ችግሩ የፊቷን እንጂ የሚከተላትን አታይም፤ እናም ጨርቅ ላይ እሷ አለፍኩ ብላ የክርና የገመድ መዓት ታስገባበታለች፡፡ የእኛ ሀገር አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦማሪዎችም ልክ እንደ መርፌዋ ናቸው።
እነርሱ ሀገር በሚወጋ መርፌያቸው እየወጉን ሲጓዙ እንደ ክር አያሌዎች መድረሻቸውን ሳይጠይቁ ይከተሏቸዋል።
ድረ ገጻቸውን የሚያነብላቸው ተከታታይና ደጋፊ ማብዛታቸውን እንጂ ሀገርና ሕዝብ ላይ እየተከሉ ያሉትን አደጋ፣ እየረጩት ያለውን መርዝ ሊያዩት አልቻሉም።
ባለፉት ጥቂት ወራት ሀገራችን ያስመዘገበቻቸውን የድል ስኬቶች በመዘርዘርና ከእርሱም ትይዩ የገባችበትን የፖለቲካ ቀውስ ለእናንተ በማስታወስ ጊዜአችሁን ማባከን ኣይገባም፡፡ አሁን ያለው ትልቁ ቁም ነገር ከዚህ ከገባንበት አሳሳቢ ቀውስ ራሳችንንም፣ ሀገራችንንም እንዴት እናውጣት የሚለው ነው።
ሁለት የገመድ ጽንፎችን ይዘው የቆሙ ኃያላን በሚያደርጉት ጉተታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አደገኛ ውጥረት ውስጥ የከተቱበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ልበ ሥውር ሆኖ ግራና ቀኝን በጥሞና ማስተዋል በተሳነው ጽንፈኛ ቡድን የሀገራችን አየር ምድሯ ሰላምና
ተስፋን ከመተንፈስ ይልቅ የስጋትና የውድመት ደመናን አርግዞ የመከራ ዶፉን ሊጥል ከአናታችን በላይ መጣሁ መጣሁ ይላል።
መካረር እዚህም እዚያም በርትቷል፡፡ ተፈጥሮ ነውና የተወጠረና የተካረረ ጉዳይ ቆይቶ መበጠሱ አይቀርም፡፡
“የማን ቤት ጠፍቶ ፣የማን ሊበጅ ፣ ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ” የሚለው የሽፍቶች ፈሊጥ እንጂ የሰላማዊ ዜጎች መመሪያ አይደለም።
በእውነት ኢትዮጵያዊነት የሚፈተንበት ወቅት እየመጣ ነው፤ ማንም ጣፋጭ ዘርና ፍሬ ነኝ ብሎ ሊኮራና ሊመጻደቅ የሚችለው የግንዱ ሥር እስካለ ብቻ ነው፡፡ የግንዱን ሥር ቆርጦና ነቅሎ በቅርንጫፉና በዘሩ መኩራት የሞኝ ጨዋታ ይሆናል።
በውስጣችን አንጠፍጥፈን ያላወጣነው ዐቅም፣ ያልተጠቀምንበት ችሎታ ካለ፣ እርሱን ኢትዮጵያን ለማዳንና ለመገንባት እንጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ዐውደ ውጊያ ሀገር ለማተራመስ ልናውለው አይገባንም ነበር።
ሥልጣኔ ሕዝብን በዕውቀት መክበብ እንጂ በሐሰት መረጃ ማጨናነቅ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኃላፊነታቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን መታደግ ነው፡፡ በጣም ጥቂት ለሆኑና ጊዜያዊ ጥቅም ለሚያስገኙ የፖለቲካ ቡድንተኞች አለበለዚያም የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይና ደጋፊን ማስደሰትና ማስፈንደቅ አይደለም።
ኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ መሥራት፣ ኢትዮጵያን ማስደሰት እንጂ ኢትዮጵያን በሐሰት መረጃዎች ማሸበር አይደለም፡፡ ሊሆንም አይገባም።
በዘመናት ውስጥ የሀገራችንን ህልውና የሚፈታተኑ አያሌ ፈተናዎች ገጥመውን ያውቃሉ፡፡ ነገራችን ቀጥኖ የሚበጠስ የሚመስልበትም ጊዜ ታልፏል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ምንም ብትቀጥን ጠጅ ናት በእንግዳ ደራሽ በውኃ ፈሳሽ የምትፈርስ አይደለችም።
በማኅበራዊ ሚዲያ በጣም የበዙ የሐሰት መረጃዎች ይተላለፋሉ፤ ሐሰት ጮኾ ስለተነገረ፣ ጎልቶ ስለተጻፈ፣ በብዙ ሰዎች ስለ ተደገፈ ወይም በታዋቂ ሰዎች ስለተወራ እውነት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ግን የዘላለም እውነት ነች።
በሐሰት ዜናም ሆነ በአሉባልታ የማትፈርስ ጽኑዕ መሠረት ያላት እውነት ናት፡፡ ታሪክ ወለል አድርጎ እንደሚያረጋግጥልን ሐሳውያን እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከንቱ ሆነው አያውቁም።
ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን እንጂ ለአንዱ እሥር ቤት ለሌላው ቤት አይደለችም፡፡ እገሌ የዚህ ወይም የዚያ ማኅበረሰብ አባል ስለሆነ በተለየ መልክ ተጠቃሚ ወይም ተጎጂ መሆን አለበት ብሎ የሚያስብ ካለ እርሱ የምናሳክመው እንጂ የምንከተለው አይደለም።
የትም እንወለድ፣ የየትኛውም ብሔር አባል እንሁን፣ ኢትዮጵያ ሁላችንንም በእኩልነት ማገልገል አለባት፡፡ ይህ፣ አቋማችን ነበር፤ አሁንም በጽኑ እናምንበታለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መጋቢት 10፣ 2011 ዓ.ም 5�