አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከ26 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን እንስሳት መሞታቸውን የክልሉ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና አደጋ ስጋት ቅነሳ ዳይሬክተር አቶ ቤኛ ዱሬሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በስምንት ዞኖች በተከሰተው ደርቅ 14 ሚሊዮን የሚሆኑ እንስሳት ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከ26 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን እንስሳት ሞተዋል።
በክልሉ የበልግና የመኸር ወቅት በተከታታይነት መጥፋቱ ስምንቱም ዞኖች ከፍተኛ ድርቅ እንዲከሰት አድርጓል ያሉት አቶ ቤኛ፤ በአጠቃላይ የምግብ እጥረትና የውሃ ችግር የገጠማቸውና ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብለው በጥናት የተለዩት 14 ሚሊዮን ከብቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለከብቶች መኖ ማቅረብ እጅግ ፈታኝ በመሆኑ በከብቶች፣ ፍየሎችና ግመሎች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ቤኛ፤ጉዳት ከደረሰባቸው ከብቶች 10 በመቶ ለሚሆኑት መንግሥት የመኖ ድጋፍ ምላሽ እየሰጠ ነው። በተጨማሪም በምስራቅ ባሌና ጉጂ አካባቢዎች ድርቁ አሁንም ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።
መጪው የበልግ ዝናብ የሚቀጥል ከሆነ ጉዳቱ የሚቀንስበት ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ቤኛ፤ እስካሁን የአየር ትንቢያ መረጃው እንደሚያመላክተው በምስራቅና በምስራቅ ደቡብ የኦሮሚያ አካባቢ ላይ የሚኖረው የአየር ሁኔታ ደረቃማ በመሆኑ ስጋት አሳድሯል ብለዋል።
በድርቁ ሳቢያ እስካሁን ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ከብቶች ወድቀው በሰው ድጋፍ የሚነሱና የሚንቀሳቀሱ መሆኑን አውስተው፤ ድርቁ በክልሉ ብሎም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ላይ ሊያስከተል የሚችለው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አቶ ቤኛ ዱሬሳ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ቤኛ ገለጻ፤ በድርቁ ሳቢያ ሰዎች አስቸጋሪ የሆነ የምግብ እጥረት፣ የውሃ እጥረት፣ እንስሳት የመኖና የውሃ እጥረት ገጥሟቸዋል። ድርቁ በተለይም በቦረናና ምስራቅ ባሌ ላይ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር ጉዳቱን የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው። እስካሁን አጠቃላይ በክልሉ፣ የፌዴራል መንግሥትና ሕዝቡን በማስተባበር፣ የተለያዩ የግልና ለጋሽ ድርጅቶችን በማቀናጀት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014