አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሳምንት አንድ ጊዜ በአፋን ኦሮሞ እየታተመ ለንባብ የሚበቃውን የበሪሳ ጋዜጣ በይዘት፣ በጥራትና በተደራሽነት አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገለፀ።
ትናንት በዋሽንግተን ሆቴል በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢና የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፤ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እየታተሙ ለንባብ ከሚበቁት ጋዜጦች መካከል የበሪሳ ጋዜጣ አንዱ ሲሆን፤ የጋዜጣውን ተነባቢነት ለማሳደግ በተለይም ለቋንቋው ተናጋሪዎች ጋዜጣው በተሻለ የጥራት መጠን ተደራሽ እንዲሆን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ድርጅቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ጋዜጦችን ስለሚያሳትም በይዘት ደረጃ ጠንካራ መረጃዎችን ይዞ መውጣት እንዳለበትና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው። እንደሳቸው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ አጠቃላይ ሪፎርም እያደረገ
ያለና አጠቃላይ የሆነ ለውጥ ለማምጣትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይም በአሁን ወቅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እጅግ የሚበረታታና ይበል የሚያሰኝ ለውጥ መታየት ችሏል። ይሄው አበረታች ለውጥ ተጠናክሮ በመቀጠል በበሪሳ ጋዜጣም ስር ነቀል ለውጥ ለማስመዝገብ ከምንግዜውም በላይ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ
ይገኛልም ብለዋል።
ድርጅቱ የጋዜጦችን ተነባቢነት ለማሳደግ እየሰራቸው ካሉ ስራዎች መካከል፤ የውጭ ፀሐፍትን ማሳተፍ፣ አጠቃላይ አሰራሩን ዘመናዊ ማድረግና መረጃዎችን ከኦንላይን ሚዲያ ጋር ለማስተሳሰር በሚያስችል ሁኔታ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ጨምረው ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ በጋዜጣው ላይ ያተኮረ የጥናት ወረቀት የቀረበ ሲሆን የጋዜጣው የቀድሞ ዕትሞችም ለእይታ በቅተዋል። በመድረኩ ላይ የጋዜጣው መስራቾች፤ ምሁራን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች፤ የፖለቲካ ሰዎች፤ የፌዴራልና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተው ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
በዕለቱ የተገኙት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ የበሪሳ ጋዜጣ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ መታተሙ በቂ እንዳልሆነና የስርጭት መጠኑን አነስተኛነት በመግለፅ ጋዜጣው በይዘት በልፅጎ በሆቴሎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በክልሎችና በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ጭምር መሰራጨት እንዳለበት አስገንዝበዋል። በሪሳ ከ1968 ጀምሮ እየታተመ የሚገኝ ጋዜጣ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2011
በፍሬህይወት አወቀ