው። በተለይም እንደኢትዮጵያ ታዳጊ ለሆኑና በራሳቸው አቅም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመስራት ላይ ላሉ ደግሞ የጀርባ አጥንት ናቸው። በመሆኑም መገናኛ ብዙሀኑ ቀድሞ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ሲያደርጉ የነበረውን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፤ ብለዋል።
ጋዜጠኛ ሽመለስ ታደሰ በበኩሉ፤ መገናኛ ብዙሀኑ በቀጣይ በህዳሴው ግደብ ግንባታ ዙሪያ መንግስት የገባውን ቃል በተግባር መተርጎሙን በመከታተልና ለህብረተሰቡ ወቅታዊ፤ ተጨባጭ፤ እንዲሁም እውነተኛ መረጃ በማቅረብ ተሳትፎአቸውን እንደገና መመለስ አለባቸው ብሏል።
በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት የተወከሉ ጋዜጠኞች ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ ምን መሰራት አለበት በሚለው ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2011
በእፀገነት አክሊሉ